Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

እየጨመረ የመጣው መብት

0 331

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

እየጨመረ የመጣው መብት

                                                          ደስታ ኃይሉ

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ተከብሮ ውሏል። የፕሬስ ነፃነት በዓለም ላይ የተለያየ ታሪክ ያለው ቢሆንም፤ በአገራችን ግን የፕሬስ ነፃነት የግንቦት 20 ውጤት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለጽ መብት ያለ ቅድመ ምርመራ (ሴንሰር ሺፕ) እውን የሆነው በግንቦት 20 ነው። ይህ መብት በአገራችን እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ የመጣ አይደለም።

በህዝቦች ትግል የወደቀው ወታደራዊው መንግስት ከሚከተለው ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ሥርዓት አኳያ ሃሳብንና አመለካከትን በነጻነት የመግለጽ መብት ተገድቦ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ የመገናኛ ብዙሃኑ ባለቤትነትም በመንግስት ብቻ ከመያዙ ባሻገር፤ የቅድመ ምርመራ ህግም ዋነኛው የማፈኛ ዘዴ ሆኖ አገልግሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሃን ሚና በዋነኛው የሀገራዊው ድህነትንና ኋላቀርነት የመቅረፍና ለህዝብ የዴሞክራሲ መብቶች መከበር የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፤ በሥርዓቱ ህልውና ቀጣይነት ላይ ሚያተኩር የፕሮፓጋንዳ ሥራ ተጠምዶ ዘመናትን ተሻግሯል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የደርግ መንግስትን መገርሰስ ተከትሎ የተፈጠረው የፖለቲካል- ኢኮኖሚ ሥርዓት ነፀብራቅ የሆነ መገናኛ ብዙሃን አሰራር መዘርጋት ተችሏል፡፡ በዚህም ለዘመናት የተሻገረው የፕሬስ ነጻነት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል፡፡ የቅድመ ምርመራ አሰራርም አክትሟል፡፡ እነዚህ ለውጦች የተገኙት በግንቦት 20 ነው፡፡

አገሪቱ የተቀናጀ የመገናኛ ብዙሃን የባለቤትነት አቅጣጫን በመከተሏ በመንግስት ብቻ ታጥረው ከቆዩ ሚዲያዎች ይልቅ በብዙ እጥፍ የሚበልጡ የግሉ የህትመት ሚዲያ ውጤቶችን መመልከት ተችሏል፡፡ በዚህም ዜጎች አመለካከታቸውንና ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸው ተከብሮ በሂደት እየጎለበተ ነው፡፡ በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን ከፖለቲካል- ኢኮኖሚው ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው መገንዘብ አዳጋች አይሆንም፡፡

ከዚህ በመነሳትም በአሁኑ ጊዜ የመገናኛ ብዙሃንን የአሰራር ፍልስፍና የሚያመላክቱ ሁለት አስተሳሰቦች ይስተዋላሉ የእነዚህ አስተሳሰብ ምንጭ ደግሞ ፖለቲካል- ኢኮኖሚው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የመጀመሪያው አስተሳሰብ የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞነት ሙያ ዋነኛ ተግባር ዜጎች በነጻነት ራሳቸውን በራሳቸው እንዲመሩ የሚያስችል መረጃ ማቅረብ ነው የሚል የሊበራል ፖለቲካ ኢኮኖሚ አቀንቃኞች አቋም ነው፡፡ ይህም መገናኛ ብዙሃንን ከፖለቲካል- ኢኮኖሚው የተለየ ህልውና እንዳላቸው የማስመሰል ጥረት ነው፡፡ ይህ አመክንዮ የመገናኛ ብዙሃኑ ተግባር የዜጎችን መብት በማስከበር ብቻ የተወሰነ ሊሆን ይገባል የሚል አስተሳሰብ ውጤት መሆኑ ግልፅ ስለሆነ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የዚህ አስተሳሰብ አራማጆች ዜጎች በመገናኛ ብዙሃኑ በየዕለቱ የሚያገኙት መረጃ እነርሱ የሚፈልጉትና በተግባርም ለነጻነታቸውና ራሳቸውን በራሳቸው ለመምራት የሚያስችል መረጃ ማቅረብ አስቸጋሪ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ይህ አስተሳሰብ በጥቅሉ ሲታይ መገናኛ ብዙሃን ተግባርና ሚና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የፖለቲካል- ኢኮኖሚው ነፀብራቅ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

ከዚህም ባሻገር መገናኛ ብዙሃኑ የፖለቲካ ኢኮኖሚው የበላይ አካል የሚቆጣጠራቸው በመሆናቸው በኢኮኖሚ የበላይነትና በፖለቲካ አስተሳሰብ ልዕልና መካከል ያለው ቀጥተኛ ትስስር የመገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካል- ኢኮኖሚው ግንኙነትም ጠንካራ ትስስር ያለው ይሆናል፡፡ የኒዮ- ሊበራል ሥርዓት የዘረጉ ሀገራት መገናኛ ብዙሃን ንብረትነታቸው የግሉ ባለሀብት በመሆኑ፤ ተቋማቱ በመረጃ ሽያጭ የሚተዳደሩና እንደ ንግድ ተቋማት የሚታዩ ናቸው፡፡ ተግባራቸውና የአሰራር ፍልስፍናቸው የመንግስትን የሥራ ሂደት መቆጣጠር ብቻ ነው፡፡ ሁለተኛው አስተሳሰብ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃንን የተቀናጀ ባለቤትነት ሞዴል በመከተል በህዝብ፣ በግልና በማህበረሰብ ባለቤትነት የሚተዳደሩ ሚዲያዎች የመኖር አስፈላጊነትን አቋም የሚገልጹ ወገኖች ምልከታ ነው፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ሚና የዜጎች የመረጃ ልውውጥና የክርክር መድረክነት የሚያገለግል፣ በህዝብና በመንግስታት እንዲሁም በንግድ ተቋማት መካከል ጤናማ ግንኙነት መፍጠር፣ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የሃሳብ ክርክር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማጎልበት መሆን ይኖርበታል፡፡ የህዝቡ ባህል፣ ልምድና እሴት መገለጫና ማሳደጊያ መድረክ የሆነ፣ የመንግስት ሥራን በግልጽነትና በተጠያቂነት የሚያሳድግ፣ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮችን የሚያጋልጥ እንዲሁም የኢኮኖሚ ልማትን ማፋጠንና ውጤታማነቱን ማረጋገጥ የመገናኛ ብዙሃን ሚና መሆን እንዳለበትም ያስረዳል፡፡

ታዲያ ይህ እሳቤ የመገናኛ ብዙሃን የልማት አቅጣጫዎች መገናኛ ብዙሃን በባለቤትነትም ሆነ በሚያቀርቡት የመረጃ ይዘት ብዝሃነትን ማስተናገድ እንደሚኖርባቸው የሚያመላክት አቅጣጫ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እናም ከዚህ ሃቅ የምንረዳው ነገር ቢኖር ‘በልክ የተሰፋ ጥብቆን’ የማጥለቅ አስፈላጊነትን ይሆናል፡፡

እርግጥ ከመጠን በላይም ሆነ በታች የሆነን ነገር ማጥለቁ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን የሀገሬ ሰው “ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጎረቤቱ አይኖርም” በማለት እንደሚገልፀው፤ የመገናኛ ብዙሃን ሚናም ከሀገራዊው ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ስርዓት ጋር የሚጣጣም መሆን የሚገባው ይመስለኛል። ምክንያቱም ከሀገራዊው ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ፍላጎት ጋር የማይጣጣም መገናኛ ብዙሃን ልክ ‘ካለ ቦታው የበቀለ ምንትስ’ እንደሚባለው በመሆኑ ጠቀሜታውና ተፈላጊነቱ እዚህ ግባ ሊባል የማይችል ስለሆነ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ የየትኛውም ሀገር ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ልማትን ማፋጠንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመገንባት አቅጣጫን የሚከተል ነው፡፡ ለዚህም ስኬታማነት የመገናኛ ብዙሃን ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ በመሆኑም የልማታዊውና ዴሞክራሲያዊ መንግስታት የፕሬስ ነጻነትን የሚያሰፍኑ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ከዚህ አኳያ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት፤ የተቀናጀ የመገናኛ ብዙሃን ባለቤትነት የሚከተል፣ የመገናኛ ብዙሃኑ ሚና ደግሞ ለልማቱ መፋጠንና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሚያስችል ዕድልን መፍጠር የቻለ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ በህገ- መንግሥቱ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ የፕሬስ ነጻነትን አስመልክቶ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሃሳቦችና አመለካከቶች በነጻ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል፤ ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነጻነትና የተለያዩ አስተያየቶች የማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው የህግ ጥበቃ ይደረግለታል የሚል ግልፅ ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡ ይህም ሀገሪቱ ከምትከተለው የፈጣን ልማትን የማረጋገጥ ጥረትና ለዴሞክረሲያዊ ሥርዓት ግንባታው መፋጠን የመገናኛ ብዙሃን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የሚያስችል ነው፡፡

እርግጥ በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ልማትን ማረጋገጥ ሀገራዊ ህልውናን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዘመናት የህዝብ ጥያቄ የሆነው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን ማፋጠንም ከልማቱ ጋር አብሮ የሚታይ ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡

በመሆኑም የሀገራችን የመገናኛ ብዙሃን ሚናና የአሰራር ፍልስፍና ከነባራዊው ሀገራዊ የለውጥ ፍላጎታችንና በብዝሃነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት የመገንባት ዓላማ ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህን ለማሳካት ድርሻቸው ከፍተኛ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህን ድርሻቸውን በተለይም ከፕሬስ ነፃነት ጋር አብረው ማጎልበት ይኖርባቸዋል፡፡

ያም ሆኖ ከእስካሁኑ ክንዋኔዎች በመነሳትከፕሬስ ነፃነት መብት ጋር ተያይዞ ሃሳብን የመግለፅ መብት በአገራችን የጨመረበት እንጂ የቀነሰበት ሁኔታ አለመኖሩን መገንዘቡ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy