Artcles

የሚያዘልቀን የትኛው ይሆን?

By Admin

May 21, 2018

የሚያዘልቀን የትኛው ይሆን?

ኢብሳ ነመራ

ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ/ም ሲነሳ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጉዳይ ይታወሰናል። የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የማንነት መብትና ነጻነት ጥያቄ አንስተው የትጥቅ ትግልን ጨምሮ በተለያዩ መንገድ ሲታገሉ ቆይተው ይህ ትግል አንድ ምዕራፍ የተሻገረው የዛሬ 27 ዓመት ግንቦት 20 ነበር። ከዚያ ቀደም የማንነት መብትና ነጻነት ጥያቄ – ራስን በራስ የማስተዳደር፣ በቋንቋ የመስራት፣ ታሪክን የመንከባከብ፣ ባህልን የማጎለበት ጉዳይ በይፋ ማንሳት ውጉዝ ከመአርዮስ ነበር፤ ያሳስራል፣ ያስገርፋል፣ ያስገድላል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የተለያዩ ብሄሮችና ብሄረሰቦች አባላት የሆኑ ኢትዮጵያውያን ይህን ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ የእስር፣ የግርፋት፣ የግድያ ሰለባዎች ሆነዋል። የብሄራዊ መንነት ጥያቄ ማንሳት የሃገር አንድነትን ለማፍረስ እንደመፈለግ ነበር የሚቆጠረው። ከግንቦት 20 በኋላ ይህ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። ግንቦት 20 ሲነሳ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የሚታወሱን ለዚህ ነው።

ኢህአዴግና ሌሎች በብሄር የተደራጁ የነጻነት ንቅናቄዎች ባካሄዱት የትጥቅ ትግል የደርግ ኢሠፓ መንግስት ግንቦት 20 ቀን 1983 መወገዱን ተከትሎ ለአንድ ወር ያህል በኢህአዴግ መሪነት የሰላምና መረጋጋት ስራ ሲካሄድ ቆይቶ ከሰኔ 24 እስከ 28 ቀን 1983 ዓ/ም የሽግግር መንግስት ምስረታ ሃገር አቀፍ ጉባኤ ተካሄደ፤ በአዲስ አበባ። ይህ ጉባኤ የቀደሙትን ስርአቶች በትጥቅ ሲታገሉ የነበሩ፣ በውጭ ሃገራት በተለያየ መንገድ ስርቱን ሲታገሉ የነበሩ እንዲሁም የደርግ ኢሰፓ መንግስት ከተወገደ በኋላ ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተወካይ የተሳተፉበት ነበር። በዚህ አንድም የውጭ አደራዳሪ ሳይገኝ ኢትዮጵያውያን ሃይሎች ብቻ ባካሄዱት ጉባኤ ለዘለቄታው በእኩልነት ላይ በተመሰረተ አንድነት የሚኖሩበትን መንግስት የማቆም ሃላፊነት ያለው የሽግግር መንግስት አዋቀሩ። ይህ የሽግግር መንግስት መሰረታዊ መመሪያና የሽግግር መንግስቱ መርሆ የሆነ ቻርተር ነበረው። ይህ ቻርተር በጉባኤው ላይ የተሳተፉ አካላት መክረው ያፀደቁት ነበር።

የሽግግር መንግስቱ ቻርተር በኢትዮጵያ የመንግስት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እውቅና የሰጠ ነበር። ቻርተሩ በክፍል አንድ “ዴሞክራሲያዊ መብቶች” በሚል ርእስ ስር በአንቀጽ 2 ላይ፤

 

 

ሀ. የራሱን ማንነት የመጠበቅና የማክበር፣ ባህሉንና ታሪኩን የማበልጸግ፣ እንዲሁም በቋንቋው የመጠቀምና ቋንቋውን የማሳደገ መብት አለው።

ለ. በራሱ የተወሰነ መልከዓምድራዊ ወሰን ውስጥ የራሱን ጉዳይ በራሱ የማስተዳደር፣ እንዲሁም በማዕከላዊ መንግስት ውስጥ በነጻነት፣ አድልዎ በሌለበትና ተገቢ በሆነ የውክልና አግባብ ውጤታማ ተሳትፎ የማድረግ መብት አለው።

ሐ. የሚመለከተው ብሄር፣ ብሄረሰብና ህዝብ ከላይ የተጠቀሱት መብቶች ታገዱ፣ ተረገጡ፣ ወይም ተሸረሸሩ ብሎ ባመነበት ጊዜ የራሱን እድል በራስ እስከነጻነት የመወሰን መብቱን ተግባራዊ የማድረግ መብት አለው። ይላል።

