Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተግዳሮቶቹን ለመሻገር…

0 1,054

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተግዳሮቶቹን ለመሻገር…

                                                            ታዬ ከበደ

ፌዴራላዊ ሥርዓታችን በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል። መንገዶቹ ግን አልጋ በአልጋ አልነበሩም። እንደ ማንኛውም ተግባር በየጊዜው ተግዳሮቶች ሲያጋጥሙት ነበር። በተለይም በአገራችን ውስጥ አሁንም ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት አለመስረጽ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት መኖር፣ የኃይማኖት ጽንፈኝነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መከሰታቸው እንዲሁም ተጨማሪ የልማት ፍላጎቶች መኖራቸው ብሎም የዴሞክራሲው በበቂ ሁኔታ  አለመጠናከርና ድህነት አሁንም መኖሩ በተግዳሮትነት የሚታዩ ችግሮች ናቸው። ይሁን እንጂ፤ ተግዳሮቶቹ በመንግሥት ቁርጠኝነትና በላቀ የህዝብ ተሳትፎ የሚፈቱ መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል።

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መግቢያ ላይ የሰፈረው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ስምምነት በተጨባጭ እየተሳካ እንደሆነ ያለፉት 27 ዓመታት ጉዞ በተጨባጭ ያሳየ ይመስለኛል። ዛሬ ሀገራችን ውስጥ ብዝሃነት የዴሞክራሲያዊ አንድነታችን መገለጫ ሆኗል። ይህም ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዝሃነትን አስመልክተው ይራመዱ የነበሩ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ሙሉ ለሙሉ የቀየረ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውሰጥ የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአጋርነት ታሪክ ህገ መንግሥታዊ ዋስትና በማግኘታቸው የአብሮነቱ እሴቶች ሊሆኑ ችለዋል። አንድ ማኅበረሰብ ማንነቱ እንዲከበርለት የሌላውን ማንነት ማክበር እንዳለበት በማመን በተናጠልና በጋራ ባህሎቻቸውንና ታሪካቸውን ማክበርና ማንፀባረቅ የተቻለበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ዛሬ በኢትዮጵያ የመገንጠል መብት ህገ መንግሥታዊ ዋስትና ቢያገኝም፤ የማኅበረሰብ ጥያቄ መሆኑ እያበቃለት ይገኛል—በጊዜ ሂደት የነበሩት አስተሳሰቦች ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ እየተመዘኑ በመክሰም ላይ መሆናቸውን መናገር የሚቻል ይመስለኛል።  

እርግጥ የደርግ ወታደራዊ አገዛዝ በወደቀበት ማግስት የነበሩት የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች አንዳንዶቹ ያነገቡት ዓላማ መገንጠልን እንደነበር አይዘነጋም። ሆኖም አብሮ በመኖር ሂደት የተገኘ ጥቅም እያደገና እየሰፋ ስለመጣ የመገንጠል አስተሳሰብ ማኅበረሰባዊ መሰረት አለው ብሎ ለመናገር የሚቻል አይመስለኝም። ለነገሩ አንድ ህዝብ መብቶቹ ተከበረው በጋራ ተጠቃሚነት ውስጥ እስካለ ድረስ ስለ መገንጠል ማሰቡ ሚዛናዊ ዕይታ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም።

ያም ሆኖ የደርግ መንግሥት በወደቀ ማግስት ኢትዮጵያ ትበታተናለች የተባለውና በብዙዎች በቋንቋ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአንድነት ዋስትና አይሰጥም ተብሎ የተነገረው አፈ ታሪክ መሰረት የሌለው ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ህዝቦች ብዝሃነት ከግምት ውስጥ ያላስገባም መሆኑን በተግባር አረጋግጧል።

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብዝኃነት የሀገራችን ጉልበትና አቅም ሆኗል። ሀገራችን ውስጥ ያሉት የተለያዩ ማንነቶች በተናጠል ከሚያስገኙት ጥቅም ይልቅ በጋራ የላቀ ጥቅም እንደሚያገኙ አብረው በቆዩባቸው ጊዜያት ማረጋገጥ ችለዋል። ህብረታቸውን የሚፈታተንና ሰላማቸውን የሚያናጋ ኃይል በጋራ ታግለው ማሸነፋቸው የዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅ ነው።

በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ብዝሃነትን ዕድል ማድረግ የሚቻለው ማንነቶች የሀገርና የሥርዓት ግንባታ ባለቤቶች ማድረግ ሲቻል እንደሆነ ያለፉት ዓመታት ልምድ ትምህርት ሰጥተው አልፈዋል።

በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ተከታታይና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገቡን በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ የብዝሃነት አያያዝ ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ምርጥ ትምህርት የሚሰጥ ሆኗል። በዚህም ብዝሃነት በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ወሳኝ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አውድ ሊሆን ችሏል። ስርዓቱ እነዚህንና ሌሎች ድሎችን ቢያስመዘግብም፤ በተለያዩ ወቅቶች ተግዳሮቶች አጋጥመውታል።

እንደሚታወቀው ሁሉ የሀገራችን ህዳሴ እንቅፋት ይሆናል ተብሎ የሚታሰበውን ሙስናንና ኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብና ድርጊት ከምንጩ ለማድረቅ ሲባል መንግስት የራሱን ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀር በህግ ፊት በማቅረብ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል። በዚህም አስተማሪ በሆነ መንገድ ትምህርት ለመስጠት ሞክሯል።

ምንም እንኳን የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ሊውል የሚችል ባይሆንም፣ ድርጊቱን በሂደት የመቅረፍ ስራዎች ተከናውነዋል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የበፊቱን ሁሉን አቀፍ ክንዋኔዎች የሚያጠናክርና አዳዲስ አሰራሮችን በመከተል ተግባሮቹን እየተወጣ ነው።

ባለፉት ዓመታት መልካም አስተዳዳርን ለማስፈን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ህብረተሰቡን በተደራጀ መልኩ የማንቀሳቀስ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በተለይም በገጠሩ አካባቢ መልካም ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ እስሁን ድረስ የተከናወኑት ተግባራት ውጤታማ ቢሆኑም አሁንም ጠንካራ ሥራ መከናወን እንዳለበት አይካድም፡፡

ልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ መገንባትና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለማዳከም የዛሬ 15 ዓመት ገደማ በተካሄደው የተሀድሶ መስመር ተግባራዊ መሆን ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መልካም ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ታዲያ አሁንም ልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት ያለው እንዲሆንና የግብርናና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣት የበለጠ መትጋት ያስፈልጋል፡፡

የሃይማኖት አክራሪነትም ሌላኛው ችግር ነው፡፡ የሃይማኖት አክራሪነትን የእኔን ብቻ ተቀበል የሚል ፅንፈኛና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው ይህን አክራሪነት ማስወገድ ካልተቻለ እንደ አገር የተተለመን ዕቅድ ማሳካት አይቻልም፡፡ የአክራሪነት መዘዝን በሊቢያ፣ በኢራቅ፣ በሶማሊያ፣ በናይጄሪያና በሌሎች ሀገራት ተመልክተናል። በሃይማኖት አክራሪነት ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን ማከናወን አይቻልም።

በሀገራችን የክርስትናውም ይሁን የእስልምና እምነት ውስጥ ብቅ ጥልቅ የሚሉ የአክራሪነት ዝንባሌ ልክ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን መታገል ይገባል። አክራሪነት በባህሪው ወደ አሸባሪነት በቀላሉ ሊያድግ የሚችል አስተሳሰብ በመሆኑ መዘዙ የከፋ ነው። አሸባሪነት ምን እንደሚመስል ደግሞ ሩቅ ሳንጎ ጎረቤት ሶማሊያ በመሸገውና ‘የአልቃዒዳ ክንፍ ነኝ’ ከሚለው አል-ሸባብ ተግባራት እንዲሁም ቦኮ ሃራም ከተሰኘው የምዕራብ አፍሪካ የሽብር ቡድን እኩይ ምግባራት ለመገንዘብ ብዙም አይከብድም።

አሸባሪነት የየትኛውንም ዜጋ (የራሳቸውን እምነት ተከታይ ሳይቀር) ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጋፋ ብሎም የመኖር ህልውናን በክር ጫፍ ላይ የሚያንጠለጥል የፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ተግባር ማራመጃ መሳሪያ ነው። በዚህ እኩይ ምግባርም የሀገራት ኢኮኖሚ ይንኮታኮታል። በተለይም በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት “የነገ ሰውነታቸውን” ራዕይ መና የሚያስቀር አስተሳሰብ ነው። ድህነትን ታሪክ ለማድረግ በቁርጠኝነት ለተነሱት የሀገራችን መንግስትና ህዝብም እሳቤው አደገኛ ብቻ ሳይሆን ህልውናቸውን ጭምር የሚፈታተን ነው። በመሆኑም በሃይማኖት ውስጥ የሚከሰቱ የአክራሪነት አስተሳሰቦችን በመከላከል ሽብርተኝነትን መዋጋት እንደሚቻል ግንዛቤ መያዝ ይገባል።

የህዝቡ ያለመርካት ጥያቄዎች አንዱ መነሻ ይኸው በመሆኑ መንግስት ይበልጥ እንዲበረታ ያደርገዋል። በአንድ በኩል በአገራችን የተፈጠረው አስደናቂ የልማት እድገት፣ በሌላው ወገን ደግሞ በልማት እድገቱ ምክንያት የተፈጠሩት ያለመርካት ሁኔታዎች ሁለት ተቃርኖዎች ሆነዋል። እነዚህን ተቃርኖዎች ለበጎ በመጠቀም ይበልጥ ተግተን መስራት እንችላለን። በአጠቃላይ የሥርዓቱን ተግዳሮቶች በመንግስት ቁርጠኝነትና በህዝቡ የላቀ ተሳትፎ መሻገር ስለሚቻል ዜጎች በዚህ ረገድ መረባረብ አለባቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy