Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በቃ … ሌባ  ሌባ ይባል!

0 411

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በቃ … ሌባ  ሌባ ይባል!

ወንድይራድ ኃብተየስ

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የህብረተሰቡን ቅሬታዎች ለማድመጥ፣ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ ከህዝብ ጋር በመነጋገር ለቅሬታዎች መፍትሄ ለማፈላለግ ወዘተ ሲሉ  ከተመረጡ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ውይይቶችን ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በማድረግ ላይ ናቸው። ከእነዚህ መድረኮች መካከል ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የተደረገው ውይይት አንዱ ነው።  በአገራችን የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ራሱን ወደውስጥ በመመልከት፣ እኔ ምን ማድረግ አለብኝ፣ ምን ማድረግስ አልነበረብኝም የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ የሚችል ከሆነ በእርግጠኝነት የአገራችን ችግሮች ሁሉም ባይሆኑ በርካቶቹ  መፍትሄ ያገኛሉ የሚል ዕምነት አለኝ።

አመልካች ጣታችንን ወደሌላው ስንጠቁም ቀሪዎቹ አራቱ ጣቶቻችን ወደራሳችን እንደሚያመለክቱ  መገንዘብ ተገቢ ነው። ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከንግዱ ዘርፍ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ  በዘርፉ ላይ ችግር መኖሩን አምነው፤ ነገር ግን የንግዱ ማህበረሰብ ራሱ የሚጠበቅበትን ያህል  ተሳትፎ እንዳላደረገ ተናግገረዋል። የንግዱ ማህበረሰብ ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር በተገናኘ ጊዜ ሁሉ ስለህገወጥ ንግድ፣ ፍትሃዊ ያልሆነ ግብር አወሳሰን፣ ወዘተ ሲያማርር አድምጠናል፣ ተመልክተናልም። ይሁንና  በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት የተለዩ ችግሮችን ለማስተካከል በተነሳበት ወቅት የንግዱ ማህበረሰብ መንግስትን ለመደገፍ ለውጥን ለማስቀጠል ያደረገው ጥረት የሚጠበቀውን ያህል አይደለም።

የንግዱ ዘርፍ በኪራይ ሰብሳቢዎች ከፍተኛ ጉዳት  የደረሰበት ዘርፍ እንደሆነ ለመረዳት የሚከብድ አይደለም። መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ለህዝብ የገባቸውን ቃልኪዳኖች ደረጃ በደረጃ በመወጣት ላይ ነው። የጸረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ የጥልቅ ተሃድሶው ውጤት አንዱ አካል ነው።መንግስት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ አሰራሮችን መተግበር እንዳለበት ሁሉ የንግዱም ማህበረሰብ የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል። ሙስና እጅግ የረቀቀና ውስብስብ አስተሳሰብና ተግባር በመሆኑ መንግስት ብቻውን የፈለገውን ያህል ቢሮጥ  የሚያመጣው ለውጥ እጅግም ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በተገኙበት የሐዋሳው መድረክ ላይ አንድ አባት የተናገሩት ዛሬም ውስጤ ነው። “… ሌባ በቃ ሌባ ይባል፤ የሰረቀን ሙሰኛ፣ ኪራይ ሰብሳቢነት ወዘተ ማለት የድርጊቱን ክብደት አያሳይም፤  ስለዚህ ሌባ ሌባ ይባል”። እውነት ነው። ድርጊቱን የፈጸመና ያስፈጸመ ነውረኛ እያለ እኛ ሌባ ማለት ለምን እንጠየፋለን። ስርቆት በየትኛውም ኢትዮጵያዊ ሃይማኖት ሆነ ባህል የተወገዘና ጸያፍ ድርጊት ነው። እንግዲህ ከሃይማኖታችንም ሆነ ከባህላችን በተቃራኒ  የሆነን ድርጊትን በጸያፍ ቃል ብንጠራው የሚያንሰው አይመስለኝም።

ከላይ እንዳነሳሁት ሌብነት በስውር የሚካሄድ ኢ-ስነምግባራዊ ተግባር ነው። በመሆኑም መንግስት ብቻውን የፈለገውን ያህል  ጥረት ቢያደርግ በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ለውጥ አያመጣም። የንግዱ ዘርፍ ተፈጥሮው ሁኔታ ከሌሎች መስኮች በከፋ መልኩ ለሌብነት የተጋለጠና የተጠቃ ዘርፍ ነው። በመሆኑም መንግስት ይህን ዘርፍ ከሌቦች ለማጽዳት እያደረገ ያለው ጥረት እንዲሳካ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገበል። በአገራችን በርካታ የሚያጓጉ ለውጦች ይኑሩ እንጂ ተግዳሮቶቹም በቀላሉ  የሚታዩ አይደሉም። መልካም ነገሮችን የማስቀጠል እንዲሁም ተግዳሮቶችን የመቅረፍ ትግል የእያንዳንዳችን ግዴታ መሆን መቻል ይኖርበታል። በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ማንም በህጋዊ መንገድ ሰርቶ መለወጥ የሚችልበት ሁኔታዎች ያሉ በመሆናቸው ህገወጥ ስራ ውስጥ መዘፈቅ ትርፉ ስጋትና ጭንቀት ነው።ይዋል ይደር እንጂ ሰርቆ የከበረ ከህግ አያመልጥም። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት “ሌቦች ሙሉ ልብስ ወይም ሱፍ ሲገዙ እንኳን አንድአይነት መልክ እንዲሆን ይመርጣሉ፤ ምክንያቱም እጠየቃለሁ የሚል ስጋት ስለሚያድርባቸው ነው።  እውነት ነው ሌብነት ያሸማቅቃል፤ ሌብነት በራስ መተማመንን ይቀንሳል።

በርካታ  የመንግስት  ሃላፊዎችና ፈጻሚዎች ህዝብን በታማኝነት በማገልገል ላይ በመሆናቸው ክብርና ኩራት ሊሰማቸው ይገባል። ይሁንና  መንግስትና ህዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት ተጠቅመው ደሃን ሲሰርቁና ሲያሰርቁ የነበሩ የስራ ሃላፊዎችና ፈጻሚዎች ይዋል ይደር እንጂ ከህግ ተጠያቂነትን አያመልጡም።  ለመሆኑ እነዚህ አካሎች የሰረቁት ደካማ እናታቸውንና አባታቸውን መሆኑን ይገነዘቡት ይሆን? እንደእኔ እንደኔ በሌብነት የተሰማሩ ግለሰቦች የህግ ተጠያቂነት ከሚያስከትልባቸው ጉዳት ይልቅ ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰው የሞራል መላሸቅ ያስፈራኛል።  ወላጀጆቻቸው በሌብነት የተሰማሩ ልጆች በጓደኞቻቸው የተገለሉና የተናቁ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም።

አሁን ላይ አዲሲቷ ኢትዮጵያ በመልካም የዕድገትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጎዳና ላይ ነች። ከያዝነው የልማት  መንገድ ሊያደናቅፈን የሚችል ማንኛውም ነገር ልንታገሰው አይገባል። የማይገባን ጥቅም የመፈለግ አስተሳሰብና ድርጊት ለአገራችን ቀጣይ ህይወት ጠንቅ ተብሎ ከተለዩ ነገሮች መካከል ቀዳሚው ነው።  መንግስት የጀመረውን የጸረ-ሌብነት ትግል ከስኬት ለማድረስ ሁሉም ባለድርሻ አካል ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል። ሁላችንም ይህን ማድረግ የሚጠበቅብን ለራሳችን ብለን መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። በመሆኑም  የተጀመረውን የጸረ-ሌብነት ትግልን በምንችለው ነገር ሁሉ መደገፍና ከዳር ማድረስ ተገቢ ነው። ይህን ትግል አልሰማሁም፣ አላየሁም ማለት አይቻልም። አልሰማሁም፣ አላየሁም ማለት በራሱ ተጠያቂ ያደርጋል።

የፅረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል የታሰበለትን ዓላማ የሚመታው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ግልፅኝነትን በማስፈንና ተጠያቂነትን በማንገስ እንጂ ግለሰቦችን በማሳደድ ብቻ ሊሆን አይችልም። ይህ ሲባል ግለሰቦች ለሰሩት ጥፋት ተጠያቂ አይሆኑም ማለት አይደልም። የህግ የበላይንት መቼም ቢሆን በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ከድርድር የሚቀርብ ጉዳይ  መሆን የለበትም። አሁንም የፅረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ስር ነቀል ለውጥ እንዲያመጣ የተለያየ አሰራሮችን ከመዘርጋት ጎን ለጎን ሌቦችን ወደ ህግ ለማቅረብ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። ይህን የመንግስት ጥረት ሁላችንም ልንደግፈው ይገባል። የንግዱ ማህበረሰብም የዚህ ወሳኝና ታሪካዊ የትግል አካል ሊሆን ይጋባል። አንዳንድ ነጋዴዎች ከጥቅመኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመቀራረብ የማይገባቸውን ጥቅም ሲያሳድዱ ታይተዋል። በዚህም ድርጊታቸው ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንደይኖር በማድረግ የህዝብንና የመንግስትን ጥቅም ጎድተዋል። ህጋዊና አገር ወዳድ የሆነውን ግብር ከፋይ  ነጋዴም ከመስመር እንዲወጣ አድርገዋል። በመሆኑም ልማታችንን ጎትተዋል።

አሁን ላይ መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት ለህዝብ የገባውን ነገሮች  ደረጃ በደረጃ እያከናወነ ይገኛል። መንግስት ለህብረተሰቡ የሚያቀርባቸውን አገልግሎቶች ማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ አሰራሮችን በመዘርጋት ላይ ነው። ከላይኛው የአመራር እርከን ጀምሮ በርካታ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተቀይረዋል። በርካቶቹ ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል፣ ቀላል የማይባሉትም ላጠፉት ጥፋት ወደ ህግ እየቀረቡ ናቸው። ይሁንና ግለሰቦችን ተጠያቂ በማድረግ ብቻ   የተፈለገው ለውጥ ይመጣል ማለት አይቻልም። ህብረተሰቡም በተሃድሶው ወቅት ለመልካም አስተዳደር መስፈን የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ቃል ገብቶ ነበር። ሌብነትን በዘላቂነት መከላከል የሚቻለው ጠንካራና አስተማማኝ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋት ሲቻል ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡም መብትና ግዴታውን በአግባብ መወጣት ሲችል ነው። አገር ስትለወጥ እጠቀማለሁ የሚል ቅን አስተሳሰብ በሁላችንም ሊዳብር  ይገባል። በቃ ሌባን ሌባ በማለት ልናሸማቅቀው ልናገለው ይገባል። እርሱ ሲሰርቅ ያላፈረውን እኛ ለምን ሌባ ለማለት እንፈራለን።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy