Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ቀጣናዊው ድጋፍ

0 266

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ቀጣናዊው ድጋፍ

                                                          ዘአማን በላይ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቀጣናው ሀገሮች ያለው ከፍትሐዊነትና ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ የመነጨ ነው። ከመሰንበቻው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሱዳንንና ኬንያን በጎበኙበት ውቅት፤ ግድቡን አስመልክቶ ከየሀገራቱ መሪዎች ጋር ሲነጋገሩ፤ የግድቡ ግንባታ የአካባቢውን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ስለመሆኑ መግባባት ላይ ተደርሷል።

በተለይም በተለያዩ የልማት መስኮች ላይ በትብብር እየሰሩ ያሉት ኢትዮጵያና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ተመሳሳይ አቋም እያራመዱ መሆናቸው ይህን እውነታ የሚያጎላው ነው። ሱዳን ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያና ግብፅ ጋር የተፈራረመችውን ስምምነት እንደምታከብርና የሶስቱ ሀገሮች የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ እንቅስቃሴን እንደምትደግፍ በፕሬዝዳንቷ ሐሰን አልበሽር አማካኝነት ገልፃለች። ይህም ከዲፕሎማሲ አኳያ ለኢትዮጵያ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።

የህዳሴው ግድባችን የሌላውን ሀገር የውሃ ዋስትና የማይጻረር እንዲሁም በፍትሃዊነትና በምክንያታዊነት መርህ የመጠቀም መብታቸውን በማረጋገጥ ያለባቸውን የኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ለመቅረፍ ያለመ ነው።

ባለፉት ዓመታት የሀገራችን የዕድገት ማነቆ ሆኖ የቆየው የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግርን የሚቀርፉ ጥቂት የማይባሉ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድቦችን በተሳካ ሁኔታ መገንባት ተችሏል። ሀገራችን ጥረቱን አጠናክራ በመቀጠልም በዓባይ ወንዝ ላይ በአፍሪካ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በማካሄድ ላይ ትገኛለች።

ግድቡ ከድህነት ለመውጣት የምናደርገው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው። ለምሳሌ ያህል ግድቡ አሁን ያለውን የሀገራችንን የሃይል አቅርቦት ከሶስት እጥፍ በላይ ያሳድጋል። ከዚህ በተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ግድቡ በሙሉ አቅሙ ስድስት ሺህ 450 ሜጋ ዋት ማመንጨት ሲጀምር ለአንድ መቶ ዓመታት ያህል በቀን ከሁለት ሚሊዮን ዮሮ በላይ ለሀገራችን ማስገኘት ይችላል። ይህም ህዝቡ በታሪካዊነቱ ያስቀመጠው ሁለንተናዊ አሻራ ተመልሶ የታሪካዊ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርገዋል።

የህዳሴው ግድብ የሚገነባው በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ላይ ተመስርቶ ነው። በዚህም ሳቢያ ግድቡ ቀደምት የተመፅዋችነት አስተሳሰብን የቀረፈ፣ ለፀረ ድህነት ትግሉ ስኬት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ የይቻላል መርህን በተግባር ማዋል ያስቻለ እንዲሁም ከራሳችን ተርፎ በሚደረገው ሽያጭ የህዝቡን ውለታ በዕድገት የሚመልስ በመሆኑ ታሪካዊነቱና ሀገራዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

ግድቡ ፍትሐዊ አስተሳሰብን ተመርኩዞ የሚገነባ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን አብሮ መኖርን፣ ማደግንና መበልፀግን ከማንም በላይ የምንቀበልና የማንነታችን መገለጫም ነው። ልክ እንደ ሌሎች ለብቻችን እንጠቀም ብለን አናውቅም። የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታችን ትኩረትም ማንንም ለመጉዳት ያለመ አይደለም። አብሮ መብላትና ተያይዞ ማደግ የቆየ ኢትዮጵያዊ እሴት መለያ ባህሪ በመሆኑ ይህን ልናደርግ አንችልም።

ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ዓለም አቀፋዊው የእኩልነትና የፍትሃዊነት መርህን መሰረት ላደረገው የኢንቴቤው የስምምነት ማዕቀፍ ተግባራዊነት በግምባር ቀደምትነት የተሰለፈችውም ከዚህ ባህሪዋ በመነሳት ነው። መላው ዜጎቿም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬታማነት ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን እያበረከቱ የሚገኙት ደግሞ ግድቡ ጉልህ ተፅዕኖ ሳያደርስ የጋራ ተጠቃሚነትን ሙሉ ለሙሉ የሚያረጋግጥ መሆኑን ጥንቅቀው ስለሚያውቁ ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ የህዳሴውን ግድብ ፋይዳ የተገነዘቡ የጎረቤት ሀገሮች መንግስታት ድጋፋቸውን ከማሳየትና አቋማቸውን ከማንጸባረቅ አልፈው፤ በተለያዩ ወቅቶች የሚታዩትን የግብፅ መንግስትን ኢ- ፍትሃዊ አቋም በግልጽ እስከማውገዝ የደረሱበት ነው።

የተፋሰሱ ሀገራት በዚህ ብቻ አልተወሰኑም። በተፈጥሯዊው የውሃ ሃብታቸው በእኩልነትና ፍትሃዊነት መርህ የመጠቀም መብታቸው የማይገደብ መሆኑን ሊገነቧቸው ያቀዷቸውን ፕሮጀክት ይፋ በማድረግ ቁርጠኝነታቸውንም አመላክተዋል። ይህ አቋማቸውም የግድቡን ሀገራዊና አህጉራዊ ጠቀሜታ በግልፅ ማመላከት የቻለ ነበር። የኢትዮጵያን የጋራ ተጠቃሚነት ጠንካራ አቋምንም እንዲሁ ያሳየ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲከናወን የተወሰነው ከጎረቤት ሀገር ሱዳን ድንበር 20 ኪሎ ሜትር ተጠግቶ ነው። ይህም ግድቡ ለመስኖ አገልግሎት ሊውል እንደማይችል ያስረዳል። ውሳኔው የኤሌትሪክ ሃይልን የማመንጨትና የሃይል አቅርቦትን በማሳደግ ሀገራዊ ልማትን ከማፋጠን ውጪ፤ ማንኛውንም ወገን “በውሃ ለማስጠማት” ያለመ አይደለም። ግድቡ የኤሌትሪክ ሃይል ከማመንጨት ባሻገር፤ አንድ ጠብታ ውሃ አያባክንም።

ግድቡ የማንኛውም ሀገር ጥቅም ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ የማያደርስ ነው። እንዲያውም በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ውስጥ በየዓመቱ ሲደርስ የቆየውን ከፍተኛ የውሃ ትነት መጠን የሚያስቀር መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል። ሳይንሳዊው እውነታ ይኸው ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሀገራችን አልፎ ሌሎች ሀገሮችም መጠናቀቁን በተስፋ የሚጠብቁት ፕሮጀክት እየሆነ ነው። ይህም ኢትዮጵያ የምትተለውና ከሁሉም ሀገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለማደግ ያላት ቁርጠኛ አቋም ፍሬ እያፈራ መሆኑን የሚያመላክት ይመስለኛል። ሀገራችን ለሩዋንዳ 400 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራርማለች።

ሱዳንና ኬንያም ቢሆኑ የህዳሴውን ግድብ መጠናቀቅ በተስፋ እየተጠባበቁ ነው። ቀደም ሲል 100 ሜጋ ዋት ከኢትዮጵያ የወሰደችው ካርቱም እንዲሁም 400 ሜጋ ዋት ሃይል ማመንጫ የምትጠብቀው ናይሮቢ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለባቸውን የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት እንደሚያቃልላቸው በማመን ፍፃሜውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት የ100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ከሀገራችን በመውሰድ ተጠቃሚ በመሆን ላይ የምትገኘው ጅቡቲም ተጨማሪ ሃይል ለመውሰድ የግድቡን ግንባታ ፍፃሜ እየጠበቀች ነው።

እነዚህ ሁሉ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦቶች ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን በመፍጠር ከሌሎች ሀገራት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ በጋራ የማደግ ትልሟን የሚያሳዩ ናቸው። ሀገራችን የምትከተው ፍትሐዊና ሁሉንም አሸናፊ ሊያደርግ የሚችል መንገድ፣ የተፈጥሮ ሃበቷን የሌሎችን ጥቅም ሳይነካ ለመጠቀም የምታደርገው ጥረት እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከግድቡ ፍፃሜ ተጠቃሚ መሆናቸውና ለመሆን መጠባበቃቸው ግድቡ ቀጣናዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ያደረገ ነው። ሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሀገሪቱን ሲጎበኙ፤ ‘ግድቡን በገንዘብ ጭምር ለመገፍ ዝግጁ ነኝ’ ማለቷ ይህን የሀገራችንን ትክክለኛ በጋራ የማደግ አቅጣጫን ስለተገነዘበች ነው።  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy