Artcles

ችግር ፈችው ህዝብ ነው!

By Admin

May 09, 2018

ችግር ፈችው ህዝብ ነው!

                                                        ይሁን ታፈረ

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአገር ውስጥ ጉብኝቶች ወቅት፤ “ሁሉም ችግሮች በአንድ ጊዜ ይፈታሉ፣ ችግሮቹንም የሚፈታው ፌዴራል መንግስት ነው” የሚሉ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። ይሁን እንጂ በአንድ ጀንበር የሚፈታ ችግር የለም። ችግሮችን መፍታት የሚቻለው ደረጃ በደረጃ ነው። ክንዋኔውም ህዝብን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ባሳተፈ መልኩ በሚካሄድ ጥረት ላይ በሚመሰረት ተግባር ይሆናል።

ሕዝብ የሚፈልገው ለውጥ፣ እድገትና ብልጽግና ሊመጣ የሚችለው በዋነኛነት የየክልሉ መንግሥታትና ሕዝቦቻቸው በሚያደርጉት የተቀናጀ ጥረት ነው። የፌዴራል መንግስት የራሱን የቤት ስራዎች መከወን ቢኖርበትም ሁሉንም ከእርሱ መጠበቅ ተገቢ አይደለም። ህዝብ ያልተሳተፈበት ማንኛውም ስራ ለውጤት ሊበቃ አይችልምና። ጥያቄዎችን መጠየቅ ይቻላል፤ ግን ህበረተሰቡም የጥያቄዎቹ መልስ መሆን አለበት።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ማንኛውም ሰው ያሻውን ጥያቄ ማቅረብ ይችላል። ማንም አይከለክለውም። ሆኖም እየኖርንበት ያለው አገር ህግና ስርዓት ያለው እንደመሆኑ መጠን፤ ጥያቄዎች ሲቀርቡ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መሆን ይገባቸዋል። የሁከት መንገድ ራስን፣ አካባቢን፣ የስራ ቦታንና አገርን ከመጉዳት ውጭ አንዳች ዓይነት ፋይዳ አይኖረውም። በሰላም እንጂ በሁከት ሰላማዊ ጥያቄዎቹን መመለድስ የቻለ፣ የበለፀገና ተጠቃሚ መሆን የቻለ አገር መኖሩን እርግጠኛ አይደለሁም። አይመስለኝምም።

የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላምን ጥቅም የሚገነዘብ ነው። የሁከትን ጥፋት ደግሞ ከቅርብ ጊዜው የኪራይ ሰብሳቢዎችና የኮንትሮባንዲስቶች ተግባር መረዳት ተቻለ ይመስለኛል። እናም የሰላሙ ጠባቂ ህብረተሰቡ ራሱ መሆኑን በመገንዘብ ጥያቄዎቹን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ያስፈልጋል።

በዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር የፀጥታ ሃይል ብቻ በማሰማራት ለውጥ ማምጣት አይቻልም። የየቀየው ባለቤት ህዝቡ ነው። በፀጥታ ሃይል የሚሰጥ ምላሽ መሰረቱ ምናልባት ነገሮችን ለማረጋጋት ይጠቅም ይሆናል። ይሁን እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም። እናም የየመንደሩ ጠባቂና የሰላም ዘብ ህብረተሰቡ እንደመሆኑ መጠን ለሰላሙ መትጋት ይኖርበታል።

ቀደም ሲል እንዳልኩት ከአገራችን ህዝብ በላይ የሰላምን ጥቅም በሚገባ የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። ከ26 ዓመታት በላይ በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ውስጥ ያገኘውን የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን ጠንቅቆ ያውቃልና። እናም ስለ ሰላም ሲነሳ የመጀመሪያውና ቀዳሚው እማኝ ሊሆን የሚችለው የአገራችን ህዝብ ይመስለኛል።

ይህ ህዝብ ላለፉት 26 ዓመታት የተራመዳቸው የልማት አባጣና ጎርባጣ ውጣ ውረዶች በአሁኑ ወቅት የሚቀራቸው ተጨባጭ ለውጦች ቢኖሩም፤ ከትናንቱ በተሻለ ቁመና እንደሚገኙ ያውቃል። እርሱንም በተሻለ ማማ ላይ እንደሚያወጡት በልማቱ ውስጥ ተዋናይ የሆነው ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ራሱን ዋቢ አድርጎ ማቅረብ ይችላል።

ትክክለኛ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ካሉ፣ ህዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግስት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና መደግ እንደሚቻል ሩብ ክፍለ ዘመንን እልፍ ባለ ዓመት ጊዜ ውስጥ ትምህርት እንደወሰደ ራሱ እማኝ ነው።

አምባገነኑና የዕዝ ኢኮኖሚ መርህን የሚከተለው የደርግ ሥርዓት ከመውደቁ በፊት የአገራችን ምጣኔ ሃብታዊ አሃዝ ከዜሮ በታች እንደነበር የማይዘነጋው ይህ ህዝብ ስለ ሰላም ቢናገር የሚበዛበት አይደለም።

አምባገነኑ ስርዓት እንደወደቀም በአንድ በኩል ሰላምን የማረጋጋት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደቀቀውን ኢኮኖሚ ለማቃናት የከፈለውን ከባድ መስዕዋትነት በሚገባ ይገነዘባል። ያኔ ተራራ የሚያክለውን የአገሪቱን ድህነት ለመዋጋት የተለያዩ መርሆዎችን ቢሰንቅም የሚፈለገው ዓይነት ለውጥ እንዳልመጣና ለረጅም ጊዜ በሀገራችን ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን የድህነት አዙሪትን ለመቀልበስ እንዳልተቻለ በማወቁ ሌላ መንገድ እንዲቀየስ ማስፈለጉን የሚያስታውስ ህዝብ ነው። ዛሬም የመልካም አስተዳደር ችግሮች ቢኖሩም ህዝቡ ራሱ የመፍትሔው አካል መሆን ይኖርበታል።

እንደሚታወቀው በእኛ ሀገር ዕውን በሆነው ባልተማከለው ፌዴራላዊ ስርዓት መሰረት፤ ህዝቡ የፖለቲካ መሪዎቹንና ተወካዩቹን ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ደረጃ ድረስ ይሾማል፤ይሽራል። ህዝቡ በምርጫ ካርዱ አማኝነት በቀጥታ የስልጣን ባለቤት የሆነበት ይህ አሰራር በስርዓቱ ውሰጥ ወሳኝ ሚና ቢኖረውም፤ በህዝቡ በቀጥታ የማይመረጡና ሊመረጡ የማይችሉ አካላት ግን መኖራቸው አይቀርም። በዚህ የአሰራር ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቀሱት ስራ አስፈፃሚው ሲቪል ሰርቪሱና የዳኝነት አካላት ናቸው።

እነዚህ አካላት ለመልካም አስተዳደር አተገባበር ያላቸው የማይተካ ሚና ስለሚታወቅም፤ እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ ሀገር በምክር ቤቶች የሚሾሙ ወይም ለምክር ቤቶቹ ተጠሪ ይሆናሉ። ሆኖም ግን የየራሳቸው ነፃነት ያላቸው አካላት መሆናቸውን መረዳት ይገባል።

በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ ስራ አስፈፃሚውና ሲቪል ሰርቪሱ ማንም እንዳሻው የሚዘውራቸው አካላት አለመሆናቸውን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል። ይህ ደግሞ የአንድን አካል ፍላጎት ለማሟላት ተብሎ የሚደረግ ሳይሆን፤ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታው አሁን ካለበት ጅምር መንገድ እየተጠናከረና ስር እንዲሰድ ካለ መሰረታዊ ፍላጎት የሚመነጭ ነው።

እናም ህዝቡና የህዝቡ ተወካዩች በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መክረው ያፀደቋቸውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ህጎች በተሟላ ሁኔታ የሚያስፈፅሙ እንዲሁም ለሁሉም ዜጋ ያለ አድልኦ ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ተቃዋሚዎች ነገሮችን በሰከነ መንገድ በማየት መቀበል ያለባቸው ይመስለኛል። ምክንያቱም እነዚህ አካላት ይህን በማድረጋቸው የህዝቡ ሉዓላዊነት መሳሪያዎች፣ አገልጋዩችና የመልካም አስተዳደር ፈፃሚዎች በመሆን ለዴሞክራሲው መጎልበት የነኩላቸውን ሚና መወጣት ስላለባቸው ነው። እነዚህ ተግባራት ህዝቡ በያለበት ቦታ በባለቤትነት መንፈስ ማስፈፀም ይኖርበታል።

በአጠቃለይ የመልካም አስተዳደር ተግባራት በራሳቸው ችግሮች ቢኖርባቸውም፤ መንግስትና ህዝቡ በጋራ እያከናወኑ ባሉት ጥምር ስራዎች ችግሮቹን በጋራ መፍታት ይኖርባቸዋል። ሁሉንም ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፍታት ይገባል። የመልካም አስተዳደር ተግባር ምንም እንኳን ጊዜንና ጥረትን የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ለፌዴራል መንግስት ብቻ የሚተው አይደለም። የክልል መንግስታትና ህዝቦች የየራሳቸውን ተግባር መወጣት አለባቸው። ችግሮች በአንድ ጀንበር ባይፈቱም ሁሉም የስልጣን እርከኖችና የየአካባቢው ህዝብ በጋራ ከተንቀሳቀሱ መፍትሔውን ማሳለጥ የሚቻል ይመስለኛል።