Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሁለት ሃገር፣ አንድ ህዝብ

0 275

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሁለት ሃገር፣ አንድ ህዝብ

አለማየሁ አ

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ጎረቤታሞች ብቻ እይደሉም። ሁለቱም ሃገራት ተመሳሳይ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግና ልማድ ያላቸው የአፋርና ኢሳ ህዝቦች መኖሪያ ናቸው።  የስጋ ዝምድና ያላቸው፣ የአንድ ቤተሰብ አባላት፣ . . . ሆነው አንዱ የኢትዮጵያዊነት ሌላው ደግሞ የጅቡቲ ዜግነት ያላቸው ሰዎች አሉ። አሁን የጅቡቲ ዜግነት ያላቸው፣ የልጅነትና የወጣትነት እድሜያቸውን በኢትዮጵያ ያሳለፉ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኢትዮጵያ ያጠናቀቁ በርካቶች ናቸው። ጅቡቲ ተወልደው ያደጉ፣ የተማሩ፣ በተወሰነ እደሜያቸው ላይ ጅቡቲ ሄደው በህይወታቸው ላይ ጉልህ ለውጥ ያመጣ ጊዜ ያሳለፉ ኢትዮጵያውያንም በርካቶች ናቸው። በርካታ ጅቡቲያውያን ኢትዮጵያን እንደ ጎረቤት ሳይሆን እንደራሳቸው ሃገር ነው የሚያስቧት። በርካታ ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ። በኢትዮጵያና ጅቡቲ ከሚነገረው ተመሳሳይ የሱማሊኛና የአፋር ቋንቋ በተጨማሪ በርካታ ጅቡቲያውያን የአማርኛ ቋንቋ ይሰማሉ፤ አቀላጥፈው ይናገራሉም። ይህ በሁለቱ ሃገራት ህዝቦች መሃከል ያለውን ጠንካራ ማህበራዊ ግንኙነት ያሳያል።

ሁለቱ ሃገራት በአንድ ሃገር ውስጥ በተለያየ ስፍራ ያለውን ያህል የኢኮኖሚ ትስስርም አላቸው። ከመቶ አመት እድሜ በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያና ጅቡቲ የባቡር መስመር ከላይ የተገለጸውን የሁለቱን ህዝቦች ማህበራዊ ትስስር ከማጠናከሩ በተጨማሪ፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ ግንኙነት መመስረት አስችሏቸዋል። መሃል ሃገር የተመረቱ የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ለዕለት ፍጆታ የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ በሌሎች የሃገሪቱ ከተሞች የሚቀርበውን ያህል ለጅቡቲም ይቀርባል። የጅቡቲያውያን ነጋዴዎች ምርትም ሽንኩርትና ቲማቲም ጭኖ በሄደው ባቡር በማግስቱ ድሬደዋ፣ አዲስ አበባ፣ ሚኤሶ፣ አዳማ፣ አዲስ አበባ ይገባል።

ኢትዮጵያ 90 በመቶ ያህል የወጪና የገቢ ንግዷን የምታከናውነው በጅቡቲ ወደብ ነው። የጅቡቲ ወደብ በከፍተኛ መጠን የሚያገለግለው ኢትዮጵያን ነው። ጅቡቲ በዚህ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው የወደብ አገልግሎት በዓመት እስከ 2 ቢሊየን ዶላር እንደምታገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም የሃገሪቱን አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ግኝት 70 በመቶ ገደማ እንደሚሸፍን ይገመታል። ይህ በኢትዮጵያና ጅቡቲ መሃከል ያለው የመጠቃቀም ግንኙነትና ከዚህ መጠቃቀም የመነጨው መፈላለግ ምን ያህል ጥብቅ እንደሆነ ያመለክታል።

ሁለቱን ሃገራት ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ በንግድ ያስተሳሰረውና ከአንድ ማሳ እንዲመገቡ ማድረግ ያስቻለ የባቡር ትራንስፖርት ግንኙነት፣ በፍጥነትም በመጠንም እንዲያድግ ተደርጓል፤ በቅርቡ ስራ በጀመረው የኢትዮጵያና የጅቡቲ የባቡር መስመር አማካኝነት። አሁን የሁለቱ ሃገራት የመሰረተ ልማት ትስስር ከባቡር መስመርም አልፏል። ጀቡቲ 60 ሜጋ ዋት ያህል የኤሌትሪክ ሃይል ከኢትዮጵያ ትወስዳለች። ጅቡቲ የውሃ ፍጆታዋንም ከኢትዮጵያ ነው የምታገኘው። በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ፣ በቧንቧ መሰረተ ልማት በጅቡቲ ወደብ በኩል ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታስቧል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰሞኑን በጅቡቲ ያደረጉት ጉብኝት ለዚህ በሁለቱ ሃገራት መሃከል ላለ ጥብቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እውቅና መሰጠትን ያለመ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ቀደም ሲል በሁለቱ ሃገራት መሃከል የኢኮኖሚ ውህደት ለመመሰረት የተያዘውን እቅድ በተጨባጭ ወደመሬት ማወረድ የሚያስችሉ እርምጃዎችንም የመውሰድ ዓላማ ነበረው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጅቡቲ ጉብኝታቸው በሁለቱ ሃገራት መሃከል ስላለውና ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ተወያይተዋል። በተለይ ቀደም ሲል የታቀደውን የሁለቱን ሃገራት የኢኮኖሚ ውህደት ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል። ይህም አንዱ ሃገር በሌላው ሃገር የመሰረተ ልማት ላይ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግን የሚመለከት የመግባቢያ ስምምነት ነው።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር ሽርክና ያላቸው መሆኑ ይታወቃል። ሰሞኑን በመሪዎቻቸው አማካኝነት የገቡት የመሰረተ ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ ስምምነት ደግሞ ኢትዮጵያን በጅቡቲ የወደብ ድርሻ ባለቤት እንድትሆን የሚያስችላት ነው። ይህም ኢትዮጵያ በወደብ ክፍያ ውሳኔ ላይ ድምጽ እንዲኖራት የማድረግ አቅም እንደሚኖረው ተጠቁሟል። ስምምነቱ ጅቡቲንም በኢትዮጵያ በተመረጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ ባለድርሻ መሆን ያስችላታል። የመሰረተ ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ ስምምነቱ ሁለቱንም ሃገራት በእኩል ደረጃ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ የሚፈጸም ይሆናል። በእርሻ ልማት፣ በመንገድ ልማትና ሁለቱን ሃገራት ተጠቃሚ በሚያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመገንባትም ተስማምተዋል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ አንዱ በሌላው የመሰረተ ልማት ላይ የሚኖራቸው ድርሻ  የየሃገራቱ ኩባንያዎች ሃብት፣ የንግድ መጠንና ትርፋቸው ታይቶ የሚወሰን እንደሚሆን ታውቋል። ይህን ለማስፈጸም በሁለቱ ሃገራት በኩል የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተቋቁሟል። ስምምነቱን መነሻ በማድረግ የሚያካሂዱትን ጥናትም ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። በኢትዮጵያ በኩልም ጅቡቲ የምትሳተፍባቸው የተመረጡ መሰረተ ልማቶች በጥናት ተለይተው ውሳኔ የሚሰጥባቸው ይሆናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ በማስፈጸም ሂደት ውስጥ የፖሊሲ ለውጥ የሚያስፈልግ ከሆነ በተቋቋመው ኮሚቴ  በሚካሄድ ጥናት እንደሚለይ ተገልጿል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው ባሻገር ፖለቲካዊ ግንኙነትም አላቸው። ኢጋድን፣ ኮሜሳን፣ የአፍሪካ ህብረትንና የተባበሩት መንግሥታትን በመሳሰሉ  አካባቢያዊ፣ አህጉራዊና ዓለምአቀፍ ተቋማት አማካኝነት በትብብር ሲሰሩ ቆይተዋል። ኢትዮጵያና ጅቡቲ ሰላም የራቃቸውን ሃገራት ሰላም ለማረጋገጥም በኢጋድ ማዕቀፍ ስር ተቀራርበው ስኬታማ ስራዎችን ሰርተዋል። ይህን ግንኙነታቸውንና ትብብራቸውን አጠናክረው ለማስቀጠል ተስማምተዋል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ዘመናትን የተሻገረ ሊቋረጥ የማይችል የህዝብ ለህዝብ ማህበራዊ ግንኙነት አላቸው። ይህ ጥብቅ ግንኙነት ኢትዮጵያና ጅቡቲ ሁለት ሉአላዊ ሃገራት ቢሆኑም ህዝባቸው ግን አንድ እንዲሆን አድርጓል። ይህ የህዝቦች አንድነት በሁለቱ ሃገራት መሃከል ላለው የኢኮኖሚ – የገበያ ትስስር መሰረት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ ሃገራት የሚገኙበት ጂኦግራፊያዊ ስፍራ ኢትዮጵያ ጅቡቲ እንድታስፈልጋት፣ ጅቡቲም ኢትዮጵያ እንድታስፈልጋት አድርገዋል። ኢትዮጵያ የጅቡቲ ወደብ ያስፈልጋታል፤ ጅቡቲም ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ መጠቀሟን ትፈልገዋለች። በወደብ አጠቃቀም ጋር በተያየዘ በሁለቱ ሃገራት መሃከል ያለው መፈላላግ ከማህበራዊ ትስስሩ ጋር ተዛምዶ በባቡር፣ በመንገድና በአየር መንገድ መሰረተ ልማት ሁለቱን ሃገራት ማስተሳሰሩን የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የግድ እንዲሆን ያደርገዋል።

በሁለቱ ሃገራት መሃከል ያለው መፈላለግና ማህበራዊ ትስስር የኢኮኖሚ ውህደት በመመስረት ማጠናከር ለሁለቱም ሃገራት አስፈላጊ ነው። ከላይ የተገለጸው የኢኮኖሚ ውህደት ስምምነት ያስፈለገው ለዚህ ነው። ኢትዮጵያና ጅቡቲ ሁለት ሉዓላዊ ሃገራት ቢሆኑም ህዝባቸው አንድ በመሆኑና አንዱ ለሌላው እጅግ አስፈላጊ በመሆናቸው በመሃከላቸው ያለውን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ማሸጋጋር ወሳኝ ነው። በሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጅቡቲ ጉብኝትም የተደረገው ይሄው ነው።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy