Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተምሳሌታዊ ትብብር

0 329

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተምሳሌታዊ ትብብር

                                                         ይሁን ታፈረ

ማንኛውንም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይገባል። ምንም ዓይነት ዓላማ ቢኖረን  በሃይል ለማራመድ መሞከር ሕገ-ወጥ ተግባር ነው። እንደሚታወቀው መንግስት የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሃላፊነትና ግዴታ አለበት። በመሆኑን የህግ የበላይነት በአገራችን ውስጥ እውን እንዲሆን ተባባሪ መሆን ያስፈልጋል።

በአገራችን የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ነው። አዋጁ ሊነሳ የሚችለው ህዝቦች በየአካባቢያቸው ሰላምን በአስተማማኝ መልኩ የመጠበቁን ተግባር በባለቤትነት ሲረከቡ ብቻ ይመስለኛል። ይህም የአንድን አገር ሰላምን የሚያደፈርሱና የህግ የበላይነትን የሚፃረሩ ጉዳዩች በህዝቡ እንጂ በአዋጅ ብቻ ሊጠበቅ እንደማይችል የሚያሳይ ነው።

በቅርቡ ኮማንድ ፖስቱ በሰጠው መግለጫ፤ በሞያሌ ከተማ በተደራጀና በህቡዕ ዝግጅት በተደረገበት የጥፋት ተልዕኮ በሁለት ጎራዎች የታጠቁ ኃይሎች መካከል ማህበረሰብን ዒላማ ያደረገ በመጠኑም ሰፋ ያለ ግጭት ተከስቶ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አድርሷል።

በወቅቱ ተከስቶ የነበረውን ግጭት የፀጥታ ሃይሉ የተቆጣጠረው ሲሆን፤ በዚህ ጥቃት የተሳተፉና ድርጊቱን የመሩ ሃይሎችን በመለየት በቁጥጥር ስር ለማዋልም ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተጠቁሟል። በተጨማሪ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በስፋት እየተካሄደ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ አመልክቷል።

ባለፈው ሚያዚያ ወር ብቻ 142 ክላሽ፣ 88 ሽጉጥ፣ 11 የእጅ ቦምቦች እና 17 ኋላ ቀር መሳሪያዎች ከበርካታ ተተኳሾች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮማንድ ፖስቱ ማስታወቁ አይዘነጋም። በሞያሌ ከተማ የተከሰተው ችግር ከህገ ወጥ መሳሪያ ጋር ተያይዞ እንደነበርም አስታውሷል።

በዚህም በሞያሌ ከተማ ከመንግስት በተሰጠ ትዕዛዝ መሰረት በፀጥታ ሃይሎች ትጥቅ የማስፈታት ስራ እየተከናወነ ነው። እናም በሌሎች ጥናት በተደረገባቸው አካባቢዎችም ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በወቅቱ ተገልጿል። ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ነገር ቢኖር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ነው። በእኔ እምነት አዋጁ ባይኖር ኖሮ ከዚህ የከፋ ችግር በህብረተሰቡ ላይ ሊከሰት መቻሉ አጠራጣሪ አይደለም።

አዋጁ ሊነሳ የሚችለው ለአዋጁ መውጣት ምክንያት የሆኑ ጉዳዩች ሙሉ ለሙሉ በአስተማማኝ ሁኔታ ሲቀለበሱ ነው። እኔ እሰከሚገባኝ ድረስ ይህ ማለት የሀገራችንን ፀጥታ ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ካልተመለሰ አዋጁ አይነሳም ማለት ነው። ሰላምና ፀጥታው ሙሉ ለሙሉ መመለሱን የሚያውቀው ደግሞ ይህን ጉዳይ በበላይነት የሚመራው ኮማንድ ፖስቱና የአዋጁን አፈፃፀም የሚከታተለው መርማሪ ቦርዱ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት የሰላምና መረጋጋት መሻሻል እዚህ ሀገር ውስጥ ቢፈጠርም፤ አሁንም ልክ እንደ ሞያሌ ዓይነት በተወሰኑ የአገራችን አካባቢዎች ህዝቡ ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በጥምረት ለከናወኑ የሚገባቸው ክስተቶች አሉ። የኮማንድ ፖስቱን ጣልቃ ገብነት የሚጠይቁ ክስተቶች በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች አሁንም ይስተዋላሉ።

በመሆኑም ለአዋጁ ምክንያት የሆኑት ምክንያቶች ሙሉ ለሙሉ እሰካልተወገዱ ድረስ፤ የአዋጁን ማስቀረት የሚቻል አይመስለኝም። የዚህን ሀገርና ህዝብ ሰላም አለመመኘት ነው። ሀገራችንንና ህዝቦቿ የጀመሩትን የዕድገት ጎዳና የማደናቀፍ ጥረትም ጭምር ይመስለኛል።

