ለለውጡ ውጤት
ታዬ ከበደ
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጉብኝቶች አገራችን እያካሄደች ካለችው የተሃድሶው እንቅስቃሴ ጋር የሚያያዙ ናቸው። በአሁኑ ሰዓት ተሃድሶው ገና ወደ መሬት አለመውረዱንና ከፍተኛ አመራሩ በሂደት በየደረጃው ካለው ህዝብ ጋር እየተገናኘ ውይይት ሲያካሂድ የጥልቅ ተሃድሶው እንቅስቃሴ በህዝብ ባለቤትነት ለውጤት ሊበቃ የሚችል ነው።
ማንኛውም የተሃድሶ ሂደት ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ውጤት ማምጣት ስለማይችል መንግስት በቀጣይ በየደረጃው ለሚያደርጋቸው ተግባሮች ህብረተሰቡ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል። ይህም አገራችን ውስጥ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን የላቀ ሚና ያበረክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመቐለ፣ በባህር ዳር፣ በጎንደር፣ በሀዋሳ፣ በባሌ፣ በአሶሳና በህዳሴው ግድብ ጉብኝቶችን አካሂደዋል። የእነዚህ ጉብኝቶች ዓላማ በአገራችን ውስጥ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ያለመና ስኬታማም የነበረ ነው። ይህም በቅድሚያ ከህብረተሰቡ ጋር ተነጋግሮ ለተጀመረው የለውጥ ስራ ህዝቡ የራሱን ሚና እንዲወጣ ያደረገ ነው።
የጥልቅ ተሃድሶው ዋነኛ ምክንያት መልካም አስተዳደርና ከእርሱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዩች ናቸው። ህዝቡ በየደረጃው ባለው የመንግስት አስፈፃሚ ምክንያት እየደረሰበት ያለው ችግርና እንግልት እንዲሰማለት ይፈልጋል። ይህን ለመፈፀም ደግሞ ቁርጠኝነት ያለውና ከእርሱ ውክልና የወሰደ መንግስት እንዳለው ያውቃል።
እርግጥ መንግስትም ቢሆን ይህን የህዝቡን ፍላጎት በመገንዘብ በጥልቅ ለመታደስ መወሰኑ፤ በአንድ በኩል የመንግስትን የግልፅነትና የተጠያቂነትን አሰራር ፍላጎት የሚያሳይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ የመደመጥ መብቱን መጠየቁ አግባብ መሆኑን የሚያመላክት ነው።
ታዲያ ይህ የመንግስት አቋም ህዝቡ በዴሞክራሲ ውስጥ ሆኖ ላቀረበው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በመስጠት ብቻ የተገታ አይደለም። ይልቁንም በጥልቅ ተሃድሶው በአቅምም ይሁን በኪራይ ሰብሳቢነት ችግር የተፈጠረውን የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶች ለመፍታት ህዝቡ ራሱ የመፍትሔው አካል ሆኖ በየደረጃው የሾማቸውን የመንግስት ስራ አስፈፃሚዎችን እስከማንሳት የደረሰ ዴሞክራሲያዊ አግባብን የተከተለ ነው።
ይህ ደግሞ ከህዝቡ ትክክለኛ ጥያቄ አንፃር ተገቢ ምላሽ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እንደ አንድ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ውጤት ያገኘበት ነው ማለት ይቻላል። ህዝቡ የሚፈልገውን ነገር እያገኘ በመሆኑ በውጤትነት መመዝገብ ያለበት ዕውነታ ይመስለኛል።
እንደሚታወቀው በሀገራችን ረጅም የፖለቲካ ሂደት ወስጥ የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ፍትሐዊ የዘመናት ጥያቄዎችን አንግቦና ከአምባገነኖች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ እንዲሁም የህይወትና የአካል መስዕዋትነትን ከፍሎ በአሸናፊነት የድል ፅዋን ያነሳው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ታሪክ በተሃድሶ ውስጥ ያለፈ ነው።
የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ድርጅቱን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊያመሩ የሚችሉ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህትና የጠባብነት የዝቅጠት አደጋዎችን በተካሄደው ተሃድሶ ችግሩን መቅረፍ ችሏል። የህዝቡን ሁለንተናዊ ዕድገት ሊያሳልጡ የሚችሉ ዙሪያ መለስ ስትራቴጂዎችም በመንደፍም ዛሬ ለምንገኝበት አስተማማኝ ሰላም፣ ዘላቂ ልማትና ስር የሚሰድ ዴሞክራሲ ዕውን እንዲሆን ተደርጓል።
በእኔ እምነት ይህ የድርጅቱ ተሃድሶ ሀገራችንን አሁን ላለችበት የዕድገት ጎዳና ያበቃት ነው። በወቅቱ በአንድ በኩል ስልጣንን የኢኮኖሚያዊ ሃብትና የብልፅግና መሳሪያ በማድረግ ፀረ-ዴክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት በሚሹ ወገኖች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን የሃብት ምንጭ እንዳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ እንዲያብብና እንዲዳብር ብሎም የጥገኝነት አስተሳሰብ የበላይነት እንዳያገኝ በሚተጉ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ግምገማና የመድረክ ትግል መካሄዱን እናስታውሳለን።
