Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የወቅቱን የወጣቶች ጥያቄ በወቅቱ

0 603

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የወቅቱን የወጣቶች ጥያቄ በወቅቱ

ስሜነህ

የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተነድፎ ወደ ተግባር ሲገባ የተለያዩ መነሻዎች የነበሩት ቢሆንም ዋናው አጀንዳ ግን ተከታታይነት ባለው ሁኔታ መመዝገብ የጀመረውን የግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገትም ሆነ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቱን በማስቀጠል የአርሶ አደሩን ብሎም የመላውን ህዝብ ተጠቃሚነት ወደላቀ ደረጃ ማሻጋገር መሆኑ ይታወቃል፡፡

ዛሬ ከዝናብ ጥገኝነት በመውጣት ላይ የሚገኘውና መስኖን መሰረት ባደረገው የግብርና ስራ ኢትዮጵያ በግብርና ምርቶች በዓይነት፣ በጥራት እና በመጠን ተወዳዳሪ ሆና በዓለም የግብርና ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲኖራት በማስቻል ውጤታማ  ሂደት ላይ የሚገኝ መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለዓለም ገበያ በመጠንና በጥራት ተወዳዳሪ ሆና የውጭ ምንዛሬ ግኝቷን የምታሳድግበት አቅጣጫም እንደሚዘረጋ የሚገልጹት መረጃዎች፤ አርሶ አደሮች ገበያ ተኮር ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ ማስቻል፣ በእንስሳት ዘርፍ ያለውን የምርምር ስራዎች ማጠናከር እና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ሁለንተናዊ የግብርና ምርምር ስራዎች  እየተከናወነ ነው።

የግብርናው ዘርፍ ወደ ኢንደስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ዋነኛ ሞተር በመሆኑ የግብርና ልማቱን ለማገዝ ወቅታዊ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም እውቀቶችን መንግስት እያቀረበ ነው። ለጋራ ሀገራዊ የልማት ግብ ስኬትም የምርምር አቅምና ብቃትን ማሳደግ እና አዋጭ ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚዎች የማቅረብም ስራ እየተፋጠነ በመሆኑ   የሁለተኛውን ዙር ጉዞ ፈጣንና ውጤታማ እንደሚያደርገው መገመት አይከብድም።

የሁለተኛው ዙር እቅድ ዘመን ከተጀመረበት ማግስት ጀምሮ በመላው ሃገራችን የሚገኙ አርሶአደሮች በየጓሯቸው የሚገኙ   ቅጠላ ቅጠሎችን  እና ተረፈ ምርቶችን እንዲሁም ሌሎች በየአካባቢያቸው የሚገኙ ቁሳቁሶችን በመጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ምርትና ምርታማነታቸውን እጽፍ ድርብ ማድረስ መቻላቸው ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም ካስቻሉና የአርሶአደሩን ተነሳሽነት በከፍተኛ ደረጃ ካሳደጉ ምክንያቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ጉዳዩ አሁን ይህ እንቅስቃሴ እንዳይቋረጥ የሚያስችሉ መንገዶችን መከተል ነው። ከነዚህም መካከል አሁን ያለንበት ወቅት የመኸር ዝግጅት የሚደረግበት እንደመሆኑ ከፍተኛ ትጋት የሚጠይቅ መሆኑን መረዳት የመጀመሪያው ነው። በዚህ ሂደት ደግሞ ወጣቶችን ማስተሳሰር ወቅቱ የሚጠይቀን የግብርና ስራዎች ቅኝት ነው።

በዚህና መሰል በሆኑ የግብና እንቅስቃሴዎች የሚገኙ ውጤቶችን መነሻ በማድረግ የገጠር ወጣቶችን በግብርና ማቀነባበሪያው ዘርፍ  በስፋት ማሳተፍ ከተቻለ በእቅድ ዘመኑ ሃገሪቱ የጣለችው አጠቃላይ የልማት ግብ መነሻና መድረሻውም ይኸው ስለሆነ የሃገሪቱ ህዳሴ በማይነቃነቅ አለት ላይ መሰረቱን የሚጥል ይሆናል፡፡

ዝናብ አጠርና እርጥበታማ በሆኑ አካባቢዎችም በተደጋጋሚ የሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎችን መከላከል የሚያስችል ስርአት መዘርጋቱ ሌላውና ስለደረስንበት አቅም ለማስላት አስረጅ ሆኖ ሊጠቀስ የሚገባው ነጥብ ነው ። ይህ ስርአት ልማታዊ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ነው። ባሳለፍነው አመት የተከሰተውን እና ያለብዙ የውጭ እርዳታ የተቋቋምነውን የድርቅ አደጋ ብናስታውስ እንኳ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች ባፈሩት ጥሪት የተፈጠረውን ችግር መቋቋም መቻላቸውን ነው።ይህም ተከስቶ በነበረው ድርቅ ሳቢያ ይፈጠር የነበረን ችግር መቋቋም የሚያስችል አቅም መገንባታችንን ያሳያል ።ከዚህ ስኬት በስተጀርባ ያለው ምስጢር  የህብረተሰቡ ሰፊና የተደረጃ ንቅናቄና ተሳትፎ ነው፡፡ በዚህ መኸርም ይኸው ንቅናቄ ተጠናክሮ እስከቀጠለ ድረስ ብቻ ነው የሁለተኛውን ዙር እቅድ በስኬት ማጠናቀቅ የሚቻለው። በእቅዱም የተመለከተው ይኸውና ይህ ብቻ ነው።

ቀጣዩ የትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ዘመን በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ላይ የተመሠረተ የግብርና ልማት በማፋጠን ይልቁንም እያንዳንዱ የምርት ዘመን ላይ መኸር ከበልግ ሳይለይ ወጥሮ መስራትን የሚጠይቅ ነው። ይህ ብቻ አይደለም  የተማሩ ወጣቶችን በማደራጀት በግብርና ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ በማድረግ፣ አገራዊ እና የተመረጡ የውጭ የግል ባለሃብቶች እንደየችሎታቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዲሳተፉ በማድረግ በሰብል፣ በአበባ፣በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፎች ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት የሚሰራበት የእቅድ ዘመን መሆኑም ተመልክቷል፡፡

በመሆኑም የአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሩ ግብርና አሁንም ዋናው የግብርና ዕድገት መሠረት ሆኖ እንዲቀጥልና የአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሩ ግብርና ፈጣን እድገት እንዲያረጋግጥ የማስፋት ስትራቴጂውን አሟልቶ መተግበር፣ የልማት ቀጠናዎችን መሠረት ያደረገ የግብርና ልማት መከተል እና ሌሎች በግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ችግሮችን መፍታት ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የወቅቱን የወጣቶች ጥያቄ በተሟላ መልኩ መመለስ የሚቻለውም በዚህና ግብርናን መሰረት ባደረገው የገጠር ስራዎች ብቻ ነው። በተመሳሳይ የግል ባለሀብቱ በግብርና ልማት ላይ የሚኖረው ድርሻ ከፍ እንዲል በማድረግ ሀገሪቱ ለያዘችው ልማትና ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት እንዲያግዝ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን በማጎልበት አስተማማኝ የግብርና ልማት ለማረጋገጥ እንዲቻል የግብርና ልማት ዕቅዶች በይዘትም በትግበራም ከአረንጓዴ ልማት ራዕይ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ማስቻል ከዚሁ ጋር የመስኖ ልማትን ማስፋፋት ሌሎች በእቅድ ዘመኑ የተያዙ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ስለሆነም የብዝሀ ህይወት ጥበቃን ከዚሁ ጋር አያይዞ  በማጠናከር የማህበረሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የተመለከተ የወቅቱ ጥያቄ በተሟላ መልኩ መመለስ ይቻላል።

የአርሶ አደሩን ገቢ በፍጥነት ለማሳደግ አርሶ አደሩ የላቀ ዋጋ ወዳላቸው ምርቶች ማምረት እንዲሸጋገር ማድረግና የግብርና ግብይትን በተቀላጠፈ አካሄድ ተግባራዊ ማድረግ፣ በገጠር ፈጣን ዕድገት የሚፈጥረውን ዕድል በመጠቀም የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በድርቅ የማይንገዳገድ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያስችላል፡፡

ለሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካትና መሠረታዊ አቅጣጫዎቹን ለመተግበር አስፈላጊ የሆኑ ስርዓቶችን አሟልቶ ማስኬድ እና ደረቅና ከፊል ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የኑሮ ማሻሻያና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ የሚያረጋግጡ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል።  

የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የግብርና ዘርፍ ዋና ዓላማ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ የግብርና ልማትን መሠረት ያደረገ በዘርፉ ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ዕድገት በማምጣት የህዝቡን ተጠቃሚነት በየደረጃው ማረጋገጥና በአጠቃላይ ኢኮኖሚውና በዘርፉ ደረጃ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻል ነው፡፡ በተጨማሪም የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ማሳደግና ለማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት ያለውን ወሳኝ ሚና መጫወት የሚያስችል የማምረት አቅም መገንባት ነው፡፡

በዘርፉ የሴቶችና የወጣቶችን እንዲሁም የዘርፉን ተዋናዮች በተደራጀ አግባብ በማሳተፍለልማቱ የሚጠበቅባቸውን እንዲያበረክቱና ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ የዘርፉ ዋና ዋና ዓላማዎች ናቸው፡፡ይህን ማሳካት የሚቻለው ደግሞ እራሳቸው ወጣቶችን እና ሴቶችን በማሳተፍ ብቻ ነው።

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የአርሶ-አደርና የአርብቶ-አደር ምርታማነትን ለማሳደግና የምርት ጥራት ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ በዘርፉ ትራንስፎርሜሽን እንዲያመጣ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል የሚባለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ከአነስተኛ አርሶ-አደር ማሳ በመኸር ወቅት የሚገኘውን የሰብል ምርት በ2007 ከነበረበት 270.3 ሚልዮን ኩንታል  2012 ላይ ወደ 406 ሚልዮን ኩንታል ለማሳደግ መታቀዱ ተመልክቷልና ነው፡፡

የዋና ዋና የሰብል ዓይነቶች ምርታማነትና ምርት ትንበያ ግቦችም በእቅዱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ የአገዳ ሰብል ምርታማነትን በመነሻ ዓመት (2007) ከነበረበት 29 ኩንታል በሄክታር በ2012 ወደ 42.64 ኩንታል በሄክታር በማሳደግ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርቱን በመነሻዉ ዓመት (2007) ከነበረበት 115 ሚሊዮን ኩንታል በ2012 ወደ 171.78 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ፣

የብርዕ ሰብል ምርታማነትን በመነሻዉ ዓመት (2007) ከነበረበት 21.1 ኩንታል በሄክታር በ2012 ወደ 31 ኩንታል በሄክታር በማሳደግ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርቱን በመነሻው ዓመት(2007) ከነበረበት 120.3 ሚሊዮን ኩንታል በ2012 ወደ 184.22 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ፣

በጥራጥሬ ሰብል ምርታማነት በመነሻዉ ዓመት(2007) ከነበረበት 17.2 ኩንታል በሄክታር በ2012 ወደ 23 ኩንታል በሄክታር በማሳደግ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርቱን በመነሻው ዓመት(2007) ከነበረበት 26.4 ሚለዮን ኩንታል በ2012 ወደ 38.75 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ፣

የቅባት ሰብል ምርታማነት በመነሻው ዓመት (2007) ከነበረበት 9 ኩንታል በሄክታር በ2012 ወደ 12.7 ኩንታል በሄክታር በማሳደግ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርቱን በመነሻዉ ዓመት (2007) ከነበረበት 7.5 ሚለዮን ኩንታል በ2012 ወደ 11.5 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ፣ እንደሆነ በእቅዱ ግብርናን የተመለከተው ክፍል በሚገባ ተመልክቷል።

የዋና ዋና ሰብሎችን ምርታማነትና ምርት የማሳደግ ዋናው ጉዳይ የአብዛኛውን አርሶ አደር የምርታማነት መጠን ምርጥ አርሶ አደሮች ከደረሱበት ደረጃ ማድረስ መሠረታዊ ግብ ነው፡፡ ይህም በዋና ዋና የምግብ ሰብሎች፣ የፋብሪካ ግብዓቶች እና የኤክስፖርት ሰብሎችን ያካትታል፡፡ ይህ መሠረታዊ ግብ እንደተጠበቀ ሆኖ በተከታታይ የሞዴል አርሶ-አደሮች ምርታማነት ደረጃ ላይ የደረሱ በርከት ያሉ አርሶ-አደሮች ያሉ በመሆኑ የግብርና ምርምር ተቋማትን አቅም በማጐልበትና በማበረታታት እነዚህ አርሶ-አደሮች ወደ ግብርና ምርምር ተቋማት የምርታማነት ደረጃ እንዲቀራረቡ ተጨማሪ ፓኬጆች በማዘጋጀት መረባረብ እንደሚገባ ያሳያል፡፡ይህ እንደሁለተኛ ግብ ሊወሰድ የሚገባው ተግባር ነው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተያዘው ግብ የግብርና ምርምር ተቋማት ለቀጣይ ምዕራፍ የግብርና ዕድገት ምንጭ የሚሆኑ ቴክኖሎጅዎችን በማዘጋጀት እንዲረባረቡ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ መስጠትና ማብቃት ይሆናል፡፡ ስለሆነም የዓለም አቀፍ ቤንች ማርኪንግ በማስቀመጥ የግብርና ምርምር ተቋሞች ወደዚሁ ደረጃ እንዲደርሱ መሥራት የሚገባ ይሆናል፡፡

ግብርናችን በቀጣይነት ያለማቋረጥ እያደገ በመምጣቱ ለአደጋ ተጋላጭነታችንና ድርቅን የመቋቋም አቅማችን እንደ ሀገር እየተገነባ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ አፈፃፀም ያለና አሁንም ለአየር ንብረት መዛባት ተጋላጭነት ያላቸው አካባቢዎች ያሉን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ጠንከር ያለ ድርቅ ቢከሰት አንኳን ችግሩን ተቋቁሞ የማለፍ አቅማችን እያደገ መጥቷል፡፡ዘንድሮ ደግሞ ሃገሪቱ በግጭትም ውስጥ ሆና ያስመዘገበችው የግብርና ውጤት ከቀደሙት የቅርብ አመታት ልቆ መገኘቱ ከግጭት የሚያጸዱ አሰራሮች ተዘርግተው ቢሆን ኖሮ የሚያስብሉና የልፋታችንን ያህል እንዳናገኝ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ በፍጥነት ማስወገድ እንዳለብን የሚያስገነዝቡ ናቸው።ስለሆነም ሰላማችንን ከማስጠበቅ ጀምሮ የወጣቱን ጥያቄ መመለስ የሚቻለው ወጣቱን ሁሉአቀፍ በሆነ መልክ በያንዳንዷ የግብርና ስራዎች ላይ በማሳተፍ ብቻ የመሆኑን እውነታ ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ማድረግ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy