የስኬቶቹ ማሳያዎች
ዘአማን በላይ
ከመሰንበቻው በሀገራችን የጀርመንና የእስራኤል መሪዎችን እንዲሁም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ተከታታይ ጉብኝቶችን አድርገዋል። የዓለም ታላላቅ ሀገራት ጉብኝቶች እየተካሄደ ያለው በጊዜያዊ ቀውሶች ውስጥ ሆነን ነው—አንፃራዊ ሰላማችን እንደተጠበቀ ሆኖ። ይህም የሀገራችን ተፈላጊነትና ተሰሚነት እየጨመረ መምጣቱን የሚያሳይ ነው።
ርግጥ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እየሰፋ ሄዷል። ይህም ለተደማጭነታችን መጨመርና ለገፅታችን መቀየር ዋነኛው መሰረት ሆኗል። ለዚህ የገፅታችን መድመቅ በሀገራችን ውስጥ በየዘርፉ እየተረጋገጡ ያሉት ስኬቶች የአንበሳውን ድርሻ ይዟል። በሀገራችን ውስጥ እውን እየሆኑ ያሉት ስኬቶች ማሳያዎቻቸው በቅርቡ የተካሄዱት ጉብኝቶች ዓይነት የውጭ ግንኙነት እመርታዎቻችን ናቸው።
እዚህ ላይ ስኬቶቻችንን መለስ ብሎ መቃኘት ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ውስጥ ካጋጠሙን ጊዜያዊ ችግሮች በስተቀር፤ በኢትዮጵያ ዛሬ ሰላም ተረጋግጧል። ፍትህ ሰፍኗል፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም ተገንብቷል።
ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ውስጥ ካጋጠሙን ጊዜያዊ ችግሮች በስተቀር፤ በኢትዮጵያ ዛሬ ሰላም ተረጋግጧል። ፍትህ ሰፍኗል፤ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም ተገንብቷል።
ሀገራችን ላለፉት 27 ዓመታት በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገቧ አያከራክርም። የምትመራበት የፖለቲካ መስመርም ትክክለኛነት አጠያያቂ አይደለም። በህገ መንግሥቱ ውስጥ የሰፈሩት ህገ መንግሥታዊ የዴሞክራሲና የልማት ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ በቅድሚያ ህገ መንግሥቱ በሰፊው የሕዝብ ተሳትፎ የተዘጋጀ ነው፤ በህገ መንግሥቱ ውስጥ የሰፈሩት ድንጋጌዎችም አገራዊ መግባባት እንዲመጣ ጉልህ ሚና የነበራቸው ናቸው።
በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሥር እየሰደደ እንዲሄድ ብሎም አገሪቱ ፈጣን ወደሆነ የልማት ጐዳና እንድትገባ ለዴሞክራሲና ልማት ድንጋጌዎች ተግባራዊነት ቁርጠኛ መንግሥት መኖር ውጤቱን አፋጥኖታል። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዓላማዎችን ማራመድ እንዳለባት በግልጽ ይደነግጋል።
ይህን ዓላማ ለማረጋገጥ መንግሥት ዜጎች በአገሪቱ የሚገኘውን ሀብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሠራር ቀይሶ ተፈጻሚ እያደረገ ይገኛል። በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎች በመንግስት ልዩ እገዛ ተደርጐላቸው ጭምር የልማቱ ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ መጥቷል። ህገ መንግሥቱም በግልፅ ለነዚህ መብቶች ዋስትና ሰጥቷል። መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብቶችን በህዝብ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለዜጎች የጋራ ጥቅምና ዕድገት የማዋል ኃላፊነቱን ባለፉት ዓመታት በብቃት ተወጥቷል። ሁሉም ዜጐች ለልማት መሰረት የሆኑ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች፣ የምግብ ዋስትና፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የመኖሪያና የማህበራዊ ዋስትና መብት እንዲኖራቸው ተደርጓል።
ዛሬ በኢትዮጵያ ሁሉም ዜጋ በማንኛውም የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመከወን መብት አለው። ሁሉም ዜጋ በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ ማህበራዊ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብቱ ተረጋግጦለታል። በተግባርም ተጠቃሚ ሆኗል። መላ ኢትዮጵያዊያን በሁሉም ዘርፎች በርካታ ድሎችን ጨብጠዋል። የድል ፍሬዎቹንም እያጣጣሙ ነው። ሕይወታቸውም ተለውጧል። ከዚህ የተቀደሰ ማዕድ ላይ የሚያፈናቅላቸውን በዋዛ ሊመለከቱት የሚችሉ አይመስለኝም።
የሀገራችን ህዝቦች የኑሮ ሁኔታቸው የመሻሻልና የማያቋርጥ ዕድገት የማግኘት መብታቸውን በተግባር እየተጠቀሙበት ነው። በብሔራዊ ልማት የመሳተፍ፣ በሚቀረፁ ፖሊሲዎችና ኘሮጀክቶች ላይ አስተያየት የመስጠት መብቶችን ዜጎች እያጣጣሟቸው ነው። ምንም እንኳን መንግስትና ህዝቡ ቀሪ የቤት ስራዎች ቢኖሩባቸውም፤ ዜጐች በመንግሥት ገንዘብ በሚካሄዱ አገልግሎቶች በእኩልነት የመጠቀም መብታቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙበት ነው።
በተለይ ባለፉት ስርዓቶች ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ፍትህ ሳያገኙ የቆዩና በዚህም ምክንያት በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመንግሥት ልዩ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። በዚህም መሠረት የፌዴራል መንግሥት ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ በተጨማሪ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ይገኛል። ይህ ድጋፍ በዋናነት የሚያተኩረው በማስፈፀም አቅም ግንባታ ላይ ነው። የመንግሥት አስተዳደርን የመገንባት፣ ቀልጣፋ አሠራርንና አደረጃጀት የመፍጠርና የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትን ከፍ በማድረግ ረገድ መንግስት ሚናውን ተጫውቷል— ከየክልሉ መንግስታት ጋር በመሆን።
በሀገራችን ውስጥ የታዩት ስኬቶች ጠቅለል ተደርገው ሲታዩ በነጻ ፍላጐት፣ በህግ የበላይነት፣ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅምና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ የመገንባት ወሳኝነትን የሚያመለክቱ ሆነው እናገኛቸዋለን። እንዲሁም ዜጐች ንብረት የማፍራት፣ በመረጡት የሥራ መስክ የመሰማራት መብቶች በማረጋገጥ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት የሚመራ ፈጣንና ፍትሀዊ ልማት የማምጣት ተጠቃሚነታቸውን የሚያመላክቱ ናቸው። እነዚህ ሃቆች የህዝቦችን ልማታዊ አቅም ማሳደግና ለአገር ግንባታ ወሳኝ ጉዳዩች መሆናቸውን በገሃድ የሚያሳዩ ናቸው።
የክልሎችን እኩል የመልማት ዕድል ማረጋገጥና ልዩ ድጋፍ መስጠት መገንባት ለሚፈለገው በነፃ ፍላጐት ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።
መንግስት ይህን ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብቶ፤ በራስ አቅምና ፍላጐት ነፃ ሀገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ወሳኝ እንዲሆኑ በርካታ ስራዎችን ከውኗል። የልማት አጀንዳ ለሀገራችን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው። ይህን ድንጋጌ መሰረት በማድረግ የኢፌዴሪ መንግስት በተለይ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን ማረጋገጥ የሞት ሽረት ጉዳይ እንደሆነ ተገንዝቧል።
የሀገራችን ኢኮኖሚ በነፃ የገበያ ሥርዓት እንዲመራ ማድረግ ብሎም የተፋጠነ ዕድገትን በማረጋገጥ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ፈታኝ የድህነትና ኋላ ቀርነት ችግር ማላቀቅን ዓላማ በማድረግ ህዝቡን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህም የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የሥራ ሥምሪት ፖሊሲዎች ተነድፈው ተግባር ላይ ውለዋል። በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ዓይነተኛ ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት በመሆኑ ይህን ማድረግ ችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ የመሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሃብት ልማት በማካሄድ ብሎም ፈጣንና ውጤታሚ የመንግሥት አገልግሎቶችን በመስጠት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና መደገፍ ችሏል—በአፈፃፀም ሂደቱ የነበሩት ህዝብን የሚያማርሩ ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው። መንግስት በተቻለ መጠን የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን ለመዝጋትና በግሉ ሴክተር የማይሰሩ የልማት ተግባራትን አከናውኗል። ይህም የስራ ዕድልን መፍጠርና ህዝቡንም በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
ለውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎችን በመፈጠሩ የንግድና ኢንቨስትመንት ፖሊሲ ሥር ነቀል በሆነ መልኩ ተለውጦ ውጤት እየተገኘበት ነው። በየጊዜውም የተለያዩ ርምጃዎችን በመውሰድ በተለይ ሀገራችን ኢንቨስትመንት የስበት ማዕከል እንድትሆን ለማድረግ ተሰርቷል፤ አጥጋቢ ውጤትም ተገኝቶበታል።
ከላይ የጠቀስኳቸው ሀገራዊ ስኬቶች በያዝነው የፈረንጆች ዓመት (በ2018) ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ቀዳሚነት ስፍራ ጠንካራ መሰረት ካላት ጋና እንደምትረከብ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ላወጡት ሪፖርቶች ትክክለኛ ማሳያዎች ናቸው። እነዚህ በሀገር ውስጥ የተከናወኑት ተግባራት ዓለም አቀፍ ተደማጭነታችንንና ከፍ ያደረጉ ከመሆናቸውም በላይ፤ ታላላቅ ሀገራት ሀገራችንን በመጎብኘት ዲፕሎማሲያቸውን ከኢትዮጵያ ጋር እንዲያጠናክሩ ሁነኛ ምክንያት የሆኑ ይመስለኛል።