Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለበለጠ ተግባር…

0 307

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለበለጠ ተግባር…

ዳዊት ምትኩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጎረቤት አገራት ያካሄዱት ጉብኝት አገራችን ካለ መረጋጋት ወጥታ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላትን ፈርጀ ብዙ ግንኙነት ለማስቀጠል ያላትን ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ግንኙነቱን በላቀ ሁኔታ ከፍ ለማድረግ በሙሉ አቅም መስራት መጀመሯን የሚያሳይ ነው። በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የምትጫወተውን የግንባር ቀደምትነት ሚና የበለጠ ለማረጋገጥና ለማስቀጠል እየተንቀሳቀሰች መሆኗንም ያመላክታል።

ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክም በአዲስ ገፅታ መታየት ከጀመረች ቆይታለች። በዚህም ሳቢያ ሀገሪቱ በምስራቅ አፍሪካም ይሁን በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረኮች ተሰሚነቷ እየጎለበተ መጥቷል። የዲፕሎማሲው ተሰሚነቷ ሁሉንም የቀጣናውን ብሎም የአህጉሪቱን ሀገራት እየሳበ በመምጣቱም ዛሬ የኢትዮጵያን ምክርና ልምድ ለመጠየቅ ወደ መዲናችን የሚያቀኑ የአፍሪካ መሪዎች እየተበራከቱ እንዲመጡ ምክንያት ሆኗል።

ለዚህም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ የሰፈሩት ወሳኝ የዲፕሎማሲ አቅጣጫዎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። ህገ መንግሥቱ የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝና በገራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ መሰረትን እውን አድርጓል። ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮንም ተጫውቷል።

እርግጥ ኢትዮጵያ ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖራት ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ በሚቀንስ ደረጃ የተተለመ ነው። ይህም ዲፕሎማሲው በበቂ ጥናት ላይ ተመስርቶ አደጋዎችን የመቀነስ እንዲሁም ቀጣናዊ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ የማድረግ መንገድን የሚከተል ነው።

ይህ ሁኔታም ሀገራችን እስከ ዛሬ ድረስ የተከተለችው ቀጣናዊ የዲፕማሲ ትስስር በተቃና ሁኔታ እንዲፈፀም ምክንያት የሆነ ይመስለኛል። ይሁንና አሁንም በቀጣናው ውስጥ የሚያታዩትን እንደ አልሸባብ ዓይነት አሸባሪዎችን ለመከላከል፣ በደቡብ ሱዳን ውስጥ የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግና የቀንዱ አንዳንድ ሀገራት የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገባዊ አካሄድ ለማስቆም ብሎም እንደ ኤርትራ ዓይነት ኃላፊነት የማይሰማቸው መንግስታት በቀጣናው ያልተቋጩ ቀውሶች ውስጥ በአሉታዊ መንገድ እጃቸውን ለማስገባት የሚያደርጉትን ጥረት ለመከላከል ያስችላል።

የክፍለ-አህጉሩ ሀገራት ዛሬም ቢሆን በጠንካራ የዲፕሎማሲ ገመድ ሊተሳሰሩ ይገባል። ትስስሩም በእኩል ተጠቃሚነት ላይ የሚያተኩር መሆን ይኖርበታል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ይህንን እውነታ በላቀ ሚና አገራችን እንድትወጣ ነው ወደ ጎረቤት አገሮች በማቅናት ጉብኝት ያደረጉት።

የዲፕሎማሲው ትስስር ገመድ የቀጣናውን ህዝቦች ጥቅም ብቻ ያማከለ ሊሆን ይገባዋል። የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በባህል፣ በታሪክ፣ በአብሮ መኖር፣ በመዋለድና አንዱ የሌላኛውን ሀገር እንደ ሁለተኛ መኖሪያው በመቁጠር የቅርብ ግንኙነት የታጠረ ነው።

በመሆኑም የቀጣናው ሀገራት ይህን ዘመናትን የተሻገረ የህዝቦች ጥብቅ ቁርኝት በዘመናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ አጥብቀው ማሰር ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ በየጊዜው እየተገናኙ የሚያደርጓቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር መለወጥ ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያ መንግስትም በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካኝነት ወደ ስምምነቶቹን ወደ ተግባር ለመለወጥ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት ገደማ ያካበተቻቸውን ተጨባጭ ተሞክሮዎች በመቀመር የመሪነት ሚናዋን በተገቢው ሁኔታ እየተወጣች ነው። እርግጥ አገራችን በራሷም ሆነ በአካባቢው ሀገራት የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ግጭቶችና ውዝግቦች በሰላማዊ ጥረት እንዲፈቱ ብቻ ሳይሆን፤ የሰላምና የትብብር አድማስ በዲፕሎማሲ ታጅቦ እንዲሰፋ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርባታል።

ለዚህም አገራችን የምትከተለው የትብብርና የሰላም ዲፕሎማሲ መርሆዎች ያግዟታል። መርሆዎቹ የቀጣናው አገራት በጋራ ለመልማት የሚያስችሏቸው በመሆናቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ ሁሉንም የጎረቤት አገራት አሸናፊ የሚያደርጉ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ወደ ጎረቤት አገር የሄዱት እነዚህን መርሆዎች ተመርኩዘው ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ኢትዮጵያ ዛሬ ጎረቤት ሀገሮችንም ሆነ ሌሎችን በጠላትነት የመፈረጅ አካሄድን አትከተልም። ከዚህ ይልቅ ለውስጥ ችግሮቿ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥታለች። ድህነት በተሰኘው አሳፋሪ ጠላቷ ላይ ጠንካራ የህዝቦቿን ክንድ እያስተባበረች ነው።

ይህም የቀጣናው ብሎም የአህጉሪቱ የልማት እመርታ ተምሳሌት ሆናለች። ሆኖም ይህ የልማት እመርታዋ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በዙሪያዋ ያሉት ጎረቤቶቿም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠንካራ አካባቢያዊ ትብብርና የዲፕሎማሲ ቁርኝት የግድ ይላታል።

በምንገኝበት 21ኛው ክፍለ ዘመን አንድ ሀገር ‘ነገር ዓለሙን ሁሉ ጥሎ’ ለብቻው እየቆዘመ ሊኖር አይችልም። ዘመኑ የሉላዊነት በመሆኑም እንኳንስ በአቅራቢያ ካሉት የቀጣናው ሀገራት ቀርቶ እጅግ በራቀ ሁኔታ ውስጥ ከሚገኙ ህዝቦችና ሀገሮች ጋርም ቢሆን መቀራረብና አብሮ መስራት ይጠይቃል።

በዚህ ዓለም እንደ አንድ መንደር በምትቆጠርበት ዘመን ውስጥ የተለያዩ ሀገራት ባለሃብቶች አህጉሮችን አቋርጠው ለኢንቨስትመንት ስራ ወደ ቀጣናው ሀገራት የሚመጡት በዲፕሎማሲያዊ ቁርኝነት ምክንያት ነው። እናም እኛ የሌለን ከባለሃብቶቹ ማግኘት ስለምንችል፤ ተቀራርቦ ለጋራ ጥቅም አብሮ መስራት ያስፈልጋል።

ከዚህ አኳያ “ሩቅ አሳቢ፣ ቅርብ አዳሪ” የሚለው ሀገራዊ ይትብሃል አይሰራም። ይልቁንም ጠቃሚው ነገር ሩቅ አስቦ፣ ለጋራ ተጠቃሚነት ሩቅ ማደርን እንደ መርህ መከተል ተገቢ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።  

ስለሆነም እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት በዲፕሎማሲያዊ የቁርኝት ድር ለጋራ ተጠቃሚነት ሩቅ ለማደር የሻተ አገር፤ እዚሁ በአቅራቢያው ካሉት ጎረቤቶቹ ጋር በዲፕሎማሲው መስክ ለመተሳሰር የግድ ይለዋል።

እናም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጉብኝት መነሻው ይኸው ነው። መድረሻውም የጋራ ተጠቃሚነት፣ በትብብር አብሮ መልማትና ምስራቅ አፍሪካን የሌሎች የአህጉሪቱ ሌሎች ክፍለ አህጉሮች ተጠቃሽ ማድረግ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተከተሉት ያሉት ትክክለኛ መንገድ በቅድሚያ በመነጋገር ተስማምቶ ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችል በመሆኑ በበለጠ ተግባር ሊጠናከር ይገባዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy