Artcles

ኢህአዴግን  ኢህአዴግ

By Admin

May 27, 2018

ኢህአዴግን  ኢህአዴግ

ያደረገው…

ወንድይራድ  ኃብተየስ

 

ሰሞኑን ትላልቅ ስብዕና ያላቸው አምስት አመራሮች ከመንግስት የስራ ሃላፊነታቸው  በጡረታ ተሰናብተዋል። እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢህአዴግ ይህችን  አገር በስኬት ጎዳና እንድትጓዝ አድርጓታል። ይህን ስል ኢህአዴግ መላዕክ ወይም ምንም ስህተት  የሚፈጽም አይደለም ማለቴ እንዳልሆነ ግን ይታወቅልኝ። ኢህአዴግ ከነጉድለቱም ቢሆን ለኢትዮጵያ ህዝቦች  ባለውለታ ነው ለማለት ፈልጌ ነው። ዛሬ በጡረታ ተገለሉ የምንላቸው ጉምቱ ታጋዮች ኢህአዴግን ኢህአዴግ ካደረጉት ሰዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ  ናችው። ሰሞኑን አንዳንድ ግለሰቦች ስለእነዚህ አንጋፋ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጎራ ለይተው  በማያገባቸው ነገር ሲነታረኩና ወዲያና ወዲህ ሲጓተቱ ተመልክቼ ነገሩ አስገርሞኛልም፣ አሳዝኖኛልም።

 

ስሜታዊነት ምክንያታዊ እንዳንሆን ያደርገናል። ይሁንና ስሜታዊነት እውነታን ለጊዜው ይሸፍነው ወይም ያሳንሰው  እንደሆን እንጂ በየትኛውም መስፈርት እውነታን ለዘለዓለሙ ሊደብቀው ወይም ሊያደበዝዘው አይችልም። እነዚህ ሰዎች ለዛሬዋ ኢትዮጵያም ሆነ  ለዚህ ስርዓት መሰረቶች መሆናቸውን መካድ ከትዝብት ላይ የሚጥል አካሄድ ይመስለኛል። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት በማህበራዊ ሚዲያ ስለእነዚህ  አንጋፋ ሰዎች የሚነሱ ጉዳዮችን ስመለከት ግራ የሚያጋባ ስሜት ውስጥ ከተውኛል።

 

አንዳንዶች  ስለእነዚህ ሰዎች ለምን  መልካም ነገር ተወርቶ፣ ለምን መልካማቸው  ተነስቶ የሚል ጽንፍ የረገጠ ሃሳብ ሲያራምዱ፤  በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ሰዎች ሰው መሆናቸው ረስተውት  ወይም ተፈጥሮዊ የለውጥ ሂደትን አንቀበልም በሚል መልክ  አዲሱ አመራር በሃይል ገፍቶ ጡረታ እንዳስወጣቸው እንደተጎዱና እንደተገፉ  አድርገው የተሳሳተ ሃሳብ ሲያራምዱ ይታያሉ። ሁለቱም ጽንፎች ለአገራችን አይበጇትም።  በአሁኑ ወቅት ለአገራችንም ሆነ ለህዝባችን የሚበጀው ሰከን ብሎ ማሰብ ይመስለኛል። ሰከን ብሎ ማሰብ  ምክንያታዊ እንድንሆን ያግዛል፤ በመሆኑም ይህን አካሄድ መከተሉ የሚበጅ ይመስለኛል።

 

እየተካሄደ ያለው የመተካካት  ሂደት አሁን የተጠነሰሰ አይደለም። በ2003 ዓ.ም ላይ  ኢህአዴግ ባስቀመጠው የመተካካት መርህ መሰረት እየተተገበረ ያለ  ነገር ይመስለኛል። በዚያን ወቅት የመተካካት መርሁ በሶስት ደረጃ እንዲተገበር  የታቀደ እንደነበር በወቅቱ እንደተገለጸ አስታውሳለሁ። እና የአሁኑ መተካካትም ለእኔ እንደሚመስለኝ  የዚያ እቅድ አካል ነው። ሰው ሊያርፍ፣ ጡረታ ሊወጣ የግድ ነው። ይህን አልቀበልም የሚል አተያይ የጤነኝነት አይመስለኝም። ዛሬ በጡረታ ተገለሉ የሚባሉት ጉምቱ ታጋዮች የወጣትነት   ጊዜያቸውን ሁሉ ለሰላም፣ ለነጻነትና ለእኩልነት ሲሉ በዱር በገደል ታግለውና አታግለው ለዘመናት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲረገጡባት የኖረችውን አገራቸውንና ህዝባቸውን ነጻ አውጥተዋል። ይህን አሌ ልንለው የማንችለው እውነታ ነው። እነዚህ የአገር አባቶች የአገራችን የሰላም፣ የልማትና የዴሞከራሲ መሰረቶች  ናቸው። ይህን አልቀበልም ማለት የጤነኝነት አይመስለኝም።

 

በአገራችን ለተመዘገቡ መልካም ነገሮች  ላይ የእነዚህ ጉምቱ ታጋዮች አሻራ በጉልህ የማይታይበት አንድም ነገር የለም።  ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን ላንሳቸው እንጂ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ሁሉንም ዘርዝሮ ማቅረብ የማይታሰብ  ነው። አገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንባት፣ ጅምርና ለጋ ቢሆንም አገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትተገብር ታግለዋል፤  ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ እነዚሀ ሰዎች የአንበሳውን ድርሻ አበርክተዋል። ዛሬ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው እንዳያፍሩ በቋንቋቸው እንዲጠቀሙ እነዚህ ጉምቱ ታጋዮች የነበራቸው  ድርሻ የሚረሳ አየመስለኝም።

 

ለኢህአዴግ  መተካካት እጅግ ወሳኝና የድርጅቱን ህልውና የሚያስቀጥል ነገር ይመስለኛለ።  ምክንያቱም ድርጅቱ በርካታ የተማሩ ቁርጠኛ አቋም ያላቸው አመራሮችና አባላት ያለው ድርጅት በመሆኑ መተካካቱ ያጠነክረዋል እንጂ ከመስመር የሚያስወጣው አይሆንም።  ድርጅቱ በየጊዜው የህዝብ ፍላጎትን ማርካት የሚችሉ አመራሮችን ወደ ሃላፊነት ማምጣት በመቻሉ ይመስለኛል ጠንካራና ተፎካካሪ መሆን የቻለው። ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን በድርጅቱ የታቀፉት እህት ድርጅቶች በቅርቡ የህዝብን  ፍላጎት ያሳካሉ ያሏቸውን አዳዲስ አመራሮች ወደፊት በመምጣት ወቅታዊ የህዝብ ጥያቄዎችን ለማሳካት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ከላይ እንዳነሳሁት ኢህአዴግ በርካታ ጠንካራ አመራሮችና አባላት ያሉት ድርጅት በመሆኑ ፓርቲው  በጥቂት ግለሰቦች ስብዕና ላይ የተንጠለጠለ እንዳይሆን ተደርጎ የተዋቀረ ፓርቲ ነው። ለዚህም ጥሩ ማሳያው በተለያየ ጊዜ በተለያየ ምክንያት ትልልቅ ስም ያላቸው የድርጅቱ አመራሮች ፓርቲውን ሲሰናበቱ ድርጅቱ በስኬት  ጎዳና መጓዙን የቀጠለበት።

 

ይህ ድርጅት ሺህ ጠንካራ ስብዕና ያላቸውን አመራሮች  ያፈራ፣ ዛሬም እያፈራ ያለ ነገም የሚያፈራ የባለራዕዮች  ፓርቲ ነው። ዛሬ በህዝብ የተወደዱትና የተወደሱትን ዶ/ር አብይን ጨምሮ አቶ ለማ መገርሳን የመሳሰሉ ወጣት አመራሮችን  ያፈራው ኢህአዴግ ነው። አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የአገራችን ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ በሄደበት ሁሉ የህዝብን ቀልብ የመግዛት አቅም  ያዳበሩት በኢህአዴግ ቤት ነው። ጠቅላያችን በውጭ አገር ጉብኝት ባደረጉባቸው አገራት ሁሉ የጠየቁት ሁሉ ማሳካት የቻሉት ወይም ብስል የዲፕሎማሲ ግንኙነት  እንዲከተሉ ያደረጋቸው ኢህአዴግ ቤት ባካበቱት ልምድ ነው። ታዲያ እርሱን (አብይን) ወዶ ኢህአዴግን ጠልቶ ወይም አንኳሶ የሚያዋጣ አካሄድ ነውን? ይህ ፓርቲ  እንደ ዶ/ር አብይ አይነት ሺህ አመራሮችን ያፈራ፣ አሁንም በማፍራት ላይ የሚገኝ፣ ነገም የሚያፈራ ፓርቲ እንደሆነም ሊታወቅ ይገባል።

 

እንደእኔ እንደኔ  ለኢህአዴግ ስኬታማነት በቅድሚያ የሚነሳው የቡድን አሰራር የድርጅቱ መርህ መሆኑ ነው።  ይህ አሰራሩ ጥቂት ግለሰቦች ወደ ድርጅቱ መምጣት እንዲሁም ጥቂት ግለሰቦች ከድርጅት መልቀቅ   በድርጅቱ ላይ ምንም ነገር አያመጣም ባይባልም በመሰረታዊነት የሚያመጣው አዲስ ነገር እንደሌለ ገን  በዕርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ለዚህ ጥሩ ማሳያው አቶ መለስ ናቸው። አቶ መለስ በኢህአዴግ እንዲሁም በኢትዮጵያ  ከዚያም አልፎ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ትልቅ ስብዕና ያላቸው ሰው ናቸው። ይሁንና ኢህአዴግ እሳቸውን አጥቶ እንኳን በስኬት መጓዝ  መቻሉ ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው።

ዛሬ በጡረታ ያሰናበትናቸው ጉምቱ ታጋዮች የወጣትነት   ጊዜያቸውን ሁሉ ለሰላም፣ ለነጻነትና ለእኩልነት ሲሉ በዱር በገደል  ታግለውና አታግለው ለዘመናት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲረገጡባት የኖረችውን አገራቸውንና ህዝባቸውን ነጻ አውጥተዋል። ይህን አሌ ልንለው የማንችለው እውነታ ነው። እነዚህ  በጡረታ የተገለሉት አዛውንቶች የአገራችን የሰላም፣ የልማትና የዴሞከራሲ አባቶች ናቸው ብንላቸው የሚበዛባቸው አይደሉም። አገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንባት፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት እንድትተገብር እንዲሁም ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ እነዚህ ታጋዮች የአንበሳውን ድርሻ አበርክተዋል። ይህን ስኬት ለማስቀጠልና የድርጅቱን ቀጣይነት አስተማማኝና የተሻለ እንዲሆን የአመራር መተካካት  አስፈላጊና የግድ ነው።