ይህን ተከትሎ 87 መቀመጫዎች ያሉት በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ብሄራዊ የነጻነት ንቅናቄዎች፣ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች የተተፉበት የተወካዮች ምክር ቤትና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያሉት የሽግግር መንግስት ተዋቅሮ የኢፌዴሪ መንግስት እስኪመሰረት ሃገሪቱን ማስተዳደር ጀመረ። የዚህ የሽግግር መንግስት ቀዳሚ ተልዕእኮ የቀጣይ መንግስት ህገመንግስት መቅረጽ ነበር። የተለያዩ የሃገሪቱን ብሄሮችና ብሄረሰቦች ነጻነት ለማስከበር ሲታገሉ የነበሩ ሃይሎች ባጸደቁት  የሽግግር መንግስቱ ቻርተር የብሄሮች ብሄረሰቦች ራስን በራስ የማሰተዳደር መብት ቢረጋገጥም በዚህ ጉዳይ ላይ ቀደም ሲል የነበረው ውዝግብ ግን ቀጥሎ ነበር።

የኢፌዴሪ ህገመንግስትም በአንቀጽ 39 ይህንኑ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መብት ቢያረጋግጥም በአንድ ወገን የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት መከበር በሚደግፉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደራቸው የሃገሪቱን አንድነት ያጠፋል የሚል አቋም ባላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች መሃከል ሙግቱ ተጧጡፎ ቀጠሏል። ይህ ሙግት በተለይ በሃገር ውስጥ ግለቱ እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም አልጠፋም። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እሰጥ አገባው እንደአዲስ ያገረሸበት ሁኔታ ይታያል። በቅርቡ ብሄራዊ ማንነትና ኢትዮጵያዊ አንድነት በሚል በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ይህ ተንጸባርቋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የማንነት መብትና ነጻነትን ጉዳይ አሁን ከተገነባው ፌደራላዊ ስርአት አኳያ መመልከቱን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በመሆኑም የግል አስተያየቴን ልሰጥበት እወዳለሁ።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ከመስጠቴ አስቀድሜ አንድ ሁለት  የማይመነዘሩ መሰረታዊ እውነቶችን (axioms) ማስቀመጥ አፈልጋለሁ። የመጀመሪያው ብሄር ወይም ብሄረሰብ የሚባል ግዙፍ ማህበራዊ ቡድን አለ የሚል ነው። ይሄ ብሄር ወይም ብሄረሰብ የተሰኘ የማህበረሰብ ቡድን የሚኖርበት ወሰን፣ የራሱ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባበህልና ወግ አለው። እነዚህ እሴቶች የብሄሩ ወይም የብሄረሰቡ የማንነት መገለጫዎች ናቸው። እርግጥ ከሌላ ብሄር ጋር የሚጋሩት ታሪክ፣ ባህልና ወግ ወዘተ ያላቸው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች መኖራቸው አይካድም። ወደኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እንመለስ። ኢትዮጵያ በምንላት ሃገር መልክዓምድራዊ ወሰን ውስጥ የተለያየ ብሄራዊ ማንነት ያላቸው ብሄሮችና ብሄረሰቦች አሉ። ይህ አሉ፤ ወይም የሉም ለሚል ክርክር የማይጋብዝ የማይመነዘር ጠጣር እውነት ነው።

እነዚህ የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በቀደሙት ስርአቶች ለማንነታቸው ህጋዊ እውቅና ተነፍጓቸው የነበረ መሆኑም እውነት ነው። በቋንቋቸው የመንግስት አገልግሎት የማግኘት፣ የመማር፣ እውነተኛ ታሪካቸውን የማውጣትና የመንከባከብ፣ ባህላቸውን የማበልጸግ፣ በሚኖሩበት ወሰን ውስጥ በመረጧቸው ተወካዮቻቸው አማካይነት የመተዳደር መብታቸው በህግ እውቅና አልተሰጠውም ነበር። ይህን እውነት የብሄሮች፣ ብሄረሰቦች መብቶች በህግ  ሊረጋገጡ አይገባም ብለው የሚያምኑትም ቢሆኑ ይቀበሉታል።

ህጋዊ እውቅና በነፈጋቸው የመንግስት ስርአት ስር የወደቁት የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ይህ ሁኔታ አልተመቻቸውም። የመንግስት የአስተዳደር መዋቅር (የሃገር ግዛት፣ ፍርድ ቤት፣ ግብር ሰብሳቢ ተቋም ወዘተ) እና ትምህርትን የመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት እሰከታች ተዘርግተው አጠገባቸው እስኪደርሱ የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በራሳቸው ነባር ስርአት ነበር የሚተዳደሩት። ለስርአቱ ባዕድ መሆናቸው የተሰማቸው እነዚህ ተቋማት አጠገባቸው ሲደረሱ ነው። ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት፣ ሃገር አስተዳደር ወዘተ በቋንቋቸው አያስተናግዷቸውም። አቤቱታቸውን በማያውቁት የስርዓቱ ኦፊሴላዊ ቋንቋ እንዲያቀርቡ፣ በራሳቸው ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤት ቆመው በዚሁ በማያውቁት ቋንቋ እንዲሟገቱ ይገደዱ ነበር። ትምህርት ቤቶች ህጻናት ልጆቻቸውን ፈጽሞ በማያውቁት ቋንቋ ነበር የሚያስተምሯቸው። ሌሎችም ማስታወስ የማያስፈልጉ የመገፋት ስሜት እንዲያድርባቸው የሚያደርጉ ርምጃዎች ይወሰዱ ነበር። እነዚህ ሁኔታዎች ናቸው ለስርአቱ ባዕድ መሆናቸው እንዲሰማቸው ያደረጓቸው።

የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ይህ ሁኔታ አልተመቻቸውም። አንዳንድ ወገኖች ይህን የማይመች ሁኔታ፣ አንድ ብሄራዊ ማንነት ያላት ሃገር ለመፍጠር እንደሚከፈል ተገቢ መስዋዕትነት ሊወስዱት ቢችሉም፣ ለብሄሮቹና ብሄረሰቦቹ ጎርባጭ መሆኑ ግን እውነት ነው። ይህ የማይመች ጎርባጭ ሁኔታ ጭቆና ነው፤ በተገኘ መንገድ ከላያቸው ላይ እንዲወገድ የሚፈልጉት አስከፊ ጭቆና።

የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በመጀመሪያ ይህ ጭቆና በምን አኳኋን እንደተጫነባቸው አያውቁም ነበር። እናም ጭቆናውን ለማስወገድ ወይም ለማቃለል የሚወስዱት እርምጃ የቁጣ ስሜት የሚቀሰቅሱ አጋጣሚዎችን መነሻ ያደረገና ግብታዊ ነበር። እያደረ ግን የየብሄሩ ልሂቃን የጭቆናውን ምንጭና እንዴት መወገድ እንዳለበት በመርህ ተንትነው ማስቀመጥ ጀመሩ። መርህ ላይ የተመሰረተ የብሄራዊ ነጻነትና የእኩልነት ትግል በዚህ ሁኔታ ነበር የተጀመረው።

ይህ የብሄራዊ ነጻነትና የእኩልነት ትግል አንድ ቦታ አልነበረም የተጠነሰሰው። በኦሮሞ፣ የኢትዮጵያ ሱማሌ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ ትግራይ ወዘተ ብሄረሰቦች ዘንድ  ነበር። ትግሉ መስመር ከያዘ በኋላ የተደጋገፉ የብሄራዊ ነጻነት እንቅስቃሴዎች የነበሩ ቢሆንም፣ የነጻነት ጥያቄውን የጠነሰሱት ግን በየራሳቸው ነበር። ኦነግና ሌሎች የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄዎች የተፈጠሩት ትግራይ ውስጥ፣ ሲዳማ፣ አፋር ወዘተ ከተነሱ የነጻነት ንቅናቄ ቡድኖች ጋር ተማክረው አልነበረም። በኋላ ግን የዓላማ አንድነት አስተሳስሯቸዋል። ስለዚህ ለብሄራዊ የነጻነት ጥያቄ መፈጠርና አሁን ለደረሰበት ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ያስቻለ ፌደራላዊ ስርአት መፈጠር አንድ ብሄር ወይም የብሄራዊ ነጻነት ንቅናቄ እውቅና ሊሰጠው፣ ፌደራላዊ ስርአቱን በሚቃወሙ ደግሞ በተጠያቂነት ሊወቀስ አይገባም። እርግጥ የቀደመውን አሃዳዊ ስርአት ለማስወገድ በተካሄደው ትግል ውስጥ እንቅስቃሴው እንደተካሄደበት ስፍራ፣ ሌሎች ታሪካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች የአንዱ ድርሻ ከሌላው ጎላ ብሎ የታየ መሆኑ ባይካድም የስርአቱ መውደቅ ውስጥ የሁሉም ድርሻ አለበት።

የአሃዳዊ ስርአት አመለካካት አራማጆችና ደጋፊዎች ይህን የብሄሮችና የብሄረሰቦች የነጻነትና የእኩልነት ጥያቄ እንደሃገር መበታተን እንቅስቃሴ ነው የሚመለከቱት። ያም ሆነ ይህ፤ የብሄራዊ ነጻነትና የእኩልነት ጥያቄ አንስተው ሲታገሉ የነበሩ ንቅናቄዎች አሃዳዊ ስርአቱን አስወግደውታል። የመጨረሻው አሃዳዊ ሥርዓት እንደተወገደ እነዚህ የብሄራዊ ነጻነትና እኩልነት ጥያቄ አንግበው ሲታገሉ የነበሩ ቡድኖች፣ የአሃዳዊ ስርአት አመለካካት ደጋፊ ቡድኖችንና ግለሰቦችንም ያሳተፈ የሃገሪቱን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስን ጉባኤ አካሄዱ፤ በአዲስ አበባ። በጽሁፉ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው የሽግግር መንግስት በእነዚህ ኃይሎች የተመሰረተ ነበር።

ከዚህ በኋላ ምን መሆን ነበረበት? ወደአሃዳዊ ስርአት መመለሻው ድልድይ ለነጻነትና እኩልነት በተካሄደው ትግል መልሶ ላይዘረጋ ፈራርሶ ነበር። በወቅቱ ሁለት አማራጮች ብቻ ነበር የቀሩት።  አንደኛው አማራጭ ብሄራዊ መብትና ነጻነቶቻቸው ተረጋግጠውላቸው ከሌሎች ጋር በእኩልነትና በመከባበር ላይ በተመሰረተ አንድነት የሚኖሩበትን ስርአት መመስረት ነበር። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ብሄራዊ መብቶቻቸውንና ነጻነታቸውን አረጋግጠው የሚኖሩበትን ወይም እንኖርበታለን ብለው የሚያምኑበትን ነጻ መንግስት መስርተው መለያየት ነበር።

የቀደመውን የተዛባ ግንኙነት በማደስ የሃገሪቱን አንድነት አስጠብቆ መዝለቅ የሚያስችለው ብሄሮችና ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ በመከባበርና በእኩልነት መኖር የሚችሉበትን ሥርዓት መመስረት ብቻ ነበር። በሃይል ወደቀደመው አሃዳዊ ስርአት ለመመለስ ቢሞከር፣ ለነጻነት የሚደረገው ትግል መቀጠሉን ማስቀረት አይቻልም። እናም ዞሮ እዛው ላይ ነው የሚመለሰው። በመሆኑም የመጀመሪያው አማራጭ – ብሄራዊ መብትና ነጻነቶቻቸው ተረጋግጠውላቸው በእኩልነትና በመከባበር ላይ በተመሰረተ አንድነት የሚኖሩበትን ስርአት መመስረት ተመርጧል። አሁን ያለው ፌደራላዊ ሥርዓት የዚህ ውጤት ነው።

አሁን ያለው ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳደሩበት ፌደራላዊ ስርአት ግብ በተጨባጭም እንደሆነው የሃገሪቱን አንድነት አስጠብቆ ማስቀጠል ነው። ፌደራላዊ ስርአቱ የአሃዳዊ ስርአት አራማጆች እንደሚሉት፣ የሃገሪቱን አንድነት ለአደጋ ያጋለጠ ሳይሆን የመበታተንን አደጋ ያስቀረ ነው። ባለፉት ሁለት ተኩል አስርት ዓመታት ከዚያ ቀደም ከነበረው አንድ አሥርት ዓመታት ጋር ሲነጻጻር ለብሄራዊ ነጻነት ወይም ለመገንጠል የሚካሄድ እንቅስቃሴ የለም ማለት ይቻላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቀደም ሲል የመገንጠል ዝንባሌ እንደነበራቸው ሲገልጹ የነበሩ ቡድኖችም ቢሆኑ ጥያቄያቸውን ወደ ህገመንግስት መከበርና የዴሞክራሲ መጎለበት ቀይረውታል። አሃዳዊ ስርአቱን በሃይል ለማቆየት ተሞክሮ ቢሆን ኖሮ ግን ምናልባት ኢትዮጵያ የምትባለውን ሃገር አሁን ባላት ቅርጽና የብሄር ብዝሃነት ላናገኛት እንችል ነበር። እናም የሚያዘልቀን የትኛው መንገድ ይሆን? ኢትዮጵያዊ አንድነት የሚባለለት አሃዳዊ ሥርዓት ወይንስ ብዝሃነትን የሚያስተናግደው ፌዴራዊ ሥርዓት።