Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የህዝባዊ ፍቅር ማሳያ

0 287

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የህዝባዊ ፍቅር ማሳያ

                                                     ቶሎሳ ኡርጌሳ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከመሰንበቻው በሳዑዲ አረቢያ ባደረጉት ጉብኝት፤ የሪያድ መንግስት በሀገሩ የሚገኙትን ኢትዮጵያዊያን እስረኞች እንዲፈታ ማድረጋቸው እንዲሁም በተሳሳተ ህክምና ከ12 ዓመታት በላይ ራሱን ስቶ የአልጋ ቁራኛ የነበረውን ታዳጊ yሳዑዲ መንግስት ካሳ ከፍሎት ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪያድ ባደረጉት ውይይት፤ ሁለቱ ሀገራት ትርጉም ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለመፍጠር እንዲሁም በሃይል ልማትና በግብርና ዘርፍ ያላቸውን ትብበር ለማሳደግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያንን በማስፈታትና የአንድ ዜጋን ችግር ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትሩና በመንግስታቸው መንግስት የተከናወነው ተግባር ምን ያህል ፅኑ ህዝባዊ ፍቅር ማሳያ እንደሆነ የሚያመላክት ይመስለኛል። ይህ የመንግስት ህዝባዊ ወገንተኝነት ባህሪ ከዜጎች ጋር ያለውን ቅርበትና የመቆርቆር ስሜት የሚያመላክት ነው።

እንዲሁም ኢትዮጵያዊውን ባለሃብት ሼህ ሙሃመድ አላሙዲንን በጥቂት ጊዜ እንዲፈቱ በሳዐዲው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን የተገባላቸው ቃል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድሃም ይሁን ሃብታም በእኩል ዓይን በመመልከት መብታቸውን ለማስከበር በኢትዮጵያዊነት ፍቅር መንቀሳቀሳቸውን አስረጅ ይመስለኛል።  

የኢትዮጵያ መንግስት ለህዝቡ ወገንተኛ ነው። በተለይ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውና የህዝቡን ዜጎችን በመቅረብ እየተከናወነ ያለው ተግባር መንግስትና አመራሮቹ ከምንግዜውም በላይ ከህዝብ ጋር ቅርብ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። በተለይ በሳዑዲ የተከናወነው ተግባር መንግስት በዚያች ሀገር ውስጥ ህገ ወጥ ሆነው በመኖር ላይ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ከመመለስና በተለያዩ ምክንያቶች ታስረውም እስከማስፈታት ድረስ የዘለቀ ቁርጠኝነት የተንቀባረቀበት ነው።

በተለይም በዚያች ሀገር ይኖሩ የነበሩ ህገ ወጦች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በርካታ ጥረቶችን አድርጓል። ከሳዑዲ መንግስት ጋር በመነጋገር ዜጎች በያሉበት ቦታ ሁሉ የጉዞ ሰነዶችን እንዲወስዱ የማመቻቸት፣ ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር የዜጎቹን ህይወትና ንብረት ለመታደግ ያደረጋቸው ስምምነቶች፣ ዜጎቻችን ንብረታቸውን ሳይቀሙና አሻራ ሳይሰጡ እንዲወጡ እንዲሁም አየር መንገዱ መዳረሻዎቹን እንዲጨምርና የትኬት ዋጋም በግማሽ እንዲቀንስ በማድረግ ያከናወናቸው ተግባራት የጥረቶቹ ማሳያዎች ናቸው። በዚህም በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ችሏል።

ታዲያ ይህ የመንግስት ጥረት ስደተኞቹ ወደ ሀገር ቤት ከመጡ በኋላም እንደ ማንኛውም ዜጋ በሀገሪቱ ውስጥ እየተሳለጠ በሚገኘው የልማት ስራዎች ውስጥ በአቅማቸው መሳተፍ እንዲችሉ ያደረገ ነው። በቂ ጥሪት ያላቸውም ሀገራቸው ውስጥ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት መስክ በግልም ይሁን በቡድን ተሳትፎ እንዲያደርጉ ዕድል ፈጥላቸዋል።

በመሆኑም ተመላሾቹ እንደ ማንኛውም ዜጋ በየደረጃው በልማቱ ላይ እንደሚያደርገው አስተዋፅኦ ተጠቃሚ እንዲሆኑና በልማቱ ላይ በሚጫወቱት ሚና ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በር ከፍቷል። አቅም በፈቀደ መጠንም እንደ ማንኛውም ዜጋ ድጋፍ በማድረግ ሀገራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ምክንያት ሆኗል።

ሰሞኑን በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተደረገው እስረኞችን የማስፈታት ተግባር እጅግ ልብ የሚነካ፣ መንግስትና አመራሩ ምን ያህል ለዜጎች የሚያስቡና የሚጨነቁ መሆናቸውን ያሳያል።

ይህ የመንግስት ጥረት በሀገራችን ውስጥ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል በዬ አስባለሁ። በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትራችንና ርሳቸው የሚመሩት መንግስት ሊመሰገኑ ይገባል እላለሁ።

በእኔ እምነት ይህ የጠቅላይ ሚኒስትራችን ጥረት ቀደም ሲል ከሳዑዲ ከተመለሱትም ይሁን አሁን ተፈትተው እየመጡ ባሉት ዜጎቻችን መደገፍ ይኖርበታል። ይኸውም አብዛኛዎቹን ዜጎቻችንን ለእስርና ለእንግልት የሚዳርገውን የህገ ወጥ ስደትን አስከፊነት ለሌሎች የሀገራችን ህዝቦች በማስተማር ነው።

ምንም እንኳን ዜጎች ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የማይችል ቢሆንም፤ በህገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው የእነርሱ ሲሳይ እንዳይሆኑ ማስተማር አለባቸው። በተጨማሪም ሁሉም ነገር ህግን የተከተለ አካሄድ ተጠቅሞ ማደግና ራስን ጠቅሞ ቤተሰብንና ሀገርን መጥቀም እየተቻለ ህገ ወጥ አካሄድን መርጦ ለችግርና ለእስር መጋለጥ እንደሌለበት ማስገንዘብ አለባቸው።

ዜጎች ወደየትኛውም ሀገር ሄደው ለመስራት እስከፈለጉ ድረስ ህጋዊ መንገዶች በመንግስት በኩል በመመቻቸታቸው ይህንኑ መንገድ መከተል እንደሚኖርባቸው ማስረዳት የሚኖርባቸው ይመስለኛል።

ከዚህ ጎን ለጎንም እዚህ ሀገር ውስጥ እየተካሄዱ ባሉት የልማት ተግባራት ላይ በመሳተፍ ራሳቸውን እንዲችሉ መንግስት ለሌላው ዜጋ እንደሚያደርገው ሁሉ ለእነርሱም ድጋፉ የማይለይ መሆኑን በተለይ ቀደም ሲል በመንግስት ጥረት ወደ ሀገር ውስጥ ከተመለሱ ስደተኞች የሚጠበቅ ነው።

ተመላሾቹ እዚህ ሀገር ውስጥ ለሚገኙት ወንድምና እህቶቻቸው ይህን መሰሉን ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የህገ ወጥ መንገድ ተገቢ ያልሆነና ራስን ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን ያመላክታሉ። ይህም መንግስት በሀገር ውስጥ በህግና በአሰራር ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የመግታት ስራ ያግዛል ብዬ አስባለሁ።

ዛሬ ሀገራችን ድህነትንና ስራ አጥነትን በየደረጃው ለመቅረፍ ደፋ ቀና በማለት ላይ ትገኛለች። ይህ ጥረቷም ውጤት በማፍራት ላይ ይገኛል። በተለይም ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች እየታቀፉ ህይወታቸውን በመለወጥ ላይ ይገኛሉ።

ገንዘብ ባይኖር እንኳን በማህበር ተደራጅቶ በመበደር የድህነት ሁኔታን መቅረፍ እየተቻለ ነው። ይህን ሁኔታ ካለመገንዘብ ወደ ውጭ ማመተር ተገቢ አለመሆኑን ተመላሾቹ ለዜጎች ማስረዳት ይኖርባቸዋል እላለሁ።

ህገ ወጥ ስደት ለእስርና እንግልት የሚዳርግ፣ ከፍ ሲልም ህይወትን ጭምር የሚያሳጣ መሆኑን በመግለፅ፣ በሀገር ውስጥ በሙሉ ዜግነት ሰርቶ ማግኘት እንደሚቻል ማስገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል። ይህም መንግስት የታሰሩ ዜጎቹን ለማስፈታት የሚያደርገውን ጥረት በማስቀረት ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ አቅሙን ኢንቨስትመንትን በማምጣት ላይ እንዲያውለው ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ። ያም ሆነ ይህ ግን አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኢፌዴሪ ንግስት በሳዑዲ አረቢያ ዜጎችን ከእስር በማስፈታት ያደረጉት ተግባር ታላቅ የዲፕሎማሲ ድል በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።

ርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት ህዝባዊ በመሆኑ መቼም ሆነ የትም ለዜጎቹ ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ነው። እናም መንግስት እያከናወነ ባለው በዚህ ህዝባዊ ተግባር የማይኮራ ዜጋ ይኖራል ብዬ አላስብም። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መንግስት እያከናወነ ያለው የዲፕሎማሲ ተግባር ከዜጎች ጋር ያለው ቅርበት መገለጫ ይመስለኛል። አዎ! የህዝብ ወገንተኝነትና ፍቅር ያለው መንግስት፤ በየትኛውም ስፍራ፣ ሁኔታና ጊዜ ከህዝቡ ጎን ይቆማል።

 

 

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy