Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

…የጠል ደመና እንዳይሆን!

0 271

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

…የጠል ደመና እንዳይሆን!

                                                    ቶሎሳ ኡርጌሳ

ነገ ሚያዚያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም፣ “ሚዲያ— ለፍትህና ለህግ የበላይነት መረጋገጥ” በሚል መሪ ቃል የፕሬስ ነፃነት ቀን በሀገራችን ተከብሮ ይውላል። ቀኑን ስናስታውስ ከፕሬስ ዴሞክራሲያዊ ነፃነትና አሰራር አኳያ አንዳንድ ነጥቦችን መለዋወጥ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ ቀኑን እንዲከበር መደረጉ በራሱ ብቻ ሀገሪቱ ለፕሬስ ነፃነት የሰጠቸውን ህገ መንግስታዊ እውቅና የሚያረጋግጥ ይመስለኛል። የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በአንቀፅ 29 ላይ፤ “የአመለካከት፣ ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት”ን ከመደንገግ ባሻገር፣ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረጉ ትናንት “ሳንሱርን” ታከናውን ለነበረች ሀገር ቀላል እመርታ አይደለም።

በእኔ እምነት የኢትዮጵያ ፕሬስ የህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ውጤት እንዲሆን ነው። ከሌላው ዓለም የመጣ አይደለም። በአስገዳጅነትም የተጫነብን አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ የፕሬስ ነፃነት እውን እንዲሆን የተደረገው የትኛውም አካል ለማስደሰት ወይም ለማስከፋት ታስቦ አለመሆኑን ልብም ይሏል። ነፃነቱን ማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ከማስፈን ከህልውና ጋር ተያይዞ ስለሚታይ ብቻ ነው።

ርግጥ በየትኛውም ሀገር ውስጥ ዴሞክራሲን ለመተግበር ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ክንዋኔውን የሚፈፅሙት በተናጠል አይደለም። በተለያዩ ደረጃዎች በጋራ በሚያከናውኑት ተግባር እንጂ። ዴሞክራሲን የህልውናቸው አካል ያደረጉ ሀገራት፤ ዴሞክራሲያዊ ባህል ያላቸውን ግለሰቦች በተደራጀ አኳኋን ለማሰማራት የሚያስችሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋሞች እንዲኖሩ ይተጋሉ። ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ ሚዲያ አንዱ ነው።

ሚዲያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በመገንባትና ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ረገድ የሚጫወተው ሚና ግልፅ ነው። ዜጎችን ያሳውቃል፣ ያስተምራል፣ ያዝናናል። በዚህ ሂደት ውስጥም በፖለቲካል-ኢኮኖሚው ውስጥ የሚታዩትን ስንክሳሮችን በመረጃና በማስረጃ ላይ ተመርኩዞ ነቅሶ በማውጣት ማህበራዊ ኃላፊነቱን ይወጣል። በዚህም ህዝብን የሚጎዱ አሊያም ተጠቃሚነቱን የሚሸረሽሩ ጉዳዩችን በማጋለጥ ይሰራል።  

እንዳልኩት ዴሞክራሲ ለሀገራችን የህልውና ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት ሲጠይቁት የነበረው አንዱ የዴሞክራሲ መብትን በመሆኑ፤ ስለ ዴሞክራሲ የሚዘምሩ ተቋማትን እውቅና መንፈግና ስራቸውም እንዳይከናወን ማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ፈፅሞ ቦታ ሊኖረው አይችልም። እናም ይህን የህልውና ማዕዘን የሚያጎለብት ማንኛውም ጉዳይ ሊደገፍና ተግባሩንም ከሀገሪቱ ህጎችና ከሙያው ስነ ምግባር ጋር አስተሳስሮ እንዲወጣ ማድረግ የመንግስት ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል።

ርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት በህገ መንግስቱ ላይ በግልፅ የተደነገጉት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብቶች እውን እንዲሆኑ የታገለ ነው። እንዳይሸራረፉም ሰርቷል ብዬ አስባለሁ። በተለይ ሚዲያ በሀገሪቱ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ እመርታዎች ላይ የራሱን እሴት እንዲጨምር ለማድረግ በህገ መንግስቱ መሰረት የህግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቶ ሚዲያው ተግባሩን ነፃና ገንቢ በሆነ መንገድ እንዲከውን ድጋፍ አድርጓል።

ይህ የመንግስት ድጋፍ የግልና የህዝብ ሚዲያዎችን የለየ አይደለም። ሁሉም ስራቸውን በነፃነትና በህጋዊ መንገድ የሚያከናውኑበትን የተስተካከለ ምህዳር በመፍጠር ላይ አተኩሮ ተንቀሳቅሷል። ረጅም ርቀትም ሄዶ ሚዲያዎቹን ለመደገፍና ለማጠናከር ጥረት  አድርጓል። ጥረቶቹ ሚዲያዎች ተግባራቸውን በነፃነትና ገንቢ በሆነ ሁኔታ እንዲፈፅሙና ለሀገራችን የለውጥ ሂደት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ከማሰብ የመነጩ ይመስለኛል።

እንዳልኩት በመንግስት በኩል የሚከናወኑት ስራዎች ‘እገሌን ለመጥቀም ወይም ለመጉዳት’ ተብለው የሚወጠኑ አይደሉም። እንዲያውም የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ እንዲጎለብት ከሌሎች የዴሞክራሲያዊ ግንባታ ስራዎች ባልተናነሰ መልኩ እነርሱም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበተክታሉ ተብሎ ስለሚታመንበት ነው።

መንግስት እነዚህን ጥረቶች ሲያደርግ ሚዲያዎቹም እንደ ዴሞክራሲ ማሳለጫ ተቋምነታቸው ዴሞክራሲውን ከማጎልበት አኳያ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይኖርባቸዋል ብዬ አስባለሁ። በማደግ ላይ የሚገኙትን የሀገራችንን ህዝቦችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ሁነቶችን የማጎልበትና የላቀ ሁለንተናዊ ዕድገትና አስተሳሰብ እንዲፈጠር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህም ገና በጅምር ላይ ያለው የሀገራችን ዴሞክራሲ ስር እንዲሰድ በማድረግ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የምታከናውውን የለውጥ ሂደት መደገፍ ይኖርባቸዋል።

የሀገራችን ሚዲያዎች ሀገራችን ለዘመናት አንገቷን ሲያስደፋት የነበረውንና የድህነት አዙሪት ቀለበት ለመቀልበስ የምታደርገውን ጥረት በግንባር ቀደምትነት ሊደግፉ ይገባል። ህዝብን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ለማላቀቅ፣ ህዝቡ ፈጣን ሀገራዊ ለውጥን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ትክክለኛ የልማት ሃሳቦችን እንዲገነዘባቸው የሚያደርጉ፣ መልሶ ከራሱ ልማታዊ ተግባሮች እንዲማር የሚያነሳሱ፣ በትግበራቸው ላይም በንቃት እንዲሳተፍ የማነቃቃት እንዲሁም አዎንታዊ የልማትና የዴሞክራሲ የለውጥ እሴቶችን የማስተጋባት ሚናን መወጣት መደበኛ ተግባራቸው አድርገው መያዝ የሚኖርባቸው ይመስለኛል።

ሆኖም አወዳሽና ነቃሽ ብቻ ሆነው መገኘት የለባቸውም። ሚዲያዎች በሀገራችን የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ስራዎች ውስጥ የሚስተዋሉ እንደ ሙስና እና መልካም አስተዳደር ዓይነት ችግሮችን እየነቀሱ ማውጣት ይኖርባቸዋል፤ ይገባቸዋልም። ችግሮችን ሲነቅሱ ግን በተጨባጭ ማስረጃና መረጃ ላይ መመርኮዝ አለባቸው። በስሚ ስሚና በጥላቻ ስሜት ሙያቸውን ወደ አላስፈላጊ መስመር ሊመሩት አይገባም—እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ውድቀትን እንጂ ልማትን አያመጣምና። የህዝቡን ሁለንተናዊ ጥረቶች ከማደናቀፍ በስተቀር ሀገራዊ ልማትን ሊደግፉም አይችሉም። እናም ዘገባዎቻቸው ከአጠቃላይ ጥላቻና ከአጠቃላይ ውዳሴ ነፃ የሆኑ፤ ትክክለኛ፣ ሚዛናዊ፣ ተዓማኒ ምልከታዎችን የሚያንፀባቅሩ መሆን ይገባቸዋል።

ሚዲያዎች የሚተገብሩት ሙያ ህዝብን የሚያስተምር፣ የሚያሳውቅና የሚያዝናና ሙያ በመሆኑ፤ የተበላሹ አሊያም መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዩች በማሳየት ለህዝብ ይፋ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ይሁንና ሙያው በትችት ስም ለፍፁም ጥላቻና ከህግ ውጭ የሆኑ አካላትን አጀንዳ ማራገቢያነት ከዋለ እንዲሁም ሳያሰልስ ፅንፈኛ አስተሳሰቦችን ብቻ የሚያራምድ ብሎም ዜጎችን ለሁከትና ለብጥብጥ የሚዳርግ ከሆነ ከልማቱ ይልቅ ጥፋቱ ያመዝናል። ሀገራዊ አንድነትንም ያፋልሳል።

እንዲህ ዓይነቱ የሚዲያ ተግባር ህዝብን ከማደናገርና ወደ አላስፈላጊ ጉዳይ ከመምራት በስተቀር ለሀገራዊው ልማትም ይሁን ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ይህ ነው የሚባል ነገር ሊከውን የሚችል አይመስለኝም። ስለሆነም ሰናይ ተግባርን የመደገፍና የማበረታታት፣ እኩይ የሆነውን ክዋኔ ደግሞ ገንቢ ትችት በመስጠት እንዲታረም መጠቆም ከሚዲያ የሚጠበቅ ተግባር ነው። ይህን ካለደረገ በታዳሚው ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። እንዲያውም ከዚህ ቀደም እንደነበሩት የሚዲያ ውጤቶች ታይቶ የሚከስም የጠል ደመና የመሆን ዕድሉ የሰፋ ይሆናል።

ሚዲያም ይሁን ሌሎች የፕሬስ ስራዎች ነፃነታቸው ተከብሯል ሲባል እንደ ሌጣ ፈረስ ያለ ልጓም ዝም ብለው ያሻቸውን ያደርጋሉ ማለት አይደለም። ማንኛውም ነፃነት ያለ ተጠያቂነት ተግባሩን ሊያከናውን አይችልም። ፕሬስ ነፃ ሆኖ ተግባሩን የሚያከናውነው ተጠያቂነቱን በመዘንጋት አይደለም። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ለፕሬስ የሰጠው ነፃነት ተጠያቂነትም ያለበት ጭምር መሆኑ መዘንጋት አይገባም። በህገ መንግስቱ አንቀፅ 29 (6) ላይ እንደተመለከተው፤ እነዚህ መብቶች (ሃሳብን በነፃነትና የመያዝና የመግለፅ መብቶችን ለማለት ነው) ገደብ ሊጣልባቸው የሚችለው የሃሳብና መረጃ የማግኘት ነፃነትበአስተሳሰባዊ ይዘቱና ሊያስከትል በሚችለው አስተሳሰባዊ ውጤት ሊገታ አይገባውም በሚል መርህ ላይ ተመስርተው በሚወጡ ህጎች ብቻ እንደሚሆን ደንግጓል። በተጨማሪም የወጣቶችን ደህንነት፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ሲባል ህጋዊ ገደቦች በመብቶቹ ላይ እንደሚደነገጉ ይገልፃል። በንዑስ አንቀፅ (7) ላይም፤ ማንኛውም ዜጋ ከላይ በተጠቀሱት መብቶች አጠቃቀም ረገድ የሚጣሉ ህጋዊ ገደቦችን ጥሶ ከተገኘ በህግ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ተመልክቷል። ይህም የነፃነትንና የተጠያቂነትን መሳ ለመሳነት የሚያሳይ ድንጋጌ መሆኑን ልብ ይሏል!

ከዚህ አኳያ በሚዲያዎች በተለይም እንደ ፌስ ቡክ ዓይነት ማህበራዊ የትስስር መረቦች ላይ የሚከናወኑት ተግባራት ህገ መንግስቱን የሚቃረንና የህዝቦችን በተለይም የወጣቶችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ታዝበናል። ይህ ሚዲያ ዘርፍ የጠቀሜታውን ያህል፤ የፈጠራ ወሬዎች የሚሰራጩበት፣ አንድ ህዝብ ከሌላው ጋር እንዲጋጭ ቅስቀሳ የሚካሄድበት፣ የጥላቻ መንፈስ የሚዘራበትና ሀገራዊ ሀብት እንዲወድም ጥሪ የሚደረግበት መድረክ እንደነበር አይዘነጋም።

በእኔ እምነት ይህ ሁኔታ ዛሬ ላይ ይህ የሚዲያ ዘርፍ በአብዛኛው ተጠቃሚዎቹ ዘንድ አመኔታን እንዲያጣ ያደረገው ይመስለኛል—የጥርጣሬ ድባብንም አስከትሏል። እናም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሲከበር ሚዲያው እንደ ጠል ደመና ታይቶ እንዳይጠፋ ራሱን ወደ ውስጥ ሊፈትሸው ይገባል። ዘርፉን ለማሳደግ በመንግስት በኩል መከናወን የሚገባቸው ቀሪ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ሚዲያውም ራሱን ወደ ውስጥ በመመልከት ምን ያህል ሙያውን አክብሬ እየሰራሁ ነው?፣ በተፈጠርኩበት ፖለቲካል ኢኮኖሚ አውድ ምን ያህል ማህበራዊ ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ?፣ የራሴን ነፃነት ሳስጠበቅ የሌላውንስ ምን ያህል ጠብቄያለሁ?…ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ለሚዲያው ዕድገት ማሰብ ይኖርበታል። በእኔ እምነት ይህ ማድረግ አንድም፣ ታይቶ ከሚጠፋ የጠል ደመናነት ራስን መታደግ ነው፤ ሁለትም፣ ህዝቡ ከሚዲያ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም በማረጋገጥ ሀገራዊ ኃላፊነትን መወጣት ነው። መልካም የፕሬስ ነፃነት ቀን!

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy