Artcles

እውቅናው…

By Admin

May 11, 2018

እውቅናው…

ዳዊት ምትኩ

የበርካታ አገራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ አገራችን እየመጡ ያሉት አገራችን በተስተካከል ቁመና ላይ የምትገኝ በመሆኗ ነው። በዚህም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት በቀውሱ ምክንያት ሳይገደብ እየጨመረ መምጣት ችሏል። በዚህም እንደ አሜሪካ፣ አውሮፓና እስያ እንዲሁም አልጀሪያና ሞሮኮ ያሉ አገራት ግዙፍ ኩባንያዎቻቸውን ወደ ስራ እንዲገቡ እያደረጉ ይገኛሉ።

ምንም እንኳን ማንኛውም የውጭ ባለሃብት ለስራ ወደ አንድ አገር ሲሄድ በቅድሚያ የሚያጠናው በዚያ አገር ሰላምና መረጋጋት አለ ወይስ የለም? የሚለውን ጉዳይ ቢሆንም በአገራችን በጊዜያዊ ቀውስ ባለበት ሁኔታ ውስጥ እንኳ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ አልተቋረጠም። ይህም በኢትዮጵያ አስተማማኝ ስርዓት ለመኖሩ እውቅና የሰጠ ማረጋገጫ ነው ማለት ይቻላል።

እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት የረሀብ፣ የቸነፈርና የጦርነት የዓለም አቀፉ ሚዲያ የዕለት ተዕለት ዘገባ ወጥታ፤ በፈጣን ልማትና ዕድገት አርአያነት መጠቀስ ከጀመረች እነሆ 16 ያህል ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህም አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ አድርጎናል።

መንግስትና ህዝብ ባካሄዱት ከፍተኛ ጥረት ሀገራችን በአለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች። በዚህም ከአፍሪካ በምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ቀዳሚውን ስፍራ እንደምትይዝ የተተነበየላት ኢትዮጵያ፤ ከላይ የጠቀስከቸውን አገራት ኢንቬስተሮችን ቀልብ በመሳብ ላይ ትገኛለች።

ባለፉት ጊዜያት የሀገራችንን ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተጠቅመው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ የሚገኙት የቻይና፣ የቱርክ፣ የህንድ፣ የአውሮፓ፣ የአረብ ሀገሮች ትልልቅ ኩባንያዎችና ባለ ሀብቶች ከመኖራቸው ባሻገር፤ እንደነ ሳምሰንግ፣ በጂኦተርማል ሃይድሮ ፓወር ፕሮጀክት ላይ ለመሰማራት በዝግጅት ላይ የሚገኘው ግዙፉ የአሜሪካ ኩባንያ፣ በማዕድን ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩት የካናዳና የአወስትራሊያ ኩባንያዎችና ሌሎች ፍላጎት ያላቸው ኢንቨስተሮች በመበራከታቸው አሳማኝ አስረጅ በመሆናቸው ነው። ከላይ የጠቀስኳቸ ሀገራትም ጭምር።

ታዲያ ለዚህ የኢንቨስትመንት ፍሰት ሰንሰለት ዋነኛው ምክንያት የኢፌዴሪ መንግስት በሀገራችን የተፋጠነ ልማት ለማምጣት የሚያስችል ትክክለኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ ከመንደፉም ባሻገር፤ በተግባር መተርጎም መቻሉም ይመስለኛል።

እርግጥ በሀገራችን እየተመዘገበ ለሚገኘው ለውጥ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ጉዳይ የጠራ መስመር የያዘ፣ ሀገራዊውን ወቅታዊና ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ በተግባር ላይ የሚያውል አመራርና በህዝባዊ ተሳትፎ የተደገፈ አቅጣጫን የሚከተል የልማታዊ መንግስት መኖሩ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣት ችሏል። አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን የተገነዘቡ በርካታ የውጭ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት የማሳየታቸው ምስጢርም ይኸው ይመስለኛል።

አገራችን በምትከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትክክለኛ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ በግሉ ባለሃብት መሰራት የሚገባቸውና በመንግስት ሊከናወኑ የሚገቡ ተግባራት ተለይተው በመካሄዳቸው በሁለቱም በኩል ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው። የአገር ውስጥም ይሁን የውጭ ባለሃብቶችን የሚሰማሩባቸውን ዘርፎች በመለየት አንፃራዊ በመሆነ መንገድ ለሀገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ተደርጓል።

የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ በመንግሥት ታምኖበት በፍትሃዊ ውድድር ላይ እንዲመሰረት በመደረጉ ባለፉት 27 ዓመታት በርካታ ሐገራዊ ባለሃብቶች ተፈጥረዋል፡፡ እነአዚህ ባለሃብቶች በዓለም የገበያ ውድድር ውስጥ ጠንካራ አቅም እንዲኖራቸው ቀጣይነት ያላቸው ድጋፎች እየተደረገላቸው ነው።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ባለሃብቶቹ የሃብት ባለቤት እንዲሆኑና ለዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ችለዋል። ብዙዎቹ ሀብት እንዲያፈሩ እና ለብዙ ዜጎች የስራ እድል እንዲፈጥሩ ከማስቻሉም በላይ በኢኮኖሚው ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ ችለዋል።

የአገር ውስጥን ባለሃብቶች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር በማቀናጀት ለመፍጠር የተቻለው የገበያ ትስስርም ምቹ የኢንቨስትመንት መሰረትን ጥሏል ማለት ይቻላል። ከእነዚህ ውስጥ የወጪ ንግድ የብድር ዋስትና ሥርዓት መተግበር፣ የውጪ ምንዛሪ ተመን ማስተካከልና የምንዛሪ ዋጋው በገበያ እንዲወሰን ማድረግ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ምቹ ሁኔታዎች ናቸው።

የኤክስፖርት ምርትን ከቀረጥ ነፃ ማድረግ፣ ለኢንቨስትመንት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ የካፒታል ዕቃዎችና ግብዓቶች ያለ ቅድመ- ሁኔታ የሚገቡበትን ዕድል የመፍጠር ብሎም ባለሃብቶቹ ለስራቸው የሚሆን መሬት በሊዝ እንዲያገኙ መደረጉ ተጨማሪ አመቺ መደላድሎች ነበሩ። እነዚህ በመንግስት በኩል አቨስትመንትን ለማበረታታት የተወሰዱ እርምጃዎች የቅጭ ባለሃብቶች ሀገራችን ላይ ዓይናቸውን እንዲጥሉ ያደረጉ ተግባራት ናቸው።

እዚህ ላይ አንድ ዕውነታን ማንሳት አግባብነት ያለው ይመስለኛል። ይኸውም ሀገራችን የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድና የንፁህ መጠጥ ውሃ መሰረተ-ልማቶች ሙሉ ለሙሉ ያልተሟሉባት በመሆኗ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ከሀገራዊው ዕድገት ጋር የሚመጣጠን ግንባታዎች ለማካሄድ በመንግስት በኩል እንደሚካሄደው በተመሳሳይ ሁኔታ የግሉ ባለሃብት ሊከናወን አለመቻሉ ነው።

የግሉ ዘርፍ የኦኮኖሚ ዕድገቱ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑ በመንግሥት ታምኖበት በፍትሃዊ ውድድር ላይ እንዲመሰረት በመደረጉ ባለፉት ዓመታት በርካታ ሃገራዊ ባለሃብቶች እንዲፈጠሩ ቢደረግም፤ ባለሃብቱ ሊሰማራባቸው በማይችላቸው ዘርፎች መንግስት በተመረጠ አኳኋን ጣልቃ ገብቶ ልማቱን በዋነኝነት በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

እነዚህ ድምር ውጤቶች የአገራችን መፃዒ ዕድል አመላካች ይመስሉኛል። መንግስት የሚከተለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችን ያሳደገና የስራ ዕድል የፈጠረ ብቻ አይደለም። እንዲያውም የአገራችንን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት እንደ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ሁሉ ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማምጣት የሚችሉ የውጭ ባለሃብቶችም ወደ ሀገራችን እንዲተሙ ያደረጋቸው ነው።

ይህ ጠንካራ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዳይደናቀፍ በመንግስት ፈፃሚዎች በኩል ብርቱ ጥረት መደረግ ይኖርበታል። በተለያዩ ወቅቶች የውጭ ባለሃብቶች የሚያሰሙትና ሆን ተብሎ በአስፈፃሚዎች የሚፈፀም የሚመስሉ አላስፈላጊ ውጣ ውረዶችን ማስቀረት ይገባል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በኢንቬስትመንት ስም ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ምንም ዓይነት እሴት መጨመር ያልቻሉ ባላሀብቶችን ሚዛኑን በጠበቀና ፍሰቱን በማያስተጓጉል መልኩ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል።

በአጠቃላይ የሚመለከታቸው አካላትና ሥርዓቱ ያፈራቸው ባለሃብቶች በአሁኑ ወቅት የውጭ ኢንቨስትመንትንና የኢንቬስተሮችን ቀልብ መሳብ የቻለውን የሀገራችንን ተመራጭ የኢንቨስትመንት ፖሊሲን በመከተል ተጨማሪ ፍሰት በመፍጠር ያለባቸው ይመስለኛል። ይህም በአሁኑ ወቅት ያለንን ተፈላጊነት ይበልጥ እንዲጨምር ያደርገዋል።