Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ወሳኙ ሚና

0 411

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ወሳኙ ሚና

ገናናው በቀለ

አገራዊ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነትና ብዝሃነት ከአገራችን አኳያ የየራሳቸው ትርጓሜ ያላቸው ናቸው። እነዚህ ትስስሮች የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ከስኬቶቻቸው፣ ከድክመቶቻቸውና ከችግሮቻቸው ተምረው አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ተግባራዊና ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንደሚገባ አምነው እየተንቀሳቀሱ ነው። ታዲያ በዚህ እንቅስቃሴ ላይ የህዝቡ ሚና ወሳኝ መሆኑ አያጠያይቅም።

በህዝባዊ ትግል አሁን ለሚገኝበት ደረጃ የበቃው ፌዴራሊዝም የአገራዊ አንድነት መሰረት ነው። ሥርዓቱ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ኃይማኖት የመከተል፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸን እንዲጎናፀፉ አድርጓቸዋል። እርግጥም የኢትዮጵያ ህዝቦች የዘመናት ትግል መንስዔም እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ በመሆኑ ይህ ውጤት ከተገኘ 25 ዓመታት ሆኗል።

እናም ይህ ሁኔታ ቀደም ባሉት ጊዜያት አንዳንድ ወገኖች ‘የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ከሆነ ሀገሪቱ ወደ ማያባራ ጦርነት ውስጥ ትገባለች፤ ሀገሪቱም የመበታተን አደጋ ይገጥማታል፣ ህዝቦቿም በየጎራው ተከፋፍለው እርስ በርሳቸው ይጨራረሳሉ’ በማለት ሲገልጡ የነበሩትን የተሳሳተ መፅሐፍ ግምት ፉርሽ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚከተሉት የፌዴራሊዝም ሥርዓት በማህበራዊ ምንነት ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል አብሮ ለመጓዝ ብሎም በማህበራዊ ምንነት ወይም በሌላ የማንነት ልዩነቶችን መሠረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ መሆኑን የመስኩ ተመራማሪዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ይህ አብሮነትም ዜጎች የጋራ ምጣኔ ሀብታቸውን ለማሳደግ ሥርዓቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል።

ከዚህ ዕውነታ የሚነሳው የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ህገ መንግሥቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያፀድቁት የተጫውተው ሚና የላቀ መሆኑ በተግባር ታይቷል። ያም ሆኖ በህዝቦች የላቀ ሚና ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አገራዊ አንድነትን መፍጠር ችሏል።

ህዝቦች ከፊውዳሎችና ከአምባገነኖች ጋር ያደረጉት ትግል ብዝሃነትንም ያረጋገጠ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውሰጥ የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአጋርነት ታሪክ ህገ መንግሥታዊ ዋስትና በማግኘታቸው የአብሮነቱ እሴቶች ሊሆኑ ችለዋል። አንድ ማኅበረሰብ ማንነቱ እንዲከበርለት የሌላውን ማንነት ማክበር እንዳለበት በማመን በተናጠልና በጋራ ባህሎቻቸውንና ታሪካቸውን ማክበርና ማንፀባረቅ የተቻለበት ዘመን ላይ ደርሰናል።

ዛሬ በኢትዮጵያ የመገንጠል መብት ህገ መንግሥታዊ ዋስትና ቢያገኝም፤ የማኅበረሰብ ጥያቄ መሆኑ እያበቃለት ይገኛል—በጊዜ ሂደት የነበሩት አስተሳሰቦች ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ እየተመዘኑ በመክሰም ላይ መሆናቸውን መናገር የሚቻል ይመስለኛል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የተለያዩ ማንነቶች በተናጠል ከሚያስገኙት ጥቅም ይልቅ በጋራ የላቀ ጥቅም እንደሚያገኙ አብረው በቆዩባቸው ጊዜያት ማረጋገጥ ችለዋል። ህብረታቸውን የሚፈታተንና ሰላማቸውን የሚያናጋ ኃይል በጋራ ታግለው ማሸነፋቸው የዚህ አባባል ሁነኛ አስረጅ ነው።

አንዳንዶች በብሔርና በጎሣ የተመሠረተ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር እንደማይሰራ ቢገልፁም፤ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ልምድ የሚያሳየው ግን ከእነርሱ ምልከታ የተለየን ሁኔታ ነው። ብዝሃነት የመጪው ዘመን ዕድላችን በር መክፈቻ ሆኗል። ሆኖም በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ብዝሃነትን ዕድል ማድረግ የሚቻለው ማንነቶች የሀገርና የሥርዓት ግንባታ ባለቤቶች ማድረግ ሲቻል እንደሆነ ያለፉት ዓመታት ልምድ ትምህርት ሰጥተው አልፈዋል።

በብዝሃነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ተከታታይና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገቡን በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተቋማት እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ የብዝሃነት አያያዝ ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ምርጥ ትምህርት የሚሰጥ ሆኗል። በዚህም ብዝሃነት በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ወሳኝ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አውድ ሊሆን ችሏል።

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ህዝቦች እና ኃይማኖቶች እኩል መሆናቸውንና አብሮ ለመኖር ያላቸውን ተስፋ በፌዴሬሽኑ ሰንደቅ ዓላማ መሃል በተቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የሚንፀባረቅ መሆኑን ይገልፃል። ሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎች እኩል እውቅና ተሰጥቷቸዋል። እያንዳንዱ ክልልም የሥራ ቋንቋ የመምረጥ መብት እንዳለው በግልፅ ተደንግጓል።

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶችና የመንግሥት ሥልጣን ምንጮች መሆናቸው በህገ መንግስቱ ላይ ሰፍሯል። ህገ መንግሥቱ የኃይማኖትና መንግሥትን መለያየት መርህ በማስቀመጥ መንግሥት ለሁሉም እምነቶች እኩል የማገልገል ግዴታን ጥሎበታል። ሰው ሁሉ በህግ ፊት እኩል የመሆኑን ያህል የትኛውም ማንነት ከሌላው የማይበልጥና የማያንስ መሆኑም ተረጋግጧል።

እያንዳንዱ ማንነት በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ ታሪኩን የመንከባከብ መበት አለው። እንዲሁም እያንዳንድ ማንነት ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት እንዲረጋገጥለት ተደርጓል።

የማንነታችን ልዩነት በብዝሃነታችን ውስጥ የምንደምቅበት አውድ እንጂ ለመለያየታችን ምክንያት ሊሆን እንደማይችል በግልፅ ተቀምጧል። የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤቶች ብዝሃነታችን መድመቂያ ጌጣችን እንጂ የመለያያ ገመዳችን አለመሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው።

የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ብዝሃነት የፌዴራላዊ ስርዓቱ የማዕዘን ድንጋይ ብቻ አይደለም። ሀገራችን ያጠናቀቀችውን የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በአብዛኛው ማሳካት የቻለ እንዲሁም ሁለተኛውን የልማት ትልም በአጥጋቢ ሁኔታ መፈፀም የምንችልበት ኃይልና ጉልበት ጭምርም ነው።

በመሆኑም በብዝሃነታችን የአንድነት ሃይል እየታገዝን የህዳሴ ጉዟችንን ማሳለጣችን አይቀሬ ነው። ያኔም ብዝሃነታችን የህዳሴ መወጣጫ መሰላል መሆኑን ሁላችንም ህያው ምስክር እንሆናለን። ኢትዮጵያዊነታችን ከምንም በላይ ነው። ይህን ኢትዮጵያ ዊ አንድነት የሚሸራርፍ ምንም ዓይነት ሃይል ሊኖር የሚገባ አይመስለኝም።

የኢትዮጵያዊነት ዋነኛ ማጠንጠኛ ሁሉም ህዝብ ነው። ኢትዮጵያም የሁላችን ናት። ኢትዮጵያዊነታችንን አክብረን እስከያዝን ድረስ አገራዊ አንድነትንና ብዝሃነታችንን በተገቢ ሁኔታ ማስተናገድ እንችላለን። ለዚህም የህዝቡ የተለመደ ወሳኝ ሚና ሊጠናከር ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy