Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ንረቱን መከላከል ይቻል ይሆን?

0 219

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ንረቱን መከላከል ይቻል ይሆን?

                                                       ይሁን ታፈረ

በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ህብረተሰቡን በዋጋ ከመደጎም ባለፈ አቅርቦት እንዳይቋረጥ እያደረገ ነው። በሌላ በኩል ግን፣ ህብረተሰቡ የሚያቀርበው እሮሮ የመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች እጥረትና አቅርቦት ችግር ቢኖርም ቅሉ፤ የተጋነነ ዋጋ የሚጠየቅበትን ምክንያት ግልፅ ነው። ይኸውም በአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች አማካኝነት የሚፈፀም መሆኑ ነው።

ይሁን እንጂ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለውን ልዩነት ግልፅ ቢሆንም፤ የአቅርቦት ችግሩንና የዋጋ ንረቱን መከላከል ይቻላል። በመንግስት በኩል እስካሁን የተደረገው ጥረት የዋጋ ነረቱን በመቆጣጠር ላይ ያለመ ነው። ታዲያ በዚህ ሂደት ውስጥ ህብረተሰቡ የማይተካ ሚና ይኖረዋል።

ህዝቡ በተለይ ሸቀጦች በስውር እጅ በኮንትሮባንድ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ በውድ ዋጋ እየተቸበቸቡና በዚያው ልክም ህብረተሰቡን እያማረሩት ስለሆነ ህዝቡ እንዲህ ዓይነት ችግርን አይቶ እንዳላየ ማለፍ አይኖርበትም። በጥቆማ ከመንግስት ጎን መሰለፍ አለበት።

እርግጥ መንግስት የዋጋ ንረትን ለመፍታት ጥረቶችን እያደረገ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ መንግስት ከመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችና ሸቀጦች ስርጭት አኳያ ስንዴን፣ ዘይትንና ስኳርን ጨምሮ እና የዋጋ ንረት እና እጥረት እንዳይከሰት የዋጋ ቁጥጥር እያደረገ ነው። የምንዛሬ ማሻሻያውን ተከትሎ ምንም ዓይነት የኤሌክትሪክና የውሃ ታሪፍ ጭማሪም እንዳይደረግ በማድረግ የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ የተረጋጋ እንዲሆን በመስራት ላይ ይገኛል።

በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ክልሎች ከውጭ የመጡ ምርቶችን በመጋዘን አከማችተው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው። እርምጃ የመውሰድ ስራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ገበያውን ለማረጋጋት የጅምላ መሸጫ ሱቆች መሰረታዊ ሸቀጦችን በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ ጥረት እየተደረገ ነው።

ይህ ሁሉ የመንግስት ጥረት ህዝቡ በዋጋ ንረት እንዳይጎዳ ለማድረግ የታሰበ መሆኑ ግልጽ ነው። እርግጥ ለዜጎቹ ሃላፊነት የሚሰማው መንግስት የሚያደርገው ይህንኑ ነው። መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል መቼም አጥፎ ስለማያውቅ ይህንንም በማድረግ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ በተለያዩ ጊዜያት የፈፀማቸው ተግባራት ህያው ምስክር ናቸው።

በተለያዩ ወቅቶች መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ተከታታይ የሆኑ ልማታዊ እርምጃዎችን በመውሰድ የህዝቡን ጥያቄ መልሷል። የዋጋ ግሽበቱ ባለ ሁለት አሃዝ በነበረበት በዚያ ወቅት፤ ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ራሱ በማስገባትና በሸማቾች ማህበራት አማካኝነት አከፋፍሏል።

በተጨማሪም ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገዛበትን እንደ የጅምላ መሸጫና የሸማቾች ማህበርን በማደራጀት የህዝቡን ጥያቄዎች የመለሰና በመመለስ ላይ የሚገኝ መንግስት ነው። ይህም የኢፌዴሪ መንግስትን ህዝባዊነትና ሁሌም ቢሆን ለህዝቡ የገባውን ቃል የማያጥፍ መሆኑን የሚያመላክት ነው።

እነዚህ የመንግሥት ተግባራት እየተካነወኑ ያሉት ፍላጎትንና አቅርቦትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። መንግሥት በዚህ ዓመት የመኸር ወቅት የሚገኘውን ከፍተኛ ምርት ታሳቢ አድርጓል። የሚገኘው ምርት አቅርቦትንና ፍላጎትን ከማመጣጠን ባሻገር፤ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ፍላጎትን መሸፈን የሚችል ነው።

በአሁኑ ወቅት የግብርናው ዘርፍ ጥንካሬ ከፍተኛ ምርት ይገኝበታል በሚባለው የመኸር ምርት እየታየ ነው። ምርቱ እያደገ ለመጣው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው ግብዓትነት እንደተጠበቀ ሆኖ ምናልባት የዋጋ ንረት ቢከሰትም ችግሩን ለመቅረፍ ጉልህ ሚና ይጫወታል።

መንግሥት ባስቀመጣቸው የግብርናው ዘርፍ የልማት ፕሮግራሞች፣ ስትራቴጂዎችና መርሀ ግብሮች በመጠቀም ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮችን በማበረታታትና በመሸለም በርካታ ውጤታማ አርሶ አደሮችን ለማፍራት ተችሏል። ሽልማቱ ብዙዎችን አነሳስቷል። በአሁኑ ወቅትም በርካታ ሞዴል አርሶ አደሮች በመፍጠርም ላይ ይገኛሉ። ስለሆነም በሂደት የተጎናፀፍነው ድል ለላቀ ሁለተኛው ዕቅድ እንዳነሳሳን ግልፅ ነው።

ከዚህ አኳያ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በትክክል ውጤትማ እየሆኑ ነው። በአፈጻጸሙ ከተጠበቀው በላይ መጓዙን መረጃዎች ያመለክታሉ። በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ዘመንም ይህን የምርትና ምርታማነት ዕድገት መጠን ለማሳደግ ስራው እየተሳለጠ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ የግሉ ዘርፍ በግብርናው ውስጥ መሳተፍ የጀመረው በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ውስጥ ነው። ከእነዚህ ዘርፎች ውጪ ባለሃብቱ የግብርና ልማት ውስጥ መሳተፍ የጀመረው በመንግስት በኩል በመስኩ በተደረገው የማበረታቻ ጥረት መሆኑ ይታወሳል። እነዚህን ባለሃብቶች ከአነስተኛ አርሶ አደሮች ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ ተግባራትን ለመከወን እየተሰራ ነው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግስት እየተከተለ ባለው የግብርና ልማት ስትራቴጂ ትርፍ አምራች ዜጋዎችን ምፍጠር ተችሏል። እነዚህ አባቢዎች በድርቅ የተጎዱት አካባቢዎችን እየሸፈኑ ነው። ይህም የድርቅ አደጋ ተጋላጭነት ቢኖርም ችግሩን በራስ አቅም ለመቋቋም አስችሏል።

ያም ሆኖ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመከላከል እየሰራ ነው። በተለይም ከውጭ የሚገባውን ነዳጅ በየጊዜው ድጎማ እያደረገ ባለበት እንዲቀጥል እያደረገ ነው። ነዳጅ ከአገሪቲ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ጋር ያለው ቁርኝት ከፍተኛ ስለሆነ በዚህ የምርት ውጤት ላይ ድጎማ ማድረግ የአገር ውስጥ ዋጋን ለማረጋጋት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የባንኮች የፋይናንስ ሥርዓት የማስተካከል ሁኔታና የዜጎች የቁጠባ አቅም እንዲያሳድጉ በመደረጉ ሳቢያ የዋጋ ንረቱን ለማርገብ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የብድር ሥርዓቱን የመቆጣጠር ተግባር በገበያው ውስጥ ከፍተኛ ገንዘብ መረጨቱ የዋጋ ንረት እንዲስተካከል የሚያደርገው የቁጥጥር ዘዴ የመፍትሄው አንዱ አካል አድርጎ በመንቀሳቀሱ ስኬታማ ሆኗል፡፡

ባለፉት ዓመታት የኢኮኖሚው የማምረት አቅም የተሻሻለ፣ ቀጣይና ተከታታይነት ያለው እንደነበር አይካድም። በእርግጥ ይህ ልዩነት እምብዛም የገነነ ነው ብሎ መጥቀስ ግን አይቻልም። ይህ ሁኔታ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ጫና እንዳይፈጥር መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ የዋጋ ንረቱን እየተቆጣጠረ ነው። በዚህም ንረቱን እየተከላከለ ነው። የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከታከለበት ንረቱን አሁን ካለበት ይበልጥ እንዲቀንስ ማድረግ  ይቻላል። ህብረተሰቡ ማን ምን እንደሚሰራ፣ የትኛው ነጋዴ ህጋዊ ትርፍ እንደሚያገኝና የትኛው ደግሞ ህገ ወጥ ትርፍ ለማጋበስ እንደሚፈልግ በሚገባ ያውቃል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ሰዓት ከንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ የራሳቸውን ፍላጎት ለማርካት ብቻ በዋጋ በመመሳጠር ክፍተት ሲፈጥሩ የቆዩበት የአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች የኮንትሮባንድ አሰራር ሁኔታም አንዱ ነው። በስኳር፣ በዘይትና በብረት ምርቶች ላይ የሚካሄዱ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ ነው።

እንቅስቃሴዎቹ መልሰው የሚጎዱት ህብረተሰቡን ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ ምንም ዓይነት ከመልካም አስተዳደርና ከሙስና ጋር የተያያዙ ጉዳዩችን ሲመለከት ያለ አንዳች ማመንታት እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ይኖርበታል። እንዲህ ዓይነቱ የህብረተሰብ ተግባር የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy