Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

… መዝጊያም፣ መስፈንጠያም  

0 227

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

… መዝጊያም፣ መስፈንጠያም  

ሆናለች!

አባ መላኩ

አገራችን በፈጣን የለውጥ ምህዋር ውስጥ ናት። ከአዲዲስ አመራሮች ጀምሮ አዳዲስ   አስተሳሰቦችንም እየተመለከትንና እያደመጥን ነው። ተሃድሶው እሽክርክሪቱን እያፈጠነው  ይመስላል። ኢህአዴግን ከምስረታው ጊዜ አንስቶ በስኬት እንዲጓዝ ካስቻለው ነገሮች መካከል ቀዳሚው ነገር ጊዜውን የሚመጥን፣ የህዝብ ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ለውጥ ማድረግ መቻሉ ይመስለኛል። አሁን ላይ የምናስተውለው  ለውጥ የጥልቅ ተሃድሶው ፍሬ ነው። የጥልቅ ተሃድሶው መዘውር ደግሞ ህዝብ ነው። የዘንድሮውን ግንቦት ሃያ የምናከብረው በጥልቅ ተሃድሶው የተለዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል በተጀመረ አዳዲስ የአስተሳሰብ ለውጥ ውስጥ ሆነን ነው።  

በኢህአዴግ ውስጥ ግምገማ ትልቅና የቆየ ባህል ነው። ይህ የግምገማ ባህሉ ድርጅቱን ጥሩ የስነ ምግባር ምንጭ እንዲሆን፣ አባላት ተጠያቂነትን እንዲያውቁና የተጣለባቸው ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ካደረጋቸው ምክንያቶች ቀዳሚውና ዋንኛው ጉዳይ ነው። ግምገማ ከኢህአዴግ ጋር አብሮ የኖረ ባህል በመሆኑ ዕድሜው ከድርጅቱ ዕድሜ ጋር እኩል ነው። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ለ17 ቀን ያካሄደው ጥልቅ ግምገማ ለአገራችን ችግሮች መፍትሄ ሰጥቷል። በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በርካታ አዳዲስ  አመራሮችን ጨምሮ አዳዲስ አሰራሮችን እያስተዋልን፤ ግንቦት ሃያን ለማክበር እየተንደረደርን ነው። “ግንቦት ሃያ” የድሎቻችን ሁሉ መስፈንጠሪያ ብቻ ሳትሆን ቅድመ 1983 ዓ.ም ይስተዋሉ የነበሩ የስቃይና የመከራ ምዕራፍ መዝጊያ በመሆኗ በለዩ ሁኔታ ልናከብራት ይገባል።

አንዳንዶች “ግንቦት ሃያ”ንና ኢህአዴግን  ለማቆራኘት ጥረት ሲያደርጉ እመለከታለሁ። በእርግጥ “ግንቦት ሃያ”ን እውን ለማድረግ  ኢህአዴግ የማይተካ ሚና አበርክቷል፤ መራራው የትጥቅ ትግሉ ማብቂያም ሆኗል “ግንቦት ሃያ” የኢህአዴግ በዓል ሳይሆን የኢትዮጵያ  ህዝቦች የድልና የነጻነት ቀን መጀመሪያ፣ የስኬታቸውም መስፈነጠሪያ ናት። ከ”ግንቦት ሃያ” ድል በፊት አገራችን ትታወቅ የነበረው በእርስ በርስ ጦርነት፣ ረሃብ እና ኋላቀርነት እንዲሁም አስከፊ ደህነት እንደነበር ለጎልማሳ ኢትዮጵያዊያን መንገር ለቀባሪው እንደማርዳት ይሆንብኛል። ኢትዮጵያ ቅድመ 1983 ዓ.ም  የህዝቦቿ ትልቋ እስር ቤት ነበረች፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማይታሰቡባት፣ ሰብዓዊ መብት በጠራራ ጸሃይ የሚጣስባት፣ ሃይማኖተኝነት የሚያስቀጣበት፣ የድህነት መጠኑ ጣሪያ የደረሰባት፣ ሁሉም ነገር ወደጦር ግንባር ተብሎ ወጣቶቿ እየታደኑ ወደ ግንባር የሚጋዙባት አገር ነበረች። ዛሬ ያ የስቃይ፣ ያ የስቃይ ጊዜ አልፏል። “ግንቦት ሃያ” የስኬቶቻችን መስፈንጠሪያ ብቻ ሳትሆን የመከራና የስቃይ ምዕራፍ መዝጊያም ሆናለች።

እነዚህ ሁሉ ሥጋቶችን ማምከን የተቻለውና  አዲሲቷ ኢትዮጵያ በጠንካራ መሰረት ላይ እንድትመሰረት አድረገችው  “ግንቦት ሃያ” ናት። የ“ግንቦት ሃያ” ድል ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ዘላቂ ሠላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማት ለማረጋገጥ መሠረት እና ዋስትና መሆን የቻለች ዕለት ናት። በአገራችን ያለውን ብዝሃነት የተቀበለ እና ያከበረ አዲስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት መፍጠር “ግንቦት ሃያ” በቀደደችልን መንገድ ተጉዘን ነው። ሕገ መንግቱ ሕዝቦች ፍላጎታቸውን እና እምነታቸውን የገለፁበት፣ በአዲስ መንፈስ የጋራ ግንባር ፈጥረው፣ ተከባብረው እና ተጋግዘው አብረው ለመኖር ቃል የገቡበት ሠነድ ነው። ይህ ሠነድ አንድ የጋራ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ቃል የተገባበት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ  ህልውና መሰረት ነው።

ሕገ መንግስታችንን ዴሞክራሲያዊ ባህርያት ከሚያላብሱት መሰረታዊ መርሆዎች መካከል አንዱ የቡድንና የግለሰብ መብቶችን በተመለከተ ያስቀመጠው ዋስትና ነው። ሕገ መንግስታችን የግለሰብና የቡድን መብቶች ሳይሸራረፉና ሳይድበሰበሱ በተሟላ መንገድ ያለገደብ እንዲከበሩ በግልጽ ደንግጓል። በህገ መንግስቱ የግለሰብ መብቶች ከቡድን መብቶች ጋር የሚመጋገቡ እንጂ የሚጣረሱ አለመሆናቸውን፣ የግለሰብ መብቶች መጣስ፣ የቡድን መብቶችን መጣስን እንዲሁም የቡድን መብቶች መጣስ፣ የግለሰብ መብቶች ጥሰትን የሚያስከትል እንደሆነ  በደንብ አስታውቋል። በተግባርም አረጋግጧል። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበርካታ አካባቢዎች የግለሰቦች ህገ-መንግስታዊ መብቶች ባለመብት ነን በሚሉ ግለሰቦችና በተደራጁ ሃይሎች በጠራራ ጸሃይ ሲደፈጠጥ፣ እየተመለከትን ሁላችንም በአያገባኝም ስሜት ዝምታን መርጠናል። እንደነዚህ ያሉ አካሄዶች በወቅቱ ባለመወገዛቸው መንግስትም በወቅቱ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ በመቻሉ አሁን ላይ በመቶ ሺዎች ለሚሆኑ ዜጎቻችን መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።

ሕገ-መንግስታችን ለፈጣንና ቀጣይ የኢኮኖሚ እድገታችን እንዲሁም ለአስተማማኝ ሰላማችን ዋስትና መሆኑ ብቻ ሳይሆን የአገራችን እስትንፋስ በመሆኑ   ሁላችንም ልናከብረው ብቻ ሳይሆን ልናስከብረው የሚገባን ግዴታ ነው። እንደእኔ እንደእኔ ከእንግዲህ ወደኋላ ለመመለስ መንገዱ ረጅምና ውስብስብ ነው፤ በመሆኑም በዚህ ስርዓት ላይ በትንሹም  በትልቁም እየተነሳን ጣት መቀሰሩ ዋጋ ያስከፍለናል የሚል ስጋት አለኝ። የፌዴራል ስርዓታችንና ህገመንግስታችን እጅግ የተቆራኙ አንዱ የአንዱ ውጤት ናቸው። አይን ሲመታ አፍንጫ ያለቅሳል እንዲሉ  የፌዴራል ስርዓቱ ላይ የተጀመረው የማጠላላት ዘመቻ ቢታሰብበት መልካም ይመስለኛል። ሕገ-መንግስታችን የአገራችን ህዝቦች የቆየ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስሮችን በአግባቡ በመዳሰስ የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶቻችን እንዳይደገሙ፤ አዎንታዊ ግንኙነቶቻችንና ዕሴቶቻችንን ደግሞ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ መደላድሎችን የገነባ የሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ የቃል ኪዳን ሰነዳቸው  ሆኗል።

የሕገ-መንግስታችን  መሰረታዊ መርህ የህገ የበላነትን ነው። ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግስት  ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ያስቀምጣል። በተጨማሪም ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማሕበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ሕገ-መንግስቱን የማስከበርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸውም በግልፅ ይደነግጋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ መርህ እየተደፈለቀ ነው።  አስርት ሺዎች ህይወታቸውን ሌሎች አስርት ሺዎች ደግሞ አካላቸውን የገበሩበት መርህ ሲደፈለቅ ኢህአዴግ አላየም አልሰማም ብዬ አላምንም። ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ዘረኝነት፣ ጥበት፣ ትምክህት፣ ሌብነት፣ ማንአለብኝነት ወዘተ በአገራችን ገንግነው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን ሊደፍቁት እየተሯሯጡ ናቸው። እነዚህ መርዘኛ አስተሳሰቦች ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ  ለስርዓቱ እንቅፋት ለመሆን የበቁት መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ ያላከናወኗቸው ተግባራት እንዳሉ በግልጽ ያመላክታል። በመሆኑም የዘንድሮውን “ግንቦት ሃያ” የድል ቀን የምናከብረው በጥልቅ ተሃድሶው የተለዩትን የመልካም አስተዳደር እንቅፋቶች በማንሳት መሆን መቻል አለበት።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy