Artcles

የሽግግሩ ደጋፊ

By Admin

May 15, 2018

የሽግግሩ ደጋፊ

ይሁን ታፈረ

የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ በቅርቡ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የቻይና የንግድ ኤግዝቢሽን ሳምንት ላይ 50 የሚሆኑ የቻይና ኩባንያዎች የንግድ ውጤታቸውን ማቅረባቸውን ዘግቧል። ዘገባው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ዘርፍንም አሳይቷል። እርግጥ የአገራችን የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ እድገትን እያስመዘገበ ነው።

 

ዘርፉ አገራችን ኢኮኖሚን ሽግግር በመደገፍ ረገድ ትልቅ አቅም ሆኗል። ይህም ኢትዮጵያ እንደ አገር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው መዋቅራዊ ለውጥ የበኩሉን ድርሻ በማበርከት ላይ ይገኛል። በተለይም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ከዘርፉ አኳያ መምጣት ይኖርበታል ተብሎ የተቀመጠውን ኮታ ለመሙላት በትጋት እየተሰራ ነው።

 

እንደሚታወቀው ሁሉ መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን በወጭ ንግዱ ለማጠናከር ባከናወነው ተግባር ከምንጊዜውም በላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ተመልክተናል። ለአብነት ያህል የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ለውጦች ታይተውባቸዋል።

እርግጥ ለዘላቂና ፈጣን ዕድገቱ ምቹ የሆነ የማክሮ ምጣኔ ሃብት ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ በኢንቨስትመንትና በቁጠባ መካከል ያለው ሚዛን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን የፈጣን ዕድገቱ አንዱ ምንጭ ኢንቨስትመንት እንዲሆን ተተልሟል፡፡

በተለይም በማኑፋክቸሪንግና በግብርና፣ በመሠረተ-ልማት፣ በማህበራዊ ልማት ዘርፎችና በሌሎች መስኮች የሚከናወኑ የግልና የመንግስት ኢንቨስትመንቶች ፈጣን ዕድገትን በማረጋገጥ በኩል የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ።

በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ላይ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን ተገልጿል። እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የዘርፉ ምርቶች ጠቅላላ የኤክስፖርት ገቢ ያላቸው ድርሻ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ውስጥ ከ1ዐ በመቶ የማይበልጥ ነው።

ይሁን እንጂ በዕቅዱ መሰረት በ2012 ላይ ወደ አምስት ቢልዮን ዶላር ገቢ እንዲያስገኝ ለማድረግ ታስቧል። ይህ ድርሻም ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግና በ2017 ዓ.ም 40 በመቶ ለማድረስ ግዙፍ ዕቅድ ተቀምጧል።

ሌላው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጡ ሽግግር አመላካች የሚሆነው በሚቀጥሉት ዓመታት ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚደረገው የሰው ሃይል ሽግሽግ ነው። ይህም በአሁኑ ወቅት በመካከለኛና በከፍተኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የተሰማራውና ሶስት መቶ ሃምሳ ሺህ የማይበልጠውን የሰው ሃይል በቀጣዩቹ አስር ዓመታት በአራት እጥፍ እንዲጨምር ለማድረግ ታስቧል።

ይህም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዩን ዜጎች የስራ ዕድል እንዲያገኙ እድል የሚፈጥር ነው። እነዚህን የማምረቻ ኢንዱስትሪውን ልማታዊ ፋይዳዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ብርቱ ርብርብ እያደረገ ነው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው።

ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

በአገራችን የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል።

እርግጥ ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ስራዎችን በሂደት በሀገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወኑ መሰረት ይጥላል። በመሆኑም ፓርኩ በውስጡ የተገነቡት ኢንዱስትሪዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በጤናማ ሁኔታ የእርስ በእርስ ውድድር የሚያደርጉበት አካባቢ ነው ማለት ይቻላል።

ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ስራው ተጠናቆ በአገልግሎት ላይ ለመዋል የተዘጋጀውና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ያሳድዋል ተብሎ የሚጠበቁት የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ከሌሎች ጋር በተመጋጋቢነት ጤናማ ውድድርን በማካሄድ ውጤታማ እየሆኑ ነው።

በዚህ ጤናማ ውድድራቸውም የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት ያሳድጋሉ። በዚህም ህበረተሰቡም ይሁን የቀጠናው ህዝቦች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህ ተጠቃሚነታቸውም ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የምስራቅ አፍሪካ ብሎም የአፍሪካ ተጠቃሽ አገር እንድትሆን ያስችላታል።

በመሆኑም መንግስት በአሁኑ ሰዓት በመላ አገሪቱ በራሱ ወጪ እየገነባቸው የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የአፍሪካ ማዕከል እንድትሆን የነደፈውን ዕቅድ ለመሳካት ጥረት እያደረገ ነው። ይሀም የወጭ ንግድን ከፍ በማድረግና ዜጎችን የስራ ዕድል ባለቤትነት ያረጋግጣል።

እርግጥ ሀገራችን የውጭ ባለሃብቶች ኤክስፖርት ተኮር በሆኑ ዘርፎች ውስጥ እንዲካተቱ ስታደርግ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ምንም ዓይነት ቦታ ሳትሰጥ ነው ማለት አይደለም። የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም መዋዕለ ንዋያቸውን በዘርፉ እያፈሰሱ ነው።

በተለይም በማደግ ላይ የሚገኙት የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ተመልምለው በቂ ድጋፍ እንደሚሰጣቸውና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ገቢ ምርቶችን በሚተኩ ዘርፎች ጭምር በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

እርግጥ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንጂ ለብቻው ተፈፃሚ እንዲሆን ብቻ አይደለም። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መቆራኘት ይኖርበታል። ይህን ታሳቢ በማድረግ እየተፋጠነ የሚገኙት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ተግባሮች መዋቅራዊ ሽግግሩን ደግፎ እውን ለማድረግ ትልቅ አቅም ይሆናል። የቻይና ኩባንያዎቹ የንግድ ኤግዚቪሽን መሰረታዊ እውነታ መታየት ያለበት ከዚህ አኳያ ነው።