Artcles

ተያይዘው ወንዝ ይሻገራሉ!

By Admin

May 15, 2018

ተያይዘው ወንዝ ይሻገራሉ!

ኢብሳ ነመራ

የሰላምን ዋጋ ሰላምን ያጣ ነው የሚያውቀቅው። ከ2008 ዓ/ም መግቢያ ወዲህ ባሉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በኦሮሚያ አጋጥሞ የነበረው የሰላም እጦት ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል። ቁሳዊና ስነልቦናዊ ጉዳትም አድርሷል። እርግጥ የዚህ የሰላም እጦት ምክንያት  የህዝብ ብሶት የወለደው ተቃውሞ ነው። እናም ተገቢ ተቃውሞ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ተቃውሞው ተገቢ መሆኑ ግን ጉዳቱን አላስቀረውም። ተቃውሞው ሰላማችንን ከነጠቀን ሁከትና ግርግር በተለየ ሰላማዊ መንገድ ቀርቦ ቢሆን መልካም ነበር። እርግጥ በወቅቱ በሰላማዊ መንገድ ለሚቀረቡ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ምላሽ መስጠት የሚችል የመንግስት አመራር ነበር ወይ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

አሁን በህዝባዊ ተቃውሞው ገፊነት የተሃድሶ አመራር ወደሃላፊነት መጥቷል። ይህ የተሃድሶ አመራርና አሮጌው አመራር የህዝብን ጥያቄና ቅሬታ ለማዳመጥ ያላቸው ንቃትና ፍላጎት የተለያየ መሆኑ አይካድም። እናም ይህ የተሃድሶ አመራር እንዲመጣ፣ ህዝብን ማዳመጥ ተስኖት የነበረው አሮጌ አመራር ያረጀ ቆዳውን ሞሽልቆ ለመታደስ ይወስን ዘንድ የሃይል ተቃውሞ ማካሄዱ የግድ ሳይሆን የቀረ ይመስላቹሃል? ያም ሆነ ይህ የህይወት፣ የአካል የሃብትና የስነልቦና ጉዳት ባደረሰ የሃይል ተቀውሞ የተሃድሶ አመራር ወደሃላፊነት መንበር መጥቷል።

የሃይል ተቃውሞው በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለው አሉታዊ ተጽእኖ አሁንም አለ። ባለንበት የ2010 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ 3 ነጥብ 66 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ ማግኘት የተቻለው  2 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ብቻ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር ሰሞኑን አስታውቋል። የበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት የታየው አፈጻጸም ከእቅድ አንጻር ሲታይ የ1 ነጥብ 58 ቢሊየን ዶላር ጉድለት አለው። ለዚህ አነስተኛ አፈጻጻም የተለያዩ ምክንያቶች ቀርበዋል። ከምክንያቶቹ አንዱ በሃገሪቱ የነበረው አለመረጋጋት አንዱ መሆኑን የንግድ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ፣ ባለነበት ባጀት ዓመት ያለፉ ዘጠኝ ወራት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ቱሪስቶች ሀገሪቷን ይጎበኛሉ ተብሎ ቢታቀድም፣ መጎብኘት የቻሉት ግን 756 ሺህ 758 ቱሪስቶች ብቻ መሆናቸውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል። በዚህም 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር እንደተገኘ ይህም ከእቅድ አኳያ ሲታይ 75 በመቶ ብቻ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ባለፉት ጊዜያት በተለይ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት በሚኖርባቸው የ2010 ዓ/ም የመጀመሪያ ወራት በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር ለአፈጻጻሙ ደካማነት ምክንያት መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ይህ ከላይ የተጠቀሰ የሰሞኑ መረጃ በሃገሪቱ የተካሄደው የሃይል ተቃውሞ ምን ያህል ጉዳት እንዳስከተለ አስረጂ ነው። ዜጎች ጥያቄያቸውን ወይም ቅሬታቸውን የሚገልጹበት ሰላማዊ መንገድ ሲያጡ ወደየሃይል ተቃውሞ መግባታቸው አይቀሬ ቢሆንም፣ የሃይል ተቃውሞ ጉዳት ያለው መሆኑ ግን እውነት ነው። አሁን አሁን የባለፉ ሁለት ዓመታት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቶ የተሃደሶ አመራር ከተፈጠረና አመራሩ ለህዝቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ያለውን ፍላጎት ከመግለጽ አልፎ በተግባር እያሳየ ባለበት ወቅት ወደየሃይል አካሄድ መግባት መነሻውም መድረሻውም ጥፋትና ጥፋት ብቻ ነው።

ሰሞኑን በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች ይህ ሁኔታ ታይቷል። በኦሮሚያ ወለጋ ቤጊ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች በክልሉ ፖሊስ አባላት ላይ ቦብም ወርውረው ጉዳት ማድረሳቸውን ሰምተናል። በጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ከሜድሮክ ጎልድ ለገደምቢ የወርቅ ማምረቻ ኩባንያ ፍቃድ እድሳት ካር በተያያዝ በተነሳ የህዝብ ተቃውሞ በሰዎች ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ደርሷል። ይህንኑ የወርቅ ማምረቻ ፍቃድ እድሳት መነሻ በማደረግ በአዶላም ተመሳሳይ የሃይል ተቃውሞ ተካሂዶ የሰዎች ህይወት ጠፍቷል። በሌላ በኩል በሞያሌ ታጣቂዎች ጎራ ለይተው በሰላማዊ ዜጎች ላይ በሰነዘሩት የመሳሪያ ጥቃት በርካቶች ተጎድተዋል።

በወለጋ ቤጊ በፖሊሶች ላይ የተሰነዘረው የቦምብ ጥቃት እንዲሁም በሞያሌ ታጣቂዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያደረሱት ጥቃት ምክንያትና የጥቃት ፈጻሚዎቹ ማንነት እስካሁን በውል አልታወቀም፤ ወይም ይፋ አልተደረገም። ስለዚህ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ እስኪገኝ በይደር እንለፈው። በጉጂ ዞን በሻኪሶና አዶላ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ግን ምክንያቱ ይታወቃል። ይህም የሚድሮክ ጎልድ ለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ ወርቅ ሲያጣራ የሚጠቀመበት ኬሚካል በአካባቢው ላይ ያደረሰውን ሰብአዊ ጉዳት መነሻ ያደረገ ነው።

በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔት ዎርክ (OBN) ከወራት በፊት አንድ ዶክመንተሪ አቅርቦ ነበር። ይህ ዶክመመንተሪ ዘገባ ከወርቅ ማምረቻው በሚለቀቅ መርዛማ ኬሚካል ምክንያት አስከፊ የአካልና የአእምሮ ጉዳት የደረሰባቸውን ህጻናትና እናቶችን አሳይቶ ነበር። እርግጥ ነው በዶክመንተሪው  የቀረበው ጉዳት ለማየት የሚዘገንን እጅግ አስከፊ ነው። የኦ ቢ ኤን ዶክሜንተሪ ችግሩ በቀጥታ ሚድሮክ ለገደንቢ የወርቅ ማዕድን ማምረቻ በለቀቀው ኬሚካል የተፈጠረ ይሁን ይሁን በማያሻማ አኳኋን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ባይኖረውም፣ በአካባቢው በአንዳች ምክንያት በእናቶችና በሚወለዱ ህጻናት ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ግን በማያሻማ ሁኔታ አሳይቷል።  እናም ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ተመርምሮ አጥፊው ላደረሰው ጉዳት መካስ፣ ስራውን የሚቀጥል ከሆነም በቀጣይ ጉዳት የማያስከትል መሆኑ መረጋገጥ አለበት። ይህን ማረጋገጥ የማይቻል ከሆነ ጉዳቱ ከሚደርስ ልማቱ ቢቀር ይመረጣል። የልማት መድረሻው ሰው ነው። በሰው ልጅ መስዋዕትነት የሚገኝ ልማት ልማት አይደለም።

ያም ሆነ ይህ የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በለገደንቢ ላለፉት ሃያ ዓመታት ሲሰራ ለቆየው ሜድሮክ ጎልድ የወርቅ ማዕድን ልማት የፍቃድ እድሳት አድርጎ ነበር፤ ለቀጣይ አስር ዓመታት እንዲሰራ። ለሜድሮክ ጎልድ የፍቃድ እድሳቱ ከመደረጉ በፊት ኩባንያው የራሱን የአካባቢ ጥበቃ ኦዲት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያቀረበ መሆኑን ሚኒሰቴሩ አስታውቋል። ሚኒስቴሩም በራሱ መንገድ ናሙናዎችን ወስዶ አውሮፓ ድረስ በመላክ ማጣራቱን፣ ከዚህ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ ወገን በመሆን በዚህ ሂደት መሳተፉንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል። ለሜድሮክ ጎልድ ለአስር ዓመት የተደረገው የፍቃድ እድሳትም በዚህ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተሰጠ መሆኑን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው። የሁን እንጂ ህዘቡ በአካባቢው በተጨባጭ የሚያየውን በህጻናትና እናቶች ላይ እንዲሁም በእንስሳት ላይ የደረሰውን ጉዳት መነሻ በማድረግ የሜደሮክ ፍቃድ መታደስ የለበትም የሚል ቅሬታ አቅርቧል።

በዚህ መሰረት ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ውይይት ተካሂዷል። ከውይይየቱ በኋላ የሚድሮክ ጎልድ የለገደምቢ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፍቃድ መታገዱን የኢፌዴሪ የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታውቀል። የወርቅ ማዕድን ልማት ስራ ላይ የአካባቢው ነዋሪ ቅሬታ ማንሳቱን ተከትሎ ነው ፍቃዱን ያገደው። በገለልተኛ አካል ጥልቀት ያለው ጥናት እስከሚጠና ድረስ የኩባንያው ወርቅ የማምረት ስራው ታግዶ ይቆያል።

ሚድሮክ ጎልድ ለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ አካባቢውን በመርዛማ ኬሚካል በመበከል በነዋሪዎቹ ላይ ጉዳት አስከትሏል የሚለውን ዶክመንተሪ የኦሮሞ ብሮድካስቲንግ ኔት ዎርክ (OBN) መስራቱ ከአንድ የህዝብ ሚዲያ የሚጠበቅና ሚዲያውን የሚያስመሰግነው፣ ሌሎችም አርአያ ሊያደርጉት የሚገባ ተግባር ነው። ህዝቡም ችግሩን ለሚዲያ መጠቆሙ፣ በማዕድን ማምረቻ ላይ ተቃውሞ ማቅረቡና በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ጋር መወያየቱ ተገቢ ነው። የማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር፣  የሜድሮክ ጎልድን ፍቃድ ያደስኩት የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት የሚያስከትል ተጽእኖ እንደሌለው አረጋግጬ ነው ቢልም፣ ህዝብ ያነሳውን ስጋትና በአካባቢው በተጨባጭ የሚታየውን ጠቋሚ መረጃ መነሻ አድርጎ እድሳቱን ማገዱ ተገቢ ነው። በአካባቢው ሻኪሶና አዶላ የተነሳው የሰዎችን ህይወት ለአደጋ የሚያጋልጥ የሃይል ተቃውሞ ግን ተገቢ አይደለም።

በአጠቃላይ ህዝብ ብሶትና ቅሬታ ሊኖረው ይችላል። ይሁን እነጂ በተለይ አሁን ህዝብ ጌታዬ ነው ብሎ በይፋ ተናግሮ ህዝቡን ለማገልገል የቆመ የተሃድሶ አመራር ባለበት ወቅት ብሶትና ጥያቄን በሃይል ተቃውሞ መግለጽ ጸያፍ ነው። አሁን ህዝብና መንግስት ከተሃድሶው አመራር ጋር ተግባብተው ተደጋገፈው የሃገሪቱን ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ለማሳደግ መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ተጨባጭ ተስፋም እየታየ ነው። በዚህ ሁኔታ ችግሮች ሲያጋጥሙ ከመደጋገፉ ህብረት አፈንግጦ ወደሁከት መግባት መንግስትን ከአካሄዱ የሚያደናቅፈው መሆኑን ማስታወስ ብልህነት ነው። ይህ መንግስትን የማደናቀፍ አካሄድ የተሃድሶው አመራር ከህዝብ ጋር በፈጠረው ህብረት የተሸነፉ አካላት ሴራ የማይሆንበት ምክንያት እንደማይኖር ቆም ብሎ ማሰብ ብልህነት ነው።  

አሁን ሃገሪቱ ያለችበትን ችግር ማቃላልና የህቡን ፍላጎት ማሟላት የሚቻለው ህዝብና መንግስት ተያይዘው ከተጓዙ ብቻ ነው። ሰዎች ተያይዘው የሞላ ወንዝን እንደሚሻገሩ ልብ ይሏል። ከተላቀቁ ግን ወንዙ ይበረታል፤ በተናጠል ይበላቸዋል። እናም በየሰበቡ ከሰላማዊ መንገድ በማፈንገጥ ተስፋ የፈጠረው የመንግስትና የህዝብ ህብረት እንዳይበተን ሁሉም ሃላፊነት ይውሰድ።