በሠላም ዲፕሎማሲው የቱን ያህል ተጉዘናል?
አባ መላኩ
ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ፋና ወጊ አገር ናት። በዚህ ረገድ ያላትን መልካም ተሞክሮ ማካፈል የሚያስችልም አቅም ገንብታለች። አገሪቱ የምትከተለው ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ሠላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ከማረጋገጥ አኳያ የቱን ያህል ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ብሎም ለቀጣው እንደጠቀመ መረዳት ቀላል ነው። ይህም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ከፍታ ምክንያት መሆኑን መረዳት ይቻላል።
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ በውስጧ ሠላም የፈጠረች አገር ናት። ጎረቤቶቿም ቢሆኑ ሠላማቸው እንዳይናጋ ከመጠበቅ አንፃር በብርቱ ጥራለች። እየከወነቻቸው ያሉ በርካታ ውጤታማ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ለውጤታማነቷ ሌላው ምስክሮች ናቸው። ኢትዮጵያ ከ27 ዓመታት በላይ የራሷን ሠላም በፅኑ መሠረት ላይ ማቆም የሚያስችል ቁመና ፈጥራለች። በዚህም ከራሷ አልፎ የአጎራባቾቿን ሠላም መጠበቅ እንደምትችል በይፋ አሳይታለች። ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ የሠላም ዲፕሎማሲ ከፍታን አመላካች መሆኑ ግልፅ ነው።
ይህ ብቻም አይደለም። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የአደራዳሪነት ሚና እየጨመረ ሄዷል። የዲፕሎማሲ ድሉ በንጉሱ ዘመነ መንግሥት ወቅትም የነበረ ነው፤ ተቋማዊና በሰለጠነ መንገድ እየተመራ ይበልጥ ተቀባይነቱም እየጎላና እየደመቀ የመጣው ግን በኢፌዴሪ መንግሥት መሆኑ እውነት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምፅ እስከመሆን የበቃችው በኢፌዴሪ መንግሥት ነው።
ኢትዮጵያ አፍሪካን ብሎም ዓለምን እያስጨነቀ በመጣው የአየር ንብረት ለውጥ የሙቀት መጠን መጨመር ጉዳይ ላይ የአፍሪካዊያን ልሣን ሆና ብቅ ያለችውም በዚሁ መንግሥት ነው። የመፍትሄው አካል ሆናም በቅድሚያ በራሷ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫን በአርአያነት ያሳየችውም በኢፌዴሪ መንግሥት ነው። ይህ ሁሉ ተግባሯም በሌሎች ዘንድ ያላት ተቀባይነት ከፍ እንዲል ረድቷታል። ተቀባይነቷም እንዲጎለብት አግዟታል።
በእርግጥ የኢፌዴሪ መንግሥት ቀደም ብሎ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ይሁን በአፍሪካ ህብረት ያበረከታቸው አስተዋፅኦዎች በአሁኑ ወቅት ለተመዘገበው የዲፕሎማሲ ድል መሠረት ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በየትኛውም አገር ውስጥ ሠላም እንዲሰፍን የተጫወተው ሚና የሚመነጨው ሌሎች ኃይሎች በተሳሳተ መንገድ እንደሚተረጉሙት ሳይሆን የአጎራባቾች ሠላም ለአገሪቱ የልማት፣ የሠላምና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ መፋጠን ካለው ጠቀሜታ አንጻር ነው። ይህም ካለምክንያት የተፈፀመ ጉዳይ አይደለም። ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የሚደረገው ጥረት የሚሳካው ጐረቤቶች ሠላም ሲሆኑ ነው።
በእርግጥም የድንበር አዋሳኞች ቀርቶ የሩቅ አገራት ሠላም መሆን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ ሠላም መጐልበት ያለው ሚና የጎላ እውነታ ነው። ይህም ሁኔታ በአፍሪካ ደረጃ በጋራ ሠላም እጅ ለእጅ ተያይዞ ለማደግና አፍሪካዊ ህዳሴን ማጎልበቱ አይቀሬ ይሆናል።
ያም ሆኖ ይህ ኢትዮጵያ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን አማፅያን መካከል የተካሄደው ዘግናኝ ግጭት በሠላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ትልቁን ድርሻ ተጫውታለች። የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ጠንካራ እምነት የገለፀበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም ኢትዮጵያ የተጎናፀፈችው ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድሏ ነው።
ደቡብ ሱዳን የራሷን ነፃ አገር ከመሠረተችበት አንስቶ ኢትዮጵያ ከአዲሲቷ አገር ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያተኮረ ነው። ይህም በንግድ፣ በመሠረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ አተኩራል። ምንም እንኳን በውስጥ ግጭቶች ምክንያት ሠላሟ ተመልሶ ቢናጋም።
አዲሲቷ አገር ደቡብ ሱዳን ነፃ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ በውስጧ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ግጭት የኢፌዴሪ መንግሥት ከኢጋድ ጋር በመሆን አሁን ድረስ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም መልካም ሊባል የሚችሉ ውጤቶች ተገኝተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር ያላት መልካም ግንኙነት ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት እንደሚያጎለብት ተስፋ ተጥሎበታል። ይህም አንዱ የዲፕሎማሲው ከፍታ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከጐረቤት አገሮች ጋር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት የመፍጠር ጥረት በዚህ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሠላምን ለማስፈን በሚካሄድ እንቅስቃሴ ውስጥ አገሪቱ ለጀመረችው የፈጣን ልማት ቀጣይነት መረጋገጥ ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ይህን ሁኔታ መነሻ በማድረግ ብሎም መንግሥት ለሠላም ካለው ጽኑ አቋም በመነሳት ለዘመናት የእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ለቆየችው ጐረቤት አገር ሱዳን በተለይ ደግሞ በቅርቡ ሠላሟ እየደፈረሰ ለምትገኘው ደቡብ ሱዳን ሠላም መስፈን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው።
ለዘመናት በአንድ ድርጅት ጥላ ሥር ሆነው ለሕዝባቸው ነጻነትና እኩል ተጠቃሚነት ሲታገሉ ቆይተው፣ የናፈቁትን ሠላምና ልማት በቅጡ ሳያጣጥሙ ወደ ግጭት የገቡት የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ዳግም ወደ እርስ በርሰ ጦርነት በመግባት ለከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት መዳረጋቸው ዛሬ ድረስ የቀጠለ እውነታ ነው።
በእርግጥ በደቡብ ሱዳን የተከሰተው ወቅታዊ ችግር የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት በከፍተኛ ሁኔታ ስቧል። ይሁንና በተጨባጭ ሲታይ መሳብ እንደ ኢፌዴሪ መንግሥትና ኢጋድን ያህል የበለጠ ጥረት ያደረ ማግኘት ይከብዳል።
ሁሉም እንደሚረዳው አዲሷ አገር በሆነችው ደቡብ ሱዳን የተከሰተው ቀውስ የአደጋው ተጋላጭ የሚያደርገው በዋነኛነት ዜጎቿን መሆኑን እስካሁን ከደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ መገንዘብ ከበቂ በላይ ማሣያ ነው። ያም ሆኖ ግን ዳፋው ለአካባቢው አገራት ጭምር መሆኑም አልቀረም።
ያም ሆኖ ይህ የኢፌዴሪ መንግሥት የቀጣናው ሕዝቦች ሠላም መሆን ቀናዒ ፍላጎት አለው። በቀጣናው ውስጥ የአንድ አገር ሕዝብ መጎዳት ዞሮ…ዞሮ ለኢትዮጵያ የሚኖረው ጠቀሜታ እንዲሁ ይታወቃል። በመሆኑም ሕዝቦች አገራቸው ውስጥ በሠላም እየኖሩ ለቀጣናው ልማት እመርታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መንግሥት ያግዛል። በሂደትም ክፍለ አህጉራዊው የምጣኔ ሀብት ትስስር ይበልጥ እንዲዳብር ይበልጥ ጠንክሮ ይሰራል።