ስለሆነም አዋጁ የሚቀጥለው አንድም በህዝቡ ፍላጎት፣ ሁለትም የተገኘው ሰላምና መረጋጋት የማይቀለበስበት ደረጃ ደርሶ ወደ ነበርንበት የቀድሞ ሁኔታ በአስተማማኝ ደረጃ እንክንደርስ ይመስለኛል። ለነገሩ የአንድ አዋጅ መውጣት ሰላምና መረጋጋትን እስካመጣ ሰላሙ አስተማማኝ እስከሚሆን ድረስ መነሳቱን መሻት ተገቢ አይመስለኝም።

እናም ሁሉም ዜጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበር አለበት። ለጥቆም ለአዋጁ ተፈፃሚነት ትብብር ማድረግ ይጠበቅበታል። አዋጁን የማያከበርና ለተፈፃሚነቱም ከኮማንድ ፖስቱ አባላት ለሚቀርብለት የድጋፍ ጥያቄ የማይተባበር ማንኛውም ግለሰብ በአዋጁ መሰረት ተጠያቂ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ ሀገርን ከውጭና ከውስጥ አሸባሪዎችና ፀረ-ሰላም ኃይሎች የጥፋት ተልዕኮ የመታደግ ብሎም ዕድገታችን ያስኮረፋቸውን አንዳንድ የውጭ ሀገራትን የእጅ አዙር ሴራ መከላከል በመሆኑ ሁሉም አገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት የሚኖርበት ይመስለኛል።

መቼም የትኛውም ሀገር ወዳድ ዜጋ  በእነዚህ ኃይሎች ሰላሙ እንዲደፈርስ፣ ማናቸውም ህገ-መንግስታዊ መብቶቹ ተነጥቀው የስርዓት አልበኞች መፈንጫ ሆኖ ህይወቱን፣ ሃብቱንና ንብረቱን እንዲያጣ ብሎም ሀገር አልባ ሆኖ በትርምስ ውስጥ እንዲኖር አሊያም በጎረቤት ሀገር ውስጥ የጥገኝነት ህይወትን እንዲገፋ የሚፈልግ አይመስለኝም።

እናም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማክበርና ተፈፃሚነቱን መተባበር ማለት እነዚህን መጥፎ ክስተቶች በአጭር ጊዜ ገቶ በተለመደው ሰላማዊ የህይወት መስመር ውስጥ መግባት ነው። ይህን ዕውን ለማድረግም እንደ ሞያሌው ዓይነት የህገ ወጥ መሳሪያ ዝውውን ለመግታት ከኮማንድ ፖስቱ ጋር መተባበር ይኖርባቸዋል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ የቀጣናውን ሀገራት ሰላም እያስከበረችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭነት እንዳላትም ይረዳል። ይህ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ቁመናችን እንዳይሸራረፍም ሰላምን በፅኑ እንደሚሻ እሙን ነው። ባለፉት ጊዜያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን ገቢራዊ ለማድረግ ያሳየው ቁርጠኝነት የዚህ እውነታ ማሳያ ነው።

ያም ሆነ ይህ ሀገራችን ሰላም መረጋገጥ መሰረቱ ህዝቡ መሆኑ አይካድም። በዚህም ሳቢያ ባለፉት አስር ወራቶች የሀገራችን ሰላም በመደበኛው ህግ ሊፈቱ ከሚችሉ ጥቃቅን ጉዳዩች ውጪ በአብዛኛው ወደ ነበረበት የተመለሰው ህዝቡ ለሰላም ካለው የማይናወጥ ፍላጎት የመነጨ ነው።

ሰላምን በፅኑ የሚሸው የሀገራችን ህዝብ ደሙን ዋጅቶና አጥንቱን ከስክሶ ያመጣው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መንገድ እንዳይደናቀፍ እንዲሁም የኋሊት እንዳይቀለበስ አይፈቅድም። እናም ሁሌም ለሰላሙ እንደተጋ ነው።

በአሁኑ ሰዓት አገራችን ውስጥ አንፃራዊ ሰላም ተገንብቷል። በዚህም ሳቢያ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሰላማዊ ትግልን ማካሄድ የሚችልበት አውድ ዕውን ሆኗል። ይህ ሰላማዊ አውድ ሊገኝ የቻለው ህዝቡ ስለ ሰላም ካለው ቀናዒ ምልከታ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆንና አዋጁ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ህዝቡ የተጫወተው ሚና የማይተካ ነው። አሁንም ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርንና የአገርን ኢኮኖሚ የሚያሽመደምደውን የኮንትሮባንድ ተግባር ከኮማንድ ፖስቱ ጋር በመቀናጀት ተምሳሌታዊ ትብብሩን ማጠናከር ይኖርበታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy