Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ስኬቶቹን ለማስቀጠል…

0 255

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ስኬቶቹን ለማስቀጠል…

ገናናው በቀለ

ኢትዮጵያዊነት ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ትርጓሜው ሰፊ ነው። ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር ናት። እነዚህ ህዝቦች አንድነታቸው የተሰናሰለው ወደውና ፈቅደው በመሰረቱት አንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ነው። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ እንዳለፉት ዘመናት አንድነትን በኃይል ለመጫን የሚደረግ ሙከራ ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ይህ ጊዜው ያዐፈበት አስተሳሰብ ነው።

ታዲያ ይህን እውነታ ታሳቢ አድርጎ የተገነባው ፌዴራላዊ ስርዓትም ይሁን በስርዓቱ አማካኝነት የተገኘው ዕድገት የግንቦት 20 ድል ውጤት ናቸው። እናም የድሉን ስኬቶች ለማስቀጠል የሁሉም ዜጋ ርብርብ ወሳኝ ነው።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መግቢያ ላይ የሰፈረው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ስምምነት በተጨባጭ እየተሳካ እንደሆነ ያለፉት 27 ዓመታት ጉዞ በተጨባጭ ያሳየ ይመስለኛል። ዛሬ ሀገራችን ውስጥ ብዝሃነት የዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መገለጫ ሆኗል። ይህም ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዝሃነትን አስመልክተው ይራመዱ የነበሩ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ሙሉ ለሙሉ የቀየረ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውሰጥ የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአጋርነት ታሪክ ህገ መንግሥታዊ ዋስትና በማግኘታቸው የአብሮነቱ እሴቶች ሊሆኑ ችለዋል። አንድ ማኅበረሰብ ማንነቱ እንዲከበርለት የሌላውን ማንነት ማክበር እንዳለበት በማመን በተናጠልና በጋራ ባህሎቻቸውንና ታሪካቸውን ማክበርና ማንፀባረቅ የተቻለበት ዘመን ላይ ደርሰናል።

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ የመገንጠል መብት ህገ መንግሥታዊ ዋስትና ቢያገኝም፤ የማኅበረሰብ ጥያቄ መሆኑ እያበቃለት ይገኛል—በጊዜ ሂደት የነበሩት አስተሳሰቦች ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ እየተመዘኑ በመክሰም ላይ መሆናቸውን መናገር የሚቻል ይመስለኛል።  

እርግጥ የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ በወደቀበት ማግስት የነበሩት የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች አንዳንዶቹ ያነገቡት ዓላማ መገንጠልን እንደነበር አይዘነጋም። ሆኖም አብሮ በመኖር ሂደት የተገኘ ጥቅም እያደገና እየሰፋ ስለመጣ የመገንጠል አስተሳሰብ ማኅበረሰባዊ መሰረት አለው ብሎ ለመናገር የሚቻል አይመስለኝም። ለነገሩ አንድ ህዝብ መብቶቹ ተከበረው በጋራ ተጠቃሚነት ውስጥ እስካለ ድረስ ስለ መገንጠል ማሰቡ ሚዛናዊ ዕይታ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም።

ያም ሆኖ የደርግ መንግሥት በወደቀ ማግስት ኢትዮጵያ ትበታተናለች የተባለውና በብዙዎች በቋንቋ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአንድነት ዋስትና አይሰጥም ተብሎ የተነገረው አፈ ታሪክ መሰረት የሌለው ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ህዝቦች ብዝሃነት ከግምት ውስጥ ያላስገባም መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መኖሪያ ብትሆንም፤ እነዚህ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ለዘመናት በአፈናና በጭቆና ስርዓት ቀንበር ስር ወድቀው ሲማቅቁ ቢቆዩም በትግላቸው ይህን ሁኔታ ድል ነስተዋል። ከዚያም ብዝሃነት ባለባት አገራቸው ውስጥ እውን መሆን ያለበትን ፌዴራላዊ ስርዓት በመገንባት ዛሬ በሁሉም መስኮች የአፍሪካ ተምሳሌት መሆን ችለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የቃል ኪዳን ማሰሪያ ሰነድ የሆነው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ጸድቆ በስራ ላይ ከዋለ ወዲህ ሀገራችን ትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ ይዛ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ በድል ለመረማመድ በቅታለች።

የብሔሮችና ብሔረሰቦች እስር ቤት እስከመባል ደርሳ የነበረችው ሀገራችን፤ የህዝቦቿ መብት የተረጋገጠባት፣ የዕድገትና ልማት ብሩህ ተስፋን የሰነቀች፣ የእኩልነትና የፍትህ አምባ ለመሆን ችላለች።

በመሆኑም የአፈና አገዛዝ፣ የግፍ ቀንበር ተጭኖት የኋላቀርነትና የበታችነት ተምሳሌት ተደርጎ ይታይ የነበረው የብሔር ብሔረሰቦቿ ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ የህዝቦቿ መኩሪያና መከበሪያ፣ የሀገራችን መድመቂያ ጌጥና የመልካም ገጽታዋ መገለጫ ወደ መሆን ተሸጋግሯል።

የተለያየ እምነትና የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመግባባትና በመረዳዳት መንፈስ አብሮ በመኖር በዓለም የሚታወቁበት የመቻቻል ባህልም ከመቼውም በላቀ ሁኔታ በመዳበር ላይ ይገኛል።

እነዚህ ታሪካዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ የጋራ እሴቶቻችን ለሀገራችን ተጨማሪ ክብርና ሞገስ ከማላበስ አልፎ ለፈጣን ልማት ስራዎቻችን የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት ወደ ሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ፤ ዜጎች በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል አግኝተዋል።

ይህንንም በተጨባጭ ስራ ላይ በማዋል የሀገራችንና የህዝባችን የማደግና የመበልጸግ ተስፋን በእጅጉ ለማለምለም ችለዋል። መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በመብቶቻቸው እየተገለገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙት ፈጣን የዕድገት ጉዞም የፌዴራላዊ ሥርዓቱ ተጨባጭ ፍሬ ነው።

በሀገራችን እውን የሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ለሀገራችንና ለህዝባችን አንድነት፣ ሠላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፤ በማበርከት ላይም ይገኛል። የዚህ አዲስ ሥርዓት ግንባታ ሂደት በተጨባጭ ተፈትኖ ፍቱንነቱ የተረጋገጠ ነው።

ህገ መንግስታችን መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን፤ ሁሉም ሰዎች በመካከላቸው የዘር፣ የብሔር፣ የብሔረሰብ፣ የፆታ፣ የሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ እኩል የሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው፣ ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የህሊናና የሃይማኖት ነዓነት፣ የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት ለብቻው ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን የማምለክ፣ የማስተማርና የመግለፅ መብት እንዳለው እውቅና የሰጠ ነው።

እርግጥም አገራችን የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት ዕውን እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ረጅም ጊዜን የወሰደና ከፍተኛ መስዋዕትነትን የጠየቀ ትግል አካሂደዋል። በዚህም ከላይ የጠቀስኳቸውን ስኬቶችን ማረጋገጥ ችለዋል።

ስኬቶቹ ቀጣይነት እንደኖራቸው የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የላቀ ሚና መረጋገጥ ይኖርበታል። ወደ ኋላ ልንመለስ አይገባም። በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የተጎናፀፍናቸው ድሎች እንዳይቀለበሱ ሁለንተናዊ ጥረት ማድረግ ያሻል። መንግሥት በግንቦት 20 የተገኙትን ስኬቶች ለማስጠበቅ በሚያደርገው ሥራዎች ህብረተሰቡ ገንቢ ሚናውን መጫወት ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy