Artcles

የትግል ድምር ውጤት  “ግንቦት ሃያ”!

By Admin

May 21, 2018

የትግል ድምር ውጤት  “ግንቦት ሃያ”!

ወንድይራድ ሃብተየስ

ግንቦት 20 የበርካታ ውድ  የህዝብ ልጆች የህይወትና የአካል መሰዋዕትነት ድምር ውጤት ናት። ዘንድሮ ለ27 ጊዜ ይህችን  የድል ቀን “ የላቀ ብሄራዊ መግባባትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለአገራዊ ስኬት” በሚል መሪ ቃል  እናከብራታለን። “ግንቦት ሃያ” ዕውን እንድትሆን በርካቶች ህይወታቸውንና አካላቸውን  ለግሰዋል። እነዚያ ውድ የህዝብ ልጆች በአገራቸው የሰፈነውነ ነጻነት፣ ዕኩልነት እንዲሁም  ፈጣን ልማታችንን ሳያዩ አልፈዋል። አዎ “ግንቦት ሃያ” የቁልቁለተ ጉዞ የተገታበትና አዲስ ምዕራፍ የጀመርንባት  ዕለት በመሆኗ ልንዘክራት ይገባል።

ከግንቦት 20/1983 ዓ.ም ጀምሮ በአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት መተግበር በመጀመሩ ነጻነትና ዕኩልነት  ተረጋግጧል። በአገራችን የዴሞከራሲ ስርዓት መተግበር ይጀመር እንጂ አያያዙን በቅጡ ያወቅንበት አይመስለኝም። ለዚህም ይመስለኛል  ከሁለት አስርት ዓመታት ብኋላ እንደገና ተመልሰን በመልካም አስተዳደር ዕጦት ወደ ወሁከትና ነውጥ የገባነው። ባለፉት 27 ዓመታት በተከናወኑ  ተጨባጭ ለውጦች ኢትዮጵያ ወደ ቀደመው ገናና ታሪኳ ለመመለስ በህዳሴ ጉዞ ላይ ትገኛች፤ የህዳሴው መሰረት የተጣለው ደግሞ በ“ግንቦት ሃያ” ነው። በአገራችን በሁሉም ዘርፎች  ፈጣን ለውጦች በተለይ ባለፉት አስራ አምስት ተከታታይ ዓመታት በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጦች ማስመዝገብ ተችሏል። የህዝቦች እኩልነት የተረጋገጠባት፣ ዴሞክራሲ አንድነቷ የተጠበቀበት፣ የበለፀገችና ለዜጎቿ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተረጋገጡባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሁላችንም ልንደመር ሁላችንም  በሃላፊነት መስራት ይኖርብናል።

የህዝብ ልጆች  ለዴሞክራሲ ስርዓት ዕውን መሆን ታግለዋል። ይሁንና በመንግስት ጥረት ብቻ  ዴሞክራሲያዊ ሊጎለብት የማይችል በመሆኑ የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ ነው። መንግስት የአገሪቱን ዴሞክራሲ ለማጎልበትና ህብረተሰቡ መበቶቹን መጠቀም እንዲችል የተለያዩ ተቋሞችን  አቋቁሞ በመትጋት ላይ ነው። ዴሞክራሲን ለማጎልበት የተቋቋሙት ተቋሞቻችን ለጋ ቢሆኑም ህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን እንዲለማመድ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

ከግንቦት 20 1983 ዓ.ም  ጀምሮ አገሪቱ ትታወቅበት የነበረው የድህነት፣ ረሃብ፣ ድርቅ እና የዕርስ በርስ ጦርነት  ገጽታ ደረጃ በደረጃ አየተቀረፈ እንዲሁም የአገሪቱም ገጽታ መቀየር ጀምሯል። የ “ግንቦት ሃያ” ድል አገሪቱን ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሯል፤  ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዛሬ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መረጋገጠ ብቻ ሳይሆን በልማትም እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነዋል፤ በአገራችን ህገመንግስት የመናገር፣ የመፃፍ፣ ሃሳብን የመግለፅ፣ የመደራጀት፣ የመቃወምና የመደገፍ ብሎም የመምረጥና መመረጥ መብቶችን ተረጋግጠዋል።  የህገ-መንግስቱ ትኩረት የአገሪቱ የህግ የበላይነት መስፈን፣ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነት መረጋገጥ ፣ በግለሰብና የቡድን መብቶች መከበር፣ በሃይማኖትና ባሕሎች መካከል መቻቻል መስፈን፣ የፆታ እኩልነት መረጋገጥ፣ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ መስፈን እና አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመገንባት ላይ መሆኑ ለህዝቦች  ዘላቂ ሰላም ምን ያህል ዋጋ እንደተሰጠ የሚያሳይ ነው።

የሕገ-መንግስታችን  መሰረታዊ መርህ የህገ የበላነትን የህዝቦች ዕኩልነት ነው። ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የምናስተውላቸው አንዳንድ አካሄዶች ኢ-ህገመንግስታዊ ሆነው እናገኛቸዋለን። ኢህአዴግ የቀድሞውን  አቅም አጥቷል ወይም በኢህአዴግ ቤት መደማመጥ መረዳዳት እየቀነሰ መጥቷል። ዜጎች ያለሃጢያታቸው ሲገደሉ፣ ሲዘረፉ፣ በመቶ ሺዎች ሲፈናቀሉ እየተመለከትን ነው። ይህ ብቻ አይደለም ዜጎች በዚህ ሁለትና ሶስት ዓመታት የመከራና የስጋት ህይወት መርተዋል። የህግ የበላይነተ ተጥሷል፤  ህገመንግስት ተሸርሽሯል። ህገመንግስታችን የአገራችን ምሰሶ ነው። ይሁንና ተገቢውን ክብርና ጥበቃ አላደረግንም። ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግስት ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በህገመንግስታችን ተደንግጓል። በተጨማሪም ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማሕበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ሕገ-መንግስቱን የማስከበርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸውም በግልፅ ይደነግጋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ መርህ እየተደፈለቀ ሁሉም በየፊናው እየተመመ ነው።  አስርት ሺዎች ህይወታቸውን ሌሎች አስርት ሺዎች ደግሞ አካላቸውን የገበሩበት መርህ  ሲደፈለቅ ኢህአዴግ አላየም አልሰማም ብዬ አላምንም። ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ዘረኝነት፣ ጥበት፣ ትምክህት፣ ሌብነት፣ ማንአለብኝነት ወዘተ  በአገራችን ገንግነው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን ሊደፍቁት እየተሯሯጡ ናቸው። እነዚህ መርዘኛ አስተሳሰቦች ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ  ለስርዓቱ እንቅፋት ለመሆን የበቁት መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ ያላከናወኗቸው ተግባራት እንዳሉ በግልጽ ያመላክታል። በመሆኑም የዘንድሮውን “ግንቦት ሃያ” የድል ቀን  የምናከብረው በጥልቅ ተሃድሶው የተለዩትን የመልካም አስተዳደር እንቅፋቶች በማንሳት መሆን መቻል አለበት።

ከ”ግንቦት ሃያ” ድል በፊት አገራችን ትታወቅ የነበረው በእርስ በርስ ጦርነት፣ ረሃብ እና ኋላቀርነት እንዲሁም አስከፊ ደህነት እንደነበር ለጎልማሳ ኢትዮጵያዊያን መንገር ለቀባሪው እንደማርዳት ይሆንብኛል። ኢትዮጵያ ቅድመ 1983 ዓ.ም  የህዝቦቿ ትልቋ እስር ቤት ነበረች፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶች የማይታሰቡባት፣ ሰብዓዊ መብት በጠራራ ጸሃይ የሚጣስባት፣ ሃይማኖተኝነት የሚያስቀጣበት፣ የድህነት መጠኑ ጣሪያ የደረሰባት፣ ሁሉም ነገር ወደጦር ግንባር ተብሎ ወጣቶቿ እየታደኑ ወደ ግንባር  የሚጋዙባት አገር ነበረች። ዛሬ ያ የስቃይ፣ ያ የስቃይ ጊዜ አልፏል። “ግንቦት ሃያ” የስኬቶቻችን መስፈንጠሪያ ብቻ ሳትሆን የመከራና የስቃይ ምዕራፍ መዝጊያም ሆናለች።

እነዚህ ሁሉ ሥጋቶችን ማምከን የተቻለውና  አዲሲቷ ኢትዮጵያ በጠንካራ መሰረት ላይ እንድትመሰረት አድረገችው  “ግንቦት ሃያ” ናት። የ“ግንቦት ሃያ” ድል ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ዘላቂ ሠላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማት ለማረጋገጥ መሠረት እና ዋስትና መሆን የቻለች ዕለት ናት። በአገራችን ያለውን ብዝሃነት የተቀበለ እና ያከበረ አዲስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት መፍጠር “ግንቦት ሃያ” በቀደደችልን መንገድ ተጉዘን ነው። ሕገ መንግቱ ሕዝቦች ፍላጎታቸውን እና እምነታቸውን የገለፁበት፣ በአዲስ መንፈስ የጋራ ግንባር ፈጥረው፣ ተከባብረው እና ተጋግዘው አብረው ለመኖር ቃል የገቡበት ሠነድ ነው። ይህ ሠነድ አንድ የጋራ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ቃል የተገባበት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ  ህልውና መሰረት ነው።

ሕገ-መንግስታችን ለፈጣንና ቀጣይ የኢኮኖሚ እድገታችን እንዲሁም ለአስተማማኝ ሰላማችን ዋስትና መሆኑ ብቻ ሳይሆን የአገራችን እስትንፋስ በመሆኑ   ሁላችንም ልናከብረው ብቻ ሳይሆን ልናስከብረው የሚገባን ግዴታ ነው። እንደእኔ እንደእኔ ከእንግዲህ ወደኋላ ለመመለስ መንገዱ ረጅምና ውስብስብ ነው፤ በመሆኑም በዚህ ስርዓት ላይ በትንሹም  በትልቁም እየተነሳን ጣት መቀሰሩ ዋጋ ያስከፍለናል የሚል ስጋት አለኝ። የፌዴራል ስርዓታችንና ህገመንግስታችን እጅግ የተቆራኙ አንዱ የአንዱ ውጤት ናቸው። አይን ሲመታ አፍንጫ ያለቅሳል እንዲሉ  የፌዴራል ስርዓቱ ላይ የተጀመረው የማጠላላት ዘመቻ ቢታሰብበት መልካም ይመስለኛል። ሕገ-መንግስታችን የአገራችን ህዝቦች የቆየ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስሮችን በአግባቡ በመዳሰስ የተዛቡ ታሪካዊ ግንኙነቶቻችን እንዳይደገሙ፤ አዎንታዊ ግንኙነቶቻችንና ዕሴቶቻችንን ደግሞ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ መደላድሎችን የገነባ የሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ የቃል ኪዳን ሰነዳቸው  ሆኗል።

ግንቦት ሃያ የህዝቦች  የድል ቀን ናት ። አንዳንዶች “ግንቦት ሃያ”ንና ኢህአዴግን  ለማቆራኘት ጥረት ሲያደርጉ እመለከታለሁ። በእርግጥ “ግንቦት ሃያ”ን እውን ለማድረግ  ኢህአዴግ የማይተካ ሚና አበርክቷል፤ ኢህአዴግ ብሶት የወለደው የጭቁን ህዝቦች ስብስብ ውጤት ነው። መጠኑ ይለያይ ይሆናል እንጂ  ለ “ግንቦት ሃያ” ዕውን መሆን ከኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያልታገለ ማን ነው። የደርግ ስርዓት ለየትኛውም ብሄር ወይም ብሄረሰብ የሚበጅ አለነበረም።   አንዳንድ አካላት ሆን ብለው የ“ግንቦት ሃያ”ን ቱሩፋቶች ለማሳነስ ወይም ለማጣጣል በዓሉ የኢህአዴግ በዓል ለማስመሰል ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ። ይሁንና “ግንቦት ሃያ”  የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል ድምር ውጤት፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የድልና የነጻነት ቀን መጀመሪያ፣ የስኬታቸውም መስፈነጠሪያ በመሆኗ ሁላችንም ልንዘክራት ይገባል።

 

ሕገ መንግስታችንን ዴሞክራሲያዊ ባህርያት ከሚያላብሱት መሰረታዊ መርሆዎች መካከል አንዱ የቡድንና የግለሰብ መብቶችን በተመለከተ ያስቀመጠው ዋስትና ነው። ሕገ መንግስታችን የግለሰብና የቡድን መብቶች ሳይሸራረፉና ሳይድበሰበሱ በተሟላ መንገድ ያለገደብ እንዲከበሩ በግልጽ ደንግጓል። በህገ መንግስቱ የግለሰብ መብቶች ከቡድን መብቶች ጋር የሚመጋገቡ እንጂ የሚጣረሱ አለመሆናቸውን፣ የግለሰብ መብቶች መጣስ፣ የቡድን መብቶችን መጣስን እንዲሁም የቡድን መብቶች መጣስ፣ የግለሰብ መብቶች ጥሰትን የሚያስከትል እንደሆነ  በደንብ አስታውቋል። በተግባርም አረጋግጧል። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበርካታ አካባቢዎች የግለሰቦች ህገ-መንግስታዊ መብቶች ባለመብት ነን በሚሉ ግለሰቦችና በተደራጁ ሃይሎች በጠራራ ጸሃይ ሲደፈጠጥ፣ እየተመለከትን ሁላችንም በአያገባኝም ስሜት ዝምታን መርጠናል። እንደነዚህ ያሉ አካሄዶች በወቅቱ ባለመወገዛቸው መንግስትም በወቅቱ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ በመቻሉ አሁን ላይ በመቶ ሺዎች ለሚሆኑ ዜጎቻችን መፈናቀል ምክንያት ሆኗል።