Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

“ይኼንን እሣት ብረት አቅልጡበት፡፡”

0 355

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

“ይኼንን እሣት ብረት አቅልጡበት፡፡”

ዮናስ

የትኛውም አይነት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ፋይዳ በዜጎች የሥራ ሥምሪት እና የኑሮ ደህንነት ሁኔታ መገለፅ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ በቀጣይ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶችና ወጣቶች መሆናቸው አያጠያይቅም። ከዚህ አንፃር ድህነትንና ሥራ አጥነትን በመቅረፍ ረገድ የሃገራችን የእስካሁኑ አፈጻጸምና በቀጣይ የዕቅድ ዘመን የሚመዘገበውን አፈፃፀም በተለይ ከወጣቶች አንጻር በግልፅ መመልከት ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡

እስካሁን እየተመዘገበ የመጣው ፈጣንና መሰረተ-ሰፊ ዕድገት ሥራ አጥነትንና ድህነትን በመቀነስ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ አሁንም ግን ድህነቱና ሥራ አጥነቱ ሰፊ በመሆኑ በቀጣዩ የዕቅድ ዘመንም ፈጣን ዕድገቱን በማስቀጠል ድህነትንና ሥራ አጥነትን በፍጥነት ለመቀነስ ከፍተኛ ርብርብ ይጠይቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ዓለም-አቀፉ ማህበረሰብ በድህረ-2015 የልማት አጀንዳ ዙሪያ እ.ኤ.አ በ2030 ድህነትን ከዓለማችን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ስምምነት እየደረሰ በመሆኑ አገራችንም ይህንን ግብ ለማሳካት በሚቀጥሉት ዓመታት ፈጣን ዕድገቱን በማስቀጠል በዕቅድ ዘመኑ የድህነት መጣኔው በ2007 ከተገመተው የ23.4 በመቶ መጣኔ በጉልህ ለመቀነስና ወደ 16.7 በመቶ ለማድረስ መረባረብ ይገባል፡፡

በእርግጥ በተመሳሳይ ኢኮኖሚያችን በፍጥነት በማደጉ ምክንያት በከተሞችና በገጠር የሚታየውን የሥራ አጥነት ምጣኔ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በያዝነው የሁለተኛው ዙር  የዕቅድ ዘመንም ፈጣን ዕድገቱ በከተሞችና በገጠር የሥራ ዕድል በሚፈጥር መልኩ ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይ የታቀደው ፈጣን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እንደዚሁም በሌሎች መስኮች የግል ኢንቨስትመንት ማበረታታት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ማስፋፋት፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ልማት ሥራዎችን ለሥራ ዕድል ፈጠራ ማዋል፣ እና በመንግስት የሚካሄዱ የልማት ፕሮግራሞች አነስተኛ ኩባንያዎችንና የሥራ ዕድሎችን በሚያስፋፉ መልኩ መተግበር ይጠበቃል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራሞቹ በችግሩ ይበልጥ ተጎጂ የሆኑትን ወጣቶችንና ሴቶችን በተለይ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሆነው ሊፈጸሙ የሚገባ መሆኑም አያጠያይቅም፡፡

ፈጣን ዕድገቱ በዚህ መልኩ ድህነትንና ሥራ አጥነትን በሚቀንስ መልኩ ለመምራት ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን እየተተገበረ የቆየውን ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራምን በገጠር ይበልጥ በማጠናከር፣ በከተሞች ደግሞ በጥናት ላይ ተመስርቶ በመተግበር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን የሚያጠይቁ ማሳያዎች ሞልተዋል፡፡

ለወጣቶች የስራ ፈጠራ  መነሻ የሚሆን ገንዘብ የአገሪቱ አቅም በሚፈቅድ መልኩ  በፌዴራልም ሆነ ክልል መንግስታት ተመድቦ ወጣቶች ተደራጅተው  ወደ ስራ እንዲገቡ በመደረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ ጎን ለጎን ወጣቶች ስልጠና እንዲያገኙ፣ የስራ ቦታ እንዲያገኙ፣  የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውም የፌደራል መንግስትን ጨምሮ የክልል መንግስታት በመሰራት ላይ ናቸው። ሁሉም ክልሎች በወጣቶች የስራ ፈጠራ ጥረት ላይ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ባይገኙም ሁሉም ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ  ግን መካድ አይቻልም። ያም ሆኖ ይህ ግን የጥበትና ትምክህት ሃይሉ ወጣቶችን ለጥፋት ተልዕኮው ማሳኪያ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት እንደቀጠለና በተግባር መሬት ላይ ከሚገኘው እውነታ አፈንጋጭ የሆኑ ፕሮፖጋንዳዎች በመንዛት ወጣቱን ለሞትና ስደት መዳረጋቸውን እየገፉበት ነው። ስለሆነም መንግስት የወጣቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  እየሰራ ያለውን በአግባቡ ማወቅና የዚሁ ተጠቃሚ በመሆን የጥፋት ሃይሎችን ተልእኮ በማክሸፍ የተጣለበትን አደራና ሃገራዊ ሃላፊነት ወጣቱ ሊወጣ ይገባል።

እናንተ ተስፋ ካላችሁ ሁላችንም ተስፋ ይኖረናል! ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሚሊኒየም አዳራሽ ለወጣቶች መረር ያለ መልእክት ያስተላለፉትም ስለዚህ ነው። ስለመልእክታቸው ጥልቀት እውቁ ግሪካዊ ዪሪፒደስ  የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሃብታም ለመሆን ከሁሉም የተሻለው ጊዜ ወጣትነት ነው፤ ድሃ ለመሆንም ከሁሉም የተሻለው ጊዜ አሁንም ወጣትነት ነው፡፡ ሁለቱም ያለው በእጃችሁ ስለሆነ፤ እባካችሁ የተሻለውን ምረጡ፡፡ እናንተ ተስፋ ካላችሁ ሁላችንም ተስፋ ይኖረናል! ሃገራችንም ተስፋ ይኖራታል፡፡ ማለታቸውንም ማስታወስና ማጤን ከወጣቶች ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ተስፋ እውን ይሆን ዘንድ ክንዳችንን አጠናክረን በጋራ ስራ ሳንንቅ እንድንተጋና ጉልበታችንን ሃብት ለመፍጠር እንድናውል በታላቅ ትህትና ልጠይቃችሁ እፈልጋለው፡፡ሲሉ ተማጽኖ ድረስ የወረዱትም ለጉዳዩ መንግስት የሰጠውን ትኩረት ለማጠየቅና ከወጣቶች የሚጠበቀውን የላቀ አደራ ለማስታወስ ነው።

መንግስት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ከዚህ ቀደም በነበረው መልክ በዘፈቀደ ሳይሆን በእውቀት ላይ ተመስርቶ መስራት የሚገባ መሆኑ ላይ የማያወላውል አቋም መያዙ ምን ያህል ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት የሰጠ ለመሆኑ አመላካች ከሆኑ አስረጂዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው። የወጣቶች ጉዳይ እንደዘርፈ ብዙ ተግባራት በሁሉም ሀገራዊ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና እቅዶች እንዲካተት መደረጉም ሌላኛው ማሳያ ነው።

መንግስት   የዛሬ አመት ግድም ዋነኛ ስራዬ ወጣቱን ማእከል ያደረገ ነው ባለው አግባብ በ2009 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ 2 ሚሊዮን 700 ሺህ ለሚጠጉ ወጣቶች የስራ እድል የተፈጠረ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 898 ሺህ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ኮንስትራክሽን ፣ማኑፋክቸሪንግ ፣የከተማ ግብርና በስፋት የስራ እድል የተፈጠረባቸው የስራ ዘርፎች  ናቸው። ይህ በከተሞች ብቻ የተከናወነ ሲሆን በገጠር ለሚገኙ ወጣቶችም በተመሳሳይ የስራ እድል ፈጠራ ዘመቻው በእቅድና በእውቀት ላይ ተመስርቶ እየተከናወነ ነው።ለዚህ ደግሞ በትግራይ ክልል ማህበረ ረድኤት ትግራይ በተባለው የክልሉ ልማት ማህበር በኩል እየተከናወነ የሚገኘው የንብ ማነብ የወጣቶችና ሴቶች ፕሮጀክት ለሌሎች ክልሎችም በተሞክሮነት ሊነሳና ሊወሰድ የሚገባው ነው።

ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው በክልሉ ስድስት ወረዳዎች የሚገኙ ከ12 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ። የፕሮጀክቱ ኃላፊን ጠቅሶ ኢዜአ እንደዘገበው  ፕሮጀክቱ ከንብ ልማት ክህሎትና ከንብ መሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ በአርሶአደሩ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለይቶ መፍታት ዓላማ ያደረገ ነው ።

በዘርፉ ለሚሰማሩ ከ12 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሴቶች ለዘመናዊ የንብ ቆፎና መንጋ መግዣ በነፍስወከፍ 10 ሺህ ብር ብድር ይሰጣል። ለዚህም 120 ሚሊዮን ብር ተዘጋጅቷል።   በፕሮጀክቱ በቀጥታ ተጠቀሚ ከሚሆኑት ወጣቶችና ሴቶች በተጨማሪ በዘርፉ የተሰማሩ 180 ሺህ አርሶአደሮች በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የምርት ገበያ ትስስር በአገር ውስጥም በውጪም ባለመኖሩ አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ የሚያመርተው የቤተሰብ ፍጆታ ከሟሟላት ያለፈ ያልነበረ መሆኑ ይታወቃል። የወጣቶችን ተጠቃሚነት በገጠር ለማረጋገጥ ደግሞ ይህንን አሰራር መቀየር አስፈላጊ ነው። በአርብቶ አደሩም ሆነ በአርሶአደሩ ዘንድ የነበረው የእንስሳት አረባብ ስርዓትም  ሆነ የንብ ማነብ ተግባር በተፈጥሮ ግጦሽ ላይ መሰረት ያደረገ እና ባህላዊ የንብ ማነብ ስራ በመሆኑ በተለያዩ ጊዚያት በሚከሰት የአየር መዛባት ምክንያት በድርቅ፣ ጎርፍና የእንስሳት በሽታ ለዓመታት ያጠራቀመውን ሀብት የሚያጣበትን አሰራር የሚቀይር ተግባር ነው ለገጠር ወጣቶች ጠቃሚ የሚሆነውና ነው ከላይ የተመለከተው አቅጣጫ ሃገራዊ ይዘት እንዲኖረው እየተደረገ ያለው።

 

በአንዳንድ ጥናቶች ላይ እንደተመለከተው በመካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ምርታማነታቸውን ለማሻሻል፣ተወዳዳሪነታቸውን ለማጎልበት የተለያዩ ድጋፎች የተደረጉ ቢሆንም አንዳንዶቹ በተለይም ነባሮቹ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች አቅማቸው ቢዳብርም የተጠበቀውን ውጤት በተለይም ከከተማ ወጣቶች አኳያ አላስገኙም።   የመካከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ኢንቨስትመንት የማስፋት፣ከአነስተኛ ኢንዱስትሪ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ እየተሸጋገሩ ያሉትን የማበረታታት ፣ ከተለያዩ ዘርፎች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ሽግግር የሚያደርጉ ባለሃብቶችን በበቂ ያለመደገፍ አመራሩ ላይ የሚታዩ ውስንነቶች ናቸው። በስነምግባር የታነጸ የአገልግሎት መንፈስ የተላበሰ ሰራተኛ እንዲኖር ጉቦና የጥቅም ሽርክና ዝምድናና አድሏዊ አሰራረር ጎጂ ባህል መሆኑን አውቆ ሙያውን አክብሮ ለሃላፊነት ክብር ሰጥቶ የሚያገለግል የመንግስት ሰራተኛና አመራር እንዲፈጠር ከመንግስት በኩል ጽኑ ፍላጎት እንዳለ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሰሞኑን አረጋግጠዋል፡፡

ይህን ለማሳካትም በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚደረግ ምደባ በእውቀት በክህሎትና ችሎታ ትክክለኛ ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛ ቦታ እንዲሰማራ በማድረግ የመንግስት የማስፈጸም ብቃትን ማሻሻል ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል ተጠቃሽ መሆኑንም መግለጻቸው ስለመንግስት ቁርጠኝነት ለማጠየቅ ነው።  

የግሉ ዘርፍ ለወጣቶች የስራ እድል ማእከል እንዲሆን ከማድረግ አኳያ መንግስት የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ ያለው ዝግጁነት በዚህ ደረጃ ከሆነ የወጠኑቱ እሳትነት ደግሞ ወሳኝ ነው።  

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩም ውድ የሃገሬ ወጣቶች ፤-ወጣትነት የእሳት ጊዜ ነው፡፡ወጣትነት ውስጥ በእርግጥም እሳትነትና ከባድ ግለት አለ፡፡ ይሄንን እሳት ብረት አቅልጡበት ወንዝ ጥለፉበት ተራና ናዱበት፤ይሄንን እሳት ፋብሪካ ገንቡበት፤ይሄንን እሳት ድልድይ አንፁበት ከምንም ከማንም በላይ ደግሞ ከምንም ከማንም በላይ ደግሞ ይሄንን እሳት ህይወት ለማዳን ተገልገሉበት፡፡ሲሉ መልእክት ያስተላለፉት ስለዚህና መንግስት የድርሻውን ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላቀ ዝግጁ ስለሆነ ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy