Artcles

ብርቱው ጥንቃቄ

By Admin

May 11, 2018

ብርቱው ጥንቃቄ

ገናናው በቀለ

የኢፌዴሪ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ፤ ዜጎች በውጭ አገር መስራት እስከፈለጉ ድረስ በህጋዊ መንገድ የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የውጭ አገር የሥራ ስምሪት አዋጅ በ2008 ዓ.ም አውጥቷል።

በዚህ አዋጅ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከጥቅምት 2006 ዓ.ም ጀምሮ ተጥሎ የነበረውን የውጭ አገር ስራ ስምሪት እግድ በመነሳቱ ምክንያት ዜጎች ህጋዊውን መንገድ መከተል ይኖርባቸዋል።

በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ህገ ወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች መንግሥት ከተለያዩ አገራት ጋር ያደረጋቸው ስምምነቶች ተግባራዊ መደረግ እንደጀመሩ በማስመሰል ዜጎቻችንን እያጭበረበሩ ናቸው። እናም ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

እነዚህ ህገ ወጥ ደላላዎችና አዘዋዋሪዎች በውጭ አገር ካሉ አዘዋዋሪዎች ጋር በተቀናጀ መልኩ በቱሪስት ወይም በአገር ጎብኚ ስም ዜጎችን ወደ ተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚልኩበት ሁኔታ ፍጹም ህገ ወጥና ውጤቱም የከፋ ሊሆን የሚችል ነው። ስለሆነም ህብረተሰቡ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ህገ ወጥ ደላላዎቹ የሰዎችን ልብ በሐሰት ተስፋ በመሙላት ከመመልመል አንስቶ እስከ መጨረሻው የብዝበዛ ሂደት ድረስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚሳተፉ ናቸው። እነዚህ ደላላዎች በየአካባቢው የሚመለምሉ፣ የሚያገናኙ፣ ሰዎችን የሚረከቡ ብሎም መንገድ በመምራት ወደ ብዝበዛው ቦታ የሚያደርሱ የራሳቸው የግንኙነት ሰንሰለት ያላቸው ናቸው።  

በእዚህ ህገ-ወጦች የሚታለሉት የሀገራችን ዜጎች የውጭው ዓለም የተሻለ ተስፋ ያለ እየመሰላቸው ራሳቸውን የበረሃና የደላላዎች ሲሳይ ያደርጋሉ። በተስፋ የሚሞሉት ዜጎች እጅግ በርካታ ገንዘብ ካወጡ በኋላ የመረጡት መንገድ ትክክል ስለሚመስላቸው ተስፋቸው ገና ከመነሻው ምሉዕ ይሆናል።

ግና የጉዟቸውን እኩሌታ እንኳን ሳያጠናቅቁ ነገሮች ይወሳሰባሉ፤ ህይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑንም ይገነዘባሉ። ይሁንና ጥሪታቸውን አሟጠው ያወጡትን ገንዘብ ላለማጣትና ሰርተው ለመመለስ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ጉዟቸውን ሊያቋርጡ አይፈልጉም።

እናም የመረጡት ጉዞ “የማርያም መንገድ” እንደሚባለው ዓይነት እጅግ የጠበበ መሆኑን እያወቁም ቢሆን ራሳቸውን ለስቃይና ለሞት አሳልፈው ይሰጣሉ። በለስ የቀናቸው እንዳጋጣሚ ወደፈለጉት ሀገር ቢሄዱም የጉዟቸው መነሻ ህገ-ወጥ በመሆኑ በየሄዱበት ሀገር በህገ-ወጥነት ተፈርጀው ይታደናሉ፤ ሲያዙም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል።

ይህ ደግሞ ከጅምሩ ከቤተሰብ አሊያም ከዘመድ አዝማድ ተበድረው ወይም ጥሪታቸውን አሟጠው ሽጠው በህገ-ወጥ መንገድ የከፈሉትን ገንዘብ ውሃ እንዲበላው የሚያደርግ ይሆናል። ድህነትን አሸንፋለሁ ብሎ ራስንና ቤተሰብን ለባሰ ድህነት መዳረግ ይሆናል።

በእኔ እምነት ዜጎች ለዚህ ዓይነቱ አደጋ የሚጋለጡት በቀዳሚነት በሚፈጠረው የአመላካት ችግር ምክንያት ነው። ይህ የአመለካት ችግር መንስኤው የተለያየ ሊሆን ቢችልም፣ ከድህነት ለመውጣት የሚኖር ፍላጎት፣ የቤተሰብና የጓደኛ ግፊት እና ህገ-ወጥ ደላሎች የሚሰጡት የማይገመጥ የተስፋ ዳቦ የተሰኙት ሃቆች የችግሩ አነሳሽ ምክንያት ናቸው ተብለው ሊፈረጁ ይችላሉ።

አብዛኛዎቹ በህገ ወጥ መንገድ የሚጓዙ ግለሰቦቹ አጠገባቸው ያለውን መልካም አጋጣሚ አሟጠው ከመጠቀም ይልቅ “የእገሌ ልጅ እዚህ ሀገር ሄዶ አለፈለት” የሚል የተሳሳተ ምልከታን በመያዝ ወደዚያው ለማቅናት ይጓጓሉ።

በአቅራቢያቸው ያለውን ሰርቶ የመለጥ ዕውነታን ላለማየት አይናቸውን በመሐረብ ይሸብባሉ። በዚህም ቀደም ሲል ለፍተው ያፈሩትን ጥሪት ወይም የቤተሰብን ወረት በማሟጠጥ ወይም ራስንና ቤተሰብን የብድር አረንቋ ውስጥ በመክተት ለከፋ የድህነት መንገድ አደጋ ይጋለጣሉ። የህይወት መስዕዋትነትንም ይከፍላሉ። በአንድ ወቅት በሊቢያ እንዲሁም በህገ-ወጥ መንገድ ባህር አቋርጠው ወደ ሌላ አገር ለመሻገር ሲሉ ህይወታቸውን ያጡት ዜጎቻችን የዚህ አባባሌ ሁነኛ አስረጅ ናቸው።

እርግጥ ሰዎች በህገ-ወጥነት እንዲዟዟሩ የሚያደርጋቸው ሌላኛው ጉዳይ ስራ አጥነትና የገቢ ማነስ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም። ይሁንና ‘ስራ አጥነት ነኝ’ ወይም ‘ገቢዬ አነስተኛ ነው’ የሚል ሰው ለህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ከመቶ ሺህ ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ በመክፈል ስደትን እንደምን በአማራጭነት ሊይዝ እንደሚችል አይታወቅም። ይህን ያህል ገንዘብ ያለው ሰው እዚሁ ሀገር ውስጥ ሰርዮ ራሱን መቀየር የሚችልበት የተመቻቸ ሁኔታ እያለ ራሱን እስ ህይወት ማጣት ድረስ ለሚያደርስ አደጋ ለምን እንደሚያጋልጥ ለማንም ግልፅ አይደለም።

እንደሚታወቀው ሀገራችን ድህነትንና ስራ አጥነትን በየደረጃው ለመቅረፍ ደፋ ቀና በማለት ላይ ትገኛለች። ይህ ጥረቷም ውጤት በማፍራት ላይ ይገኛል። በተለይም ወጣቶችና ሴቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች እየታቀፉ ህይወታቸውን በመለወጥ ላይ ይገኛሉ።

ገንዘብ ባይኖር እንኳን ተደራጅቶ በመበደር የድህነት ሁኔታን መቅረፍ እየተቻለ ወደ ውጭ የምናማትርበት ምክንያት ሊኖር አይችልም። እዚህ ላይ በአስገራሚነት የሚነሳው ጉዳይ ‘ደህና ኑሮ አለው’ የሚባል ሰውም ሳይቀር ልቡን ለስደት እያዘጋጀ በስተመጨረሻው ህይወቱን ጭምር እያጣ መሆኑ ነው። እናም ሁሉም ወገን ህገ-ወጥ መንገድን እንደ አማራጭ ከመያዙ በፊት አስቀድሞ እነዚህን ሃቆች ማገናዘብ ይኖርበታል።

ቤተሰቦች ጥቂት የአካባቢያቸው ሰዎች ውጭ ሀገር ሄደው ሰርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ኑሮ ማሻሻላቸውን ሲያይ ‘የእኔም ልጅ ምናለ በሄደ?’ የሚል ቁጭት ሲድርባቸው ይስተዋላል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ቤተሰቦች የጎረቤቶቻቸው ልጆች በሚልኩት ገንዘብ በመማረክ ልጆቻቸው ወደ ውጭ ሄደው እንዲሰሩ ጫና ይፈጥራሉ። ይህ ጫናም ልጆች ወደ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል።

ይህ ግፊትም በህገ-ወጥ ደላላዎች በባዶ ሜዳ ላይ የተንጠለጠለ ተስፋ ጋር ታግዞ ልጆችም ‘እኔም ለምን እንደ ጓደኛዬ ውጭ ሰርቼ አልለወጥም’ የሚል ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ፍላጎት ገና ከጅምሩ በቤተሰብ የሚደገፍ በመሆኑ የተሻለ ኑሮ ለማግኘት ሲባል ህይወትን ማጣት እንዳለበት እንኳን ግምት ውስጥ አይገባም። እናም ከሰላማዊ ኑሮ ተነጥሎ የህገ-ወጥ ደላሎች ሲሳይ መሆንን ያስከትላል።

የአገራችን ዜጎች በህገ-ወጥ ደላላዎች ምክንያት በሚያጋጥማቸው ችግር በርካታ ውጣ ውረዶችን ከማለፍ ባሻገር በህገ ወጥ መንገድ ተጉዘው ያሰቡበት ሀገር ሳይደርሱ መንገድ ላይ የሚቀሩበት ሁኔታ እየተከሰተ ነው።

ለችግሩ እልባት ለመስጠት መንግስት ዜጎች ወደ ውጭ ሄደው መስራት እስከፈለጉ ድረስ በህጋዊ መንገድ መጓዝ የሚችሉበትን ስልት ቀይሷል። ህገ ወጥ ደላሎች ለአላስፈላጊ እንግልት እንዳይዳርጓቸው ከመንግፅት የሚሰጠውን መመሪያ በአግባቡ በማዳመጥና ብርቱ ጥንቃቄ በማድረግ ህጋዊውን መንገድ መከተል ይኖርባቸዋል።