Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የአጋርነት ደረጃው

0 368

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአጋርነት ደረጃው

ገናናው በቀለ

በቅርቡ የቻይና ህዝባዊ ብሄራዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር ሊ ዛንሹ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል። ሊቀመንበሩ በጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት መክረዋል። በቻይና መንግሥት ድጋፍ የተገነቡ የተለያዩ መሰረተ ልማት አውታሮችንም ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ሊቀመንበር ሊ ዛንሹ ቻይና ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለንታዊ ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸው፣ በቻይና መንግሥትና ኮሚኒስት ፓርቲ እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግሥትና ገዥ ፓርቲ መካከል ያለውን አጋርነት የሚያረጋግጥ ይመስለኛል።

ሁለቱ አገራት በባቡር መስመር ዝርጋታ፣ በኢኮኖሚያዊ ልማት፣ በአዲሱ ቻይና በምትዘረጋው “ዋን ቤልት፣ ዋን ሮድ” መንገድ እና በሌሎች ልማታዊ ትስስሮሽ ከፍተኛ ቁርኝት መፍጠራቸው፤ የአገራቱ የአጋርነት ደረጃ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ይመስለኛል። በምዕራቡም ይሁን በምስራቁ ዓለም ምን ያህል ተፈላጊና አብረዋት ሊሰሩ የሚችሉ መሆኗንም የሚያስረዳ ይመስለኛል፤ የሊቀመንበር ሊ ዛንሹ ጉብኝት።

ምንም እንኳን አገራችን ለልማታችን እመርታ በዕድገታችን ላይ አንዲትም ጠጠር ከሚወረውር ማንኛውም ሀገር ጋር መስራት ቢኖርብንም፣ ከልማት ጉዳዩች አንፃር ከቻይና ጋር ያለን ግንኙነት ረብ ያለው ነው፤ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ።

 

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያና ቻይና በጋራ የስልጣኔ እሴቶች ላይ የተመሰረተና ረጅም ዕድሜን ያስቆጠረ ታሪካዊ ቁርኝት ያላቸው አላቸው። ሁለቱም ሀገራት ግንኙነታቸውን ሲያስቡ ጥናታዊ ስልጣኔያቸውንና ረጅም የታሪክ ባለቤትነታቸውን ከግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ ነው። ይሁንና የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸው የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1970 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ታዲያ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ግንኙነቶችን መመስረት ችለዋል።

 

በዚህም ዛሬ ለደረሱበት በጋራ ጥቅምና መከባበር ላይ ለተመሰረተው፣ አንዱ በሌላኛው ሀገር የውጥ ጉዳይ ጣልቃ ለማይገባበትና ሰላማዊ ትብብር ለጎለበተበት ከፍተኛ የሁለትዮሽ ትስስር መሰረት ጥለዋል ማለት ይቻላል።

 

ቻይና በእነዚህ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዓመታት ውስጥ እውነተኛ እና ሊተማመኑባት የሚገባ ሀገር መሆኗን በተግባር አሳይታለች። በተለይም ሀገራችን ለምታደርገው የፀረ-ድህነት ትግል ወሳኝ ሚና ተጫውታለች፤ በመጫወትም ላይ ትገኛለች። ለዚህም ሁለቱ ሀገራት በአሁኑ ወቅት የደረሱበት የግንኙነት ደረጃና ጥንካሬ ህያው ምስክር ነው ማለት ይቻላል።

 

ከዚህ በተጨማሪም ሀገራቱ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ በየጊዜው የሚያደርጉት ግንኙነት እንዲሁም በተለያዩ ጠቃሚ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያደርጉት ውጤታማ ስምምነቶች የግንኙነቱን ጥንካሬና የሁለቱን ሀገራት የተፈላላጊነት ደረጃ የሚያሳዩ ናቸው።

 

ቻይና ፖታሽን በማልማት፣ የነዳጅ ዘይትን በማውጣት እንዲሁም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችን በማልማትና በማስተዳደር ረገድ ከሀገራችን ጋር ተባብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳለት በተደጋጋሚ በመግለፅ ከሀገራችን ጋር እየሰራች ነው። ኢትዮጵያ የምዕራቡን ዓለም ብቻ ሳይሆን፣ የምስራቁን ልዕለ-ኃያል የኢኮኖሚ ሀገርንም ጭምር ምን ያህል ቀልብ የሳበች ሀገር መሆኗን የሚያመላክት መሆኑ ከማንም የሚሰወር ዕውነታ አይመስለኝም።

 

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በመሰረተ-ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በህዝብ-ለህዝብ ግንኙነቶች በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደደርሳለች። ይህም አገሪቱ ሀገራችን ጋር ያላት ትብብር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመረኮዘ ነው ማለት ይቻላል።

በተለይም እ.ኤ.አ ከ2015 እስከ 2024 የሚቆየውና በኢትዮጵያ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትርና በቻይና በንግድ ሚኒስትር መካከል የተፈረመው የአስር አመቱ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ፣ የድሬዳዋ-ደወሌ የባቡር መስመር ዝርጋታን ብድር መልቀቅ፣ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካን የመደገፍ እንዲሁም ከወለድ ነፃ የሆነ ከ150 ሚሊዮን ብር ስምምነት መደረጉን እናስታውሳለን።

 

እንዲሁም እ.ኤ.አ ከ2014 እስከ 2017 የሚቆይ የባህል ትብብር ማካሄጃ ፕሮግራም፣ በሲቪል አና በንግድ ጉዳዩች ላይ የሚያተኩሩ የጋራ የህግ መደጋገፍ፣ የኢትዮ-ቻይና የኢኮኖሚና የንግድ ትብብር ዞኖች፣ አራት የቻይና ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ኢትዮጵያ ውስጥ ማቋቋም እና ሌሎች በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ጉዳዮች ናቸው።

 

ታዲያ እነዚህን ጉዳዩች ስንመለከት አንድ መዘንጋት የሌለብን ሃቅ አለ። ይኸውም ሀገራችን ከቻይና ጋር የምታናውናቸው ተግባራት ሀገሪቱ የዓለምን ኢኮኖሚ በሁለተኛ ደረጃ የምትመራ ከመሆኑም በላይ፣ በፖለቲካውም ረገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያላት መሆኑን ነው።

 

እናም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር የሚኖራት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የሁለትዮሽ ግንኙነት የማዕዘን ድንጋይ ነው ማለት ይቻላል። እርግጥ የትኛውም ሀገር በራሱ የውስጥ ዕምቅ አቅም መተማመንና ይህንንም አጎልብቶ ማደግ ያለበት መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ከራሱ አቅም ውጭ የሆነን ነገር ከሌሎች ጋር ተባብሮ መስራት የግድ ይለዋል። በተለይም አሁን ባለንበት በዘመነ-ሉላዊነት አንድ ሀገር ብቻውን ምንም ሊያደርግ አይችልም።

 

‘ብቻዬን ከሌላው የዓለም ክፍል ተለይቼ እኖራለሁ’ የሚባልበት ዘመን አክትሟል። ዛሬ ዓለማችን ወደ አንድ ትንሽ መንደርነት በመቀየሯም አንዱ የሌለውን ነገር በቀላሉ ከሌላኛው ማግኘት ስለሚችል የግንኙነቶቹ ጥልቀት ያን ያህል የተንሰላሰለ ነው ማለት ይቻላል። እናም የአሜሪካም ከቻይና ግንኙነት ሀገራችን ምን ያህል ተመራጭ መሆኗን ለመገንብ አይከብድም።

 

እንደ ቻይና ያሉ የዓለም ሀገራት ለምን እንደሚመርጡንና በተለይም በኢንቨስትመንትና በንግድ ረገድ አብረውን ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት በሌሎች አብነታዊ ምሳሌዎችም መመልከት ይቻላል። እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የሀገራችንን ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተጠቅመው መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ላይ የሚገኙት የቱርክ፣ የህንድ፣ የአውሮፓ፣ የአረብ ሀገሮች ትልልቅ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች አሉ።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ፣ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማመቻቸት በሩን ከፍት በማድረግና በተለያዩ አለም አቀፋዊ መድረኮች ተጨባጭ ሁኔታውን በማስረዳት በርካታ ባለሃብቶችን በመሳብ ላይ ነው፡፡

ቻይናም የዚህ ተግባራችን ውጤት ናት፡፡ ሊቀመንበር ሊ ዛንሹ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ ለመስራትና የኢትዮጵያን ልማት ለመደገፍ ቁርጠኛ አቋም መያዟን ማረጋገጣቸው የአገራችንን ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ፣ ለኢንቨስትመንት አመቺነት፣ በቀጣናው፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት አቅም በሚገባ ስለተገነዘቡ ይመስለኛል፡፡ በዚህም ሳቢያ የቻይና የአጋርነት ደረጃ ለልማታችን ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy