ሰላምን የሚወልዱት ሰላማዊ ጥያቄዎች
ቶሎሳ ኡርጌሳ
ማናቸውም ዓይነት ህዝባዊ ጥያቄዎች ሰላማዊና ህጋዊ አቀራረብን ይሻሉ። በዴሞክራሲያዊ ሀገር ውስጥ መነጋገር፣ መመካከርና መወያየት ይቻላል። ይህ አካሄድም ጥያቄዎችን በአግባቡ ለማቅረብ፣ የሚሰጡ ምላሾችን ለማጤንና ትክክለኛውም አቋም ለመውሰድ የሚያገለግል ነው። ህዝብ የሰላም መሃል ዳኛ ነው። ያለ ህዝብ ተሳትፎ ሰላምን ማምጣት አይቻልም። እናም ህዝቡ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ አግባብ ባለው ሁኔታ የማቅረብ ባህልን ሊገነባ ይገባዋል።
ማናቸውም ዓይነት ጥያቄዎች የሚመለሱት በሰላማዊ መንገድ እንጂ በሁከት አይደለም። ሁከት የሰላማዊ ጥያቄዎች ማስፈፀሚያ የመሆን አቅም የለውም። ኖሮትም አያውቅም በመሆኑም ጥያቄዎችን ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው፣ በተቀመጠው አሰራርና የህግ ማዕቀፍ መሰረት ማቅረብ ተገቢ ነው። ይህን እውነታ በተለይም ወጣቶቻችን ማጤን ይኖርባቸዋል።
የሰላም አለመኖር የሀገርን ዕድገትን የኋሊት ያስኬዳል። በመሆኑም ህዝቡ አሁንም ቢሆን ለሰላምና መረጋጋት በቂ ትኩረት መስጠት ብቻ ሳይሆን ሰላምና መረጋጋትን ሊያሳጡን ከሚችሉ ሃይሎች ራሱን መጠበቅም ይኖርበታል።
እነዚህ ሃይሎች ዋነኛው ግባቸው በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፤ ማንኛውም መንግስታዊ ስራ በመደበኛ መልኩ እንዳይሰራ፤ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲስተጓጎል፤ የንግድ ልውውጥና ግብይት እንዳይኖር፤ ህብረተሰቡ በሰላም ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር፤ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ…ወዘተ ከማድረግ ቦዝነው አያውቁም።
የአገራችን ሰላም ላለፉት 27 ዓመታት በጥሩ መሰረት ላይ የተገነባ ነው። የህዝቡ አንድነትም እንዲሁ ጠንካራ ነው። ሰላማችን በቀላሉ ፈራርሶ ደብዛው የሚጠፋ አይደለም። አይደለም።
ምንም እንኳን በየትኛውም ማህበረሰብ ውሰጥ ሰላም ያለው እሴታዊ ዋጋ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ያላቸው ሀገራት ሰላማቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲደፈርስ ብሎም በትርምስና ሁከት ውስጥ ሲቆዩ የተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። ይህም የህዝብን እንቅስቃሴ በማገድ ተጠቃሚነትን ሲጎዳ እንደነበር ተመልክተናል።
አዎ! ሰላማችን ሲጀመር የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ በቀላሉ ሊናጋ አይችልም። ዳሩ ግን ልክ እንዳለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ሰላማችን የመሸራረፍ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሰላሙ ባለቤቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው በቀላሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ድንጋጌዎችን በማውጣት መጠገን ይቻላል፤ ተችሏል፤ እየተቻለም ነው።
በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ለወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት አንዷ እየሆነች ነው። ሰሞነኛውን ጨምሮ በተለያዩ ወቅቶች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋሞች ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ የኢኮኖሚ መሪ ሀገር እንደምትሆን ሲተነብዩ መጥተዋል። እየተነበዩም ነው።
ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ የዛሬ ሁለትና ሶስት ዓመታት ገደማ በተወሰኑ አካባቢዎች የነበረው ሁከትና ብጥብጥ የሀገራችንን ዕድገት ከማቀዛቀዝ ውጭ፤ በልማት ግስጋሴያችን ውስጥ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ አለመፍጠሩን ያመላክታል ብዬ አስባለሁ። ያም ሆኖ ሰላምን ልንከባከበውና ፍሬውንም ልናጣጥመው ይገባል።
ርግጥ ግጭቶች ሁሌም በማንኛውም ጊዜና ቦታ የሚከሰቱ ናቸው። የሰው ልጅ ከግጭቶች ተለይቶ አያውቅም። በዓለማችን ላይ ያለው የተፈጥሮ ሃብት እጥረት አንዱ ምክንያት ነው። ሀገራችንም የዚህ ነባራዊ ክስተት አካል መሆኗ አይቀርም።
ግና ግጭቶች ቢኖሩም ዋናው ጉዳይ ግጭቶቹን ፌዴራላዊ ሥርዓቱና ማህበረሰቡ ባካበታቸው የግጭት አፈታት መንገድ መፍታት ከመቻሉ ላይ ነው። በጌዴኦና በጉጂ ብሔረሰቦች መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተሄደበት መንገድ የዚህ አባባሌ ጉልህ ማሳያ ነው።
በተለይ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ካለፉት ጊዜያት ጋር ፈፅሞ በማይገናኝ መልኩ ለዚህ ነባራዊ ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ሁኔታውን በመለወጥ ላይ ይገኛል። የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ከሌሎች ህዝቦች ጋር በመተሳሰብ የጋራ ሀብታቸው እንዲሆን ለማድረግ ጥረት አድርጓል።
ዳሩ ግን ያለፉት ሥርዓቶች በሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ ፈጥረውት ያለፉት የተዛቡ አመለካከቶች እንዲህ በቀላሉ በጥቂት ዓመታት በቀላሉ የሚቀየሩ አይደሉም— ሂደትን፣ ጊዜንና የአስተሳሰብ ለውጥን ይጠይቃሉ። ይህን ዕውን ለማድረግም ሥርዓቱ አንድነትን በሚያጠናክሩና በሚያፀኑ መሰረቶች ላይ በመመርኮዝ እየሰራ ይገኛል።
በሀገራችን በመገንባት ላይ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሚፈጠሩ ሁነቶች ወቅታዊና አስተማማኝ ምላሽ እየሰጠ ዛሬ ላይ ደርሷል። በዚህም ሊፈጠሩ የሚችሉ አነስተኛ ኑባሬያዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሁሉም የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተሳስበውና ተፈቃቅደው በአንድነት የሚኖሩበትን አስተማማኝና ህዝቦችን ተጠቃሚ ያደረገ ሥርዓት እየፈጠረ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ችግሮች በሥርዓቱና በህዝቦች የግጭት አፈታት ባህል መሰረት እልባት የሚያገኙ ናቸው። ያም ሆኖ አሁንም ሰላምን አጠንክሮ መያዝ ያስፈልጋል።
በተለያዩ ግጭቶች ሳቢያ የሚፈጠረው የሰላም እጦት፤ ሌላው ቀርቶ ጧት ወጥቶ ማታ የመግባት ጉዳይ በህግና በስርዓት ሳይሆን በጉልበተኞች ፍላጎት እንዲወሰን ያደርጋል። ጉልበተኞቹ ከሚፈልጉት ጊዜና ዕውቅና ውጭ ማንም ሰው መነቃነቅ አይችልም።
ታዲያ ያኔ ህግ የበላይነቱን ተነጥቆ ጉልበት ባላቸው አካላት እጅ ይወድቅና ሁሉም ነገር ምስቅልቅሉ ይወጣል። ሃይል ያለው ሁሉ በህገ ወጥ መንገድ ሰላምን አስጠባቂ ነኝ ብሎ ይነሳል። የነገር ካራውን አንጠልጥሎም ወደ ዘረፋና ህዝብን ወደማሰቃየት ተግባር ይገባል።
እናም ህዝቡ ከሁሉም ነገር በላይ ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ይኖርበታል። በመሆኑም የሚያቀርባቸው ማናቸውም ጥያቄዎች ህጋዊና ሰላማዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለበት። በሀገራችን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ጥያቄዎችን ማቅረብ መብት ነው።
ጥያቄዎቹ ግን ህግንና ስርዓትን የተከተሉ መሆን ይኖርባቸዋል። ከዚህ ውጭ ለጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሲባል ህገ ወጥ አካሄድን መከተል መልሶ የሚጎዳው ጥያቄ አቅራቢውን አካል ነው። እንዲህ ዓይነቱ የተሳሰተ መንገድ የሀገርን አቅም ከመፈታተን በላይ የጥያቄው ባለቤት የሚፈልገውን እንዳያገኝ ያደርጋል።
ሰላምን ሊወልዱ የሚችሉት ሰላማዊ ጥያቄዎች በመሆናቸው እነርሱን ለማጎልበት መጣር ያስፈልጋል። በዚህ የእርቅ ዘመን ለሰላም መደፍረስ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ መንገዶችን መከተል ተገቢ አይደለም። አዋጭም ሊሆን አይችልም።