ለሰላሙ እውን መሆን…
ገናናው በቀለ
የአገራችን ህዝብ የሰላሙ ባለቤት በመሆኑ ምክንያት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመላው አገሪቱ ውስጥ አጠቃላይ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ይህ ሰላምና መረጋጋት ይበልጥ አስተማማኝ ሲሆን አገራችንን ወደ ነበረችበት የኢንቨስትመንት ማዕከልነት መመለሷ አይቀርም።
በዚህም እያንዳንዱ ዜጋ ከሰላም በሚገኘው የዕድገት ትሩፋት በየደረጃው ተጠቃሚ ይሆናል። በመሆኑም በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ሳንዘናጋ ሁላችንም በየአካባቢያችን ለሰላማችን መረጋገጥ ጥረታችንን ማጠናከር ይኖርብናል። አሁንም ካላስፈላጊ ውዥንብሮች በመራቅ የተገኘውን ሰላም ማቀብ ይገባል።
አገራችን ውስጥ ሰላም ሰፍኖ ህዝቡ ከሰላሙ ተጠቃሚ በመሆን ወደ ጀመረው የልማት ተግባራት ላይ እንዳያተኩር የሚሹ አንዳንድ አካላት መኖራቸው ይታወቃል። “አዋጁ ቱሪዝምን እየጎዳ ነው፤ የኢንቨስትመንት ፍሰትንም ይጎዳል” የሚል ውዥንብር በመንዛት ላይ ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ በእነዚህ ወገኖች የሚሰነዘረው አሉባልታ ከአዋጁ መንፈስ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል—የአዋጁ ዓላማ የሰላሙ ባለቤት ለሆነው ህዝብ ተጨማሪ ጉልበት ለመስጠት እንጂ፣ እነዚህ አካላት እንደሚሉት ቱሪዝምንና ኢንቨስትመንትን ለመገደብ አይደለም።
እንደ እውነቱ ከሆነ የእነዚህ አካላት ፍላጎት ለሀገራችን ከማሰብ የመነጨ አለመሆኑ ይታወቃል። እንዲያውም ከመንግስትና ከህዝቡ በላይ ለዚህች ሀገር አሳቢ ሆነው በመቅረብ በተዘዋዋሪ አዋጁን ለማጥላላት የሚሰነዝሩት አባባል መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።
ያም ሆኖ መሬት ላይ ያለው ዕውነታ እነርሱ ከሚሉት ጋር የሚጋጭ ነው። ይኸውም የአዋጁ ግብና ዓላማ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተስተዋለውን የፀጥታ መደፍረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ለማዋል ብሎም የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ስለሆነ ነው።
በተለይም አዋጁ በየቦታው ተከስቶ ለነበረው ሁከት፣ ረብሻና ሥርዓት አልበኝነት ዋነኛ ምክንያቶችን በመግታት፤ ሀገራችንና ህዝቦቿ ወደ ነበሩበት የቱሪዝም ኢንዱስትሪና አሁንም ድረስ ያልቆመው የኢንቨስትመንት ፍሰት ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያደርግ እንጂ እነዚህን የልማት ዘርፎች የሚያላላ አይደለም።
ለሁሉም ዓይነት ልማት ሰላም መኖሩ የግድ ነው። ለቱሪዝም ፍሰት እና ለኢንቨስትመንት መስፋፋትም እንዲሁ የሰላም መኖር ወሳኝ ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ ቱሪዝምም ሆነ ኢንቨስትመንት ሊስፋፉና ሊያድጉ የሚችሉት አስተማማኝ ሰላምና ለዘርፎቹ ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ሲኖር ነው።
ከዚህ አኳያ ባለፉት 27 ዓመታት መንግስትና ህዝቡ የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ የሰላም መሰረት ላይ ለማቆም ባረደጉት ጥረት እንዲሁም መንግስት ለቱሪዝምም ሁነ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫን በመከተሉ፤ ሁለቱም ዘርፎች ከፍተኛ የሆነ እመርታ አሳይተዋል።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሀገራችን ሰላማዊነት በአደባባይ የተመሰከረ ጉዳይ ነው። ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገቧና የነገ ራዕይዋ ከወዲሁ እየታየ በመሆኑም የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች መዋዕለ ነዋያቸውን ሀገራችን ውስጥ በማፍሰስ አብረውን ለማደግ ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ገደማ ያህል ሀገራችን ውስጥ በተፈጠረው የመረጋጋት ችግር ወደ ነበርንበት የተረጋጋ ቦታችን ለመመለስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወጥቶ ከተለያዩ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ አካላትን ባቀፈ ኮማንድ ፖስት አማካኝነት ተግባራዊ እየሆነ ነው። አጠቃላይ ሰላምና መረጋጋት ተገኝቶ ተጨባጭ ውጤትም ተመዝግቧል። ህዝቡ ይህን ውጤት በማቀም ለላቀ ሰላማዊነት ይበልጥ መስራት አለበት።
የኢትዮጵያ ሰላም ላለፉት 27 ዓመታት በተከናወነው ተግባርና ባለፍናቸው ውጣ ውረዶች ሳቢያ በጥሩ መሰረት ላይ የተገነባ ነው። በቀላሉ የሚናድ አይደለም። ምንም እንኳን በየትኛውም ማህበረሰብ ውሰጥ ሰላም ያለው እሴታዊ ዋጋ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ያላቸው ሀገራት ሰላማቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲደፈርስ ብሎም በትርምስና ሁከት ውስጥ ሲቆዩ የተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም።
ከእኛ ሀገር አንፃር ግን ሰላማችን ሲጀመር የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ በቀላሉ ሊናጋ የሚችል አይመስለኝም። ሆኖም ልክ እንዳለፉት ጥቂት ዓመታት ሰላማችን የመሸራረፍ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሰላሙ ባለቤቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው በቀላሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ድንጋጌዎችን በማውጣት ማስተካከል ይቻላል።
አገራችን ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ እየሆነች ነው። ለዚህም ሰሞኑን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF)፤ ኢትዮጵያ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት የአፍሪካን የኢኮኖሚ መሪነት ከጋና እንደምትረከብ ተንብዩዋል።
ይህም ሀገራችን ውስጥ ለሁለት ዓመታት ያህል በአንዳንድ አካባቢዎች የነበረው ሁከትና ብጥብጥ በሀገራችን የልማት ግስጋሴ ውስጥ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ አለመፍጠሩን የሚያረጋግጥ ነው ማለት ይቻላል።
እርግጥ ሁከትና ብጥብጥ በነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የንብረት ውድመት ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ አልፈጠረም ሊባል አይቻልም። ይሁንና ችግሩ ከመንግስትና ከህዝብ አቅም በላይ የሚሆን አይደለም። በቀላሉ በመንግስትና በህዝቡ ጥረት ሊስተካከል የሚችልና እየተስተካከለ ያለ ጉዳይ ነው።
የሰላም መታጣት ትንሽ ባይኖረውም፤ ከጠቅላላው የሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ፣ ችግሩ ያስከተለው የልማት መስተጓጎል ትርጉም ያለው ነው የሚባል አይመስለኝም፤ የገንዘብ ተቋሙ ማረጋገጫም ይኸው ይመስለኛል።
በአጠቃላይ አዋጁ ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር ለልማት ምቹ ምህዳርን እየፈጠረ ነው ማለት ይቻላል። ይህ እውን ሊሆን የቻለውም በዋነኛነት ህብረተሰቡ የየአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ በመቻሉ ነው። ይህ ሰላምን በባለቤትነት ስሜት ተረክቦ የመጠበቅ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።