Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ድሉና ከፍታው

0 320

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ድሉና ከፍታው

ዳዊት ምትኩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእስራኤሉን ፕሬዝዳንት ሬውቨን ሪቭሊን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ማነጋገራቸው ይታወሳል። አንድ የእስራኤል ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን ሲጎበኝ ይህ የመጀመሪያው ነው። ይህም የሁለቱ አገራት ግንኙነት የበለጠ እየተጠናከረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። በዚህም ሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን የበለጠ በማጠናከር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ተባብረው ለመስራት ዝግጁ ናቸው። ይህም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ድል የደረሰበትን ከፍታ የሚያሳይ ይመስለኛል።

ኢትዮጵያና እስራኤል ከሶስት ሺህ ዓመታት በላይ የዘለቀ ግንኙነት አላቸው፤ በንግስት ሳባና በንጉስ ሰሎሞን ዘመን። በኘሬዚዳንት ሪቭሊን የሚመራው የእስራኤል የልዑካን ቡድን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን ያቀፈ ነው። ሬዩቪን ሪቭሊን ኢትዮጵያን የሚጎበኙ የመጀመሪያው የእስራኤል ኘሬዚዳንት ናቸው። የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ግንኙነት ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው።

ኢትዮጵያና እስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1956 ነው። ሁለቱም አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ኤምባሲ ከፍተው እየሰሩም ይገኛሉ። አገራቱ በግብርና ዘርፍ ጠንካራ ትስስር ያላቸው ሲሆን፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በደህንነት፣ በፀጥታና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ጠንካራ የጋራ ትብብር አላቸው።

የኢትዮጵያና እስራኤል የንግድ ልውውጥ በአሁኑ ጊዜ 60 ሚሊዮን ዶላር እንደደረሰ የደረሰ ሲሆን፤ በተለይ የእስራኤሉ ኩባንያ ‘ጊጋዋት ግሎባል’ የስራ ሃላፊዎች በያዝነው ዓመት ታህሳስ ወር መጨረሻ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ በኢትዮጵያ በታዳሽ ሃይልና በሰው ሃብት ልማት የ500 ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ተዘጋጅቷል። ኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ቡና፣ ቅመማ ቅመሞች፣ የቅባት እህሎች፣ የፍራፍሬና የጥራጥሬ ምርቶችን ስትልክ፤ የካፒታል እቃዎች፣ ማሽነሪዎች፣ የፕላስቲክ፣ የብረታ ብረትና የኬሚካል ውጤቶችንና የምግብ ምርቶችን ታስገባለች። ይህም በሁለቱ አገራት መካከል ካለው ታሪካዊ ግንኙነት ባሻገር በንግድና በኢንቨስትመንት ያላቸው ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።

ርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ የእስራኤል ኩባንያዎች ሊጠቀሙበት የሚገባ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የገበያ መር ኢኮኖሚ ሥርዓትን ተከትሎ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተነድፎ በሥራ ላይ ውሏል፡፡

በዚህም በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት የመሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሀብት ልማትን በማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት በመስጠት ለልማታዊ የግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የመደገፍ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

እርግጥ ማንኛውም የውጭ ግንኙነት ስራ ምን ያህል ለአንድ ሀገር ልማት ለማምጣት የውጭ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ አስተዋፅኦ አድርጓል ከሚል አኳያ የሚታይ ነው። በዚህረገድ ይህን ስራ የሚያከናውነው የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እጅግ በርካታ ተግባራትን ፈፅሟል፤ እየፈፀመም ነው።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መጥቷል ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት የማሳየታቸው ምስጢርም ይኸው ይመስለኛል።

አገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ትክክለኛ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ በግሉ ባለሃብት መሰራት የሚገባቸውና በመንግስት ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራት ተለይተው በመካሄዳቸው በሁለቱም በኩል ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው። የአገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሃብቶችን የሚሰማሩባቸውን ዘርፎች በመለየት አንፃራዊ በመሆነ መንገድ ለሀገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ እየተደረገ ነው።

የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ በመንግሥት ታምኖበት በፍትሃዊ ውድድር ላይ እንዲመሰረት በመደረጉ ባለፉት 27 ዓመታት በርካታ አገራዊ ባለሃብቶች ተፈጥረዋል። እነአዚህ ባለሃብቶች በዓለም የገበያ ውድድር ውስጥ ጠንካራ አቅም እንዲኖራቸው ቀጣይነት ያላቸው ድጋፎች እየተደረገላቸው ነው።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ባለሃብቶቹ የሃብት ባለቤት እንዲሆኑና ለዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ችለዋል። አሁንም በማሳየት ላይ ይገኛሉ። በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ዘርፍ የተገኘው ውጤት አበረታች ነው።

የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው ጥረት ቀጥተኛ የውጭ ምንዛሬን ከማምጣት ባሻገር በአገር ውስጥ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችንም እየደገፈ ነው። ኢትዮጵያ የምታከናውነው የልማት ፕሮጀክቶች ተገቢ የማይመስላቸው አንዳድ ወገኖችንም ጭምር ከነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ በሂደት ፈቀቅ እንዲሉ ያደረገ ነው።

የአገር ውስጥን ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በማቀናጀት ለመፍጠር የተቻለው የገበያ ትስስርም ምቹ የኢንቨስትመንት መሰረትን ጥሏል ማለት ይቻላል። ከእነዚህ ውስጥ የወጪ ንግድ የብድር ዋስትና ሥርዓት መተግበር፣ የውጪ ምንዛሪ ተመን ማስተካከልና የምንዛሪ ዋጋው በገበያ እንዲወሰን ማድረግ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ምቹ ሁኔታዎች ናቸው።

የኤክስፖርት ምርትን ከቀረጥ ነፃ ማድረግ፣ ለኢንቨስትመንት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ የካፒታል ዕቃዎችና ግብዓቶች ያለ ቅድመ- ሁኔታ የሚገቡበትን ዕድል የመፍጠር ብሎም ባለሃብቶቹ ለስራቸው የሚሆን መሬት በሊዝ እንዲያገኙ መደረጉ ተጨማሪ አመቺ መደላድሎች ነበሩ።

እነዚህ በመንግስት በኩል አቨስትመንትን ለማበረታታት የተወሰዱ እርምጃዎች የውጭ ባለሃብቶች ሀገራችን ላይ ዓይናቸውን እንዲጥሉ ያደረጉ ተግባራት ናቸው። እስራኤሎችም በአገራችን ውስጥ በኢንቨስትመንት ዘርፉ በስፋት በመሳተፍ ራሳውን ጠቅመው አገራችንንም ሊጠቅሙ ይችላሉ።

የእስራኤሉ ፕሬዚዳንት የአገራቸው ባለሃብቶች ወደ አገራችን በመምጣት ያለውን የተመቻቸ ሁኔታ ይበልጥ እንዲጠቀሙበት መገፋፋት ይኖርባቸዋል። የእስራኤል ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያካሂዱትን ኢንቨስትመንት በራሳቸው አገር ውስጥ እያደረጉ እንደሆነ ማመን ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የረዥም ጊዜ ታሪካዊ ቁርኝት ይህን ማድረግ የሚያስችል ስለሆነ ነው። ያም ሆኖ አሁን ባለው ሁኔታ የእስራኤል ፕሬዚዳንት ለመጀመሪያ ጊዜ አገራችንን መጎብኘታቸውና ከዚህ ቀደም ከነበረው ይበልጥ በጋራ ተባብሮ ለመስራት መፈለጋቸው በራሱ የአገራችንን የዲፕሎማሲ ድል ከፍታ የሚያሳይ ነው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy