Artcles

      ማጣጠያው ሲጣጣል

By Admin

May 03, 2018

 

      ማጣጠያው ሲጣጣል

ዮናስ

ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የተሰኘው የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ቡድን ይፋ ያደረገው የዚህ ዓመት የዓለም የጋዜጠኞችና ሃሳብን የመግለፅ ይዞታ ዘገባ ኢትዮጵያን በፕሬስ ነፃነት እርከን ከ180 የዓለም ሃገራት 150ኛ ላይ  ያስቀመጣት መሆኑን የተመለከቱ ዘገባዎች እየወጡ ነው። ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች የተሰኘው ይህ ድርጅት በየዓመቱ በሚያወጣው ዘገባው ላይ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ እንዲሰደዱ በማድረግና በማዋከብ ከሚነሱ ሃገራት መከከል በግንባር ቀደምትነት ሲጠቅሳት መመልከት የተለመደ ነው።

የድርጅቱ የአፍሪካ ክንፍ ተጠሪ የሆኑት አርኖውድ ፍሮጀር “አሁን ድረስ እንደ አውሮፓዊያኑ 2009 የወጣው የፀረ-ሽብር ሕግ ጋዜጠኞችን ያለፍርድ ለረጅም ጊዜ ለማሰር ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ሃገሪቱ በድጋሚ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር በመሆኗ ጋዜጠኞች ያለእስርና እንግልት ሥራቸውን እንዳይሰሩ መሰናክል ነው” ለቢቢሲ መናገራቸውን ሰምተናል።ይህና መሰል ድርጅቶች ስለነዚህ ተደጋጋሚ ክሶቻቸው  ምስክር የሚያደርጉትን ተደጋጋሚ ግለሰቦች ይልቁንም ደግሞ በተቃዋሚ ፓርቲ አባልነትና በጋዜጠኝነት ስም የሚንቀሳቀሱ ያኮረፉ አልያም የውጭ ጉዞን እና ሽልማትን በተራ ጀብደኝነት ለማመቻመች የሚሹ ሃይሎችን ነው።እውነታው ይህና ይህ ብቻ ለመሆኑ ደግሞ እነዚህ ከሳሾች ከሚሉት ባሻገር ተቃራኒ የሆነውን ጉዳይ ማንሳት ያስፈልጋል።

በሃገራችን ሕገ መንግሥት የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ እንዲሁም የመደራጀት መብት በግልጽ ተደንግጓል፡፡የመደራጀት መብትን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 31 ላይ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው ይላል፡፡ በማስከተልም አግባብ ያለውን ሕግ በመጣስ ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሕገወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሠረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ መሆኑን ደንግጓል፡፡ ተቃርኖው የሚመጣው እዚህኛው እና የትኛውም ሃገር ስራ ላይ ያዋለው ድንጋጌ ጋር ሲደረስ ነው።

ከላይ በተመለከተው አግባብ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ በመደራጀት የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ከመቻልም በላይ ህገ መንግስታዊ ዋስትና ተሰጥቶታል፡፡በሌላ በኩል በሙያና በጥቅም ማኅበራት፣ እንዲሁም በሲቪክ ማኅበራት ውስጥ ተደራጅተቶ ዓላማን ማሳካት ይቻላል፡፡  

በተመሳሳይና ከላይ በተመለከተው አግባብ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ቀን በተከበረ ቁጥር ገና ከዋዜማው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነን በሚሉ ተቋማትና አንዳንድ ሚዲያዎች በኩል የሚወጡ አለም አቀፍ ሪፖርቶችና ዘገባዎች በሃገራችን ያለው የጋዜጠኝነት አፈና ያልተቀረፈ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው።  

ተቋማቱም ሆኑ ዘገባዎች ይህን ቢሉም ከላይ በተመለከተው አግባብ አንድ ጋዜጠኛ በህገመንግስታዊ ማእቀፍ ውስጥ ሆኖ እስከሰራ ድረስ ሊደርስበት የሚችል ጉዳት ወይም ስጋት እንደሌለ በአስራዎቹ ለሚቆጠሩ አመታት በስራ ላይ ካሉት ፕሬሶቻችን በላይ ዋቢ የለም።(ሪፖርተር ፎርቹን እና አዲስ አድማስን ልብ ይሏል)።ወዲህ ደግሞ ተቋማቱ ተሰደዱ ከሚሏቸው ጋዜጠኞች አብዛኞቹ የጋዘጠኝነትን ካባ ያጠለቁ ጀብደኛ ተቃዋሚዎች ናቸው። ማኅበራቱም ቢሆኑ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲነትን እና የማህበራትን ሚና ደበላልቀው ለመጫወት የሚሹ ስለመሆናቸው ምርጫ 97ን እና ምርጫውን ሲታዘቡ የነበሩ ማህበራትን በማስታወስ ማጠየቅ ይቻላል።  

ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት ጋር ተያይዘው የሚቀርቡት ክሶች ውሃ የሚያነሱ አይመስሉም። ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አንቀጽ 19 እንዳለ ተወስዶ፣ የሃገራችን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 የሆነው መብት በተግባር መከበሩን ከላይ የተመለከቱት የፕሬስ ውጤቶችን ጨምሮ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር ከሚሰጧቸው መግለጫዎችና ቃለ ምልልሶች በላይ አስረጅ ከየት ይመጣል፡፡ ሊያውም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ተሁኖም። ይህ አንቀጽ ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት የመያዝና ሐሳቡን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዳለው አረጋግጧል፡፡ ይህ ነፃነት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በኅትመት፣ በሥነ ጥበብ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሠራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሠራጨት ነፃነቶችን ያካትታል፡፡

የፕሬስና የሌሎች መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም የሥነ ጥበብ ፈጠራ ነፃነት ተረጋግጧል ይላል፡፡ የፕሬስ ነፃነት በተለይ የተለያዩ መብቶች ተዘርዝረውለታል፡፡ ሕጋዊ ገደቦችን ጥሶ የተገኘም በሕግ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም በህግ የሚጠየቁቱ በህገ መንግስቱ ከተደነገገው ገደብ ውጪ ሲሆኑ ብቻ ነው።ይህ ደግሞ ህጋዊነት እንጂ ህገወጥነትን አያመላክትም።ጋዜጠኛ ስለሆንኩኝ እንዳሻኝ ልፈነጭ ይገባኛል ብሎ ሙግት የባሰው ህገወጥነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩ ከላይ የተመለከቱ መብቶች ይከበሩ የሚል ሚዲያ እና ጋዜጠኛ ህገመንግስቱ ላይ የሰፈሩ ክልከላዎችንም ሊያከብር ይገባል። ሃገራችን ከዚህም በላይ የሆኑ ሌሎች ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት የምታከብርበት ምክንያቶች አሏት። ሃገራችን የሰብዓዊ መብት ሁለንተናዊ ድንጋጌዎች፣ የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን፣ የአፍሪካ የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መርሆዎች ድንጋጌ፣ የዊንድሆክ ድንጋጌ፣ የአፍሪካ ብሮድካስቲንግ ቻርተርና የአፍሪካና የኔፓድ ኮሚሽን የተጠቃለሉ መርሆዎች ፈራሚ መሆኗ ሊዘነጋ አይገባም፡፡

ከህግ ውጭ ሆና በተገኘች ጊዜ ከህዝቧና ከህገ መንግስቷም ተጨማሪ እነዚህ አካላት ጠያቂዎች መሆናቸው በሚታወቅበት አግባብ የተሻለ ኑሮ ፍለጋና በኪራይ ሰብሳቢነት ስብእና ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች በህግ የተከለከሉ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን ነክረው ቪዛ ከሸመቱ ኋላ መዘባረቃቸው ፤ ተሟጋች ነን የምንለው ደግሞ እነርሱ በቀደዱት ፈሰን የምንጮህ ከሆነ የምንሞላው የእነርሱን ከርስ እንጂ በሃገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ ጠብ የምናደርገው ነገር አይኖርም።

የአገሪቱ ፕሬስ 120 ዓመታትን ቢያስቆጥርም፣ በተሟላ ሁኔታ የግሉ ፕሬስ በዚህች አገር ውስጥ በይፋ መሥራት የጀመረው ከዛሬ 26 አመታት በኋላ መሆኑንም መዘንጋት አይገባም፡፡ ይህ አንድ ነገር ሆኖ ከክሶቹ አስቀድሞ የግል ፕሬሱ ለሙያው አዲስ ከመሆኑም በላይ፣ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ውስጥ የሙያ ሥነ ምግባርና የልምድ ጉድለቶች ያሉበት መሆኑንም መካድ ፋይዳ የለውም፡፡በሃገራችን ገበያው በሚፈልገው መጠን ጋዜጠኞችን የሚያፈሩ የትምህርት ተቋማት የሌሉ መሆኑስ ስለምን ይደበቃል።  ብዙዎቹ የግል ፕሬሶች የሙያ ሥነ ምግባር መመርያም ሆነ የኤዲቶሪያል ፖሊሲ የሌላቸው እንደሆነም ፍቃድ ሰጪው አካል በተደጋጋሚ መናገሩ ስለምን ይዘነጋል፡፡ ይህ በሌለበት ሜዳ ደግሞ ገለልተኝነት እየጠፋ ጽንፈኝነት መንገሱ እየከፋ ሲሄድ ደግሞ ወደ ፖለቲካ አቀንቃኝነት (Activism) ውስጥ የተገባ መሆኑን እያወቅን ፤ እነዚህን ሃይሎች በጋዜጠኝነት ካባ ማንገስና ስደተኛ ሆኑ ብሎ ማሞካሸት ስለሃገራችን ፕሬስ እድገት አንዳች አበርክቶ አይኖረውም፡፡

ሚዲያ ለህብረተሰቡና ለሃገር የሚያስፈልገው አንዳች ቁምነገር / Purpose / ስላለው ነው፡፡ ነገር ግን ፕሬስ የሃላፊነት   ጉዳይ እንደሆነ ከቁብ የገባ አይመስልም፡፡ በእኛ ሀገር ጋዜጠኝነት አላፊ አግዳሚውን ጨምሮ በሥርዓቱ ላይ የተናደደው ሁሉ ንዴቱን ለማወራረድ የተሠማራበት ዘርፍ እንደሆነ በግልጽ ታይቷል፡፡  

በህክምናና በህግ እንዲሁም በሌሎች የሙያ ዘርፎች ተጠያቂነት እንዳለ የሚያውቁትና ይህንኑም የሚጽፉት በሚዲያም ተጠያቂነት እንዳለ ታሳቢ በማድረግ ነው ስለፕሬስ ነፃነት መከራከር የሚጠበቅባቸው፡፡ የትኛውንም ርዕዮተ አለም አንድ ጋዜጠኛ ቢከተል መብቱ ነው። ግን ደግሞ እንደ ጋዜጠኛ ለመፃፍ የሚያስችል ሙያዊ ህግጋት እንዳለም ሊገነዘብ ይገባል፡፡ ይህም ስለሆነ እና የተደራጀ የንግድ ሚዲያ(commercial media) በብዛት በሌለባት ሃገራችን ፕሬሱ በፖለቲከኞች እንዲጠለፍ ምክንያት ሆኗል።በሠላማዊ ሠልፍ ሱስ የተጠመዱ ተቃዋሚ ሃይሎች ቅደሚያ መፈክሮቻቸው ነፃ ፕሬስ የሚል የሆነበት ምክንያት ስለዚህ ነው፡፡ የተለየ አስተሣሠብ መስተናገድ የለበትም በሚሉ የራሣቸው ሃይሎች የተያዘ መሆኑ አንድ ምክንያት ነው፡፡ ወደ መፍትሄው ልንመጣ ከሆነ መጀመሪያ የከሳሾቻችን ምስክር የሆኑት ፕሬሶች ሃሳብን በነጻ የመግለጽ ህገ መንግስታዊ መብትን ሽብርተኝነትን ለማበረታታት ጐሳን ከጎሳ ለማጋጨት የሃይማኖት እኩልነትን ለመናድ ተጠቀመውበታል፤ እየተጠቀሙበትም መሆኑ ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡

የፕሬስ ነፃነትም ሆነ ሚዲያ የሚያስፈልገው የፕሬሱ ምንጭ የሆነው ህብረተሰብ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ግንባታ ተሣታፊ እንዲሆን ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን የሙያተኛው ቦታ በጩኸትና በግርግር ተይዟል፡፡ ፖለቲከኞች ጋዜጠኛ ሆነው የፖለቲካ አላማቸውን እያራመዱበትና ሌሎች እንዳይደመጡ እያደረጉ ነው፡፡   ስለሆነም አሁን የሚያስፈልገን ስለሃገራችን ፕሬስና ጋዜጠኞች ታሰሩ ቆሰሉ (ሊያውም ያለአንዳች ምክንያታዊነትና ህጋዊነት)ብሎ የሚያወራልን አይደለም። የሚያስፈልገን የሃገራችን ሚዲያ ደካማ፣ ጽንፈኛና ስሜታዊ፣ ከሙያውም ከሥነ ምግባሩም የሌለበት፣ ኢኮኖሚያዊ አቅሙ ደካማ፣ በሙያውም እዚህ ግባ የማይባል፣ እንዲሁም ኢንቨስትመንትና ሙያተኞችን መሳብ የማይችል መሆኑን አምኖ በማሳመን ከዚህ የሚወጣበትን መላ የሚመታልን ነው፡፡ የሚያስፈልገን የፖለቲካን እና የፓርቲን ድንበር ለይተው የሚያውቁ ሚዲያዎችና ማህበራት የሚፈጠሩበትን መላ የሚዘይድልን አካል ነው ። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊት ሃገር ልንገነባ ከሆነ ያለጠንካራ የግል ፕሬስ እና የሲቪክ ማህበራት ስለማንችል፡፡