Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አስተማማኝነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል

0 274

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አስተማማኝነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል

አቅርቦትን ለዜጎች ለማዳረስ

 

ስሜነህ

ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግብን እና የድህነት ቅነሳ ፕሮግራምን ለማሳካት ከያዘቻቸው መርሐ ግብሮች መካከል አንዱ አስተማማኝነት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለዜጎች ማዳረስ ነው፡፡ ይህን እውን ለማድረግና ለማሳካትም የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም በ1998 ዓ.ም ይፋ ተደርጎ በፕሮግራሙ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋንና አቅርቦት የሚያሳድጉ ልዩ ልዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡

 

የአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ለገጠር ከተሞች፣ ቀበሌዎችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን በማዳረስ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ሽፋንን የማሳደግ እንዲሁም የቀበሌዎችና መንደሮችን የመልሶ ግንባታ ሥራን በማከናወን የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስተማማኝነትን የመጨመርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት፡፡

 

ከ2002 ዓ.ም እስከ 2007 ዓ.ም በተተገበረው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ላይ 4727 ከተሞች በአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ ሽፋኑም 54 ነጥብ 25 በመቶ መድረሱን መረጃዎች አመላክተዋል ፡፡ ይህንን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ሽፋን እውን ለማድረግም ከመካከለኛ እና ዝቅተኛ መስመር ግንባታ በተጨማሪ 1ሺ 513 ኪሎ ሜትር የሚሆን የማስተላለፊያ መስመር እንዲሁም የ65 የማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ እና የማስፋፊያ ሥራዎች መከናወናቸውን የተመለከተ መረጃ ተሰጥቶን እንደነበረ ይታወሳል፡፡

 

በኢነርጂ መስክ በፍላጐትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ከማጣጣም ባሻገር አሁን ያለውን ዝቅተኛ የነፍስ ወከፍ ዓመታዊ ፍጆታ በማሳደግ ለኤክስፖርት በሚያበቃ ሁኔታ አቅርቦቱን ማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር እንደሆነ በአንደኛውም ሆነ በሁለተኛው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ አንፃር የኢነርጂ ልማትን በመላ ሀገሪቱ በማስፋፋትና በማሳደግ ለሁሉም አካባቢዎች እንዲዳረስ ለማድረግ የተቀረፀው ሀገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ሀይል የማዳረስ ፕሮግራም ከአቅምም ይሁን ከአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች የተነሳ የተሳካ አይመስልም፡፡

 

በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች ይልቁንም የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ አሁንም የኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ የተቆራረጠ  ነው። በቀን ለ3 እና 5 የሚደርሱ ሰዓታት ብቻ የተፈቀደላቸው ከተሞች እና መንደሮች የተበራከቱ ሲሆን የፈረቃን ዘመን መናፈቃቸውም ተሰምቷል።  ችግሩን በነፃ ስልክ ንገሩን የሚለው መስሪያ ቤት ስልኩ አይሰራም፣ ስልኩ ሰርቶና ተነስቶ ችግሩን ቢያሳውቁም መፍትሄ እንደማያገኙ ነዋሪዎች ቅሬታ እያሰሙ ነው፡፡  

 

ሀይል የማመንጨት፣ የማስተላለፍና የማከፋፈል ሥራዎች የመንግስት ከፍተኛ ድርሻ በመሆኑ የሀገሪቱን ኢነርጂ ልማት ለማስፋፋት የሚረዱ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ተፈፃሚ ማድረግ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ይሆናል፡፡ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ችግር ሙሉ በሙሉ እንዲፈታ ይደረጋል ሲባል የነበረው ሁሉ ከንቱ የሆነም ይመስላል፡፡ይህን ለማጠየቅ አሁን ያለንበትን ደረጃና ከላይ የተመለከተውን ምሬት በሁለተኛው ዙር ከተቀመጠው ግብ አኳያ መመልከት ጠቃሚ ይሆናል።

የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን በ2007 ከነበረበት 4,180 ሜጋ ዋት በ2012 ወደ 17,208 ሜጋ ዋት ለማድረስ የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከውሃ ኃይል ማመንጫ የሚገኘውን ኃይል 13,817 ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ ኃይል የሚገኘውን 1,224 ሜጋ ዋት፣ ከጸሐይ ኃይል 300 ሜጋዋት፣ ከጂኦተርማል ኃይል 577 ሜጋዋት፣ ከመጠባበቂያ/ጋስ ተርባይን/ከነዳጅ 509 ሜጋ ዋት፣ ከቆሻሻ 50 ሜጋዋት፣ ከስኳር 474 ሜጋ ዋትና

ከባዮጋስ 257 ሜጋዋት ኃይል የሚመነጭ ይሆናል ተብሎ ነው፡፡

 

የኤሌክትሪክ ኃይል የማምረት አቅምን በ2007 ከነበረበት 9,515.27 ጌ.ዋ.ሰ በ2012 ወደ 63,207 ጌ.ዋ.ሰ ከፍ ለማድረግ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋንን በ2007 ከነበረበት 60 በመቶ በ2012 ወደ 90 በመቶ ከፍ ለማድረግ ግብ መጣሉም ተመልክቷል፡፡

 

የደንበኞችን ብዛት በ2007 ከነበረበት 2.31 ሚሊዮን በ2012 ወደ 6.955 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ ግብ ተጥሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ ሃይል የማከፋፈል፣ የማሰራጨትና የማስተላለፍ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድጉ ኢንቨስትመንቶች የሚካሄዱ ሲሆን በዚህም አጠቃላይ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ርዝመትን በ2007 ከነበረበት 16,018 ኪ.ሜ በ2012 ወደ 21,728 ኪ.ሜ ከፍ ለማድረግ ግብ ተጥሏል፡፡ ዛሬም ግን ከላይ ለተመለከተው ቅሬታ አብዛኛውን ጊዜ አገልግሎት ሰጪው የሚያቀርበው ምክንያት የማስተላለፊያ መስመሮችን እርጅና እንጂ ከተጣለው ግብ አኳያ አለመስራቱን አይደለም።

 

ሌላም የተመለከተ ጉዳይ አለ። ባለ 500 ኪ.ቮ በ2012 በጀት ዓመት 1,240 ኪ.ሜ ለማድረስ ግብ የተጣለ ሲሆን ባለ 400 ኪ.ቮ በ2007 ከነበረበት 1,397 ኪ.ሜ በ2012 ወደ 2,137 ኪ.ሜ፣ የባለ 230፣132ና 66 ኪ.ቮ መስመርን በ2007 ከነበረበት 13,383 በ2012 ወደ 18,351 ኪ.ሜ ከፍ ለማድረግ ግብ ተጥሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሁን

የሚታየው የኤሌከትሪክ መቆራረጥና የኤሌከትሪክ ኃይል ብክነት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ተብሎም የነበረ ቢሆን በነበረ የቀረ ይመስላል።

 

ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ የኤሌክትሪክ ፍጆታን በ2007 ከነበረበት 86 ኪሎ ዋት ሰዓት በ2012 ወደ 1,269 ኪ.ዋ.ሰ ከፍ ማድርግና የኤሌክትሪክ ሃይል ብክነት በ2007 ከነበረበት 23 በመቶ በ2012 ወደ 11 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ግብ ተጥሏል። የተጀመረውን የተቋም አቅም ግንባታ ፕሮግራም አጠናክሮ በመተግበር የኩባንያዎቹን ተቋማዊ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ዕቅድ ተይዟል፡፡ግን ደግሞ 3ቱን ዓመታት ጨርሰነው ባለንበት አግባብ እቅዱ የተበላ እቁብ መስሏል።

 

ከአማራጭ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎች አኳያ በ2007 ከነበረበት 8.88 ሚሊዮን በድምሩ 11.45 ሚሊዮን የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች፣ 31,400 የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ፣ 20,000 የቤተሰብ የባዮ ዘይት ምድጃ እና የባዮ ዘይት መጭመቂያ ቴክኖሎጂዎች ለማሰራጨት ግብ ተጥሏል፡፡ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂዎችን በተመለከተ 3,600,000 አነስተኛ ማሾዎች፣ 400,000 የቤተሰብ ሶላር ሲስተሞች፣ 3,600 የተቋማት ሶላር ሲስተሞች፣ 5,000 የውሃ ማሞቂያ መሳሪያዎች እና 3,600 በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ማብሰያዎችን ለማሰራጨት ግብ ተጥሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 300 በንፋስ ኃይል የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ ቴክኖሎጂዎች ሥርጭት፣ 135 ከአነስተኛ ወንዞች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትና 33 የአማራጭ ቴክኖሎጂዎች ጥናትና ልማት ለማካሄድ ታቅዷል፡፡እቅድ ብቻ ሆኖ ባይቀር ኖሮ ታዲያ ፈረቃን መናፈቅን ምን አመጣው? ማስባሉ አያጠራጥርም።

 

በሁሉም በሀይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎች መፍጠርና ያሉትን ማጠናከር፣ በራስ ኃይል ጥናት፣ ዲዛይንና ግንባታ ማካሄድ፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን (አነስተኛ ጥቃቅን ማህብራትን) አቅም በማሳደግ አስፈላጊ ግብዓቶችን እንዲያመርቱ፣ በግንባታ ላይ አንዲሰማሩ በማድረግ የወጪ ምንዛሪ ድርሻን መቀነስም መታሰቡ በዚሁ እቅድ ላይ የተመለከተ ቢሆንም ችግሩ ሲፋፋም እንጂ ሲተነፍስ አላየንም።

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy