Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለቀጣዩ ትውልድ የቀረበ

0 285

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለቀጣዩ ትውልድ የቀረበ

ገጸ-በረከት!

አባ መላኩ

 

ዛሬ አገራችን  በፈጣን የለውጥ ምህዋር ውስጥ ነች። በአገራችን የሚስተዋለው ለውጥ ሁለንተናዊና ፈጣን ነው። መንግስት ለውጡን ለማስቀጠል እንዲቻል የወቅቱ የአገራችን ተግዳሮት  የሆነውን መልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጎልበት በርካታ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው። የተሻለች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማስተላለፍ  መልካም ጅምሮችን ማስቀጠል እንዲሁም ድክመቶችን ማስወገድ ይኖርብናል። በዚህ ረገድ የአሁኑ ትውልድ በርካታ መሰዋዕትነትን በመክፈል ዘመን ተሻጋሪ የሚባሉ ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ወጪን የሚጠይቁ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያ አድርጌ  የማቀርበው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ነው። ይሁንና አንዳንዶች ኢትዮጵያዊ ሆነው ሳለ ለዚህ ግድብ ያላቸው አመለካከት የተዛባ ሆኖ አገኝቼዋለሁ። ይህ ግድብ የኢትዮጵያዊያኖች እንጂ የመንግስትም ሆነ የኢህአዴግ አይደለም።

 

በየትኛውም አገር ሰዎች በሃይማኖት፣ በብሄር፣ በቋንቋ፣ በመልክ እንደሚለያዩ ሁሉ በሚከተሉት አይዲዮሎጂ ወይም የፖለቲካ ዕምነትም የተለያዩ ናቸው። ይህ ተፈጥሯዊና የሚጠበቅ ዕውነታ ነው። እነዚህ  ልዩነቶች ሁሉ ይስተዋሉ እንጂ በአገራቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ወይም ዘለቄታዊ ጥቅም ላይ ከቶ ሲለያዩ አንመለከትም። ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆኑት ግብጻዊያን ናቸው። ግብጻዊያን በውስጥ ጉዳያቸው ሲባሉና ሲናከሱ ይቆዩና የአባይ ጉዳይ ሲነሳ ሁሉም በአንድነት ተሰልፈው ፍትሃዊ ያልሆነውን  አቋማቸውን እንድንቀበል ሲወተውቱን ተመልክተናል። እንዲህ ያሉ አገራዊ ጥቅምን ታሳቢ ያደረገ አንድነትን ስመለከት ቅናት ይሰማኛል። እንዲህ ያለ አካሄድም በእኛ አገር እንዲለመድ ጓጓለሁ። ልዩነታችንን ልናራምድ የምንችለው እንኳን አገር ስትኖር አገራችን ሰላም ስትሆን መሆኑን እስክንዘነጋ   ድረስ አገር ሊያጠፋ ህዝብ ሊያጫርስ የሚችሉ አስተሳሰቦችን ካላራመድን ነጻነታችን ተገደበ የምንል አካላት አለን።

 

ከላይ ለማንሳት  እንደሞከርኩት የርካታ አገራት ዜጎች በውስጣዊ ጉዳያቸውና  በብሄራዊ ጥቅማቸው አንድ አይነት አቋም ያራምዳሉ ባይባልም ተቀራራቢ ሃሳቦች እንደሚኖራቸው ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።  በዚህ ረገድ እኛስ የት እንሆን ብለን ራሳችንን መጠየቅ የሚኖርብን ይመስለኛል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከውጩ ዓለም አለባበሶችንና አነጋገሮችን መኮረጅ  ብቻ ሳይሆን አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩና ብሄራዊ አንድነታችንን ሊያጠናክሩ የሚችሉ አካሄዶችንም መማር ይኖርብናል። ዛሬ ላይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎችን ለተመለከተ ሁኔታው አስፈሪ ሆኗል። በብሄርና በጎጥ ተከፋፍለን ምክንያታዊነትን አፈር ከዲቤ አስገብተነዋል።  

 

አሁን ላይ አገራችን የምስራቅ  አፍሪካ የኢኮኖሚ መዕከል ለመሆን  በርካታ ትላልቅ ስራዎችን በማከናወን ላይ ነች። እኛ በተለይ ወጣቱ የነገ አገር ተቀባይ ትውልዱ አገራችን የምትፈልገውን ዓይነት ደረጃ የሚመጥን አይመስለኝም።  ግብጻዊያን ለዘመናት ራሳቸውን ከአባይ ጋር ለማቆራኘት ባደረጉት ጥረት ዛሬ ላይ የአሰዋ ግድብ ለግብጻዊያን ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳነት ባሻገር የአንድነታቸው ማስተሳሰሪያ እና የአገራቸው ህልውና  አድርገው ይቆጥሩታል። እኛ ድርቅ እየተመታን፣ የሃይል እጥረት ክፉኛ እየተፈታተነን አባይን የሚያህል ውሃ እያመነጨን ለሌሎች ገጸበረከት ስናቀርብ ኖረናል።

 

ለሁሉም ጊዜ አለው እንደሚባለው  አገራችንም ዛሬ ላይ አቅም ፈጥራ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በራሷ አቅም መገንባት ጀምራለች። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አንዱና ዋንኛው ነው። ታላቁ  የህዳሴ ግድባችንም ለእኛ ኢትዮጵያዊያን ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባለፈ ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የትብብር መገለጫና የአንድነት ማሳያ መሆን ችሏል። ከዚህም ባሻገር ታላቁ   የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የብሄራዊ ኩራታችን መገለጫና የገጽታችን መለውጥ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ፕሮጀክት ነው። ይህ ፕሮጀክት እኛ ለልጆቻችን የምናቀርበው ገጸበረከት ነው።

 

የኢፌዴሪ መንግስት ከራሱ ዜጎች አልፎ የአካባቢው አገራት ህዝቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክቶችን  በመገንባት ላይ ነው። ይህ የመንግስታችን ጥረት ለሌሎች መንግስታት ተመሳሌት ሊሆን የሚችል ነው። የአገራችን ኤኮኖሚ በፈጣን ሁኔታ ማደግ ሲጀምር ከጎረቤት አገራት ጋር በንግድ፣ በባህል፣ በሰላም ማስከበር፣ ወዘተ  ትስስሩ እየጠነከረ መምጣት ጀምሯል። ኢትዮጵያና ጅቡቲ እጅግ የጠነከረ ግንኙነት በመፍጠር ዛሬ ላይ አንዷ አገር ለሌላኛዋ የህልወና ምንጭ እስከመሆን መድረሳቸውን በቅርቡ የሁለቱ አገራት መሪዎች ተናግረዋል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ማለትም  ሱዳን፣ ኬንያ፣ ከደቡብ ሱደን እንዲሁም ሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት ከፖለቲካው ባሻገር በኢኮኖሚውም ለመድገም የተለያዩ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለአብነት ዘመናዊ የመንገድ ግንባታ፣ የባቡር ሃዲድ ዝርጋታ፣ በአየር በረራ መስመሮች ማስፋፋት፣ የሃይል አቅርቦት ወዘተ  በማካሄድ ነች።

 

የኢትዮጵያ መንግስት የሚገነባቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ ከጎረቤት አገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱና መልካም ጉርብትናን የሚያጠናክሩ ናቸው።  የኢትዮጵያ መንግስት የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ይፋ ሲያደርግ ያራምደው የነበረው “በተፋሰሱ አገራት መካከል ፍተሃዊ የውሃ  ክፍፍል” የሚለው መርህ  አሁንም የአገራችን  ጠንካራ አቋም ነው። ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ለሃይል ማመንጫነት እንጂ ከዚያ ባለፈ ለመስኖ የሚሰጠው ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደ ግብጽ ወይም ሱዳን  ሰፊ የመስኖ መሬት የሌላት ከመሆኑም በላይ የግድቡ ስፍራ ወደ ሱዳን ጠረፍ የተጠጋ በመሆኑ የህዳሴው ግድብ ለመስኖ ስራ እምብዛም የሚያገለግል ግድብ አይደለም። ይህን ጉዳይ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ አሳውቃለች። ሱዳን ከኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች በተለይ ከተከዜ የሃይል ማመንጫ ግድብ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት  በመቻሏ የኢትዮጵያ የልማት ስራዎች አካባቢውን ሊጠቅሙ የሚችሉና የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስሩን የሚያሳድጉ መሆናቸውን ስትመለከት ለታላቁን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትም የማይናወጥ ድጋፉን ለግሳለች። አሁን ላይ ግብጻዊያንም ኢትዮጵያ ይዛው የተነሳቸውን ዕውነታ መረዳት የጀመሩ ይመስላሉ። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ሰሞኑን በመዲናችን የተደረገው የሶስቱ አገራት ውይይት በስምምነት መጠናቀቁ ነው።    

 

የአገራችን ኤኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ በሚያደርገው የመዋቅር ሽግግር  ሂደት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሃይል አቅርቦት ይፈልጋል። ኢትዮጵያ የጀመረችውን  ፈጣን የኤኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል የሚቻለው አሁን ላይ ያለውን ከፍተኛ የሃይል አቅርቦት ችግር መቅረፍ ሲቻል መሆኑን  መንግስት በማመኑ በርካታ የሃይል ማመንጫዎችን በመገነባት ላይ ይገኛል። ሁሉም የአገራንች የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የአካባቢ ብክነትን የማያስከትሉ ናቸው። እነዚህን ፕሮጀክቶቻችንን ዘላቂ ህይወት ለማረጋገጥ የተጀመሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎቻችንን አጠናክረን መቀጠል የኖርብናል።  

 

ኢትዮጵያ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል  በናይል ተፋሰስ አገሮች መካከል እንዲኖር  ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች። ይህ የአገራችን  አቋም የሁሉም የተፋሰሱ አገራት አቋም እንዲሆን መንግስት ተገቢውን የዲፕሎማሲ ስራ አከናውኗል። ይህ የአገራችን  የዲፕሎማሲ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት የተነሳቸው የግብፅን ወይም ሱዳንን ወይም ሌላ አገርን ጥቅም  ለመጉዳት አስባ ሳይሆን የሚስተዋልባትን ከፍተኛ የሃይል አቅርቦት ለመቅረፍ ነው። ይህ ፕሮጀክት ከምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳው ባለፈ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች   የትብብር መገለጫና የአንድነት ማሳያ በመሆን የአገራችንን አንድነት አጠናክሯል። ከዚህም ባሻገር ይህ ፕሮጀክት እኛ ለልጆቻችን የምናቀርበው ገጸበረከት ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy