Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የደም ውጤት ነው!

0 558

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የደም ውጤት ነው!

 

ወንድይራድ  ኃብተየስ

አንዳንድ ሰዎች የፌዴራል ስርዓታችን  አገራችንን ወደ ቀውስና ሁከት እንዳመራት አድርገው አስተያየት ሲሰጡ አደምጣለሁ፤ ተጽፎም አንብቤለሁ። ይሁንና ባለፉት  27 ዓመታት ይህ ያልተማከለ ስርዓት የአገራችን የስኬት እስትንፋስ እንደሆነም በርካቶች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ይህ ስርዓት አበቃላት፣ ልትፈርስ ነው፣ ህዝብች ሊተላለቁባት ነው፤ የተባለችን አገርን በሁለት እግሯ መቆም እንድትችል አድርጓል። አንዳንዶች ለፌዴራል ስርዓቱ የሚሰጡት አስተያየት አመክኖዊነት የሚጎድለው፤ በጥላቻ ላይ የተመሰረተ፣ የብዙሃኑን ጥቅም ታሳቢ የማያደርግ፣ የደም ውጤት መሆኑን የሚዘነጋ፣ የወቅቱን የዓለም ሁኔታ ከግንዛቤ ያላስገባ ሆኖ እናገኘዋለን።   

የአገራችን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ  አወቃቀር በዕውኑ ለቀውስ ዳርጓናልን? ስል ራሴን ሁሌም  እጠይቃለሁ። እኔ ይህ ስርዓት ለቀውስ ዳርጎናል የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ አንድም መነሻ ማግኘት አልቻልኩም። እውነት መነጋገር ለሁላችንም ይበጃል፤ ጥላቻ እውነታን ይደብቃል፤ ከጥላቻ ርቀን ሁኔታዎችን እንመርምር፤ ይህን ስርዓት ለማፍረስ መሞከር እንደእኔ እንደኔ  ራስን እንደማጠፋት እቆጥረዋለሁ። አሁን ላይ አህዳዊ ስርዓትን ማሰብ ለማንም የሚበጅ አካሄድ አይደለም። አህዳዊ ስርዓትም ዳግም ለኢትዮጵያ የሚበጃት አስተዳደር ይሆናል ማለት የሚዋጥ ነገር አይደለም፤ ይህን አይነት ነጻነት ተለምዶ እንደገና ወደኋላ መመለስ የሚሆን ነገር  አይመስለኝም። ከእንግዲህ አህዳዊ ስርዓትን ለኢትዮጵያ መመኘት የሚበጃት ነገር አይመስለኝም። ሂደቱም ወደኋላ የማይመለስ ፈረንጆቹ እንደሚሉት (irreversible) ዓይነት ነው። በዕርግጥ ይህን ዓይነት ውሳኔ የህዝብ ምርጫ ቢሆንም ህብረተሰቡ ወደ አህዳዊ አስተዳደር ለመመለስ ምርጫው የሆናል የሚል እምነት የለኝም።

እውነት እውነቱን እንነጋገር ከተባለ  አገራችን በታሪኳ አይታው የማታውቀው ስኬቶች የተመዘገቡት በዚህ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ  ስርዓት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያስተዋልናቸው ተግዳሮቶች የተፈጠሩት አገራችን ይህን አይነት አስተዳደራዊ መዋቅር ስለተከተለች አይደለም። ለዚህ በርካታ አስረጂዎችን  ማንሳት ይቻላል። ሲጀምር ይህ ስርዓት መንግስት በህዝቦች ላይ የጫነባቸው ስርዓት ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸው መክረውና ዘከረው ይሆነናል ይበጀናል ብለው ያጸደቁት ስርዓት ነው። ሁለተኛ ይህ ስርዓት አገሪቱን  25 ድፍን ዓመታትን በስኬት ጎዳና እንድንጓዝ ካደረገ ብኋላ መልሶ ወደ ለቀውስ ሊዳርጋት የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም። በዚህ ስርዓት ማንም የበላይ ሆነ የበታች የለም።

በዓለማችን 26 አገራት እና 40 በመቶ የሚሆነው የዓለማችን ህዝብ  ፌዴራላዊ የመንግስት አወቃቀር ሥርዓትን ይከተላሉ። በርካታ የህዝብ ብዛትና ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላቸው አገሮች በዚህ ስርዓት የሚተዳደሩና ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ የቻሉ ሆነው እናገኛቸዋለን። ለአብነት እንደህንድ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሩስያ  ከአፍሪካ ደግሞ እንደናይጄሪያ ያሉ አገራት ፌዴራሊዝምን የሚተገብሩ አገራት ናቸው። ሁሉም አገራት የፌዴራል ስርዓትን ከራሳቸው ፍላጎት፣ ከአገራቸው ታሪክ፣ ከወቅታዊ ሁኔታና ከህዝቦቻቸው ፍላጎት በመነሳት በተለያየ መንገድ ይተገብሩታል።

የፌዴራላዊ ሥርዓት እንደ እኛ ላሉ ብዝሃነት ለሚስተዋልባቸው  አገራት አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው። ብዝሃነታችንን ወደን በሌላ በኩል ደግሞ ፌዴራሊዝምን መጥላት አይቻልም። ፌዴራሊዝም ራሱን በራሱ ማረም የሚችል ነው፤ ይህን ስርዓት በአግባብ መተግበር ከተቻለ በማንኛውም ወቅት የሚፈጠሩ ነባራዊ ችግሮች መፍታት የሚችልበት የፖለቲካ ምህዳር (political space) ያለው ስርዓት ነው። በየትኛውም የፌዴራል ስርዓት  ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም። በፌዴራል ስርዓት ውስጥ የችግሩ መጠንና ዓይነት ይለያይ እንደሆን እንጂ ችግር መፈጠሩ አይቀርም። ነገም ይሁን ከነገወዲያ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀርም፤ ዋናው ነገር ችግሮችን የምንይዝበት መንገድ ሳይንሳዊና ወጥነት ያለው እንዲሆን ማድረግ ነው። የኢፌዴሪ የፌዴራል ስርዓት ለጋ ይሁን እንጂ ራሱን በራሱ ማረም የሚያስችል አሰራር ያለው ነው።

አገራችን የምትከተለው ፌደራላዊ ስርዓት ከሌሎች አገራት ፌዴሬሽኖች የሚጋራቸው ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የሚለየባቸውም የራሱ ብቻ የሆኑ  ባህሪያት ይኖሩታል። የመጀመሪያው መለያ ተደርጎ የሚወሰደው የኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ ሰፍኖ የነበረውን የተዛባ የሕዝቦች ግንኙነት በማስተካከል አዲስ የኢትዮጵያዊነት ሕብርና አንድነት መመሥረቱ ነው፡፡  እንዲሁም የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን እኩልነትና ዴሞክራሲን ማስፈን እንዲሁም ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ቀዳሚው ዓላማው መሆኑ ነው።

የፌዴራል ሥርዓታችን የአገራችንን ውለው ያደሩ ችግሮች ሁሉ  እልባት እንዲያገኙ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ሃይማኖት በሰላማዊ መንገድ የማራመድ፣ በቋንቋቸው የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን የማሳደግ፣ ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለፅ፣ አካባቢያቸውን የማልማት እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ይህ የፌዴራል ስርዓት አረጋግጦላቸዋል። በአገራችን ዛሬ ስለጭቆና ወይም ነጻነት እጦት  የሚወራበት ሁኔታ የለም። ይሁንና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለፌዴራል ስርዓቱ አደጋ እየጋረጠ መሆኑ የማይካድ እውነታ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህት ጠባብነት እንዲሁም የሃይማኖት አክራሪነት ለአገራችን የፌዴራል ስርዓት ድርስ አደጋዎች ናቸው።

እነዚህ የአገራችን የፌዴራል ስርዓት ተግዳሮቶች  ሁላችንም በጋራ ሆነን ልንዋጋቸው ይገባል። እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የደም መስዋዕትነት የሚጠይቁ  አይደለም። ከደርግ አምባገነን ስርዓት ጋር የተደረገው የ17 ዓመታት መራራ ትግል የበርካቶችን ክቡር ህይወት ቀጥፏል፣ አካል አግድሏል፣ ንብረት ወድሟል።  ዛሬ ይህን አይነት መሰዋዓትነት የሚጠየቅበት ወቅት ላይ አይደለንም። ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቀው ሁሉም በተሰማራበት መስክ በቅንነትና ታማኝነት መንግስትና ህዝብ የሰጠውን ሃላፊነት በአግባብ መወጣት ብቻ ነው። የአገራችን የፌዴራል ስርዓት  የህዝቦች የዘመናት የደም ውጤት ነው። በመሆኑም ይህን ስርዓት በዋናነት የሚፈታተነውን የኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሁም የዚህ ውላጅ የሆኑትን የትምክህትና ጥበት ተግባርና አመለካከትን በጽናት መታገል ብቻ ነው።

 

የሕግ የበላይነት መረጋገጥና ለፌዴራል ስርዓቱ ዘላቂነት የመጀመሪያውና ትልቁ  መስፈርት ነው። የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ዜጎች  ባለሃብቱም ይሁን ጋዜጠኛው፤ ምሁሩም ይሁን ያልተማረው፤ የህብረተሰብ ክፍል በሕግ ፊት እኩል ሲሆኑ ብቻ ነው።  በየትኛውም አገር መንግስት መንግስት ሊባል የሚችለው በስልጣን ላይም የሚቆየው፣ በህዝቦች ተቀባይነት የሚኖረውም የህግ የበላይነትን በሁሉም ዜጋ ላይ እኩል ማረጋገገጥ ሲችል ብቻ ነው።  በዕርግጥ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ መንግስት የማይተካ ሚና ይኑረው እንጂ ህብረተሰቡ ለአካባቢው ጸጥታ መጠበቅና ለህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ያለው አስተዋጽዖም ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም የየድርሻውን ሊወጣ የገባል።

 

የፌዴራል ስርዓታችን አገራችን የነበሩባትን የዘመናት ችግሮች  ማቃለል የቻለ ስርዓት ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በፌዴራል  ስርዓቱ ላይ አንዳንድ ተግዳሮቶች እየተስተዋሉ ነው። በመሆኑም ችግሮች እንዲቀረፉና መልካም ነገሮች እንዲጎለብቱ በማድረግ ረገድ ወጣቱ የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ ሃላፊነት ሊሸከም ይገባል።  ችግሮች እንኳን በታዳጊ አገር ይቅርና አድገናል በሚሉት በምዕራብ አገራትም ይፈጠራሉ። ይሁንና እኛ አገር ችግርን ወይም ልዩነትን በሃይል ለማራመድ ሲሞከር እነርሱ ጋር ግን ለማንኛውም ችግር መፍትሄ የሚፈለገው በጠረጴዛ ዙሪያ  ነው። ይህን አይነት አካሄድ በእኛም አገር ሊለመድ ይገባል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy