‘…የእኔ ናት’
ታዬ ከበደ
ግንቦት 20 የድል በዓል የመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የትግል ውጤት ነው። ይህን ትግል መርቶ ለድል በማብቃት ረገድ ኢህአዴግ የመሪነቱን ሚና ተጫውቷል። ድሉ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ከመሠረቱ በመቀየር ሁሉንም ህዝቦች ተጠቃሚ ያደረገ ነው።
በድሉ አማካኝነት በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ መምጣቱ እንዲሁም አገራችን አሁን ለምትገኝበት የሰላም፣ የልማት የዴሞክራሲ እና የዲፕሎማሲ ዕድገት ከፍተኛ ደረጃ ልንደርስ ችለናል።
በግንቦት 20 ድል ምክንያት ሁሉም ህዝብ ‘ኢትዮጵያ የእኔ ናት’ ብሎ በኩራት የሚናገርላት አገር ተፈጥሯል። እንዲሁም ኢትዮጵያ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አገር መሆኗ ዕውቅና ማግኘት ችሏል። አስተማማኝ ሰላም ኖሯት የተፋጠነ የልማት ትግል እንድትጀምርና ሕዝቦቿ የተሻለ ተስፋ እንዲኖራቸው ያደረገ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት የፈጠረ የድል በዓልም ነው፤ የዛሬ 27 ዓመት እውን የሆነው ግንቦት 20።
ባለፉት ሥርዓቶች መላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተነፍገው ከነበሩ መብቶቻቸው መካከል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አንዱ ነው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በተባበሩት መንግስታት ቻርተርና በሌሎች ዓለም አቀፍ ዶክመንቶች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ዕውቅና እግኝቶ የነበረ ቢሆንም ያለፉት የኢትዮጵያ ገዢ መደቦች ይህንን መብት አፍነውት ኖረዋል፡፡
በመሆኑም በተለይም ተገልለውና ተረስተው የነበሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርም ሆነ ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ሆነው በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በእኩልነት የመሳተፍ መብት አልነበራቸውም፡፡
በአካባቢያቸው አስተዳደር ውስጥ በአመራር ላይ የሚቀመጡ አስተዳደሮችና ዳኞች በማዕከላዊ መንግስት የሚሾሙ ነበሩ፡፡ የመንግስት ሠራተኞችን ሁኔታ ብንመለከት እንኳ ሙሉ በሙሉ የሌላ አካባቢ ተወላጆች ነበሩ፡፡
የአካባቢው ተወላጆች እንኳንስ መሾም ይቅርና በሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ውስጥ የመካተት ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታ ግመል በመርፌ ቀዳዳ የመሽሎክ ያህል አስቸጋሪ ነበር፡፡ በመሆኑም እነዚህ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር መብት ተነፍጓቸው በሌሎች እየተተዳደሩ፤ ሀብታቸውም እተየመዘበረ ሊኖሩ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡
የየራሳቸውን አኩሪ ባህልና ቋንቋ የሚጠቀሙበትና የሚያበለጽጉበት ዕድል ተነፍጓቸውም ኖረዋል፡፡ ባለፉት ሥርዓቶች የአብዛኛዎቹ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ቋንቋና ባህል የሀገሪቱ ቋንቋና ባህል ተደርገው ከመቆጠር ይልቅ፤ ገሚሶቹ “ብረት ሰባሪ…ወዘተ” እየተባሉ የሚጠሩ ነበሩ፡፡ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቋንቋቸው የመዳኘት፣ የመማር ወዘተ. መብት አልነበራቸውም።
አብዛኛው ቋንቋዎችን እንኳንስ በአደባባይ ለመጠቀምና ስራ ላይ ለማዋል ይቅርና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ለመጠቀም እጅግ የሚያሸማቅቅ ሁኔታ እንደነበረም አይዘነጋም፡፡ ባህላቸውን የመግለጽ፣ የማዳበር እንዲሁም የማስፋፋት መብታቸው የተነፈገ እንደነበርም የኋላ ታሪካችን ያስረዳል፡፡
ያለፉት ሥርዓቶች መለያ ባህሪይ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የሰብዓዊ መብቶች አለመከበር ነው፡፡ የአካል ደህንነት፣ በህይወት የመኖር መብት፣ ክብርን ከሚያዋርዱ አያያዞች የመጠበቅ ወዘተ. የሚጣስባቸው ነበሩ፡፡
ከዚህም አለፎ ኢ- ሰብዓዊ ለሆነ እስር መዳረግ፣ እገታ ወዘተ. ወንጀሎች የሚፈጸምባቸው በመሆኑ ዜጎች ለከፋ ስቃይና ስደት ሲዳረጉ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩል ሆነው የሚታዩበት ሁኔታዎች ያልነበረባቸው መሆናቸውን የኋላ ታሪካችን ያመለክታል፡፡
ከላይ ለማሳያነት ከተገለጹት ጉዳዩች ባሻገር በሌሎች መብቶች ላይም ከፍተኛ አፈና ሲካሄድላቸው የቆየበት ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ግን የደርግ ሥርዓት በመላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መራር ትግል ዳግም ላይመለስ ሥርዓተ- ቀብሩ በተፈጸመ ማግስት ሊወገዱና የመላው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ ለሙሉ ሊከበሩ በቅተዋል፡፡
ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ ተወያይተው ያጸደቁት ህገ መንግሥት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን፣ በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት፣ በቋንቋ የመጠቀምና የማሳደግ ፣ባህልን የመግለጽ፣ ማዳበርና ማስፋፋት እንዲሁም ታሪክን የመጠበቅ እና ሌሎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለገደብ አረጋግጧል፡፡
ከላይ በውስን ደረጃም ቢሆን ባለፉት ሥርዓቶች የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲጨፈለቁ የነበሩባቸው መሆኑን ለመመልከት ተችሏል፡፡
ይህን ሁኔታ ግን መላው ህዝቦች በመስዋእትነታቸው እውን ባደረጉት የኢፌዴሪ ህገ- መንግሥት ለዘመናት ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ለማግኘት የበቁበት ድልን ተጎናጽፈዋል፡፡ እርግጥ የትናንቷ ኢትዮጵያ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦቿ የሰቆቃ ምድር ነበረች፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ዜጎች ኑሯቸውን በቅጡ እንዳይገፉ የተቸገሩበት፣ ተስፋቸው ተሟጥጦ ግራ የተጋቡበት፣ መቋጫ በሌለው ጦርነት፣ ረሃብና ስደት የሚንገላቱበት አስከፊው ወቅት ዳግም ላይመለስ ተሰናብቷል፡፡
ዛሬ ዜጎች ለአዲስ ህይወት ማበብ ተስፋ ሰንቀው፣ በፀና ህብረት ላይ ቆመው፣ እጅ ለእጅ ተቆላልፈው ኑሮን ማጣጣም ይዘዋል፡፡ ንፁህ አየር መማግ፣ በሠላም ገብቶ መውጣት፣ በነፃነት መንቀሳቀስን ችለውበታል፡፡
ለዚህ መብቃት የተቻለው ደግሞ ግንቦት 20ን ለማምጣት በተከፈለው የህይወት መስዋዕትነት ነው፡፡ በውጤቱም በመላ አገሪቱ ሠላም ተገኝቷል፤ የልማት መስመር ተይዟል፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በፅኑ መሠረት ላይ ቆሟል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተለያዩ ገዥዎች ይደርስባቸው የነበረውን የሃይማኖትና የእምነት ጭቆናና መድሎ በማስወገድ በእኩልነትና በመቻቻል የመኖር ራዕያቸውን ለማሳካት ባካሄዱት ህዝባዊ ትግል አዲሲቷ ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ ችለዋል፡፡
ግንቦት 20 የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት የግልና የቡድን መብቶችን የሚያስከብር በመሆኑ የሃይማኖት ጉዳይ በዚሁ አግባብ ምላሽ ማግኘት ችሏል፡፡ እናም በህገ-መንግስቱ ስፍረው የሚገኙት ሦስቱ መርሆዎች ማለትም የእምነት ነጻነት፣ የሃይማኖት እኩልነትና የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ማደግና ማበብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ እመርታዎች የግንቦት 20 ውጤቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ‘ኢትዮጵያ የእኔ ናት’ በማለት እነዚህን የግንቦት 20ን ድሎች ልንንከባከባቸው ይገባል፡፡