Artcles

የፈርጣማው ኢኮኖሚ አብነቶች

By Admin

May 03, 2018

የፈርጣማው ኢኮኖሚ አብነቶች

ስሜነህ

የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ ኤም ኤፍ  ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የ8.5 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደምታስመዘግብ የሰጠው ሳይንሳዊ ትንበያ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ከወሰዱ ሰሞንኛ ጉዳዮች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። ሲ ኤን ኤን   በዘገባው እንዳስታወቀው ይህ እድገት ኢትዮጵያ በድርቅ በተመታችበት ጊዜ መሆኑና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይም ሆና መሆኑ 8.5 አገሪቱ በጠንካራ መሰረት ላይ መሆኗን ያሳያል ብሏል። በነገራችን ላይ እድገቱ የዛሬ ብቻ ሳይሆን ተከታታይነት ያለው ለመሆኑም የባለፈው አመት ተመሳሳይ የአይ ኤም ኤፍ መረጃ ያመለክታል። የባለፈው አመት የተቋሙ መረጃ የሃገራችንን ኢኮኖሚ እንደወረደ የሚጠቅስ ሳይሆን ከጎረቤት ኬኒያ ጋር በንጽጽር የፈተሸ መሆኑ የእድገታችንን ልክ እና የእድገቱ አብነት የሆኑ ዘርፎችን ለይቶ ለማውሳት ይመቻል።  

ኬኒያ ለረጂም ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ሆና ብትቆይም አሁን ግን በጎረቤቷ ኢትዮጵያ የመሪነት ቦታዋን እየተነጠቀች መሆኗን የገለጸው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ቀመር እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ ( ጂዲፒ ) እስከባለፈው  ዓመት መጨረሻ ድረስ 78 ቢሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ባለፈው ዓመት 72 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ ማስመዝገቧን ጠቅሷል ፡፡ኬንያ በ2016 በጀት አመት 68.91 ቢሊዮን ዶላር ስታስመዘግብ የ2015 አመታዊ ገቢዋ 63,62 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ፡፡ በሚቀጥለው አመት ደግሞ ወደ 75 ቢሊየን ዶላር እንደሚጠጋ ይጠበቃል፡፡እንደገንዘብ ተቋሙ አሃዛዊ መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከኬኒያ ጋር ሲነጻጸር አብላጫ ያለው በመሆኑ የምስራቅ አፍሪካን የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤትነት ደረጃን ሊያሠጣት ችሏል ፡፡

ሀብት ከማይባክንባቸው አገሮች መካከል አይቮሪኮስት ፣ ኢትዮጵያ ፣ኬኒያ እና ሴኔጋልን የጠቀሰው የሲ ጂ ቲ ኤን ዘገባ ሃገራቱ ጠንካራ የመልማት ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ እድገታቸውም ቀጣይነት ይታይበታል ብሏል ፡፡ ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ ከሚባሉት ውስጥ ቢሆንም ህዝብን ያሳተፈ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ በመስፋፋቱ ምክንያት ሃገሪቱ ወደዕድገት ጎዳና ተሸጋግራለች ብሏል ዘገባው ፡፡

ስለሆነም የዚህ አመት ትንበያውም የሚጠበቅና ለዚህም መነሻ የሆነው ከላይ ለተመለከተው ፍላጎት የሚመጥን የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት በማስፋፋቷ ነው። በኢትዮጵያ የመጣውና የገንዘብ ተቋሙ የመሰከረው ይህ እድገት በኢንዱስትሪና በመሰረተ ልማት ዘርፎች ላይ በውጭና በመንግሥት በኩል በተከናወኑ የኢንቨስትመንት ተግባራት አማካኝነት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በአፍሪካ ከሰሃራ በታች የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያስመዘግቡት ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆና እንደምትቀጥልና (የዚህ አመት የተለየ ቢሆንም) በአማካይ ከስድስት በመቶ በላይ ኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧንም እንደምትገፋበት የሚያመላክቱት መረጃዎች ከመንግስት ብቻ የተገኙ ሳይሆን አለምአቀፉን የገንዘብ ድርጅት  ጨምሮ በርካታ የምጣኔ ሃብት የምርምር እና የጥናት ማእከሎችም ያረጋገጡት ነው ።

በሃገሪቱ እየታየ ያለው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ እድገት የተለያዩ የውጭ ባለሃብቶችን ትኩረት እንዲስብ ካስቻሉ እና ከላይ ከተመለከቱት በርካታ ምክንያቶች  በተጨማሪነት እና ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአቱ ውጤት የሆነው የመሰረተ ልማት እድገታችን ነው።

ሃገሪቱ ፈርጣማ ኢኮኖሚ ይኖራት ዘንድ በተለይ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርት፣ በኃይድሮ ፓወር፣ በቴሌኮም፣ በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በአግሮ ኢንዱስትሪና በመሳሰሉት ግዙፍ ኢንቨስትመንቶችን ማግኘት ግድ ይላታል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በአስተማማኝነት የሚቀጥለውና ሃገሪቱም መለወጥ የምትችለው፣ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ማድረግና ማስተናገድ ሲቻል ብቻ ነውና፡፡

በ2016 አፍሪካ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የቀነሰ ሲሆን የኢትዮጵያ 46 በመቶ ጨምሯል። ይህን የገለጸው ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ድርጅት ነው። ድርጅቱ የአውሮፓውያኑን የ2017 ኢንቨስትመንት ትንበያን በተመለከተ ይፋ ባደረገው  ሪፖርት እንዳመለከተው ባለፈው ማለትም ከጥር ወር 2008 እስከ ታህሳስ ወር 2009 ድረስ ኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መጠን ያለው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት አግኝታለች።ወደ አፍሪካ የፈሰሰው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን በ3 በመቶ ቅናሽ አሳይታል። በአህጉሪቱ ግንባር ቀደም የቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ተቀባይ ሆና የቆየችው እና በነዳጅ ሀብቷ የበለፀገችው አንጎላ 2016 ላይ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን አሽቆልቁሏል። በአህጉሪቱ ትልቁን ኢኮኖሚ የያዙት ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያም በዚሁ ዓመት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ግኝታቸው ቀንሷል። ምስራቅ አፍሪካ ላይ ኢትዮጵያ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ጠንካራ እድገት የታየበት እና ከዚህ ቀደም ያላየችው ነው ብሏል ተመድ በሪፖርቱ።

በ2016 የምስራቅ አፍሪካ 7.1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት አግኝቷል። ከዚህ ውስጥ ግማሹ የሚሆነውን የወሰደችው ኢትዮጵያ፤ በአጠቃላይ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያገኘችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ከቀደመው ዓመት በ46 በመቶ እድገት አሳይቷል።ይህም አፈፃፀሟ በዓለም ላይ በዝቅተኛ የልማት ደረጃ ላይ ከሚገኙ አገራት መካከል በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል።በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ የምታገኘው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን እድገት የተቀጣጠለው አገሪቱ በመሰረተ ልማት እና በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እያዋለችው ያለው መዋዕለ ንዋይ ነው ይላል የተመድ ሪፖርት።

እንደ ሪፖርቱ በዝቅተኛ የልማት ደረጃ ላይ በሚገኙ አገራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቢያ የተፈጥሮ ሀብት ነው።ነገር ግን አገራት የኢንቨስትመንት አማራጫቸውን ዓይነት አስፍተው ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ባደረጉት ጥረት እየተሳካላቸው ነው ብሎም ኢትዮጵያን በምሳሌነት አስቀምጧል።  

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎች አሉ።የሃገሪቱ የተረጋጋ ፖለቲካና ማክሮ ኢኮኖሚ፣ ሰፊ የሰው ኃይልና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቷ በዋናነት የሚጠቀሱት ናቸው።ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የምትከተል በመሆኗ በኢነርጂው ዘርፍ ለመሰማራት ለሚፈልጉም ሰፊ እድል አለ።በተለይ በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ሃገራችን የሄደችባቸው ስኬታማ ርቀቶች የአለም የገንዘብ ተቋማትን አመኔታ እንድታገኝና የበለጠ እንድትተጋ የሚያስችላትን እድል ፈጥሮላታል።

በዚሁ መነሻም አገራችን ለህዝቦች በፍትሃዊነት የምታቀርበውን የማህበራዊ አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ ለሚሰሩ ስራዎች ማስፈፀሚያ የሚውል 700 ሚሊዮን ዶላር በቅርቡ ከዓለም ባንክ ድጋፍ ያገኘች ሲሆን፤ በተጓዳኝ  ለገጠር የምግብ ዋስትና ማስፈፀሚያ የሚውል ተጨማሪ 600 ሚሊዮን ዶላር በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር አግኝታለች። ይህም የሚያሳየው በዓለም ኢኮኖሚ ላይ በተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚታወቁት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን ጨምሮ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ያላት አመኔታ እየጨመረ በመምጣቱ መሆኑን ነው።

ባለፉት 26 ዓመታት ጉዟችን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ለማዳረስ በመቻሉ በአሁኑ ወቅት የትምህርት ተቋማት ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶችና 3,300 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ27 ሚሊዩን በላይ ተማሪዎችን ማስተናገድ ተችሏል። በዚህም ታሪካችንን በልማታዊ አቅጣጫ መርተን መሰረታዊ ለውጥን ማምጣታችን ለሌላው ዓለም ምሳሌ መሆን የምንችልበት ደረጃ ላይ አድርሶናል።የአንደኛ ደረጃ ተሳትፎን ከ96 በመቶ በላይ እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኩልም በውስን አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ የነበረውን ስርጭት በማስፋፋት ተሳትፎውን 43 በመቶ በላይ ለማድረስ የተቻለ መሆኑን የሚገልጹ መረጃዎች፤ በመሰናዶ ትምህርት ፕሮግራም ከግማሽ ሚሊዩን በላይ ተማሪዎችን በመማር ላይ ሲሆኑ በየዓመቱ ለከፍተኛ ትምህርት ተገቢውን ማለፊያ እያስመዘገቡ ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ የተማሪዎችን ቁጥር ወደ ሁለት መቶ ሺህ መድረሱን ይጠቁማሉ።

በሌላ በኩል በማህበራዊ ልማት ዘርፍ ድንቅ ውጤት ያስመዘገብንበትና በገንዘብ ተቋማቱ አመኔታን ያተረፈልን የጤናው መስክ ነው።የጤና ፖሊሲያችን በዋናነት በሽታን በመከላከል ላይ የሚያተኮር ቢሆንም ከዚሁ ጐን ለጐን መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን የማስፋፋቱም ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።መሰረታዊ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ጣቢያዎችን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ለማስፋፋት በተደረገዉ የተቀናጀ ርብርብ በ1983 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ 153 ብቻ የነበረው የጤና ጣቢያዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከ3500 በላይ ደርሷል። ለ25ሺ ህዝብ አንድ የጤና ጣቢያ ለማዳረስ የተያዘውን ግብ ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉን የሚገልጹት የጤና ጥበቃ ሚንስቴር መረጃዎች፤የጤና ተቋማቱን አገልግሎት የማሻሻልና ግብአቶችን የማሟላት ሥራም ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱን ያረጋግጣሉ።

በ1996 ዓ.ም ተቀርፆ ሥራ ላይ የዋለው የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር የመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መሻሻልና በሽታን በመከላከሉ ስራ ላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍተኛውን ድርሻ አበርክቷል። በመላ ሀገሪቱ በገጠርና በከተማ የተሰማሩ ከ39ሺ የሚበልጡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በጤናው ዘርፍ የህብረተሰቡን ባለቤትነት በማሳደግ ጤናማና አምራች ዜጐችን ለመፍጠር የተነደፈውን ራዕይ ለማሳካት ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ ናቸው። በሁሉም የአገራችን የገጠር ቀበሌዎች ቢያንስ አንድ የጤና ኬላ የተገነባ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ከ16251 የሚበልጡ ጤና ኬላዎች ለህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ።

መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የሆስፒታል አገልግሎት ለማሻሻልም የሃገራችን አቅም በፈቀደ መጠን ትኩረት ተሰጥቶ ተሰርቷል። በ1983 ዓ.ም 72 ብቻ የነበረው የሆስፒታሎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት በግሉ ዘርፍና በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተሰሩትን ሳይጨምር የመንግስት ሆስፒታሎች ብቻ ቁጥራቸው በአራት እጥፍ አድጎ ከ310 በላይ ደርሷል።

ከላይ በተመለከተው መልኩ ሃገራችን ከአለም ባንክ ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ በድጋፍና በብድር መልክ ሊገኝ የቻለው መንግስት ትምህርትን፣ ጤናን፣ ግብርና፣ ንፁህ ውሃን እና የገጠር መንገድን በመላ አገሪቱ ለማዳረስ እያደረገ ያለው መጠነ ሰፊ የልማት ጥረት እና በዚህም እየተገኘ ያለው ውጤት ከፍተኛ መሆኑን በባንኩ መስፈርቶች መሠረት ሊረጋገጥ በመቻሉ መሆኑን  መረዳት ይቻላል።ስለሆነም በዚህ ባለመዘናጋት ከዚህ ለበለጠ ድጋፍና እርዳታ በገንዘብ ተቋማት ዘንድ አመኔታን ሊያተርፉ በሚያስችል አግባብ የተያዙ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ እና ከኪራይ ሰብሳቢነት በጸዳ መልክ መፈጸም ይገባል።