ታዲያ በድርጅቱ ውስጥ ተፈጥረው በነበሩት በእነዚህ ሁለት ፅንፍ አመለካከቶች ዙሪያ በተካሄዱ ግምገማዊ የሃሳብ ፍጭት፤ ስልጣን የጥቂቶች የሃብት ማካበቻ እንዳይሆን እንዲሁም ዴሞክራሲና ዴክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት ብሎም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ የበላይነት እንዳያገኝ የታገለው ወገን ነጥሮ በመውጣት ተሃድሶው ግቡን መትቷል፤ ውጤትም አምጥቷል።
እንደ እውነቱ ከሆነ በወቅቱ እንዲህ ዓይነቱ የተሃድሶ ርምጃ በድርጅቱ ውስጥ ባይካሄድ ኖሮ፤ ሀገራችን የምትመራባቸው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ስልቶች ባልተነደፉ ነበር። በድርጅቱ ውስጥ አቆጥቁጦ የነበረው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብም በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ ጋር አብሮ ባልከደሰመ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም በአንደኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕድገት የተገኘው ሁለንተናዊ እመርታ አይታሰብም ነበር። ሁለተኛ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕድገት ዕቅድም ሊታለም አይችልም።
ከሁሉም በላይ ለህዳሴያችን ጉዞ የመረባረብ ሃሳቡም አይኖረንም ነበር። እናም በወቅቱ የተካሄደው ተሃድሶ ውጤታማ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ ላለንበት ሀገራዊ ቁመና ፈር የቀደደ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ራሱን በራሱ እያረመ ለሚሄደው ኢህአዴግ ጠንካራ ትምህርት የሰጠው ይመስለኛል።
እርግጥ ኢህአዴግ ተሃድሶን ለታይታ የሚያደርግ ድርጅት አይደለም። የዛሬ 15 ዓመት ገደማ የተካሄደው የተሃድሶ መስመር የዚህ አባባሌ ሁነኛ አስረጅ ነው። በወቅቱ ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የተካሄደው ግምገማ ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ዋነኛ እንቅፋት የነበሩትን አስተሳሰቦች ማስወገድና አዲስ እሳቤን ማረጋገጥ ተችሏል።
ይህ ሁኔታም ድርጅቱ በውስጡም ይሁን እንደ ገዥ ፓርቲነቱ በሀገር ላይ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ በአስተማማኝ ሁኔታ በማስወገድ ፊቱን ወደ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲያዞር ያደረገው ነው።
በተሃድሶው ውጤትም መላው የሀገራችን ህዝቦች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት በበጎ ገፅታ ይበልጥ ጎልታ እንድትታይ ያደረጋት ይመስለኛል። የምትከተለው በሳል የዲፕሎማሲ መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷን ከማረጋገጥ ባሻገር፤ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች የሰላም ጠባቂ፣ መጠጊያና መጠለያ ሆናለች።
ኢህአዴግ ዳግም በመታደስ ሂደት ውስጥ ራሱንና የመንግስት አሰራሮችን ሲፈትሽ መነሻውም ሆነ መድረሻው ስር ነቀል ለውጥን ማዕከል ያደረገ መሆኑን በግልፅ ገልጿል። አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት የትኛውንም ወገን የሚለይ አይደለም።
መንግስት ከህዝቡ ጋር የተጀመራቸው የትግበራ ዓይነተኛ ሚና ተጫውተዋል። የዚህ ውጤትም በቅርቡ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል።
ይህ ተግባር ሁከትንና ብጥብጥን ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ ለሚሹ ኃይሎች የራስ ምታት ሆኗል። በዚህም የበሬ ወለደ አሉባልታ እያሰሙ ነው። እናም ጥልቅ ተሃድሶ በሁከት ሃይሎቹ አማካኝነት “አይሳካም” በማለት የሚነዛው አሉባልታን ባዶ ያስቀረ ነው። ያም ሆኖ የሁከት ኃይሎቹ በህዝቡ ውስጥ ውዥንብርና አሉባልታ በመንዛት ውይይቶቹን ለማደናቀፍ ለመጣር ቢሞክሩም ህዝቡ ራሱ የሰላሙ ባለቤት በመሆኑ ለቅጥፈታቸው ቦታ አልሰጣቸውም።
ይህ የመንግስት ቁርጠኛ አቋም መንግስት ዛሬም እንደ ትናንቱ ቃሉን የማያጥፍና ሁሌም የሚያካሂደው ተሃድሶ በውጤት የሚታጀብ መሆኑን ያሳየ ነው። መንግስት ትናንትም ይሁን ዛሬ ያከናወናቸውና የሚያከናውናቸው ተሃድሶዎች ተጨባጭ ውጤቶችን ያመጡ ናቸው።
መንግስት በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የተሃድሶ ሂደት የመንግስት መዋቅሮችን የህዝቡን እርካታ በሚፈጥሩ መንገድ እያከናወነ ነው። ይህ ሁኔታም ከዚህ ቀደም በነበሩ የተሃድሶ መንገዶች የተከናወኑ ተግባራትን የሚያጠናክርና ይበልጥ የሚያሰርፅ ነው።
ይህ የመንግስት የተሃድሶ ቁርጠኛ አቋም በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ መጎልበት አለበት። ኪራይ ሰብሳቢዎችንና መዝባሪ ሙሰኞችን ህዝቡ በሚገባ ያውቃቸዋል። ከህዝብ ዓይን የሚሰወር ምንም ዓይነት ተግባር ባለመኖሩ መንግስት እያካሄደ ላለው ቁርጠኛ አቋም ህዝብ የማይተካ ሚና አለው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ያደረጓቸው ጉብኝቶች እንዲህ ዓይነት መነሻዎችና ያሉትና ህዝባዊ መነቃቃትን የፈጠረ ነው።