የኢህአዴግ መንሸራተት ጅማሬ እና የግብረሶዶማውያን ባንዴራ በአዲስ አበባ የመውለብለቡ አንደምታ
ከመክብብ
ልባም እና አስተዋይ ህዝቦች ምንጊዜም ብሄራዊ ክብራቸውን እና ጥቅማቸውን ያስጠበቁ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡
ለውጥ ምንግዜም አስፈላጊ ነው፡፡ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን እንግታው ብንል እንኳ የማይቻለን የስነ ፍጥረት እውነታዊ ሃቅ ነው፡፡ የምንችለው ነገር ይሄን ለውጥ ቅርፅ እያስያዙ ጠቅላላ ውጤቱ ጠቃሚ ሆኖ እንዲያልፍ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ለውጥ የማይቀር ሃልዮት እና እንደ ሰው ሊኖረን የሚችለው አስተዋፅዖ በጎ እና ጠቃሚ ሆኖ እንዲወጣ ማድረግ ብቻ መሆኑ ልናሰምርበት ይገባል፡፡
ይህንን ፅሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ በ06/05/2018 በብሉምበርግ (Bloomberg) ላይ “New challenge of Ethiopian leaders: unleashing the Economy” በሚል ርዕስ የወጣው ፅሁፍ ነው፡፡ ፀሀፊውም የቀድሞውን የሀገራችንን ጠቅላይ ሚኒስትር ጠቅሶ አስነብቦናል፡፡ ባልሳሳት ስልጣን ባስረከቡ ማግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጪ ሚዲያ የሰጡት ቃለ መጠይቅ ነው፡፡
ባጭሩ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በፅሁፉ እንዲህ ብለዋል
“የኢትዮጲያን ኢኮኖሚ በከፊል ሊበራላይዝ ለማድረግ ባለፈው አመት ለኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸውንና በዚህም የአብዛኛውን ይሁንታ ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሂደቱን በማስቀጠል አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከፍፃሜ እንደሚያደርሱት እንደሚተማመኑ ገልፀዋል፡፡”
ግልፅ ለማድረግ ከዚህ በፊት በህዝብ እና ለሀገሪቱ ዜጎች ብቻ በህግ ተፈቀደው ለውጭ ዜጎች እና ኩባንያዎች በፍፁም የተከለከሉ ዘርፎች ከአሁን በሗላ በከፊል ክፍት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት እስካሁን በቀላሉ እስካሁን ለውጭ ኩባንያዎች እና ዜጎች ክልክል የነበሩት እንደ ኢትዮጲያ አየር መንገድ፣ የፋይናንስ ዘርፍ፣ ኢትዮ ቴሌኮም እና የመሳሰሉት የውጭ ኩባንያዎች እንዲሳተፉ ወይም እስካሁን የግለሰብ ሳይሆን የህዝብ ንብረት ሆነው የቆዩት እንድ የኢትዮጲያ አየር መንገድ አይነቶቹ ለሽያጭ ቀርበው ለውጭ ኩባንያዎች በተለይ ለምዕራባውያኑ የባለቤትነት መብቱ ይዞራል ማለት ነው፡፡
እኔም እንደአንድ ዜጋ በእሳቤውና ሂደቱ ላይ ያለኝን ተቃውሞ እና ተዓቅቦ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
ሀገራችን ኢትዮጲያ እንደ ጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤትነቷ እና እንደ የጥቁር ህዝቦች ዋካንዳ እንደመሆኗ እሴታችንን እና ማንነታችንን የሚያሳይ ከራሷ አልፎ ለጥቁር ህዝቦች ብሎም ለሰፊው የአለም ህዝብ የሚበጅ ሪዕዮተ አለም ብታመነጭ የሚለው እሳቤዬ የዘወትር ምኞቴ ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ይህ እንደማይሆን እና የሗለኞቹን ሃያላት ተፅዕኖ የምንቋቋምበት ብልሃት እንዳለቀብን ተገንዝቤያለሁ፡፡
ሀገራችን ባለፉት አመታት ያለፈችበትን የፖለቲካ ቀውስ እና የምዕራባውያንን ባህሪ በጥቂቱ እንመልከት፡፡
ሪዕዮተ አለም ልክ እንደ ሃይማኖት ነው፡፡ አራማጁ የትኛውም ጥግ በመራመድ ማስፋፋት እና እንዲተገበር ለማድረግ ማንኛውንም ጥረት ያደርጋል፡፡ በሶሪያ ያለውን የውክልና ጦርነት ማንሳት በቂ ነው፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲን ለመተግበር ማንኛውም ዋጋ ቢከፈል ደንታ ሳይሰጣቸው በነሱ ተፀንሶ በነሱ ተወልዶ በራሳቸው ጭምር ውጤታማነቱ ጥያቄ ውስጥ እየገባ ያለውን ይህን ዕሳቤ በማንኛውም ዋጋ ሊያስፋፉ ይተጋሉ፡፡ ልክ እንደሃይማኖት ለሪዕዮተ አለምም የራሱ ሰባኪ የራሱ አስፈፃሚ እና የራሱ አማኝ አለው፡፡ ዋናው ጥያቄ በማመናችን የምናገኘው ጥቅምና ጉዳት ላይ ነው፡፡
አሁን ባለንበት እድገት ደረጃ ማንን ነው የሚጠቅመው? ሰፊውን ህዝብ ነው ወይስ የተወሰኑ አለምአቀፍ ሃያል ቡድኖችን?
አሜሪካም ሆነ ምዕራብ አውሮፓ ከ700 ባልበለጡ ግዙፍ ኩፓንያዎች ምርት እና ሽያጭ የሚተዳደሩ ሃገራት ናቸው፡፡ እነዚህም ኩባንያዎች ከመንግስታት በላይ አቅም ያላቸው እንዲያውም መንግስታትን በቁጥጥር ስር አውለው እንዳሻቸው የሚዘውሩ ናቸው፡፡ የነዚህ ኩባንያዎች እይታም ሆነ ምዘናቸው ከሚያገኙት ኢኮኖሚያዊ ትርፍ እና ያልተገባ ባህላቸውን ከማስፋፋት አንፃር ነው፡፡ ለዚህም እጅግ በርካታ አለማዊ ምሳሌዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡
ነገር ግን ጨቋኝነታቸው እና አምባገነንነታቸው እንዳለ ሆኖ የምዕራባውያን ኩባንያዎችን እና ተገቢ ያልሆኑ ዕሴቶቻቸውን አንቀበልም ብለው የነዳጅ ሀብታቸውን ሆነ አሉታዊ የባህል ወረራቸው ላይ በራቸው በመጠርቀማቸው የገጠማቸውን የ2 ሀገሮች እጣ ፈንታ ማንሳቱ በቂ ነው፡፡ በኢራቅ የሳዳም ሁሴን በስቅላት መቀጣት፣ በሊቢያ የጋዳፊ እንደውሻ መገደል እና ህዝቦቻቸው ሆነ ሀገራቱ ያለሰብሳቢ መቅረታቸው በቂ ማሳያ ነው፡፡ ህዝቡ ማባሪያ በሌለው ስቃይ ውስጥ እንዲወድቅ ፈርደውበታል፡፡ ይሄ ግን ለምዕራባውያኑ ደንታቸውም አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ነዳጁን እየጫኑ ጦር መሳሪያቸውን ደግሞ እየቸበቸቡ ነውና፡፡
ስለነሱ ይህን ያህል ካልን እኛን ወደሚያዩበት መንግድ እንምጣ፡፡
እኛ ለምዕራባዊያን የራሳቸው ሊያደርጉን የሚጎመጁልን ሃገር ነን፡፡ ከላይ እንደገለፅኩት ህዝብን በሰባዕዊ መነፅር ሳይሆን በትርፍ እና ኪሳራ የሚመዝኑት ምዕራባያን የኢትዮጲያ የ100 ሚሊዮን ህዝብ ባለቤትነት እና ገና ያልተነካ የተፈጥሮ ሃብቷ ሲያልሙ ውለው ሲያልሙ የሚያድሩ እና ህልማቸውንም እውን ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ይታወቃል፡፡ በአጭሩ አንድ የራበው ሰው መብላት ከመጀመሩ በፊት ከፊቱ የቀረበለትን ክትፎ የሚያይበትን መንግድ ነው ሃገራችንን የሚመለከቱት፡፡
የገነቧቸው ተቋሞች (ሚዲያዎቻቸው፣ የገንዘብ ተቋሞቻቸው ወዘተ) በተቀናጀ መልኩ ህልማቸውን እውን ለማድረግ እስከዛሬዋ እለት እየሰሩ እንደሆነ ሁላችንም እንገነዘባለን፡፡
አቶ ሃይለማሪያም መግለጫ የሰጡበት ብሉምበርግ የተባለው ሚዲያ የዚሁ የምዕራባውያን የቅንጅት ስራ አንድ ሰበዝ መሆኑ ልብ ይሏል፡፡
ባለፉት አመታት በሃገራችን የተነሳውን ፖለቲካዊ ቀውስ ከወትሮው በተለየ የምዕራባውያንን ሚዲያዎች የአየር ሽፋን ያገኘ አልነበረም፡፡ ይነሱ በነበሩት ሁከቶች በዜጎች ህይወት ላይና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ የነበረ ቢሆንም እነዚህ ሚዲያዎች እንዳላዩ ሆነው ማለፍ ነበር የመረጡት፡፡ ይሄም ብቻ ሳይሆን የመንግስትን አካሄድ ለወትሮው ለመኮነን የሚፈጥኑት የምዕራቡ መንግስታት ዝምታን መርጠው ነበር ያለፉት፡፡መግለጫ ያወጡትም ቢሆን የነበረውን እውነታ የማይገልፅ እና አላወጡም እንዳይባሉ የወጡ መግለጫዎች ነበሩ፡፡ ሚዛናዊነት በጎደላቸው ዘገባዎቹ ከሚታወቀው ቪኦኤ የአማርኛው ክፍል በስተቀር በጉዳዩ ላይ ተኩረት ሰጥቶ የዘገበ አንድ የምዕራቡ አለም ሚዲያ አልነበረም፡፡
ይህ ደግሞ ምርጫ 97ን ተከትሎ በተከሰተው ረብሻና የዜጎች ሂወት መጥፋት ወቅት ምዕራባውያን መንግስታት እና ተቋማት የነበራቸው ሚና ጋር በእጅጉ የተቃረነና ፈፅሞ የማይገናኝ መሆኑን ልብ ብለን ያለፍነው ሂደት ነው፡፡
በወቅቱም ይህን ዝምታቸውን በጥርጣሬ የተመለከትነው ኢትዮጲያውያን ቀላል አልነበርንም፡፡ እንኳን እንዲህ አይነት ጮማ ወሬ አግኝተው ይቅር እና ተንሽ ክስተትን አጋነው እና አጉነው አላማቸውን ለማሳካት የሚጥሩት ምዕራባውያን ኢህአዴግ የሚመራው መንግስትና እንደፈለጉ እንዳይሆኑ ገድቧቸው የቆየ መንግስት ላይ እንዴት ዝምታን መረጡ የሚለው ነግር አጠያያቂ ነበር፡፡
ታዲያ በስትመጨረሻ የተገኘው መላምት የሚከተለው ነበር፡፡
ኢህአዴግ ከምዕራባውያኑ ጋር የሚስጥር ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡ ይህም ስምምነት ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት አሁን ያለበትን ፖለቲካዊ ቀውስ ይውጣው እንጂ ሰፊውን የኢትዮጲያ ገቢያ ለነሱ ፍላጎት ክፍት እንደሚያደርግ እና ገዳቢ ፖሊሲዎቹን እና ህጎቹንም እንደሚቀይር፣ እነሱም በምላሹ ይህንን እንዳያራጋቡ እና በፖለቲካ ፍልሚያው እጃቸውን እንዳያስገቡ (ልክ እንደ97ቱ) የሚል ነበር፡፡
መራር ቢሆንም ሊቀመጥ የሚችለው መላምት ከዚህ የዘለለ ሊሆን አይችልም፡፡
በኢህአዴግ ቤት ውስጥ በከፍተኛ አመራር ደረጃ በሊበራል ሃይሎች የተጠለፈ ወይም ሰርጎ የገባ አሊያም ደግሞ የከለሰ እንዳለ ለመረዳት ጊዜ የሚወስድ አልነበረም፡፡ ምስጋና አቶ ሃይለማሪያም ለብሉምበርግ ለሰጡት ቃለመጠይቅ ይሁንና የዚህ የመከለስ ወይም የኑፋቄ ቁንጮ እሳቸው መሆናቸውን ለመገንዘብ ችለናል፡፡
እዚህ ጋር በአንድ ወቅት እኙሁ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ታንዛኒያን በጎበኙበት ወቅት በታንዛንያው ፕሬዝዳን ጆን ሙጉፉሊ የተባለውን ንግግር አንደምታ ከመቼው ሊረሱት እንደቻሉ እግረ መንገዴን መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡
ጆን ሙጉፉሊ በኢትዮጲያ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ያላቸውን አድናቆት ገልፀው እና የኢትዮጲያ አየር መንገድ ቴሌኮም እና የሃይል ዘርፍ በህዝብ ቁጥጥር መሆኑ እና ከስኬታችንም ብዙ መማር እንደሚፈልጉ ለኚሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ገልፀውላቸው ነበር፡፡
ለኔ እስከሚገባኝ ጆን ሙጉፉሊ መግልጫ በተዘዋዋሪ እኛን ሊበራሊዝም ለህዝባችን ጥቅም እንዳንሰራ ቀፍድዶ ይዞናል እናንተ ግን የምርጫ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከውጭ የሚጫን ሃይል የለባችሁም የሚል ነበረ፡፡ ይሄን ንግግር እንኳን አቶ ሃይለማሪያም ይቅርና ማንም ሊረሳው የማይችል ንግግር ነው፡፡
የሆነ ሆኖ ኢህአዴግ እስካሁን እንዳደንቀው ያስገድደኝ ከነበሩ ነገሮች አንዱ ይህን የምዕራባውያንን የድህረ ቅኝ ግዛት ተስፋፊነታቸውን ተቋቁሞ መቆየቱ ነበር፡፡ እነሆ ይህቺም የምትሄድበት ቀን ሩቅ አንደማይሆን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቃለመጠይቅ ለመረዳት ችለናል፡፡ አዲሱ ጠቅላያችን ምን ያህል እንደሚስማሙበት ባናውቅም፡፡
እስካሁን ማረጋገጥ የቻልነው እውንታ ግን የከለሰ ወይም ሪዕዮተ አለሙን በመተው ኑፋቄን እየተለማመደ ያለ በመንግስት ውስጥ ማገንገኑን ነው፡፡
ይህ ማለት ደግሞ አሁን ያለንበትን የህብረተሰብ እና የኢኮኖሚ እድገት ደረጃ ከመጤፍ ሳይቆጥር ሀገሪቷን ለመሸጥ እና ምናባዊ ልዐላዊነቷን ለማሳጣት እየተጋ ያለ ሃይል ኢህአዴግ ውስጥ የበላይነቱን እየያዘ መጥቷል፡፡ ይህንንም ሀገር የመሸጥ ሃሳብ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው ስራ አስፈፃሚ እንደተቀበለው በቃለ መጠይቃቸው ነግረውናል፡፡
አሁን በሚከተለው ሪዕዮተ አለም ሌብነትን ባግባቡ ሌብነት መቆጣጠር ያልቻለ መንግስት እንደኛ ባልዳበረ ኢኮኖሚ እና ህብረተሰብ የበለጠ ሌብነት የሚያንሰራፋውን የሚያቀጣጥለውን የሃብታሞች ዕሳቤን ለመከወን ማሰብ ለኔ የክህደቶች ሁሉ ክህደት ነው፡፡
ህዝብን ንብረቱን ሸጦ የበዪ ተመልካች በማድረግ የሚያገኙት ለልጅ ልጆቻቸው የሚተርፍ ቢሊዮን ዶላሮች እያለሙ ያሉ ካህዲዎች በኢህአዴግ ቤት ይታዩኛል፡፡
የህዝብ የልማት ተቋማትን በመሸጥ እና መሬትን የግል ይዞታ ብሎ በማወጅ ምን አይነት ሃገራዊ እድገት እና ብልፅግና ለማስመስገብ እንደተፈለገ ለማንም ግልጥ አይደለም፡፡
ሰዎች እጅ ሰጥተናል፡፡ የሄ በጣሊያን እንደመሸነፍ የውርደቶች ሁሉ ውርደት ነው፡፡ ምናልባት እነዚህ ሰዎች ይህን አላማቸውን ከፈፀሙ በሗላ የአድዋ ድልን ማክበር ማቆም ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለምን ቢባል ከዛ በባሰ ቅኝ ግዛት እንድንገባ ያሁኖቹ ሰዎች እየዳዳቸው ነውና፡፡
ምዕራባዊያኑ ግን አሸናፊነታቸውን እየነገሩን ይገኛል፡፡ በአውሮፓ ህብረት፣ በዴንማርክ እና በኖርዌይ ኤምባሲዎች ላይ የግብረሰዶማውያንን ባንዴራ በመስቀል መጪው ግዜ ከነሱ ጋር እንደሆነ ጠቁመውናል፡፡ ነገም ይቀጥላሉ
ለማንኛውም ነሐሴ ላይ የሚደረገው የኢህአዴግ ስብሰባ ሁሉንም ነገሮች ይነግረናል፡፡
እኔ ግን እላለሁ
እውን የኢህአዴግ እንሽርት ይቆማል
ወይስ የሶዶማውያን ባንዴራ ተሰቅሎ ይቀራል?
ቻው