Artcles

መውጫው መንገድ

By Admin

May 03, 2018

መውጫው መንገድ

ገናናው በቀለ

የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት የአገራችንን ውስብስብ ችግሮችና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ የፈታና በቀጣይም ሊያጋጥሙን የሚችሉትን ችግሮች የመፍታት አቅም ያለው ነው። አሁንም ይሁን ወደፊት የሚያጋጥሙንን ተግዳሮቶች በህግና በህግ አግባብ እንዲሁም በሰላማዊ መንገድ ብቻ በመፍታት የችግሮች መውጫ መንገድ የሆነና የሚሆንም ነው። አገራዊ አንድነታችንን ጠብቀን ለትውልድ ማሸጋገር እንደሚኖርብን መግባባት ላይ በተደረሰበት በአሁኑ ወቅት፤ ህገ መንግሥቱ የህዝቦችን ጥቅም እያረጋገጠ ወሳኝ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ይቀጥላል።

ህገ መንግስቱና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲኖርና ህዝቦች ማናቸውንም ዓይነት ጥያቄዎችን ማንሳት እንዲችሉ እድል ከመስጠት ባለፈ፤ በህግና በስርዓት ምላሽ መስጠት የሚችል አቅም ያለው ነው። በቅርቡ መነጋገሪያ አጀንዳ የነበረው የቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ህገ መንግስቱ ምን ያህል ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ እንዳለው የሚያሳይ ነው። ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ በኢትዮጵያ ለሚነሱ ማናቸውም ጥያቄዎች በቂ ምላሽ የመስጠት አቅምና ብቃት ያለው መሆኑን አንድ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአገራችን ውስጥ እያንዳንዱ ማንነት በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ ታሪኩን የመንከባከብ መብት አለው። ከዚህ በተጨማሪ እያንዳንድ ማንነት ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት እንዲረጋገጥለት ተደርጓል። የማንነታችን ልዩነት በብዝሃነታችን ውስጥ የምንደምቅበት አውድ እንጂ ለመለያየታችን ምክንያት ሊሆን እንደማይችል በግልፅ ተቀምጧል። የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤቶች ብዝሃነታችን መድመቂያ ጌጣችን እንጂ የመለያያ ገመዳችን አለመሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው።

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዝሃነት የፌዴራላዊ ስርዓቱ የማዕዘን ድንጋይ ብቻ አይደለም። ሀገራችን ያጠናቀቀችውን የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በአብዛኛው ማሳካት የቻለ እንዲሁም ሁለተኛውን የልማት ትልም በአጥጋቢ ሁኔታ መፈፀም የምንችልበት ኃይልና ጉልበት ጭምርም ነው። ብዝሃነትን አክብሮ ለማንነት የሚሰጥ ምላሽ የህገ መንግስታችን ዋነኛ መገለጫ ነው።

ሁላችንም እንደምናስታውሰው የደርግ መንግሥት በወደቀ ማግስት ኢትዮጵያ ትበታተናለች የተባለውና በብዙዎች በቋንቋ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአንድነት ዋስትና አይሰጥም ተብሎ የተነገረው አፈ ታሪክ መሰረት የሌለው ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ህዝቦች ብዝሃነት ከግምት ውስጥ ያላስገባም መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብዝሃነት የሀገራችን ጉልበትና አቅም ሆኗል። ሀገራችን ውስጥ ያሉት የተለያዩ ማንነቶች በተናጠል ከሚያስገኙት ጥቅም ይልቅ በጋራ የላቀ ጥቅም እንደሚያገኙ አብረው በቆዩባቸው ጊዜያት ማረጋገጥ ችለዋል። ህብረታቸውን የሚፈታተንና ሰላማቸውን የሚያናጋ ኃይል በጋራ ታግለው ማሸነፋቸው የዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅ ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የታየውን የብዝሃነት ህብረትን እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያለውን ከፍተኛ መነቃቃትና ተነሳሽነት ብቻ መጥቀሱ ከበቂ በላይ ማሳያዎች ይመስሉኛል።

ምንም እንኳን አንዳንዶች በብሔርና በጎሳ የተመሠረተ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር እንደማይሰራ ቢገልፁም፤ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ልምድ የሚያሳየው ግን ከእነርሱ ምልከታ የተለየን ሁኔታ ነው። ብዝሃነት የመጪው ዘመን ዕድላችን በር መክፈቻ ሆኗል።

ሆኖም በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ብዝሃነትን ዕድል ማድረግ የሚቻለው ማንነቶች የሀገርና የሥርዓት ግንባታ ባለቤቶች ማድረግ ሲቻል እንደሆነ ያለፉት ዓመታት ልምድ ትምህርት ሰጥተው አልፈዋል።

በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ተከታታይና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገቡን በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ የብዝሃነት አያያዝ ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ምርጥ ትምህርት የሚሰጥ ሆኗል። በዚህም ብዝሃነት በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ወሳኝ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አውድ ሊሆን ችሏል።

ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የብዝሃነት መሰረቶች የፌዴራላዊ ስርዓቱ ምሶሶና ማገር ናቸው። መሰረቶቹም በስርዓቱ የፖለቲካ ግንባታ ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ናቸው።  በኢፌዴሪ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው አካሄድም ይህንኑ ሃቅ የሚደግፍ ነው።

የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት በብዝሃነት ውስጥ ላሉ ማንነቶች የሰጠው መብት ከብዙ ፌዴሬሽኖች ጋር ሲነጻጸር የላቀና ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ ነው ማለት ይቻላል።

የሥርዓቱ የማንነቶች አያያዝ ብዝሃነትን እንደ እድል ከሚያይ አስተሳሰብ ይመነጫል። ይህም በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አጠቃላይ መንፈስና በተለያዩ አንቀጾች ውስጥ እንዲደነገግ ተደርጓል። ብዝሃነትን እንደ እድል ስንጠቀም ደግሞ ሁሉንም ማንነቶች በማክበርና ለሚነሱት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ በመስጠት ነው። ህገ መንገስቱ ደግሞ ይህን ለማድረግ ከበቂ በላይ ብቁ ነው።

ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የህገ መንግስቱ መግቢያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በብዝሃነታቸው ውስጥ ያሏቸውን ልዩ ልዩ የማንነት መገለጫዎች አምነውና አክብረው ለመኖር፣ ካሳለፉት ታሪክ የወረሱትን መልካም ትስስር ተጠቅመው ለወደፊት የላቀ ትስስር ለመፍጠር ቃል ገብተዋል። ለዚህም ለብዝሃነት ከፍ ያለ ቦታ ይሰጣል። ይህም ብዝሃነታቸው ለአብሮነታቸውና ለጋራ ተጠቃሚነታቸው ዕድል መሆኑን ተስማምተው ቃል ኪዳንም በማሰራቸው መረጋገጡን ያስረዳል።

ይህ የሚሆነውም ህዝቦች በህገ መንግስቱ ላይ ባሰፈሯቸው የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መንፈስን እውን ያደርጋል። የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት መንፈስ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የሚመለስ አይደለም። ሁሉንም ማንነቶች በተገቢው መንገድ በማክበርና በማስከበር ገቢራዊ መሆን ይኖርበታል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በባህሪው ተራማጅ ነው። ይህም ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ይፈጥራል። የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህገ መንግስቱን ሲያፀድቁ በጋራ ፍላጎት ላይ ተመስርተው በመሆኑ ገና ከጥንስሱ ጀምሮ ህገ መንግስቱ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጎናፅፍ መሆኑ ግልፅ ነበር። በመሆኑም በዚህ ሂደት ውስጥ ህገ መንግስቱ የሁሉንም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነትን አጎልብቷል።

ለዚህም ህገ መንግስቱና በህዝቦች መካከል የነበረው ዴሞክራሲያዊ አንድነትና ለሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ተገቢውን ሚና ተጫውተዋል። ዛሬም የሚነሱ ጥያቄዎች በህገ መንግሥቱ መሰረት እልባት የሚያገኙ ናቸው። ጥያቄዎቹን ለመመለስ መንግሥት እየሰራ ነው። በለውጥ ሂደት ስራውም ህገ መንግስቱን በመመርኮዝ ምላሽ ይሰጣል። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው። ነገም ለሚነሱ ማናቸውም ጥያቄዎች የመውጫ መንገድ ሆኖ ያገለግላል።