Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

         የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ሊገታ ይገባል

0 461

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

         የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ሊገታ ይገባል

ይልቃል ፍርዱ

ግርግር ለሌባ ይመቻል ይሉ አይነት ሆነና በሀገር ደረጃ የተፈጠረውን ፖለቲካዊና የኢኮኖሚ ቀውስ በመጠቀም በዚህ ትርምስ ውስጥ ሕብረተሰቡ በሚፈልጋቸው ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ውድነት በመጨመር የማስመረርና እንዲከፋ በዚህም ከመንገድ የወጣ ተቃውሞ እንዲከሰት ሲሰራ በነበረው ስራ የተጠቀሙት ሕገወጦች ሲሆኑ የተጎዳው ደግሞ ሕብረተሰቡ ነው፡፡የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት እንዲፈጠር የሚሰራውን ሴራ ለማምከን መንግስትና ሕዘብ በጋራ ሊሰሩ ይገባል፡፡

በኢኮኖሚ አሻጥር ውስጥ ተሰማርተው ሲሰሩ የነበሩ ክፍሎች ዛሬ ይህ ሁኔታ እንደማያዋጣ ሊረዱት ይገባል፡፡በመሰረቱ በሀገሪቱ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ችግር የለም፡፡ለተወሰነ ወቅት ለቀናት በተፈጠረው የትራንስፖርት ችግር ከክልሎች ወደ ከተማ የሚገቡ ሸቀጦች በመጠነኛ ደረጃ እጥረት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ወዲያውኑ በነበረበት ሁኔታ ተመልሶአል፡፡

በግብርና ምርቱም ሆነ ለገበያ በሚቀርቡ የተለያዩ የሰብል አይነቶች ጤፍና ጥራጥሬዎችን በተመለከተ በሀገር ደረጃ የተትረፈረፈ ምርት አለ፡፡እጥረቱን የሚፈጥሩት ወገኖች ሆን ብለው ሕብረተሰቡን ለማማረር እንደገናም ያልተገባ ትርፍና ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሲሰሩት የነበረ ስራ ነው፡፡ተፈላጊ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ በገበያው የሚፈጠረውን እጥረትና የዋጋ ጭማሪ ከመጠን በላይ እንዲሄድ የሚያደርጉት አንዳንድ አልጠግብ ባይ ነጋዴዎች ናቸው፡፡  

እንዲያውም በብዙ ያደጉ ሀገራት በጣም በርካሽ ዋጋ በሳንቲሞች ደረጃ ገበያ ላይ ሞልቶ የተትረፈረፈው ምግብ ነው፡፡የምግብ ዋጋ እጅግ በጣም ርካሽ ነው፡፡በሀገራችን ለምግብ የሚውሉ የሰብል ምርቶች እጥረት የለም፡፡እጥረቱ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ነው ዜጎች  ከትንሽ አስከ ትልቅ ባሉ ሆቴሎች ውስጥ ለመመገብ ከገቡ ከአቅማቸው በላይ እንዲከፍሉ የሚገደዱት፡፡ጤፉ፤ ሽሮው፤ ስጋው፤ አትክልቱ በውጭ ምንዛሪ ከውጭ የገባ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ መሬት ያፈራው ያበቀለው ነው፡፡የምግብና የሸቀጦችን ዋጋ በማናር በሕዝብ ላይ የሚፈጸመው በደል መገታት አለበት፡፡በሕግና በስርአት ሊቆም ይገባዋል፡፡

ለሕዝቡ ለሽያጭ በሚቀርበው መሰረታዊ የሰብል ምርትም ሆነ በሚቀርበው የምግብ ሽያጭ ከሕዝቡ አቅምና የመግዛት አቅም በላይ በሆነ ዋጋ የሚሸጠው አንድም ሕዝቡን ለማማረር ሲሆን ሌላው ከሕግና ከስርአት ውጪ የተትረፈረፈ ትርፍ ለማጋበስ ካለ ፍላጎት የመነጨ ነው፡፡

ይህ የሚያሳየው በመንግስት አካላት የኑሮ ውድነትን ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ ሕገወጥ ንግድ በሚያካሂዱ አካላት ላይ የሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል እጅግ የላላ ከመሆኑም በላይ ተገቢ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ አለመወሰድ ያስከተለው ውጤት መሆኑን ነው፡፡ለሕዝቡ ከሚቀርበው የምግብ ሽያጭ ጋር በተያያዘ የጥራትና ቁጥጥር ስራ በተገቢው መንገድ የማይካሄድ በመሆኑ ከባሕላችን ውጭ በምግብ የማንጠቀምባቸውን ጅብና አሕያ እያረዱ አይጥን ጭምር እየተጠቀሙ ለምግብነት ሲሰሩ ቆይተው የተጋለጡ የተያዙ መኖራቸውን ስናስታውስ ሀዘናችንን የበረታ ያደርገዋል፡፡

እንደገናም በበርበሬ ውስጥ ቀይ አፈር አስፈጭተው(ፈጭተው) በማስገባት፤ዘይትና ቅቤ ውስጥ ባእድ ነገር በመቀላቀል በሕዝብ ጤናና ሕይወት ላይ እየቀለዱ ሲጫወቱ የኖሩ በሕዝብ ጥቆማ የተጋለጡበት በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉበት በርካታ አጋጣሚዎች ተከስተዋል፡፡ፖሊስ ብዙ መረጃዎች አሉት፡፡ዛሬም ይሄ ሕገወጥ ድርጊት ቆሞአል ለማለት አይቻልም፡፡ይህ ሁሉ የሚያሳየው ለዚህ ስራ የተመደቡት መንግስታዊ የንግድ ፍቃድ ሰጪና የቁጥጥር አካላት በጥምረት መስራት ያለባቸው የጤና ቁጥጥር አካላት ስራቸውን በተገቢው መንገድ መስራት አለመቻላቸውን ነው፡፡

በሕብረተሰቡ በተለይም በሕጻናትና እናቶች በአረጋውያን በወጣቱ በአጠቃላይ በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው የጤና አደጋ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ቻይናን በመሰሉ ሀገሮች  በዚህ ተግባር በፖሊስ ማስረጃ የተገኙ ሰዎች ሕገወጥና ቀናቸው ያለፈ የታሸጉ ምግቦችን ለሕዝቡ በስውር አስገብተው የሚሸጡ፤በሀገር ውስጥም ቢሆን ለጤንንት ብቁ መሆናቸው ሳይረጋገጥ ለሕዝብ የምግብ ሽያጭ አቅርበው በሚገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ  የሚወሰደው እርምጃ በሕይወታቸው ጭምር የሚቀጡበት ነው፡፡ምክንያቱም እነሱም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘትና ለመክበር ሲሉ በብዙ ሺህ ዜጎች ሕይወት ላይ ፈርደዋል፡፡

የኑሮ ውድነት ከመፍጠር አልፎ ለሽያጭ በሚቀርቡት የምግብ እህሎች ላይ ጭካኔ በተሞላበት ሰብአዊነትና ርህራሔ በሌለው መልኩ ይህን የመሰለ ወንጀልም ይሰራል፡፡ለዚህ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው የንግድ ቢሮዎችና የጤና ቢሮ አካላት የምግብ የጤና ባለሙያዎችን በብዛት በመመደብ ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ ተቀናጅተው እንዲሰሩ ጉድለት የተገኘባቸውን ለሕዝቡ ጤንንት ሲባል እንዲታገዱ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡በሕዝብ ጤንንት ላይ ወንጀል የሚፈጽሙትን በበቂ ማስረጃ ለሕግ አቅርቦ ከበድ ያለ ቅጣት መጣል ለሌላውም አስተማሪ ይሆናል፡፡

የኑሮ ውድነቱን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወቱት ሁሉም ምርትና ሸቀጥ እያለ ለሕዝቡ እንዳይደርስ በመጋዘኖቻቸው እያከማቹ እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ የሚሰሩ አካላት ናቸው፡፡ተመሳሳይ የግንኙነት ሰንሰለቶችን በመጠቀም እጥረቱ እንዲባባስ ያስተባብራሉ፡፡በዚህ መልኩ መቀጠል ስለማይቻል መንግስት ሁኔታውን ተከታትሎ ችግሩን ከምንጩ ማምከን ይጠበቅበታል፡፡

ለግል ጥቅማቸው በማሰብ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ችግር እንዲፈጠር ቀን በቀን እየሰሩ ያሉትን አካላት ተከታትሎ የማያዳግም መፍትሔ ለመስጠት መንግስትና ሕዝብ እንዲሁም የተለያዩ መንግስታዊ አካላት ሕዝባዊ ድርጅቶች  ተቀናጅተው ተናበው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ሁሉንም ነገር ለመንግስት መተው ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ መንግስት ውጤታማ ሆኖ መስራት የሚችለው የሕዝቡ ከፍተኛ ትብብርና እገዛ ከጎኑ ሲሆን ነው፡፡ይህን እውነት በመረዳት የኑሮ ውድነት በመፍጠር የተግበሰበሰ ትርፍ በመፈለግ ሕዝብን በማስከፋት መክበር በሚፈልጉ አካላት ላይ ሕዝቡ ያየውን የተመለከተውን ሁሉ ለመንግስት አካላት በመጠቆም ማጋለጥ ይጠበቅበታል፡፡

ችግሩን ለመፍታት የሚቻለው በመንግስት አካላት ስር ሆነው ተገቢ ቁጥጥር የማያደርጉትንና ለሕገወጥነት መስፈን ለሕገወጦች መበረታታት በር የሚከፍቱትን ነቅሶና ለይቶ በማውጣት ተጠያቂ ማድረግ እንደገናም የኑሮ ውድነቱን ለማባባስ በሚሰሩት አካላት ላይ ተገቢ ሕጋዊ እርምጃ በተከታታይና በማያቋርጥ መልኩ በመውሰድ ነው፡፡አንድ ሰሞን በሕገወጦች ላይ እርምጃ መውሰድ ይጀመርና ወዲያው ይቆማል፡፡ይህ ለሕብረተሰቡ የሰጠው ትምህርት ተውት የአንድ ሰሞን ጫጫታ ነው ነገ ይቆማል የሚል ነው፡፡እውነትም በዚሁ መልኩ ብዙ ግዜያትን አመታትን አሳልፈናል፡፡ችግሩ ተመልሶ መልክና ዘዴውን ቀይሮ ይከሰታል፡፡ዘላቂ እልባት ያስፈልገዋል፡፡

ሕግና ስርአት የሰፈነበት የንግድ ልውውጥ መኖር ይሄንንም የሚከታተሉ የሚያስፈጽሙ የመንግሰት አካላት መኖር ግድ ይላል፡፡ችግሩ የግድ ከስረ መሰረቱ መፈታት አለበት፡፡ጉዳዩ የጥቅም ጉዳይ ስለሆነ ሕገወጦች በሕጋዊ መንገድ ሲመከቱ ሌላ ዘዴና መንገድ ፈልገው እንደገና በአዲስ መልክ እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል፡፡ለዚህ የሚሆን ቋሚ ሕግና ደንብ በማውጣት መቆጣጠር ይገባል፡፡

በውጭ ምንዛሪውም በኩል የሚሰራው ሸፍጥና ደባ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡የውጭ ምንዛሪውን በጥቁር ገበያ ዋጋውን ከማሳደግ ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጣ የሚደረግበትም ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡በሌላ መልኩ ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲገጥማት በዚህም የተጀመሩትን ግዙፍ ብሔራዊ ፕሮጀክቶችን የማዳከም ሴራ ነው፡፡እነዚህ ሁሉ ሀገርንና ሕዝብን የሚጎዱ ተግባራት ናቸው፡፡ሊመከቱ ይገባቸዋል፡፡

ማጠቃለያ

ሀገራዊ የሰብል ምርትና አቅርቦት በስፋት ባለበት ሁኔታ ውስጥ ሆን ብለው የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር የሚሰሩ ግለሰቦችና ቡድኖችን መንግስትና ሕዝብ ተከታትለው ለሕግ ማቅረብ ይገባቸዋል፡፡ሕብረተሰቡን በማማረር የሚገኝ ትርፍ አለ ብለው አስበውም ከሆነ መሰረታዊ ስሕተት ነው፡፡ነግደውም ሆነ አትርፈው የሚኖሩት ሕዝብ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ሸቀጦችንና የሰብል ምርቶችን በመደበቅ በመጋዘን በማከማቸት በሕዝብ ላይ እንግልትና ምሬት የሚፈጥሩ አንዳንድ ነጋዴዎችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲፈጠር የሚሰሩ አካላት ስላሉ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግስታዊ አካላት በሕብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መሰራት አለባቸው፡፡የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚያስከተለውን ከፍተኛ ጉዳት የማሳየት ስራ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮችን በማዘጋጀት ማሳወቅ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶችን ማድረግ ጉዳቱ የመንግስት ብቻ ሳይሆን በዋነኛነት ተጎጂው ሕዝቡና ሀገራዊ ኢኮኖሚው መሆኑን ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡የሀገር ኢኮኖሚው ሲጎዳ ቀጥተኛ ተጎጂው ሕዝብ ነው፡፡የተጀመሩ ፕሮጀክቶች፤ፋብሪካዎች፤የመንግስታዊ ተቋማት ስራ እንዲሁም በንግዱ በኢንቨስትመንት በትራንስፖርት በጤናው አገልግሎት በትምህርት ዘርፎች በመሰረተ ልማቱ በግንባታው  በእርሻና ኢንዱስትሪው ወዘተ መስኮች ሁሉ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ይሄንን ችግር ፈጥኖ መከላከል ለመንግስት አካላት ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡የችግሩ ግዝፈት የእያንዳንዱን ዜጋ ጓዳ ይነካል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጫናው ይደርሰዋል፡፡ሁሉም ዜጋ ሊገነዘበው ይገባል፡፡በግልጽ መታወቅም አለበት፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy