Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

             የመታደስ አቅም

0 294

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

             የመታደስ አቅም

ይልቃል ፍርዱ

የሕብረተሰብ የእድገት ሕግጋት ለውጥ ተፈጥሯዊና ግድ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡የፖለቲካ ድርጅቶችም በዚሁ ማሕበራዊ ሕግ ውስጥ ያልፋሉ፡፡ኢሕአዴግ እንደ መሪ ድርጅት የራሱ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ቢኖሩትም ጠንካራና ብርቱ ጎኖቹ ያመዝናሉ፡፡መራመድና መሄድ ያለበትን ያህል ቢሄድም የግድ በውስጡ ለውጥ ማድረግ ያስፈለገበት አስገዳኝ ሁኔታ ላይ ነው የደረሰው፡፡በለውጥ ሕግጋት መሰረት እድገት ሊመጣ የሚችለው በውስጥ በሚፈጠር ሽኩቻ ወይንም ቅራኔ ነው፡፡የውስጥ ቅራኔ የእድገትና የለውጥ ምንጭ ነው ይለዋል፡፡አሁን በኢሕአዴግ ውስጥ የታየውም ለውጥ ይሄንኑ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ሂደቱ የበለጠ አቅምን ይገነባል፡፡አዳዲስ ለውጦችን ያስገኛል፡፡የመታደስ አቅምን ያጎለብታል፡፡

በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩት ተከታታይ እድገቶች የግድ ይህን ሊሸከም የሚችል አመራርን ይጠይቃሉ፡፡ትላንት ዛሬ አይደለም፡፡በትላንት እሳቤ የዛሬውን እውነታ መምራትና መስተዳደር አይቻልም፡፡ወቅቱን ዘመኑን የተደረሰበትን የእድገት ጣሪያ በኢኮኖሚውም ሆነ በማሕበራዊው ደረጃ የሚመጥን አመራር ይጠይቃል፡፡የሕብረተሰቡን እድገቱን ተከትሎ ሊራመድ ካልቻለ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በአስተሳሰብም በቁመናም ያረጃል፤ይደክማል፤ይጃጃል፤ይሞታል፡፡ይህ እውነት ለመላው አለም ይሰራል፡፡

የሕዝቡ የእድገት ደረጃ የሚጠይቀውን አመራር ግዜውን ተከትሎ መስጠት ካልቻለ፤ የሕዝቡን ጥያቄ በአግባቡ እያነበበና እየፈታ መሄድ ከተሳነው ይዳከማል፡፡የዛኑም ያል እንደ ንስር እየታደሰ መሄድ ከቻለ ለግዜው የሚመጥኑ መሪዎችን እያበቃ ከተጓዘ አቅሙና ኃይሉ ይታደሳል፡፡ከፍተኛ ሀገራዊ አዳዲስ ለውጦችን በማምጣት የሕዝብን ተስፋና እምነት መቀዳጀት ይችላል፡፡አዲሰ ታሪክ በአዲስ ምእራፍ ይመራል፡፡ኢህአዴግ ውስጥ አሁን የታየው የመታደስ አቅም ድርጅቱ ያለውን ብቃት የሚያሳይ ነው፡፡

በውስብስብ ችግሮችና ፈተናዎች ውስጥ ያለፈው ኢሕአዴግ ብርቱ ሁኖ ለሀገራዊ ለውጥ የመስራቱን ያህል በውስጡ የተከሰቱት ችግሮች የመስራት አቅሙን ተፈታትነውታል፡፡ ሙስና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የፍትሕ እጦት በመንሰራፋታቸው የሕዝብን ተቃውሞ ወልደዋል፡፡ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋትን የተፈታተኑበት ሁኔታም ተፈጥሮአል፡፡ ይህን ተከትሎም ከፍተኛ የሰው ሕይወት መጥፋት የንብረት መውደም፤የዜጎች ከመኖሪያ ቀኤያቸው መፈናቀል ደርሶአል፡፡ለሀገራዊ ሰላም መደፍረስ ምክንያት ሆኖአል፡፡ይህን መሰረታዊ ችግር ከስሩ ለመፍታት የተንቀሳቀሰው ኢሕአዴግ እልህ አስጨራሽ በሆነ የከፍተኛው አመራር ግልጽ ውይይትና ግምገማ ከፍተኛ ውሳኔዎችን በማሳለፍ የመታደስ አቅሙን አሳይቶአል፡፡አዲስ አመራር በመሰየም በቀጥታ ወደተግባራዊ እርምጃዎች ገብቶአል፡፡

ድርጅቱ ከገባበት ውስብስብ ችግር ለመውጣት የወሰዳቸው እርምጃዎች አዲስ አመራር መሰየሙ፤ለሕዝብ የገባውን ቃል ጠብቆ እስረኞችን መፍታቱ፤የማእከላዊ እስርቤትን መዝጋቱ፤ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በትብብር ለመስራት የዲሞክራሲ ምሕዳሩን ለማስፋት የሚሰራ መሆኑን ማሳወቁ ፤የሕግ ማሻሻያዎች የሚያደርግ መሆኑን መግለጹ፤በብዙ መልኩ ሀገራዊ ለውጦችን እንደሚያመጣ ተስፋ ሰጪዎች ናቸው፡፡የመታደስ አቅሙን በገሀድ አሳይተዋል፡፡

ሀገራዊ ኃላፊነትን የመሸከም ብቃትን ማረጋገጥ፤ ለሕዝብ መታመን፤ ሀገራዊ አንድነትን የበለጠ ማጎልበት ወቅቱ የሚጠይቀው አቢይ ጉዳይ ነው፡፡ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በተመረጡ በአጭር ግዜያት ውስጥ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ሕዝቡን በቀጥታ በማነጋገርና በማወያየት የሰሩት ስራ በተለያዩ ምክንያቶች ሳስቶ የነበረውን ሀገራዊ አንድነት የበለጠ እንዲጎለብት አድርጎአል፡፡በሀገሪቱ ዜጎች ዘንድ ታላቅ አድናቆትና ከበሬታ አግኝተውበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በቅርቡ በሀዋሳ ስታድየም ለተቀበላቸው በብዙ መቶ ሺሕ ለሚቆጠር ሕዝብ ባደረጉት ንግግር የሕግ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡በውጭ ሀገር የሚገኙ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚሰሩ ተቃዋሚ ሚዲያዎች እዚሁ አዲስ አበባ መጥተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡ከዚህ ቀደም ባለፉት ሀያ አምስት አመታት ባልታየና ባልተለመደ መልኩ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ማጠናከሩ መለያየትን መከፋፈልን በዘርና በጎሳ መናቆርን ይገታል፡፡የበለጠም ብሔራዊ አንድነት እንዲዳብር ያደርጋል፡፡በሕዝቡ ውስጥ ተቀዛቅዞ የነበረው ብሄራዊ ስሜት መግለጽ ከሚቻለው በላይ ገንፍሎ ወጥቶአል፡፡ይህ የሚያሳየው ቀድሞም ሕዝቡ በጋራ የመኖር ባሕሉን እሴቱን አብሮነቱን ቤተሰብነቱን ከልብ እንደሚወደውና እንደሚያፈቅረው ነው፡፡ልዩነትን በማስፋት መራራቅን መጋጨትን በመፍጠርና በመስበክ ሀገራዊ ሰላምን ከመጉዳት ውጭ ለሕዝብ የሚጠቅም ምንም ነገር የለውም፡፡

ዛሬ የአዲሱ አመራር ዘመን የፍቅር የእርቅና የሰላም መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የገለጹ ሲሆን ብቸኛ ሀገራዊ ሰላም ልማትና እድገት የሚያስገኘው መፍትሄም የሚሆነው ትላንትን በመርሳት ይቅርታን በመልመድ መጪውን የወደፊት ግዜ በጋራ መስራት ብሩህ ማድረግ ብቻ መሆኑን ደጋግመው ገልጸዋል፡፡

ቂም በቀል ቋጥሮ የፈረሰ እልቂት ያስከተለ እንጂ የለማና ያደገ የተገነባ ሀገር የለም፡፡ አስተዋይ መሪና ሕዝብ ይቅርባይነትን ምሕረትን ይቀበላል፡፡ሀገርን ከጥፋትና ከውድመት ይታደጋል፡፡በእኛም ሀገር ይሀው ይሆን ዘንድ የሁሉም ዜጋ ምኞት ነው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ እንዳሉት ክፉ ክፉውን በደልን ቂምን እያስታወሱ መበቀልን እንደ ግብ ይዞ መንቀሳቀስ ለሀገር አይበጅም፡፡ መልካምና ቅን አሳቢ መሆን መልካሙን መመኘት ብቻ ነው ለበለጠ ውጤት የሚያበቃን፡፡እንደ ሀገር እንደ ሕዝብም  ከተሰሩት ስህተቶችና ጥፋቶችም ባሻገር መልካም አሳቢዎች መሆን ይገባናል፡፡በአስተሳሰብም መታደስ ግድ ይላል፡፡

የብሔር ብሔረሰቦች የባሕል የእምነት ብዝሀነት በሰፈነባት ሀገር ሁሉም ተከባብሮ ተደጋግፎ ተደማምጦ ልዩነትን አቻችሎ ሲኖር ነው ሀገርን ማሳደግ የሚቻለው፡፡ሀገር የግለሰቦች አይደለችም፡፡ሁሉም ሕዝቦችዋ በእኩልነት የሚጠቀሙባት የሚሰሩባት የሚያድጉባት ስትሆን ነው ዜጎችም ሀገራዊ ፍቅራቸው የበለጠ ሊያድግ የሚችለው፡፡ ኢሕአዴግ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መሪነት ወደ አዲስ ምእራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡በድንቅ የለውጥ ምእራፍ ላይ ይገኛል፡፡ብሩህ ተስፋን ያዘሉ ሀገራዊ እርምጃዎች መግባባቶች በመፈጠር ላይ ይገኛሉ፡፡የመታደስ አቅሙ እየታየ ነው፡፡

የሕዝብ አደራና ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ድርጅቱ ውስጡን በማጥራት አዲስ ጉልበትና ብቃትን በመላበስ ከስህተቶቹና ከውድቀቶቹ በመማር እራሱን እያደሰ እየለወጠ መሄድ ቀዳሚ ስራው አድርጎ ይዞታል፡፡አንድ የፖለቲካ ድርጅት ወቅቱን በሚገባ ማንበብ ሕዝቡ ለሚጠይቃቸውም ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ እየመለሰ መሄድ ሲችል ብቻ ነው ሰፊ ሕዝባዊ መሰረት ሊገነባ የሚችለው፡፡በቆየ አስተሳሰብ አዲስ ዘመንን መምራት አይችልም፡፡ለዘመኑ የሚመጥን ብቃት ሊኖረው ሊፈጥርም ግድ ይለዋ፡፡ሁልግዜም እራሱን እያበቃ መሄድ ሲችል ብቻ ነው ውጤታማ ስራ ሊሰራ የሚችለው፡፡

የድርጅቱ መታደስ መገለጫዎች የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር የፍትሕ ጥያቄዎች በብቃት ለመመለስ መብቃትና መቻል ነው፡፡ሙሰኞችን አጣርቶ ለሕግና ለፍትሕ ማቅረብ  ሙሰናን ከድርጅቱም ሆነ ከመላው ሕዝብ ውስጥ ለማጥፋት ተግቶ መስራትን ይጠይቃል፡፡ሙስናና ሙሰኝነት ሀገርና ትውልድ ገዳይ በሽታዎች ናቸው፡፡የሀገርን ልማትና እድገት ያደናቅፋሉ፡፡

ግለሰቦች የሀገርና የሕዝብን ሀብት በመዝረፍ ለብዙ ሕዝባዊ ጠቀሜታ የሚውሉ በጀቶችን ለግላቸው በማዋል ቀርጥፈው ይበላሉ፡፡ይከብሩበታል፡፡ሕዝብ ከድሕነት ለመውጣት የሚያደርገውን ትግል ያደናቅፋሉ፡፡በሕዝቡም ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታ እንዲነሳ ምክንያትና መሰረት የሆነውም ይሀው ነው፡፡አንዱም በሀገራችን ጎልቶ የተከሰተው ችግር ለተፈጠረውም ሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት መነሻ ምክንያት የሆነው ይሀው አይን ያወጣ ሙስና ነው፡፡

ማጠቃለያ

ዛሬ በሀገራችን እጅግ ከፍተኛ የለውጥ ንፋስ እየነፈሰ ይገኛል፡፡ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖአል፡፡ሕዝቡ ዳር እስከከዳር ወደአንድ ጎራ መሰባሰብ ችሎአል፡፡አዲሱ ካቢኔ ብዙ ስርነቀል እርምጃዎችን በመውሰድ የመታደስ አቅሙን እንደሚያሳይ ይጠበቃል፡፡ መንግስታዊ መዋቅሮች በአዲስ መልክ እንደሚዋቀሩ እስከ ቀበሌ ድረስ፤ሀገራዊ የትምህርት ስርአታችንን በተመለከተ በተግባር የሚለውጡ ስራዎች እንደሚሰሩ፤የሕግ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ፤በተለይም ከዚህ በፊት በግልጽ በሕገመንግስቱ ላይ ያልሰፈሩ በኢትዮጰያ የመንግስት ስልጣን የአመራር ዘመን ከሁለት ግዜ በላይ መሆን እንደማይገባው በሕግ እንደሚደነገግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ይህም የስልጣን ብልግናን ለመከላከል በሕግ መስፈር የሚገባው በመሆኑ ነው የሚሰፍረው፡፡ የመታደስ አቅም ሲጎለብት ገና ብዙ ለውጦችን ያሳየናል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy