Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

             ለውጥ የዕድገት መሠረት

0 272

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

             ለውጥ የዕድገት መሠረት

ይልቃል ፍርዱ

የደፈረሰው ሀገራዊ የፖለቲካ አየር ትኩሳቱና ቀውሱ የሚለባለበው ትንፋግ ተገግ ብሎአል፡፡ምን ይመጣብን ይሆን የሚለው በሕዝቡ ውስጥ ነግሶ የነበረው የፍርሀት ድባብ ተገፎአል፡፡በየኮሪደሩ በየመንደሩ በየሰፈሩ በየመስሪያቤቱ በየእድሩ ሲጠበብ የነበረው የመሸበርና የመጨነቅ ትኩሳት ግለቱ በርዶአል፡፡በሀገሪቱ ዳር እስከ ዳር አንዳች ተአምራዊ ጸበል የተረጨ ነው የሚመስለው፡፡አዎን አሁን ካለውም በላይ ሰላማችንን ያብዛልን፡፡ ሀገራችን የሰላምና የፍቅር የተረጋጋች ምድር ትሆንልን ዘንድ ሁሌም ምኞታችን ነው፡፡

የትላንት ጭንቀት ዛሬ የለም፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ በመላው ሀገሪቱ ሊባል በሚችል መልኩ በመዘዋወር ከሕዝብ ጋር በቀጥታ በመገናኘት በመወያየት የሰሩት ስራ ነው ሀገሪቱን ወደመረጋጋት የመለሳት፡፡ከጭንቀት የተላቀቀ ነፍስ የዘራባት፡፡ የሰላም ተስፋ አየር እነሆ በምድሪቱ እየነፈሰ ነው፡፡የምንፈልገውም ይሄንኑ ነበር፡፡የሰላም ዋጋ ውድና ተመን የሌለው መሆኑን እናውቃለን፡፡የሀገር ሰላም የሕዝብ ሰላም ነው፡፡ድንቅ ስራ ታላቅ ስራ ነው በአጭር ቀናት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ የሰሩት፡፡ የሰላም መስፈኑም ምስጢር ይሀው ነው፡፡ለውጥ ይበረታታል፡፡የእድገት ሞተር ነው፡፡

ከሰሜን ጫፍ እስከ አዋሳ ፤በምስራቅ ከጅጅጋ እስከ መሀል ኦሮሚያና አምቦ፤ አባይ ማዶ ባሕርዳርና ጎንደር ሲናጥ የከረመው፤በሰላም እጦትና በሕዝብ አቤቱታ በመብቴ ይከበርልኝ ጥያቄ ሲናጋ ለሶስት አመታት የዘለቀው ትርምስ እነሆ ጸጥ እረጭ ብሎአል፡፡የደፈረሰው ሀገራዊ ሰላም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደመንበረ ስልጣኑ ከመጡ ወዲህ ተረጋግቶአል፡፡ በአራቱም ማእዘናት የሀገሬው ወግ ሙሉ በሙሉ ተቀይሮአል፡፡ሰላም፡፡ ሰላም፡፡ ሰላም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥንትም ሆነ ዛሬ ለሀገሩ ያለውን ጥልቅ ፍቅር በቃላት ለመግለጽ ያዳግታል፡፡መለኪያ መስፈሪያ የለውም፡፡ግንባሩን ለጥይት ደረቱን ለጦር እየሰጠ ሀገሩን ያስከበረ ጀግና ሕዝብ ነው፡፡ዛሬም ወደፊትም ይህንኑ የጸና ቃሉን ጠብቆ ይኖራል፡፡ የሀገሩን ሰላምና ደሕንነት ጉዳይ በተመለከተ ከማንም ጋር ድርድር አይቀመጥም፡፡ ተቀምጦም አያውቅም፡፡ያለንን ይዘን የበለጠ በመስራት ሀገራችንን መለወጥ ማሳደግ ባለን ላይ መደመር ብቻ ነው ምርጫችን፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ እንደገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን የአያቶቻቸው የአባቶቻቸው በደም ውርስና ማሕተም የታተመች የጸናች የአደራና የቃልኪዳን መሬታቸው ናት፡፡በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት ላይ ከሰማይ በታች ድርድር ንግግር የለም፡፡ዛሬ ደግሞ በአዲስ መንፈስ ብርታትና ጉልበት ኢትዮጵያዊነት ዳግም ትንሳኤውን አግኝቶአል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ደግመው ደጋግመው አበክረው የገለጹትም ይህን እውነት ነው፡፡   

ይህ ከትውልድ ትውልድ የጸና ለሀገር ፍቅር ያለ ጥልቅ እምነት ጥንት ተጠብቆ እንደኖረ ሁሉ ዛሬም ጸንቶ በትውልድ ፈረቃ ይቀጥላል፡፡በጥንታዊ ስልጣኔ ታላቅ የነበረችው ሀገር የቁልቁለት መንገድ ለመሄድ የበቃችው የራስዋ ልጆች በጋራ መቆም መነጋጋር መወያየት መደማመጥ እየተሳናቸው እርስ በእርስ በሚያደርጉት መናቆርና ፍትጊያ መጠፋፋትና መበላላት ምክንያት ነው፡፡ የእድገት ጉዞዋ ለዘመናት ሲጓተት የኖረበት ሁኔታ መነሻ ምክንያቱም ይሀው ነበር፡፡

አዲስ የእድገት እርምጃ ተጀምሮ በመልካም ጉዞ ላይ በነበረበት ሁኔታ ላይ ዳግም ሀገራዊ ችግር ተከስቶ ቆይቶአል፡፡ዛሬ ከዚህ ውስብስብ ችግር ለመውጣት እንደገና በአዲስ የለውጥ ምእራፍ ደጃፍ ላይ ነን፡፡በአዲስ አመራር አዲስ የለውጥ ጉዞ እየተካሄደ ነው፡፡

የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር የፍትሕ እጦት ዜጎችን የሚያማርር በመሆኑ ሀገር ገዳይ በሽታ ነው፡፡ከዚህ ችግር ለመውጣትና ለመላቀቅ የቱንም ያህል ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከትና ልዩነት ቢኖራቸውም በሰለጠነ መንገድ በመቀራረብ በመወያየት በመነጋጋር በመደማመጥ በመከባባር ችግሮቹ ሁሉ እንዲፈቱ ለማድረግ መስራት ለሀገርም ለሕዝብም ይጠቅማል፡፡ሁለግዜም መወነጃጀሉ፤መካሰሱ፤ስም ማጥፋቱ፤አንዱ በሌላው ላይ ጣት መቀሰሩ ችግሮችን ብቻ ማውራቱና ማግዘፉ ሀገራዊ መፍትሄ አያስገኝም፡፡ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻና ኃላፊነት ሲወጣ ነው ትክክለኛ ለውጥ ሊገኝ የሚችለው፡፡

የሰለጠኑና ያደጉ የሚባሉት ሀገሮችም በአንድ ግዜ የላቀና የመጠቀ ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ሰፊ ግዜና ሂደት ጠንክሮ መስራት ነው ለውጥ የሚያመጣው፡፡ ሌሎችም ሀገራት የውስጥ ችግሮቻቸውን በሰለጠነ መንገድ እየፈቱ ነው ለትልቅነት የበቁት፡፡ እየተፋጁ እየተላለቁ አይደለም፡፡እኛም ከበርካታ ሀገራት ውድቀት በመማር ሀገራችንን መጠበቅ ልዩነቶቻችንን አቻችለን አጥብበን የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ በሰላማዊ መንገድ የመስራት ፖቲካዊ ባሕልን ማዳበር አለብን፡፡ተከታዩ ትውልድ ይሄንን በአርአያነት እንዲከተል መንገዱን ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ የሚመራው አዲሱ ካቢኔ ታላቅ ሀገራዊ ተስፋዎችን ሰንቆ ከፍተኛ ለውጦች ለማስመዝገብ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ይሄንን መልካም ጅምር ሁሉም ዜጋ በቀናነት ማገዝ ለችግሮችም መፍትሄ ለማስገኘት የየበኩሉን ድርሻ መወጣት ይገባዋል፡፡ሀገራዊ ችግሮቻችን የቆዩና ስር የሰደዱ በመሆናቸው በአንድ ግዜ ሊፈቱ አይችሉም፡፡

ወደተሻለ ሀገራዊ እድገት ለመረማመድ ኃላፊነቱ ለመንግስት ብቻ የሚጣል አይደለም፡፡ መንግስት በሕዝብ ምርጫ በመሪነት ይቀመጥ እንጂ ዋናው የሀገሩ ባለቤት ወሳኙ ኃይል ሕዝብ ነው፡፡ሀገር ስታድግ ስትለማ ስትበለጽግ ተጠቃሚው ሕዝብ ነው፡፡በሚፈጠር ችግርም ተጎጂው ሕዝብ ነው፡፡ይሄንን የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድን አመራር በመልካም አጋጣሚነት በመጠቀም የተሻሉ ሀገራዊ ለውጦች እንዲመጡ ማገዝ ሀገራዊ ሰላማችንን ነቅተን መጠበቅ በተፈጠረው ሁከት የተቀዛቀዘው ሀገራዊ ኢኮኖሚያችን እንዲያድግ ተግቶ በርብርብ መስራት ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባን ጉዳይ ነው፡፡ መንግስታት በታሪክ አጋጣሚ ይመጣሉ፡፡ይሄዳሉ፡፡ሀገርና ትውልድ በፈረቃ ይቀጥላሉ፡፡

ሀገር ቀጣይ እንደመሆኗ መጠን ከመጠፋፋት ከመገዳደል ወንድም ወንድሙን ከማሳደድ  ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጅ ትሩፋት ማስገኘት አይቻልም፡፡ዛሬ ሕዝብን ከዳር እስከዳር ያስደሰተ ከልብ ያስፈነደቀ ታላቅ ሀገራዊ ብሩህ ተስፋን የሰነቀ አዲስ የኢሕአዴግ አመራር ወደ መድረክ መጥቶአል፡፡ኢሕአዴግ በጥልቀታዊ ተሀድሶው በገባው ቃል መሰረት ቃሉን ጠብቆ የሚታዩ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡የሕዝብንም ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ይፈታል፡፡ለዚህ ትእግሰት ሊኖረን ይገባል፡፡ለውጥ የሕብረተሰብ እድገት የማእዘን ድንጋይ ነው፡፡ኢሕአዴግ ዛሬ ለውጥ እንዳመጣ ሁሉ ወደፊትም በለውጥ ምእራፍ ይቀጥላል፡፡

ኢሕአዴግ በሀገር ደረጃ ታላላቅ የኢኮኖሚ ልማትና እድገት ስራዎችን የሰራ በዚህም በሀገራችን ታሪክ ቀድሞ ያልነበሩ የመሰረተ ልማት መስፋፋትን ዳር እስከዳር እውን ያደረገ በርካታ ግድቦችን ታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ እውን ያደረገ በብዙ መስኮች ለቀጣዩ ትውልድ የሚበጁ ተግባሮችን የከወነ ፓርቲ ነው፡፡

በውስጡ የተፈጠረውን የአመራር ችግር በመፍታት አዲስ አመራር ሰይሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ይህ አይነቱ የአመራር  ችግር በኢትዮጵያ ብቻ የተከስተ አይደለም፡፡ በበርካታ ሀገራት ውስጥ ተከስቶአል፡፡ትልቁ ነጥብ ችግሩንና ቀውሱን ለመፍታት የሚኬድበት መንገድና ስልት ነው፡፡በዚህም መሰረት የተሻሉ ስርነቀል ለውጦችን ለማምጣት የተቻሉባቸው ታሪኮች ተመዝግበዋል፡፡እኛ ሀገር በአመራር ደረጃ  የተፈጠሩት ችግሮች በሌሎችም ሀገራት በስፋት ታይተዋል፡፡

አንዳንዶቹ ለሀገር መበታተንና መፍረስ ምክንያት ሲሆኑ በሌሎች ደግሞ የተሻሉ ለውጦችን ለማምጣት ምክንያት ሆነዋል፡፡በዚህም አፍራሽና ገንቢ ታሪክ ተመዝግቦ አልፎአል፡፡ኢሕአዴግ ዳግም አዲስ ታሪክ ይሰራል፡፡ይሄንን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ስራዎቹ እውን ሁነው ለማየት ግዜ የሚጠይቁ መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡፡በጥድፊያና በችኮላ የሚገኝና የሚመጣ ለውጥ የለም፡፡

የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ ሰው ሁሉ ይወለዳሉ፤ያድጋሉ፤ያረጃሉ፤ይሞታሉ፡፡በምትካቸውም ከውስጣቸው የሚወጣ አዲስዘር ይበቅላል፡፡ዘመኑን ተከትሎ ወቅቱን አንብቦ የሕብረተሰቡን እድገት ሕግ ተከትሎ የሚራመድ ፓርቲ በአዲስ የለውጥ ምእራፍ የመምራት አቅም ያገኛል፡፡ኢሕአዴግ አሁን የተከተለው የለውጥ መንገድ የእድገት ሕግጋትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ከትላንት የበለጠ የተሻሉ ለውጦች ይመጣሉ፡፡ለውጥ የእድገት መሰረት ነው፡፡

ማጠቃለያ

ፓርቲዎች ከዘመን ተለዋዋጭነት፤ከሕብረተሰብ እድገት፤ከቴክኒዪሎጂው ምጥቀት አንጻር ሲመዘን በበርካታ ማሕበረሰባዊ ፈተናዎች ውስጥ ይፈተናሉ፡፡ፈተናዎቹን በብቃት ማለፍ የሚችሉት በአዲስ የታሪክ ምእራፍ ይቀጥላሉ፡፡የማይችሉት በታሪክ ፊት ይወድቃሉ፡፡ በታሪክ ውስጥ በሚፈጠር ሂደት ጥሎ ማለፍ የነበረና ያለ ነው፡፡አዲሱ ከአሮጌው ውስጥ ይወለዳል፡፡ተፈልቅቆ ይወጣል፡፡አዲስ ሁኖ በአስተሳሰብም በተግባርም ብቃት ተላብሶ በመቀጠል ይሰራል፡፡ደግሞ በተራው አዲሱም አዲስነቱ ያበቃል፡፡ሌላ ለውጥ ሌላ ሂደት ይጠይቃል፡፡ዳይሌክቲክሱ እንዲህ ነው፡፡በዛሬው ላይ ለተገኙት ወሳኝ ለውጦች ዋናው የውስጥ ትግሉ ውጤት ነው፡፡የሕዝቡም ግፊትና ጫና ታላቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ለሁሉም ለውጥ የሕብረተሰብ እድገት ቅመም ነው፡፡ሰላማዊ ለውጥ የበለጠ ለሀገር ለሕብረተሰብ ለመስራት ያተጋል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy