Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአብሮነት ድር

0 427

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአብሮነት ድር

                                                      ዘአማን በላይ

ሰሞኑን የዓለም ባንክ አገራችን በመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ ከምስራቅ አፍሪካ መሪ መሆኗን ሪፖርት አውጥቷል። ኢትዮጵያ ለዘርፉ ከፍተኛ የሆነ ኢንቨስትመንት መድባ እየሰራች የምትገኝ ሀገር መሆኗንም ሪፖርቱ ገልጿል። በቀጣይም ዕድገቱ ከፍተኛ እንደሚሆን አስረድቷል።

ኢትዮጵያ የመሰረተ ልማትን በማስፋፋት እና የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ ሀገር ውስጥ በመሳብ ከፍተኛ የሆነ የስራ እድል በመፍጠር ላይ እንደምትገኝ ሪፖርቱ አመልክቷል። ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር የትራንስፖርት ዘርፉን እያሳለጠች ቀጣናውን በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማስተሳሰር ጥረት እያደረገች ነው። ይህም ሀገራችን የቀጣናው አብሮነት የትስስር ድር እየሆነች መምጣቷን የሚያሳይ ነው።

በአሁኑ ወቅት ይህ የምስራቅ አፍሪካ የጦርነት ታሪክ በአንፃራዊ ሁኔታ ጋብ በማለቱ፤ የቀጣናው ሀገራት ከሁለንተናዊ ትስስር የሚገኘውን ጥቅም ለማጣጣም በርካታ ውጥኖችን ይዘዋል። ማንኛውም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው፤ ሀገራችን እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ በእርስ በርስ ግጭትና ስር በሰደደ ድህነት ውስጥ ኖራለች—ባለፉት ስርዓቶች።

ሆኖም ምስጋና ለኢፌዴሪ መንግስትና እርሱ የሚከተለውን ስርዓት እውን ለማድረግ ህይወታቸውን ለሰጡ ውድ የህዝብ ልጆች ይሁንና በዚህ መጥፎ ምሳሌነት የተሳለችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ገፅታዋን በመለወጥ ላይ ትገኛለች። መንግስትና መላው ህዝቦቿ አንድነት ፈጥረው ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ባከናወኗቸው ዘርፈ- ብዙ ቅንጅታዊ ስራዎች ከቀጣናው አንፃራዊ ሰላም ተጠቃሚ እየሆነች ነው። ለመሆንም ጠንክራ በመስራት ላይ ትገኛለች።

አዲሲቷ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክም በአዲስ ገፅታ መታየት ከጀመረች ቆይታለች። በዚህም ሳቢያ ሀገሪቱ በምስራቅ አፍሪካም ይሁን በዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረኮች ተሰሚነቷ እየጎለበተ መጥቷል። የዲፕሎማሲው ተሰሚነቷ ሁሉንም የቀጣናውን ብሎም የአህጉሪቱን ሀገራት እየሳበ በመምጣቱም ዛሬ የኢትዮጵያን ምክርና ልምድ ለመጠየቅ ወደ መዲናችን የሚያቀኑ የአፍሪካ መሪዎች በርካታ ናቸው። ይህ ሁኔታም ሀገራችን ከራሷ አልፋ ቀጣናውን በመሰረተ ልማት እንድታስተሳስር ያደረጋት ይመስለኛል። ታዲያ ከዚህ አኳያ የሀገራችን ወጪና ገቢ እቃዎች ወደሚመላለሱበት መስመሮች የየብስ ትራንስፖርት ዘርፍ ወሳኝነት አያጠያይቅም።

ርግጥ ሀገራችን ልትጠቀምባቸው ከምትችለው ዋና ዋና ወደቦች ጋር የሚያገናኝ የባቡር መስመር ያስፈልገናል፤ በአገር ውስጥም ዋነኛ የትራስፖርት ኮሪደሮችን የሚያገናኝ የባቡር መስመር እንደሚያስፈልገን ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው።

እንደሚታወቀው ቀደም ባሉት ጊዜያት ለባቡር ትራንስፖርት በቂ ትኩረት ስላልተሰጠውና የሚፈልገውም ወጪ እጅግ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ፋይዳ ያለው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ዛሬ ላይ ደርሰናል። ይሁንና መንግስት ይህንን ሁኔታ ለመቀየር አቅም በፈቀደ መጠን በርካታ ስራዎችን እየከወነ ይገኛል።

እርግጥ አሁን በምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ የመንገድ ትራንስፖርትንና የባቡር ትራንስፖርትን በማቀናጀት ፈጣንና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ የትራንስፖርት ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባን አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም። ይህን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ የሚረዳው የኢፌዴሪ መንግስትም ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ልማት የበለጠ ማረጋገጥ የሚያስችለውን የየብስ ትራንስፖርት ስርዓት ገንብቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ይህ ዘርፍ ለሀገራችን ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግር ልምድ እየተኘበት የሚገኘው የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር መስመር አንዱ ማሳያ ነው።

የዘርፉ ጠቀሜታ ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ የትራፊክ መጨናነቅ ከመቀነስ አንጻር የሚጫወተው ሚና የላቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሰዎችን በፍጥነት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ማስቻሉም እንዲሁ፡፡ ባቡር በርካታ ስዎችን በአንዴ ከቦታ ቦታ ስለሚያንቀሳቀስ ጊዜንና ወጪን ከመቆጠብ አኳያም ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

የተለያዩ ዓለምና አህጉር አቀፍ ተቋማት የሚገኙባትንና ስብሰባዎች የሚሄዱባትን የመዲናችንን ውበትና ዘመናዊነት በመጨመር ረገድም አስተዋፅኦው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያም እንዲሁ፡፡

የቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ በኤሌትሪክ የሚሰራ በመሆኑ ሀገራችን ለነዳጅ ታወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ለመቆጠብ እንዲሁም የአየር ብክለትን በመከላከል ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ በኩልም ጠቀሜታ አለው። በዚህም ሀገሪቱ በቀጣይ ለምታከናውናቸው መሰል ግንባታዎች የሀገራችን ሰራተኞች የሚቀስሙትን ዕውቀት ተጠቅመው ሙሉ በሙሉ የመስራት ችሎታቸውን ሊያዳብሩ ይችላሉ፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ የባቡር መስመር ዝርጋታ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማረጋገጥ አኳያ የላቀ ሚና ይጫወታል ሲባል፤ ሽግግሩ ሀገራችን ለወጠነቻቸው የልማት ፕሮግራሞች ማሳኪያ ምን ዓይነት ቴክኖሎጂ እንደሚያስፈልጋት ለይቶ መጠቀም ወሳኝነቱ አያጠያይቅም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም በቅድሚያ በሂደት መቅዳት፣ መላመድና ማሻሻል በስተመጨረሻም ቴክኖሎጂውን በማመንጨት የሚጠበቁ ተግባራት መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል፡፡

እርግጥ የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ ለመረዳት እንደሚቻለው የጎንዮሽና የቀጥታ የቴክኖሎጂ ማሸጋገርያ መንገዶች አሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያን በመሰሉ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ሊከተሉት የሚገባው አካሄድ፤ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካስመዘገቡት ሀገራት ልምድ በመቅሰም የሚከናወነው የልማት ስራ የተሻለ ውጤት ያስገኛል።

እናም ፈጣን ለውጥ ለማምጣት መሰረታዊ የሚባለው የጎንዮሽ የቴክኖሎጂ ሽግግር በብዙ መንገዶች ሊገኝ ይችላል፡፡ የባቡር ዝርጋታ ፕሮጀክት ነው ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ እየዋለ የሀገሪቱ ባለሙያዎች ትምህርት ይቀስማሉ፡፡

ለወደፊትም መሰል ፕሮጀክቶች በሀገራችን ሲገነቡ በእኛው መሃንዲሶች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ይታመናል፡፡ ስለሆነም ሀገራችን ላለፉት 10 ዓመታት በተከታታይ ያስመዘገበችው የአስራ አንድ በመቶ አማካይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሀገሪቱ በ2025 ልትደርስበት ያሰበችውን የመካከለኛ ገቢ ጎራ ካላቸው ሀገራት የመቀላቀል ዕድልን መደላድል እንደሚፈጥር ጥርጥር የለውም። በተለይም የሀገራችንን ከተሞች፣ ክልሎችንና አጎራባች ሀገሮችን የሚያስተሳስሩ መሰረተ ልማቶች ለዚህ ትልም ወሳኝ ሚና አላቸው።

በኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ በቴሌኮም፣ በመንገድ እና በባቡር መስመር ዝርጋታ እየተደረጉ ያሉ ሰፊ መሰረት ያላቸው የልማት ፕሮጀክቶች ያለ ምንም እንቅፋት እየተከናወኑ ናቸው። በተለይም በትራንስፖርት መሰረተ ልማት እንደ ባቡር ዓይነት በፍጥነት ግዙፍ የሆነን ሎጀስቲክካዊ አቅርቦት ወደ ተፈለገበት ቦታ የሚያደርስ ዘርፎችን እየገነባች መሆኗ አገልግሎቱ የወጭ ንግድን በመደገፍ ረገድ የሚጫወተው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን በኬንያ ባካሄዱት ጉብኝት ይህ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የትስስር ድር በስፋት ተነስቷል። በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና በኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መካከል የተካሄደው የሁለትዮሽ ውይይት፤ በኢኮኖሚያዊና ፀጥታ ጉዳዮች፣ በላሙ ወደብ ልማትና ኬንያ በየዓመቱ ከኢትዮጵያ ለመግዛት ባሰበችው 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ሽያጭ አተገባበር ላይም ምክክር ተደርጎባቸዋል።

መሪዎቹ ሁለቱን ሞያሌዎች (የኢትዮጵያና የኬንያ ሞያሌን ማለቴ ነው) የምስራቅ አፍሪካ የቢዝነስና ንግድ ማዕከል አድርጎ በጋራ ለማልማት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህም በሀገራቱ መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። ሀገራችን ከጂቡቲ፣ ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን ጋር የምታደርገው የኢኮኖሚ ትስስር ድር ለቀጣናው ሀገራት በአርአያነት የሚታይ ነው። ይህ የሀገራችን ጥንካሬ በሀገር ውስጥ በመሰረተ ልማት መስክ የተከናወኑት ስራዎች ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። ይህም ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የአብሮነት ድር መሰረት እንድትሆን አድርጓታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy