Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ተግዳሮቶችን ለማለፍ…

0 275

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ተግዳሮቶችን ለማለፍ…

                                                      ቶሎሳ ኡርጌሳ

ባለፉት ስርዓቶች ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያዊያን ምቹ አልነበረችም፡፡ ለብሔሮቿ፣ ብሔረሰቦቿና ህዝቦቿ የሰቆቃ ምድር እንደ ነበረች የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ሆኖም ዜጎች ኑሯቸውን በቅጡ እንዳይገፉ የተቸገሩበት፣ ተስፋቸው ተሟጥጦ ግራ የተጋቡበት፣ መቋጫ በሌለው ጦርነት፣ ረሃብና ስደት የሚንገላቱበት ዘግናኝ ወቅት ዳግም ላይመለስ ተሰናብቷል፡፡ በአዲስ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ቅያድ ውስጥ ገብተናል፡፡

ግንቦት 20 የዛሬ 27 ዓመት እውን ከሆነ በኋላ፤ ዜጎች ለአዲስ ህይወት ማበብ ተስፋ ሰንቀው፣ በፀና ህብረት ላይ ቆመው፣ እጅ ለእጅ ተቆላልፈው ኑሮን ማጣጣም ጀምረዋል፡፡ ንፁህ አየር መማግ፣ በሰላም ገብቶ መውጣት፣ በነፃነት መንቀሳቀስን ችለዋል፡፡ ለዚህ መብቃት የተቻለው ደግሞ የመላው የሀገራችን ህዝቦች ውድ ልጆች በከፈሉት የህይወት መስዋዕትነት ነው፡፡ በውጤቱም በመላ አገሪቱ ሰላም ተገኝቷል፤ የልማት መስመርን አምጥቷል፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በፅኑ መሠረት ላይ እንዲቆም ማድረግም ተችሏል፡፡

እነዚያ አስከፊ የህይወት ጉዞዎች ተገትተዋል፤ ጨቋኙ አምባገነናዊ ስርዓት ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፤ በሕዝብ ጫንቃ ላይ ተፈናጥጦ መንገስ አብቅቷል፤ የመንግሥት ሥልጣን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ የሚረከቡባት ሀገር መፍጠር ተችሏል፤ ምንም እንኳን አሁንም ብዙ የሚቀሩ ጉዳዩች ቢኖሩም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የተጎናፀፉትን ሰላምና ዴሞክራሲ መሰረት በማድረግ ከልማቱ በፍትሃዊነትና እኩልነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ታዲያ የዚህ ሁሉ መነሻ መሰረቱ መራር ግን ጣፋጭ ውጤት ያስገኘው የግንቦት 20 ድል ነው፡፡

ግንቦት 20 የክልሎችን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በተለይም በልማትና በዕድገት አፈጻፀም ረገድ በጎ ርምጃዎች ተወስደው ውጤቶች እንዲገኙ አድርጓል፡፡ በህገ መንግሥት በተደነገገው እኩል የመልማት መብት በመጠቀም በሁሉም ክልሎች በተነፃፃሪ ፈጣን የሚባል ልማትና ዕድገት እየተመዘገበ ነው፤ አሁንም የሚቀሩ ስራዎች ቢኖሩም፡፡ በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ህዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያስቻለ ነው፡፡

በዚህም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተሳትፏቸውና በየደረጃው ተጠቃሚነታቸው ጎልብቷል፡፡ አካባቢያቸውንም በማልማት ለአገር ብልፅግናና እድገት ከፍተኛ ደርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ፤ የልማትና ዕድገት አፈጻፀም በእኩል ተጠቃሚነት እውን እየሆነ ነው፡፡

ለዚህም መንግሥት ባለፉት 27 ዓመታት ምጣኔ ሃብታዊ ህጎችን፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በየአካባቢው ተጨባጭ እቅድ እየተመነዘሩ የሚፈፀሙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በአፈጻፀም ሂደት የተገኙ በጎ ልምዶችም መቀመርና ያልተፈፀሙትን በመለየት የህዝቦችን ተጠቃሚነት በአግባቡ በመለየት የተገኘውን ድል ማስቀጠል ይገባል፡፡

የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች የሚለዩበትን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ካለፉት ልምዶች በመነሳት እንዲፈተሹና እንዲስተካከሉ ማድረግም ያስፈልጋል። የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መስራት ይገባል፡፡

ክልሎች በገጠርና ከተማ የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅዶችን በመንደፍና ህዝቦቻቸውን ዋናው ፈፃሚ አካል በማድረግ ባለፉት ዓመታት በአማካይ ለተመዘገበው ከሁለት አሃዝ በላይ ዕድገት የድርሻቸውን ያበረከቱ ቢሆንም፤ አሁንም በተለይ በመልካም አስተዳደር ረገድ የሚታዩ ጉድለቶችን በየጊዜው እየፈተሹ እልባት መስጠት ያስፈጋል፡፡

ርግጥ የፌዴራል መንግሥት ክልሎችን ከክልሎች ብሎም ከአዋሳኝ አገሮች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን በመስራትና ፈጣን የቴሌኮም አገልግሎቶችን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማፋጠን፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትንና የአገር ውስጥና የውጭ አገር የገበያ ትስስርን በመፍጠርና በማጎልበት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱ ግብ በአስተማማኝ ሁኔታ መሰረት እየጣለ ነው፡፡ በእነዚህ መንግሥታዊ ስራዎች ውስጥ የሚታዩት የተጠቃሚነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳይገነግኑ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል።

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት መግቢያ ላይ የሰፈረው  አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ስምምነት በተጨባጭ እየተሳካ እንደሆነ ያለፉት ዓመታት ጉዞ በተጨባጭ አሳይቷል፡፡

አንድ ማኅበረሰብ ማንነቱ እንዲከበርለት የሌላውን ማንነት ማክበር እንዳለበት በማመን በተናጠልና በጋራ ባህሎቻቸውንና ታሪካቸውን ማክበርና ማንፀባረቅ ችለዋል፡፡ ይሁንና አሁንም ዴሞክራሲያዊ አንድነትንና ኢትዮጰያዊነትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች ኢትዮጵያ የእኔ ናት የሚል አስተሳሰብ በመያዝ የችግሯም ይሁን የስልጠቷ ማገር እነርሱ መሆናቸውን ማመን አለባቸው፡፡  

እንደሚታወቀው የደርግ መንግሥት በወደቀበት ማግሥት ኢትዮጵያ ትበታተናለች የተባለውና በብዙዎች በቋንቋ ወይም በማንነት ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአንድነት ዋስትና አይሰጥም ተብሎ የተነገረው ታሪክ መሰረት የሌለው መሆኑን ባለፉት ዓመታት ጉዞ በተግባር ታይቷል፡፡

ያም ሆኖ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ጉዳዩች ብንለያይም፤ ያለችን አንድ ሀገር ናት፡፡ ለዚህች ሀገራችን ያለንን ሁሉ በመክፈል ልዩነታችንን ጌጥ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን የእኛነታችን ምንጭ ልናደርጋቸው ይገባል፡፡ ይህን ስናደርግ የግንቦት 20ን ድሎች የበልጥ አጠናክረን እናስቀጥላለን፡፡

ግንቦት 20 ትሩፋቶቹ ይበዛሉ፡፡ ሆኖም አሁንም ከኢትዮጵያዊነትና ከዴሞክራሲያዊ አንድነት አኳያ የሚታዩ ክፍተቶችን መድፈን ይገባል፡፡ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የራስን ማንነት እንደሚያከብር ሁሉ ሌሎችም በተመሳሳይ አሉ ብሎ የመቀበል ጉዳይ ነው። ይህም እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ መተሳሰብንና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ ያስችላል፡፡ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ማስቻያ መንገድ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህም ዜጎች እርስ በርሳቸው በመተሳሰብና በመደጋገፍ የጋራ ቤታቸው የሆነችውን ኢትዮጵያ አሁን ካለው ፍጥነት በላይ እንዲያንጿት ምክንያት ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያችን ውስጥ የጋራ የልማት ተጠቃሚነትን ለሚያረጋግጥ መንግሥትም ይሁን ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን ካጠበቁ፤ የሰላም አየርን በአስተማማኝ ሁኔታ እየተነፈሱ የግንቦት 20ን ድሎች በማስቀጠል ችግሮቻቸውንም በዘላቂነት መፍታት የሚችሉ ይመስለኛል፡፡ የግንቦት 20ን የድል በዓል ስናስብ፤ የተገኙት ለውጦች ግለታቸውን ጠብቀው እንዲጓዙ እንዲሁም ከወቅቱ ጋር እየተፈጠሩ ያሉ ተግዳሮቶችን ማለፍ እንደሚገባን ልንዘነጋ አይገባም፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy