Artcles

ደረግ ስርዓት ነበረ፡፡ የተደረገውም የህዝቦች መራር ትግል ስርዓት የማፍረስ ትግል ነው፡፡

By Admin

May 27, 2018

ደረግ ስርዓት ነበረ፡፡ የተደረገውም የህዝቦች መራር ትግል ስርዓት የማፍረስ ትግል ነው፡፡

መክብብ                                                                                                                       27 05 2018

በሃገራችን ሁልግዜም የሚስተዋል አንድ ችግር ይታየኛል፡፡ እሱም አንድን ታሪክ በተፈፀመበት አግባብ አለመዘገብ፣ አለመመዝገብ እና በአግባቡ የተመዘገበውን ታሪክ ማንሻፈፍ፣ ማጠልሸት እና እድሉም ከተገኘ ከነጭራሹኑ በልብ ወለድ ታሪኮች መቀየር የተለመደ ክስተት ነው፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የሚመስለኝ አርቆ አለማሰባችን፣ ራዕይ አልባ መሆናችን፣ ማህበረሰባዊ አስተዳደጋችን ያላበሰን ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት እና  ስለሀገር ግንባታ ያለን ከስልጣኔ የራቀ የደኸየ አመለካከት በማያዛችን ነው፡፡ ቀለል ያለ ምሳሌ ከታሪካችን እንነሳ እና በተዛባ ታሪካዊ አዘጋገባችን እና አመዘጋገባችን ለወደፊት ተስተካክለው መፃፍ አለባቸው የምላችውን ጥቂት ታሪኮች ላንሳ፡፡

አንደኛ የአህመድ ግራኝ እንደወራሪነት መቀመጥ፡፡

በኔ እምነት አህመድ ግራኝ ወራሪ አልነበረም፡፡ ኢትዮጲያዊ ሆኖ በሃገሪቱ በነበረው የስልጣን ትግል ህብረተሰባዊ የመደብ ምንጩን የተገዳደረ እና የተወሰነ ርቀት የሄደ ኢትዮጲያዊ ነበረ፡፡ የዚህች ምድር ብቃይ እና የአብራክ ክፋይ! ወራሪ ለመባል ምንም መስፈርት አያሟላም፡፡ ስለ ሶስት ሺህ የኢትዮጲያ ታሪክ የምናም ከሆነ ማለት ነው፡፡

ሁለተኛ የአፄ ቴዎድሮስ አባት፣ የአፄ ሚኒሊክ እና የአፄ ሃይለስላሴ እናት ማን ናቸው?

ሆን ተብሎ ወይም በሌላ ምክንያት የነዚህ ሦስት ንጉሶች ሙሉ ቤተሰባዊ ቅርፅ እንዳይታወቅ ተደርጓል፡፡ አብዛኛው እትዮጲያዊ የአፄ ቴዎድሮስ አባት፣ የአፄ ሚንሊኪን እና የአፄ ሃይለ ሥላሤን እናት እንዳያውቅ ተሰውሮበታል፡፡

ሶስተኛ በቅርብ የነበረን የአድዋ ጦርነት እና የተዘገበበት እውነታ

የአዳዋ ጦርነት በተፈፀመበት እና የኢትዮጲያ ህዝቦች ባደረጉት አስተዋፅኦ ልክ አልተዘገበም፡፡ ያልነበረውን ሁኔታ እና አፈፃፀም እንዲሁም የህዝቦችን አስተዋፅኦ በሚያንኳስስ መልኩ ያልነበረውን ምስል እንዲይዝ ተደርጓል፡፡

አራተኛ ዛሬም ይኸው የማይበጅ እና ከማቀጣጠል በሗላ ራስን መለኮስ (backfire) የሚገለፅ እውነታ

ይህን ለመገንዘብ እኔ ከምዘረዝረው ይልቅ ብሔራዊ ትያትር እና ለገሃር አካባቢ መፅሐፍ ዘርግተው የሚሸጡትን ሰዎች ሄዶ መጎብኘት በቂ ነው፡፡ በአብዛኛው ማለት ይቻላል በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ያልነበረን ታሪክ በልብ ወለድ ለመተካት እና ለማንቋሸሽ በሾሉ ብዕሮች የተከተቡ መፃህፍት ተሞልቶ ታገኙታላችሁ፡፡

የሆኖ ሆኖ ይህን ርዕስ ገታ እናድርግና ወደዋናው ሃሳቤ ልመለስ፡፡ አሁን ያለንበት ወቅት 27ኛውን የግንቦት 20 የድል በአል የምናከብርበት ጊዜ ነው፡፡

ከላይ እንደጠቀስኩት ይህንን የህዝቦች በዓል የተለየ ምስል ለመስጠት እና ያልተገባ ልብ ወለዳዊ ታሪክ ለማላበስ ያለማቋረጥ ላለፉት 27 አመታት መፃህፍት ተፅፈዋል፣ የሚዲያ ተቋሞችም ሰርተውበታል፡፡  እጅግ ብዙ ብዙ ነገረ ተብሏል፡፡ ላሁን ግን አንዷን እንደሰበዝ መዝዤ ለማየት እሞክራለሁ፡፡

የግንቦት ሃያን ድል ማክበር በውንድማማቾች ማሃከል የተደረገን ጦርነት እንደማክበር ነው የምትል ብሂል፡፡

ይህቺ ብሂል ቀላል የማይባሉ ዜጎች ጋር ደርሳለች፡፡ ይህችን ቢሂል በተለይ ደርግ ወገን የነበሩና ዛሬ ማላይቸውን ቀይረው የበሄር መሰረታቸውን በመላበስና በማላበስ ያቀነቅኗታል፡፡ ለምን በዓሏን እንደማይፈልጓትም ግልፅ ነው፡፡

እኔ ግን እላለሁ ከደርግ ጋር የተደረገው ትግል የስረዓት ለውጥ ትግል ነው፡፡ ከደርግ ጋር የነበረው ትግል ጨቋኝ እና ገዳይ የነበረውን ፀረ ህዝብ ስርዓት የመደምሰስ ትግል ነው፡፡ ዛሬ ተሸንፈው እና ኮብልለው ማሊያ ገልብጠው እንደሚነግሩን ሳይሆን ደርግ ማንንም ብሄር አይወክልም፡፡ እንዲያውም ደርግ ብሄር የሚባል ነገርን ጨፍልቆ ለማጥፋት ይተጋ የነበረ የዕኩይ ዕሳቤዎች ምንጭ የሆነ ስርዓት ነበረ፡፡ ደርግን ለመደምሰስ የተደረገውን እልህ አስጨራሽ ትግልን ጥላሸት ለመቀባት ሲፈለግ በወንድማማቾች ማሃከል የተደረገ ጦርነት ነው ሲሉ ትሰማቸዋለህ፡፡

እኔ ግን እላለሁ ይህ ጦርነት በወንድማማቾች መሃከል የተደረገ ጦርነት አልነበረም፡፡ በዕኩይ አድራጊዎች እና በነፃነት ፈላጊዎች መሃከል የተደረገ እንጂ፡፡

ስለዚህ ይህንን የህዝቦች ድል በደንብ አርገን እናጣጥመዋለን፡፡ እናከበረዋለን፡፡ የደርግን እሳቤ ነቅሎ ለማጥፋት ቃልኪዳናችንን እናድሳለን፡፡

ለመላው የኢትዮጲያ ህዝቦች እንኳን ለግንቦት 20 የድል በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

ቻው