የተግባቡ ደጅ አያድሩም
ለሚ ዋቄ
ባለፉ ሁለት ዓመታት በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተካሄደው ህዝባዊ የተቃውሞ ንቅናቄ ፍሬ አፍርቷል። ህዝባዊ ንቅናቄውን የፈጠረው ምሬት ነበር። ከፌደራል እስከቀበሌ ያሉ የመንግስት ተቋማት ዓላማ ህግ ላይ ተመስርተው ህዝብን ማገልገል መሆኑ ተዘንግቶ የተሿሚዎቹንና የአንዳንድ ባለሞያዎችን ፍላጎት ማስጠበቅ ሆኖ ነበር። ዜጎች በእነዚህ ተቋማት መብቶቻቸውን በገንዘብ እንዲገዙ የሚገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ጉቦ መስጠት በሚስጢር የሚከናወን መሆኑ ቀርቶ፣ ተመን ወጥቶለት ጉዳይ አስፈጻሚ በሚባሉ አቀባባዮች አማካኝነት በይፋ የሚከፈል ለመሆን በቅቶ ነበር። ፍርድ ቤቶች ፍትህ የሚገኝባቸው ሳይሆኑ ገንዘብ ላለው ፍርድ የሚሸጥባቸው ተቋማት ለመሆን በቅተው ነበር። ዳኞች ፍርድ ይሸጣሉ፤ ጠበቆች ፍርድ ይደልላሉ። ባለጉዳዮች የሚወክሉትን ጠበቃ ሲመርጡ፣ የሞያ ብቃቱን ሳይሆን ከዳኞች ጋር ስላለው መግባበት ነበር የሚጠይቁት። ጠበቆች ምንም ያህል የሞያ ብቃት ቢኖራቸው ለወከሏቸው ባለጉዳዮች ህግ ላይ ተመስርተው ፍትህን ማስገኘት ተስኗቸዋል። ፍትህ ገንዘብ ያለው የሚገዛው ሸቀጥ ሆኖ ነበርና።
መሬት ጥቂቶች በድንገት ወደባለጸጋነት የሚሸጋገሩበት፣ ብዙሃን ደግሞ ያላቸውንም አጥተው የድህነት አዘቅት ውስጥ የሚወድቁበት ሃብት ሆኖ ነበር። አርሶ አደሮች ለኢንቨስትመንትና ለሌሎች ማህበራዊ ልማቶች መሬታቸውን እንዲሰጡ ሲደረግ፣ ዘላቂ ህይወታቸው ከግምት አይገባም። አርሶ አደሩ እድሜ ልኩን እያረሰ ቤተሰቡን የሚቀልበበንት፣ የሚለብስበትን፣ ልጆቹን የሚያስተምርበትን . . . መሬት ከአንድና ሁለት ዓመት ቀለብ በማያልፍ ካሳ እንዲለቅ ሲደረግ ቆይቷል። በተለይ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የኦሮሚያ ከተሞች የነበረው ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነበር። አርሶ አደሮች መሬታቸውን ሰጥተው የሪል እስቴት አልሚ ባለሃብቶችን አበልጽገው፣ እነረሱ በመሬታቸው ላይ የተገነቡት ውብ የመኖሪያ ቤት ህንጻዎች ውስጥ በዘበኝነት ተቀጥረው ለመኖር የተገደዱበት ሁኔታ የነበረ መሆኑ እውነት ነው። በዚህ ሁኔታ አርሶ አደሮች ከነቤተሰባቸው ሞያቸውን በአንድ ዓመት ከአርሶ አደርነት ወደዘበኘነትና የቀን ሰራተኝነት እንዲለውጡ ተገደዋል።
ሜሬታቸው ለልማት የተወሰደ አርሶ አደሮች ለዘለቄታው መኖር የሚያስችላቸው ካሳ ከማጣታቸው በተጨማሪ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ልጆቻቸው የተፈቀደላቸውን 2 መቶ ካሬ ሜትር መሬት አብዛኞቹ ማግኘት ያልቻሉበት ሁኔታ ነበር። ይህን በህግ የተፈቀደ መብት ለማረጋገጥ ለዓመታት ማዘጋጃ ቤት ተመላልሰው ያልተሳካላቸው ብዙዎች ናቸው። አሁንም ይህን መብታቸውን ያላረጋገጡ አሉ። በሌላ በኩል ከመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር የጥቅም ግንኙነት መስርተው በርካታ ቦታዎችን እየወሰዱ በመሸጥ የከበሩ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች መኖራቸው ይታወቃል።
በገጠር ባለው የመሬት ጥበት ወደከተማ የሚፈልሱ፣ በከተሞች በተለያየ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁ ወጣቶች ቁጥርና የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የሚፈጥረው ተጨማሪ የስራ እድል ባለመመጣጠኑ ከተሞች የስራ አጥ መናኸሪያዎች ሆነዋል። የስራ አጦችን ቁጥር ለማቃለል ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የአነስተኛና ጥቃቅን የስራ ፈጠራ ፕሮግራም በሚጠበቀው ልክ ውጤታማ መሆን ሳይችል ቀርቷል።
በአጠቃላይ ከላይ ለማሳያነት ያህል የተጠቀሱ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት፣ የሃብት ምዝበራና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖር ወዘተ ህዝብ በመንግስት ላይ እንዲማረርና እምነት እንዲያጣ አድርገዋል። ህዝብ ለገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የስልጣን ውክልና የሰጠው በሃገሪቱ ባለው ፌደራላዊ ስርአት፣ የሃገሪቱን አንድነት አስጠብቆ ማስተዳደር ይችላል የሚል እምነት የሚጣልበት አማራጭ ፓርቲ በማጣቱ ብቻ ነበር። እርግጥ በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የኢኮኖሚ እድገት መመዝገቡና የእድገቱ ቀጣይነት ተስፋ የሚታይበት መሆኑ፤ በተለይ በትምህርትና በጤና ማህበራዊ ልማት፤ በመንገድ፣ በሃይል፣ በቴሌኮም የመሰረተ ልማት ዘርፍ የታየው እመርታዊ እድገት ገዢው ፓርቲ ችግሮቹን ካረመ የህዝቡን ኑሮ የመቀየር አቅም ሊኖረው ይችላል የሚል እምነት ማሳደሩም ውክልናውን እንዲያገኝ አግዞታል።
ይሁን እንጂ፣ ከሁለት ዓመታት በፊት ተከማችቶ ሊናድ ጥቂት ቀርቶት የነበረውን ችግር በድንገት እንዲናድና ህዘቡ እንዲቆጣ ያደረገ አጋጣሚ ተፈጠረ። በጽሁፉ መግቢያ ላይ የጠቀስኩት ህዝባዊ የተቃውሞ ንቅናቄ በዚህ አጋጣሚ ነበር የተለኮሰው። ሌሎች ፖለቲካዊ ሁኔታዎች፣ ለምሳሌ የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን ረቂቅ ተቃውሞውን በማቀጣጠል ረገድ አስተዋጽኦ ነበረው። ይህን ተቃውሞ ለራሳቸው የተለየ የፖለቲካ ግብ ለመጠቀም የተነሱ አካላት በማህበራዊ ሚዲያ ያካሄዱት የሁከት ቅስቀሳ አውዳሚ የሃይል ተቃውሞ እንዲባባስ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ የነበረው መሆኑ አይካድም።
በዚህ ሁኔታ ተቀስቅሶ በተለይ በመላ ኦሮሚያ እንዲሁም በአንዳንድ የሃገሪቱ ክልሎች የተወሰኑ አካባቢዎች ያለማቋረጥ የተካሄደ ህዝባዊ ተቃውሞ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ራሳቸውን በጥልቀት እንዲመረምሩ አስገድዷል። መንግስትና ገዢው ፓርቲ ራሳቸውን በጥልቀት ሲመረምሩ፣ በሽታው ስር የሰደደ መሆኑን ተገነዘቡ። እናም በጥልቀት መታደስ እንደሚያስፈልጋቸው ተረድተው የመታደስ እንቅስቃሴ አወጁ። ይህ የመታደስ እንቅስቃሴው አንዴ ከተለኮሰ በኋላ፣ በራሱ መንገድ ሄዶ በርካታ ፖለቲካዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማደረግ አሁን የምንገኝበት እጅግ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ሁኔታዎች የሚታዩበት ደረጃ ላይ አድርሶናል። በጽሁፉ መግቢያ የመጀመሪያ አረፍተ ነገር ላይ የተጠቀሰው የህዝባዊ ተቃውሞ ፍሬ ይህ ነው። ይህ ተስፋ በራሱ እውን አይሆንም። እውን መሆኑ ቁርጠኝነት ያለውን መንግስት ብቻ ሳይሆን፣ እውን ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታና የህዝብን እገዛ ይሻል።
አሁን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በመንግስትና በህዝብ መሃከል የመተማመን ድልድይ ተዘርግቷል። መተማመኑን የፈጠረው መንግስት ህዝብን ያማረሩ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት ችግሮችን፣ ሌብነትን በተጨባጭ ያቃልላል፤ በፖለቲካው ዘርፍ ቅሬታ የፈጠሩና አለመግባባቶች የሃገር ደህንነት ስጋት ወደመሆን እንዲለወጡ የሚያደርጉ የፖለቲካ ምህዳር መስፋት፣ በሁሉም ወገን ተቀባይነት ያለውና ውዥንብር ለመፍጠር የማያስችል ነጻና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መካሄድና ተያያዥ ችግሮች መፍትሄ ይበጅላቸዋል፤ የሰብአዊ መብት አያያዝ ይሻሻላል ወዘተ የሚል ተስፋ ነው።
ህዝብ እነዚህ ነገሮች አሁን ባለው የሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ መሆን በሚችለው ልክ እውን ሆነው ማየት ይፈልጋል። በመሆኑም መንግስትም ተጨባጭ ሁኔታው በሚፈቅደው ልክ እውን ለማድረግ መስራት ይጠበቅበታል። መንግስት ይህን ማድረግ እንዲችል ከህዝብ የሚጠበቅ ሁኔታም አለ፤ አሁን የተገኘውን የሰላም ፋታ ዘላቂነት ማረጋገጥ።
ቀደም ሲል የጠቀሰናቸው ችግሮች አንዳንዶቹ በአጭር ጊዜ ተጨባጭ መሻሻል ሊያሳዩ ይችላሉ። የመንግስት ተቋማት አገልግሎት ፍለጋ የሚመጣውን ሰው በአገልጋይነት መንፈስ ህግ በሚያዘው መሰረት ማስተናገድ እንዲችሉ ማድረግ ዓመታትን የሚፈጅ ጉዳይ አይመስለኝም። በአጭር ጊዜ የአገልጋይነት መንፈስን መፍጠር ባይቻል እንኳን፣ በተገቢው መንገድ አገልግሎት መስጠት ግዴታ መሆኑን፣ ይህን ግዴታ መወጣት አለመቻል ከስራ ውጭ እንደሚያደግ በማስገንዘብ አስገዳጅ ሁኔታ መፍጠር ይቻላል የሚል ግምት አለኝ። በፍትህ ዘርፍ ከዚህ ቀደም የደረሱ ጉዳቶችን መካስ በቀላሉ ይሳካል ተብሎ ባይገመትም፣ ፍርድ ቤቶች ፍርድ የሚሸጥባቸው መደብሮች እንዳይሆኑ በማድረግ ረገድ የሚታይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም እገምታለሁ።
በሌላ በኩል፤ ዴሞክራሲን ማሰፈን የወራት ስራ አይደለም። ዴሞክራሲን ማስፈን የመንግስት ብቻም ድርሻ አይደለም። ተፊካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ህዝብም ባለድርሻ ናቸው። ዴሞክራሲን ማስፈን በእነዚህ ባለድርሻ አካላት ውስጥ የአመለካከትና የአሰራር ለውጥ የማምጣት ጉዳይ ነው።
ዴሞክራሲ እነዲሰፍን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግባቸው ያደራጇቸውንና በዙሪያቸው ያሉ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ፍላጎት ማሳካት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎትና ጥቅም፣ መብትና ነጻነት ማረጋገጥ መሆኑን ሊገነዘቡ የግድ ነው። ዴሞክራሲን ማስፈን የፖለቲካ ፓርቲዎች አነሳስ አንድ ወገን ላይ ያለ ጥላቻ ሳይሆን፣ በህዝብ ጥቅምና ፍላጎት፤ መብትና ነጻነት ላይ ተመስርተው የሚደራጁና የሚንቀሳቀሱ እንዲሆኑ ይሻል። የሌላውን ወገን ችግር ማጉላት ሳይሆን የሚያስፈጽሙትን ተጨባጭ ፋይዳ ሊያስገኝ የሚችል አማራጭ ፖሊሲን በማሰተዋወቅ ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግን ይጠይቃል። ወቅት ተኮር ስሜት ኮርኳሪ አጀንዳዎችን በማቅረብ፣ ህዝብን በስሜት በማነሳሳት በህዝበኝነት ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ፣ ዘላቂና ህዝባዊ መሰረት ያላቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮርን የግድ ይላል።
እነዚህን ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቁ ሁኔታዎች መንግስት ሊያከናውን አይችልም። ይህ በዋናነት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጉዳይ ነው። ህዝብ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ማንነት ከዚህ አኳያ እየመዘነ እንዲያንጓልላቸው ይጠበቅበታል። በዚህ ዙሪያ የሚታይ መሻሻል በአዋጅ የሚመጣ ሳይሆን በአመለካካት ለውጥ የሚመጣ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ ክፍተት ይታያል። ይህን ማስተካካል ጊዜ ይጠይቃል። በሂደት እየተሻሻለ የሚሄድ እንጂ በአዋጅና በዘመቻ በአፍታ የሚደረስበት አይደለም።
ዴሞክራሲ እንዲጎለብት በህዝቡ ዘንድም በተመሳሳይ ሁኔታ የአመለካከት ለውጥ መፈጠር አለበት። ዜጎች ድምጽ የሰጡትን ሳይሆን አብላጫው ዜጋ ድምጹን የሰጠው አካል የስልጣን ውክልና መውሰድ ያለበት መሆኑን መቀበል መለማመድ ይኖርባቸዋል። አብላጫ ድምጽ ሳያገኝ የቀረ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ድምጽ ሰጪዎቹ ከድምጽ ውክልና ውጭ ወደስልጣን የሚመጣበትን እድል እንዲያስገኙት ለአመጽና አድማ ሲጠራቸው መሰለፍ አይኖርባቸውም። ይህ በሃገራችን የተለመደ የፖለቲካ አካሄድ እንዲቀየር ማድረግ የአጭር ጊዜ ስራ አይደለም።
የህዝቡን ጥቅምና ፍላጎት ብቻ ታሳቢ ያደረጉ ዴሞክራሲን፣ ሰብአዊ መብቶችንና ነጻነቶችን ማረጋገጥ ብቻ ግባቸው የሆነ፣ ከውጭም ሆነ ከሃገር ውስጥ ቡድናዊ ተጽእኖ ነጻ የሆኑ ሲቪክ ማህበራትን መፍጠርም ጊዜ ይጠይቃል። በእዘኒህ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ የህግ ማሻሻያዎች ማደረግ ቢቻልም፣ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ግን አዋጅን እንደማሻሻል ወይም ማውጣት የአጭር ጊዜ ተግባር አይደለም።
ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ማረጋገጥ፣ ስራ አጥነትን በጉልህ ማቀላል ወዘተም በአዋጅና በዘመቻ ብቻ የሚገኝ ውጤት አይደለም። ይህ ችግር ከመንግስት አፈጻጸምና ከፖሊሲ ችግር ብቻ የመነጨ እንዳልሆነ መስተዋል አለበት። በሃገሪቱ ለዘመናት ስር ሰዶ ከኖረው ድህነት የመነጨም ነው። እነዚህ ችግሮች መንግስት ስለፈለገ፣ ቁርጠኝነት ስላለው፣ ወይም አዲስ መንግስት ወደስልጣን ስለመጣ በአንድ ቀን ጀንበር አይቃለሉም። እናም ጊዜ ይጠይቃል።
አሁን በመንግስትና በህዝብ ዘንድ መተማመን የፈጠረው ተስፋ ጊዜውን ጠብቆ እውን እንዲሆን ከላይ በሰፈሩት ጉዳዮች ዙሪያ በህዝቡ መሃከል፣ በህዝቡና በፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል፣ በመንግስትና በፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል ወዘተ የሚፈጠር መግባባትን የግድ ይላል። ይህ መግባባት ሰበብ እየፈለጉ ሁከት፣ ግጭትና ግርግር የሚቀሰቅሱ አካላትን ማምከን ያስችላል። አሁን የተገኘውን ሰላም ዘላቂነት ማረጋገጥ ያስችላል ማለት ነው።
በዚህ ዘላቂ ሰላም ውስጥ መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ተስፋውን እውን ማድረግ የሚያስችለው ምቹ ሁኔታና እድል ያገኛል። መግባባት ጠፍቶ የራሳቸውን ፍላጎት ለሟሟላትም ይሁን በየዋህነት ስህተት ለሁከትና ግርግር፣ ግጭት አመቺ ሁኔታ የሚፈጠር ከሆነ፣ ዘላቂ ሰላም ይጠፋል፤ ተስፋውም እንደበጋ ጉም በኖ ይጠፋል። የተግባቡ ደጅ አያድሩም እንደሚባለው፣ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ላይ መግባባት ከተቻለ ተስፋው እውን ይሆናል። መግባባት ካልተቻለ ግን ባክኖ ይቀራል።