Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የብተናን መንገድ የዘጋ…

0 275

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የብተናን መንገድ የዘጋ…

                                 ዳዊት ምትኩ

የግንቦት 20ን የድል በዓል ለማክበር እየተዘጋጀን ነው። በዝግጅቱ የድሉን ውጤታማ ተግዳሮቶችን ብቻ ሳይሆን እየተፈታተኑን ያሉትን ተግዳሮቶችንም እናስታውሳለን። ይሁን እንጂ ተግዳሮቶቹ በመንግስት የመሪነት ሚና እና በህዝባችን የባለቤትነት መንፈስ ተባብረን የምናስወግዳቸው መሆናቸውን ግንዛቤ መያዝ ይገባል።

መንግስት በሪፎርም ውስጥ ገብቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ እያከናወናቸው ያሉት እጅግ አኩሪ ተግባራት ህያው ምስክር ናቸው። ባለፉት ዓመታት የተከናወኑት ተግባሮች የፌዴራል ሥርዓቱ ኢትዮጵያን ከብተና የሚያድንና አንድነታችንን በፅኑ መሰረት ላይ በማኖር መሰረት ጥሏል፤ የተወሰኑ ችግሮች ቢስተዋሉም።

እርግጥ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ለአገራችን የሚጠቅመው ከሃይል አንድነት ይልቅ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መሆኑን ተገንዝበናል። እንደ አገር የግል መብቶችን ብቻ ከማክበር ይልቅ የግለሰብና ቡድን መብቶችን በጋራ መከበራቸው አስፈላጊ መሆናቸውንም ተገቢነታቸው አያጠያይቅም። ታዲያ እነዚህ መብቶችና ህዝባዊ ተጠቃሚነቶች የተገኙት በግንቦት 20 ድል ነው።

ሥርዓቱ የአንድነት መንገድ ነው። ዛሬም እየተፈቱ የሚገኙና ሊፈቱ የሚገባቸው ተግዳሮቶች ሀገራችን ውስጥ ቢኖሩም ቅሉ፤ እነዚህን ተግዳሮቶች ፌዴራላዊ ስርዓቱ ያልፈጠራቸው በመሆናቸው ልክ እንደ ያኔው ከህዝቡ ጋር ሆኖ እየፈታቸው ነው። ያልተፈቱ ጉዳዩች ካሉም አሁንም ከህዝቡ ጋር በመሆን እንደሚፈታቸው በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ምክንያቱም ሀገራችን እየተከተለችው ያለችው ፌዴራላዊ ስርዓት ማናቸውንም ጉዳዩች ከህዝቡ ጋር መክሮና ዘክሮ የመፍታት የካበተ ባህልን ያዳበረ በመሆኑ ነው።

እንደሚታወቀው ወታደራዊው የደርግ ስርዓት በወደቀ ማግሥት ሟርተኞች ስለኢትዮጵያ መጻዒ ሁኔታ ሲተነብዩ ያላሉት ነገር አልነበረም። ‘ኢትዮጵያ የሶማሊያና የዩጎዝላቪያ ዕጣ ፋንታ ይገጥማታል፤ መበታተኗም አይቀሬ ይሆናል’ ሲሉም ተንብየዋል። እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ነው የሆነው። በወቅቱ ኢሕአዴግና የሽግግር መንግስቱ በያዙት የተጠና መስመር አገሪቱን ከብተና ታድገዋታል። ይህ ተግባራቸውም ዛሬ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የልማት ለውጥ አብነት እንድትሆን መሠረት ጥለውላታል። ትናንት ከህዝብ ጋር ሆነው በቀየሱት መንገድ ተመርተው ዛሬ ለሁለንተናዊ ለውጥ እንዳበቁን ሁሉ፤ ነገም በአሁኑ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉት ተግዳሮቶች ነገ ደግሞ እነዚህ ተግዳሮቶች ተፈትተው ለህዳሴያችን አበቁን ማለታችነ የሚቀር አይመስለኝም።

ላለፉት 27 ዓመታት በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ከፍተኛ እመርታ ማስመዝገቧ አያከራክርም። ለዚህም የምትመራበት የፖለቲካ መስመር ትክክለኛነት ተጠቃሽ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም! በህገ መንግስቱ ውስጥ የሰፈሩት የዴሞክራሲና የልማት ድንጋጌዎች ጭምር እንደሆነም ይታመናል። በቅድሚያ ህገ መንግሥቱ በሰፊው የሕዝብ ተሳትፎ የተዘጋጀ ነው። በህገ መንግሥቱ ውስጥ የሰፈሩት ድንጋጌዎችም በጋራ ጉዳዩች ዙሪያ መግባባት እንዲመጣ ጉልህ ሚና ነበራቸው።  

በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሥር እየሰደደ እንዲሄድ ብሎም አገሪቱ ፈጣን ወደሆነ የልማት ጐዳና እንድትገባ ለዴሞክራሲና ልማት ድንጋጌዎች ተግባራዊነት ቁርጠኛ መንግሥት መኖር ውጤቱን አፋጥኖታል። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አገሪቱ ፍትሃዊ የምጣኔ ሀብት ዓላማዎችን ማራመድ እንዳለባት በግልጽ ይደነግጋል።

ይህን ዓላማ ለማረጋገጥ መንግሥት ዜጎች በአገሪቱ የሚገኘውን ሀብት በፍትሃዊነት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አሰራር ቀይሶ ተፈጻሚ እያደረገ ይገኛል። በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ክልሎች በመንግሥት ልዩ እገዛ ተደርጐላቸው ጭምር የልማቱ ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ መጥቷል።

ህገ መንግሥቱም በግልጽ ለነዚህ መብቶች ዋስትና ሰጥቷል። መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሃብቶችን በህዝብ ስም በይዞታው ሥር በማድረግ ለዜጎች የጋራ ጥቅምና ዕድገት የማዋል ኃላፊነትን ተቀብሎ ውጤት ማምጣት ችሏል።  

በደርግ ሥርዓት ማንኛውም ዜጋ ተገፍፎ የነበረውን የግል ንብረት ባለቤት የመሆን መብት ጠብቆ ሁሉም ዜጋ የግል ንብረት ባለቤትነት መብቱ በህገ መንግሥቱ እንዲከበር አድርጓል። ከሁሉም በላይ ህገ መንግሥቱ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የማይሸጥ የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ንብረት እንደሆነ በግልፅ አስፍሯል። በመሬት ጉዳይ የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት በጽኑ መሠረት ላይ ጥሏል።

እናም የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ እንዲሆን አድርጓል። የኢትዮጵያ አርሶና አርብቶ አደሮች መሬትን በነፃ የማግኘት፣ በመሬታቸው የመጠቀምና ከመሬታቸው ያለ መፈናቀል መብታቸው ህገ መንግሥታዊ ዋስትና አግኝቷል።

የፌዴራል መንግሥት ፍትሃዊ የልማት እንቅስቃሴ ከማረጋገጥ ባሻገር፤ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ ህዝቦች መላ አቅማቸውን አሟጠው እንዲጠቀሙ ለማስቻል ልዩ ድጋፍ እየሰጣቸው ነው። እገዛው በዋናነት የሚያተኩረው በማስፈፀም አቅም ግንባታ ላይ ነው። የመንግሥት አስተዳደርን የመገንባት፣ ቀልጣፋ አሰራርንና አደረጃጀት የመፍጠር እንዲሁም የሰው ኃይል አቅም ማጎልበትን በአቅም ግንባታ ስር ተካትተው እገዛ እየተደረገ ነው።

ክልሎች ከፌዴራል መንግስቱ በሚያገኙት ድጋፍ ተመርኩዘው ክልሎቻቸውን የተረጋጉ፣ ፀጥታ የሰፈነባቸውና ለልማት ምቹ እንዲሆኑ በማድተግ ላይ ይገኛሉ—በአንዳንድ አካባቢዎች ‘ብልጭ ድርግም’ የሚል የፀጥታ መደፍረስ ጉዳይ ቢኖርም።

የሀገራችን ፌዴራላዊ ስርዓት በነፃ ፍላጐት፣ በህግ የበላይነት፣ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅምና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በጋራ መገንባትን እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው። በፌዴራላዊ ስርዓቱ ውስጥ ማንኛውም ዜጋ ንብረት የማፍራት፣ በመረጠው የስራ መስክ የመሰማራት መብቶች አሉት። እነዚህ ህገ መንግስታዊ መብቶች የህዝቦች ይሁንታ ስለሆኑ ማንም ሊሽራቸው አይችልም።

እነዚህ ጉዳዩች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ለመሻር መሞከር ሀገራችን የምትመራበትን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ስርዓት አለመቀበል አሊያም ፈጣንና ፍትሃዊ ልማት የማምጣት ርምጃን መፃረር ይመስለኛል። እንዲሁም የዜጐችን የልማት ባለቤትነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ላይ “ውሃ የመቸለስ” ያህል መስሎ ይሰማኛል። እርግጥ የዜጎችን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስንና በማንኛውም የሀገሪቱ ክልል ውስጥ ሃብት የማፍራት መብቶችን መገደብ አይቻልም።

ይሁን እንጂ በኪራይ ሰብሳቢዎችና በኮንትሮባንዲስቶች እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ትስስር ባላቸው አንዳንድ የመንግስት ስራ አስፈፃሚዎች ህገ መንግስታዊ ስርዓቱንና ህገ መንግስቱን የሚፃረሩ ተግባራት ተፈፅመዋል። ይህም የክልሎችን እኩል የመልማት ዕድል ከመጋፋት ባሻገር በነፃ ፍለጐት ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚደረገውን ርብርብ እንደሚያደናቅፍ ይታወቃል።

ክልሎች ከፌዴራል መንግስቱ ከሚያገኙት ድጋፍ ባሻገር በራስ አቅምና በራስ ፍላጐት ነፃ አገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት የመኪያደርጉትን ጥረቶች ይገድብባቸዋል። ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሚያደርጉትን ጥረትንም መና የሚያስቀርባቸው ይመስለኛል።

የልማት እንቅስቃሴ ዋና ዓላማም የዜጐችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል በመሆኑ የእነዚህ ተፈናቃይ ዜጎች ኑሮን ከማሻሻል መንግስታዊ ስራዎች ተቋዳሽ አለመሆን ክልሎች በሀገር አቀፋዊ አስተዋፅኦዋቸው ላይ ጥላ እንዲያጠላበት ያደርጋል።  

እርግጥ በአሁኑ ወቅት የልማት ስራ ለሀገራችን ምን ያህል የሞት ሽረት ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል። ሆኖም ከላይ የጠቀስኳቸው ተግዳሮቶች መጠናቸው አነስተኛ ቢሆንም በሞት ሽረት ጉዳይ ላይ ያነጣጠሩ በመሆናቸው የፌደራላዊ ስርዓቱ ተግዳሮቶች ተደርገው የሚወሰዱ ይመስለኛል።

ለነገሩ በኮንትሮባንዲስቶችና በኪራይ ሰብሳቢዎች እንዲሁም ከእነዚህ አካላት ጋር ግንኙነትን በመፍጠር የመንግስትን ስልጣን ለራሳቸው በማዋል ላይ በሚገኙ ጥቂት የፖለቲካ አመራሮች ሳቢያ ዜጎችን የማፈናቀል፣ ለዘመናት ተቻችሎ በኖረው ህዝብ ውስጥ ጥርጣሬ እንዲፈጠር በማድረግ፣ ህይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም የሚሳተፉ ሃይሎችን ከህዝቡ ጋር በመሆን የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እየተሰራ ነው። እነዚህ ሁሉ ተግባራት የተከናወኑት ፌደራላዊ ሥርዓቱ በቀየሰው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ መስመር ነው። ሥርዓቱ የብተናን መንገድ የዘጋ ነው። የተግዳሮቶች ቢኖሩም ከላይ በጠቀስኳቸው መንገዶች መንግሥትና ህዝብ የሚፈቷቸው ናቸው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy