Artcles

የማይጠቅመው መንገድ

By Admin

May 15, 2018

የማይጠቅመው መንገድ

                                                         ሶሪ ገመዳ

በአሁኑ ጊዜ የአገራችን አጠቃላይ ሁኔታ ሰላማዊና የተረጋጋ ነው። ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች የታዩ የተቃውሞና የሰላም መደፍረስ ችግሮች ነበሩ። የችግሮቹ መነሻ ምንም ይሁን ምን ችግሮቹ አንድን አካባቢና ህዝብ የሚገልጹ ብቻ ናቸው።

ችግሮቹ የአካባቢውን ሰላም በማደፍረስ መፈፀም እንደሌለባቸውና ምላሽ ለማግኘት የሚሞከርባቸው አካሄዶችም ጫናን በመፍጠር ወይም ኃይልን በመጠቀም ሊሆን አይገባም። በሰለጠነ መንገድ ጥያቄን ማቅረብ ያስፈልጋል።

ሕብረተሰቡ ጥያቄ ባቀረበ ቁጥር ሰላምን ወደ ማደፍረስ የሚወስድ መንገድ ሊከተል አይገባም። እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ጠያቂውን ሕብረተሰብ ጨምሮ ማንንም የማይጠቅም ነው።

አገራችን ውስጥ ዛሬ ማንኛውም ሰው ያሻውን ጥያቄ ማቅረብ ይችላል። ከልካይ የለውም። ሆኖም እየኖርንበት ያለው አገር ህግና ስርዓት ያለው እንደመሆኑ መጠን፤ ጥያቄዎች ሲቀርቡ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ መሆን ይገባቸዋል።

የሁከት መንገድ ራስን፣ አካባቢን፣ የስራ ቦታንና አገርን ከመጉዳት ውጭ አንዳች ዓይነት ፋይዳ አይኖረውም። በሰላም እንጂ በሁከት ሰላማዊ ጥያቄዎቹን መመለድስ የቻለ፣ የበለፀገና ተጠቃሚ መሆን የቻለ አገር የለም።

የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላምን ጥቅም የሚገነዘብ ነው። የሁከትን ጥፋት ደግሞ ከቅርብ ጊዜው የሰላም እጦት መረዳት የቻለ ነው። በመሆኑም የሰላሙ ጠባቂ ህብረተሰቡ ራሱ መሆኑን በመገንዘብ ጥያቄዎቹን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ያስፈልጋል።

በዴሞክራሲያዊ አገር ውስጥ አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር የፀጥታ ሃይል ብቻ በማሰማራት ለውጥ ማምጣት አይቻልም። የየቀየው ባለቤት ህዝቡ ነው። በፀጥታ ሃይል የሚሰጥ ምላሽ መሰረቱ ምናልባት ነገሮችን ለማረጋጋት ይጠቅም ይሆናል። ይሁን እንጂ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም። እናም የየመንደሩ ጠባቂና የሰላም ዘብ ህብረተሰቡ እንደመሆኑ መጠን ለሰላሙ መትጋት ይኖርበታል።

ህብረተሰቡ ከ27 ዓመታት በላይ በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም ውስጥ ያገኘውን የልማትና የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን ጠንቅቆ ያውቃልና። ስለሆነም ስለ ሰላም ሲነሳ የመጀመሪያውና ቀዳሚው እማኝ ሊሆን የሚችለው የአገራችን ህዝብ ነው።

በአሁኑ ሰዓት ሕዝቡን ከዳር እስከ ዳር የሚያንቀሳቅስ ልማታዊ መንግስት ካለና በዚሁ መሪ አካል አስተባባሪነት ብሎም በህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ የሚዘወር ሰላም እስካለ ድረስ፤ ሰርቶ መለወጥና መደግ እንደሚቻል ሩብ ክፍለ ዘመንን እልፍ ባለ ዓመት ጊዜ ውስጥ ትምህርት እንደወሰደ ራሱ እማኝ ነው።

በአሁኑ ሰዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተፈጠረውን ሁከት በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። ይህ የሆነው ህዝቡ የየቀየው ሰላም ባለቤት ሆኖ ስለተንቀሳቀሰ ነው። ህዝቡ የሰላሙ ባለቤት እስከሆነ ድረስ የሚፈጠር የሰላም እጦት አይኖርም። የሚነሱ ጥያቄዎችንም አግባብ ባላቸውና በሰላማዊ መንገዶች ማቅረብ ይቻላል።

የሰላም አስተማማኝነት እንደ እኛ ላለ አገር የህልውና ጉዳይ ነው። ህዝቡ ጥያቄዎቹን ሰላማዊና ህጋዊ ማድረግ ይኖርበታል። በህገ መንግስታችን ላይ ማንኛውም ሰው የመሰለውን ዓይነት ዓላማ ማራመድ እንደሚችል ተደንግጓል። በዚህ ድንጋጌ መሰረትም ጥያቄዎችን በህጋዊ መንገድ ማቅረብ ያስፈልጋል። ጥያቄው ህዝባዊ በመሆኑም የየትኛውም ሁከት አራማጅ ሃይል እጅ መኖር የለበትም።

የአገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ብቻ አይደለም። ዋነኛው ተዋናይ ህዝቡ ነው። ሕዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ሃይል አቅም አይኖረውም። የሰላምን ምንነት የሚገነዘብ ህዝብ ውስጥ ፀረ ሰላምነትን ማንገስ ከባድ መሆኑ አያጠያይቅም።

ስለሆነም ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሃብት ለማውደም አይበቃም። ማናቸውንም ጥያቄዎቹን በሃይልና ኢ ህጋዊ በሆነ መንገድ አያቀርብም።

ለፀረ ሰላም ሃይሎች ፕሮፖጋንዳ የማይፈታ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የዜጎች ንብረት በምንም ዓይነት መንገድ እንዲወድም አይሻም። በተለይ ወጣቶች ከእነዚህ ሃይሎች የተንሸዋረረና ሰላምን ከሚያሳጡ አስተሳሰቦች ራሳቸውን መቆጠብ ይኖርባቸዋል ብዬ አስባለሁ።

ወጣቶች እንደ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆን ይፈልጋሉ። ተጠቃሚነታቸውን ግን ማሳካት ያለባቸው በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። አገራችን ውስጥ ከተገኙት የልማት ውጤቶች አቅም በፈቀደ መጠን ተጠቃሚ መሆንም አለባቸው። መንግሥትም ይህን ለማሳካት በትጋት በመስራት ላይ ይገኛል።

የወጣቶች ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ የሚችለው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንጂ ከሁከትና ከብጥብጥ አይደለም። እንዲህ ዓይነቱ ተግባር የጥያቄው ባለቤት ለሆነው ሕብረተሰብም ትክክለኛ አቅጣጫ ሊሆን አይችልም።

መንግሥት በአሁኑ ሰዓት በሁሉም መስኮች የሕብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ነው። ጊዜ ያስፈልገዋል። ሁሉም ችግሮች በአንድ ጀነበር የሚፈቱ ላይሆኑ ይችላሉ።

ጥያቄን ካቀረቡ በኋላ ችግሮቹ እስኪፈቱ ድረስ መታገስ የግድ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ቀና መንገድ ለጥያቄ አቅራቢው ሕብረተሰብ የማታ ማታ ውጤት የሚያስገኝለት ነው። ሰላማዊ ጥያቄ ሁሌም ትርፋማና የሕብረተሰብን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው።

አገራችን ውስጥ የሚፈጠሩ ማናቸውም ችግሮች ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በህዝብ የተዋቀረው፣ በህዝብ ያደገውና የጎለበተው እንዲሁም በህዝብ እየተገመገመ ከስህተቶቹ እየተማረ በመጣው ብሎም ተግባሮቹን ሁሉ ከህዝብ ተጠቃሚነት አኳያ በሚያከናውነው በኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ነው።

በዚህ መሰረትም የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት የመሳሰሉ ችግሮች እንዲሁም ሰሞኑን መነጋገሪያ የሆነው የቀን ገቢ ግምት ትመና ቅሬታዎች ካሉ መፍትሔ የሚያገኙት መንግስትና ህዝቡ በጋራ በሚያደርጉት ውይይትና መግባባት እንጂ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎችን የሁከት አጀንዳ በሚያራግቡ ፅንፈኞች አለመሆኑን ህብረተሰቡ መገንዘብ ይኖርበታል። ጥያቄዎች ካሉትም የሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ህጋዊና ሰላማዊ መንገዶችን ተከትሎ መሆኑን ደግሞ ደጋግሞ ማረጋገጥ ይኖርበታል።