አገራዊው ኃላፊነት
ዳዊት ምትኩ
በአሁኑ ወቅት መንግሥት እየተከተለ ባለው የለውጥ ሂደት የተለዩ ተግዳሮቶችን ለማስተካከል ቃል ተገብቷል። በዚህም መልካም አስተዳደር የማስፈንና ኪራይ ሰብሳቢነትን የመዋጋት ተግባሮችን ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንደሆነም ተገልጿል። ሚዲያ እንደ ማንኛውም የዴሞክራሲ ተቋም እነዚህን የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫዎችን መደገፍ ይኖርበታል። ሚዲያ የአንድ ሥርዓት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ነጸብራቅ እንደመሆኑ መጠን፤ የትኩረት አቅጫጫውን በመደገፍ ሙያዊና አገራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።
እንደሚታወቀው ሁሉ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ላይ የህዝብ እርካታንና አመኔታን አሁን ካለበት ደረጃ ወደ 85 በመቶ ለማሳደግ ውጥን ተይዞ ስራው እየተከናወነ ነው። ሶስት ዓመታትንም ሊደፍን ነው። ይህም አገራችን ለመልካም አስተዳደር መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው። እናም በየደረጃው መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የግልፅነትና የተጠያቂነት ስርዓትን በሁሉም መንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ዕውን ለማድረግ ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው።
መንግስት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታን በግብነት አስቀምጦ እየተረባረበ ነው። ሃሳቡን ወደ ድርጊት ለመለወጥ በጥረት የታገዙ ጠንካራ እንቅስቃሴዎችን ጀምሮም ዛሬ በለውጥ ሂደት ላይ ይገኛል። እነዚህ የመልካም አስተዳደር ጥረቶች የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት አልቻሉም። በተለያዩ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙና የመንግስትን ስልጣን የግል ኑሮ ማደላደያነት የሚጠቀሙ ግለሰቦች ሳቢያ የህዝቡን እርካታ መፍጠር አልተቻለም።
መልካም አስተዳደርን ዕውን ለማድረግ ከህዝቡ ባሻገር፤ በዴሞክራሲ ማሳለጫ ተቋምነት የተገራጁ አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በዴሞክራሲ ተቋምነት ተመዝግበው እዚህ ሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ አደረጃጀቶች በመንግስትም ይሁን በህዝቡ ዘንድ የሚጠየቀውን የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን በመፍታት እንዲሁም ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው።
በየትኛውም ሀገር ውስጥ የማስተማር፣ የማሳወቅና የማዝናናት ሚናን ይወጣል ተብሎ የሚጠበቀው ሚዲያ፤ የመልካም አስተዳደርን ምንነት ከማስተማር ባሻገር፣ በሀገራችን ውስጥ በጉዳዩ ዙሪያ የሚከሰቱ ችግሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ በማሳየትና ችግሮቹን በማረም ረገድ የሚኖረው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ሚዲያ አግባብ ባልሆነና ከራሱ ስነ ምግባር ባፈነገጠ መንገድ ጥቅም ላይ ከዋለ የሚያስከትለውን ችግር ያህል፤ በአግባቡና ስነ ምግባሮቹን ጠብቆ ከሰራ የሚያበረክተው ማህበራዊ ኃላፊነት ከፍተኛ ነው። በተለይም የሚዲያ ሙያ እምብዛም ባልዳበረባቸው እንደ እኛ ባሉ ሀገራት ውስጥ ሚዲያ የህብረተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎት ተመርኩዞ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባዎችን ከሰራ የሚጠበቅበትን ተግባር በበቂ ሁኔታ የሚወጣ ይመስለኛል። እናም እንደ መልካም አስተዳደር ዓይነት ተግባሮችን የማስተማርና የማሳወቅ ብሎም ከህብረተሰቡ የሚነሱ ችግሮችን በመመርኮዝ ተግባሩን ከተወጣ ሀገራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
ሚዲያው በቅድሚያ በግርድፉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመንቀስ በፊት በጉዳዩ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲያዝ ማስተማር ይኖርበታል። ይህም በተለያዩ ወገኖች መካከል በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን የተለያየ አስተሳሰብ በተቻለ መጠን ወደ አንድ ለማምጣት ያግዛል ብዬ አስባለሁ።
መልካም አስተዳደር የሂደት እንጂ የአንድ ጀምበር ስራ አለመሆኑን ማስተማር ይገባል። እንኳንስ እንደ እኛ ያለ የዴሞክራሲ ጀማሪ ሀገር ቀርቶ፤ ተግባሩን ዕውን በማድረግ ከሁለት ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠሩት ምዕራባውያንም ቢሆኑ ዛሬ የደረሱበት የመልካም አስተዳደር አፈፃፀም የተሟላ ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። ይህ ሃቅም በአንዳንድ ወገኖች ውስጥ ‘መልካም አስተዳደር ለምን አሁን ሙሉ ለሙሉ ዕውን አልሆነም?’ በማለት ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ብቻ ሳይሆን ብዥታንም የሚያጠራ ይመስለኛል።
ይህን ማለቴ ግን ‘መልካም አስተዳደር ጊዜ ስለሚያስፈልገው ምንም ዓይነት የማስተካከያ እርምጃ አይወሰድ አሊያም በደፈናው እዚህ ሀገር ውስጥ የመልካም አስተዳደር ችግር የለም’ ማለት አይደለም። መንግስትም ቢሆን የሚክደው ሃቅ አይደለም፤ በግላጭ ችግሩን ከማመን ጀምሮ፣ በችግሩ ፈጣሪዎች ላይ ተገቢውን አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎችን እስከመውሰድ የደረሰበት አስቸጋሪ ክስተት ነውና።
እናም ሚዲያው ስለ መልካም አስተዳደር ሲያስተምር ስለ ምንነቱ፣ አፈፃፀሙና ተግዳሮቶቹ በተገቢውና ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ በማንሳት ጭምር መሆን ይኖርበታል። ይህ ሲሆንም በመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት የሚፈጠሩ የሙስና እና የኪራይ ሰብሳቢነት ወንጀሎችን በተጨባጭ ማስረጃዎችና መረጃዎች ላይ ተመርኩዞ በማሳየት ህዝባዊ ኃላፊነቱን ይወጣል።
ሚዲያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስኬታማነት የህዝብን ተሳትፎ የሚያጎለብት አጀንዳ በመንደፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪም የመንግስት አሰራር ግልፅነትንና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ ሙስናንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማሳወቅ ከፍ ሲልም በማጋለጥ ሀገራዊ ሚናውን መወጣት ያለበት ይመስለኛል።
ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚነሳውን የህግ የበላይነትን ማስተማርና ህፀፆች ሲኖሩም የመጠቆም ስራዎች ከሚዲያ ይጠበቃል። ይህን በመመስረትም ሚዲያው የህግ የበላይነት ለሁሉም ዜጎች የተሰጠና ምንም ዓይነት ልዩነት የማይደረግበት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ መሆኑንም ማሳወቅና ማስተማር ይገባዋል።
የህግ የበላይነት ሲኖር፤ ህጎች በምክር ቤት ውይይት አማካኝነት ፀድቀው ካልሆነ በስተቀር በየቀኑ ሊቀያየሩ እንደማይችሉ ማስተማርና ማሳወቅ አለበት። ማንኛውም ሰው በእነዚህ ህጎች ስር ሆኖ ስለሚሰራና ህጎቹንም የሚተላለፍ ተጠያቂ ስለሚሆን ከህግ ውጪ እንዳሻው የሚሆን ዜጋ ሊኖር አይችልም። ይህም የህግ ልዕልናን ያረጋግጣል። ከዚህ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ውጪ በመንግስት ስራ አስፈፃሚዎችም ይሁን በተቃዋሚዎች ዘንድ መኖሩ አይቀርም።
ለዚህ አባባሌ በተለያዩ ወቅቶች ሲነሱ የቆዩ ሁለት ፅንፎችን ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል፤ በሀገር ውስጥ ተቃዋሚዎችና በመንግስት አስፈፃሚ አካላት መካከል። ተቃዋሚዎች በአንድ በኩል አባሎቻቸው በተለያዩ መንገዶች ከሀገሪቱ ህጎች ውጪ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተው በህግ ጥላ ስር ሲውሉ “የህግ የበላይነት የለም” ይላሉ፤ በሌላው ወገን ደግሞ የመንግስት አስፈፃሚዎች ‘በህግ በተያዘ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አንገባም” ሲሉ ይደመጣሉ።
እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ሚዲያው አንዱን ፅንፍ አንጠልጥሎ መሄድ አይኖርበትም። የትኛው ወገን ትክክለኛ እንደሆነ ለህዝቡ ግልፅ የሆነ ምስል መፍጠር አለበት። ለዚህም በጉዳዩ ዙሪያ ጥልቅ ግንዛቤ ያላቸውን ባለሙያዎች በማነጋገር ተገቢውን የምስል ክሰታ ከራሱ ፍረጃ ውጪ በማሳየት የህግ የበላይነትን እንዲጎለብት ማድረግ ይኖርበታል።
በዚህም ተቃዋሚዎቹ እንደሚሉት ዕውን የህግ የበላይነት እዚህ ሀገር ውስጥ የለምን?፣ ዕውን ለተቃዋሚዎቹ አንድ ይም ሁለት አባላት ሲባል የሚቀለበስ ህግ ይኖራልን? የህግ የበላይነትን በማስከበር መልካም አስተዳደርን ዕውን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?…ወዘተ. የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት አግባብ ያለውን ዘገባ ጥልቀት ባለው መንገድ የመስራት አገራዊ ሃላፊነት አለበት።
ለፍትህና ለመልካም አስተዳደር እመርታዎች የሚያከናውናቸው ስራዎች የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ህዝብ በቀዳሚ የመረጃ ምንጭነት መጠቀም ይኖርበታል። ምክንያቱም የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት ለዘገባው የሚሆን የዳበረና ተዓማኒ መረጃና ማስረጃ ማግኘት ስለማይቻል ነው። በመሆኑም ሚዲያ ፍትህን ለማጎልበትና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው አገራዊ ጥረት የበኩሉን እገዛ ማድረግ ይኖርበታል።