Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ድህነትን የማይሸከም ጫንቃ

0 253

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ድህነትን የማይሸከም ጫንቃ

                                                     ቶሎሳ ኡርጌሳ

በሃብታምና በደሃው መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት የሰለጠነውን ዓለም ጨምሮ የሌሎች ሀገሮች ድሃ ህዝቦች በፀጋ ተቀብለውት እየኖሩ ነው። በእኛ ሀገር ግን ይህን ከመቀበል ይልቅ ለጥቅሙ መከበር የሚከራከር ህዝብ እየተፈጠረ ነው። እንዲህ ዓይነቱ “ለምን ከልማቱ ተጠቃሚ አልሆንም?” የሚል ህዝብ ሀገራችን ውስጥ መፈጠሩ የምንከተለው ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውጤት መሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም።

 

በአንድ ሀገር ውስጥ ጥቅሙን በማወቅ በተለያዩ ወቅቶች ጥያቄ የሚያቀርብና ክርክር የሚያደርግ ህዝብ መፈጠሩ እንዲሁም በየጊዜው ጎተራው እየጨመረ የሚሄድ አርሶ አደር የሚያቀርበው ጥያቄ መኖሩ አንድ የሚያሳየን እውነታ አለ። እርሱም በዚያች ሀገር ውስጥ ልማት በመሳለጡ ምክንያት ተጠቃሚነቱን ይበልጥ ማረጋገጥ የመፈልግ ሀዝብ መኖሩን ነው። ይህ እውነታም የልማታዊ መንግስት ባህሪ መሆኑ ግልፅ ነው። በሀገራችን ውስጥ የተፈጠረው ጠያቂና ተከራካሪ ህዝብ ስርዓቱ የፈጠረውና የልማታዊ መንግስት ትግበራ ውጤት መሆኑ አያጠያይቅም።

 

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተገነባ ያለው ኢኮኖሚ ብዙሃኑን የሚያሳትፍና ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ የመጣ መሆኑን ጥናቶች ያመላከቱት እውነታ ነው። ይህም ዛሬ በሀገራችን ድህነትን አሜን ብሎ የማይቀበል ትውልድ እንዲፈጠር፣ ተስፋው እየጨመረ የመጣ ህዝብ እንዲኖርና ይህ ህዝብም ጥቅሙ እንዲነካበት የማይፈልግ እንዲሁም ተጨማሪ ጥቅም የሚፈልግ ዜጋ እንዲፈጠር ምክንያት የሆነ ይመስለኛል።

 

ስርዓቱ የሁሉንም ህዝብ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑንም የሚያሳይ ነው። በድምሩም የሀገራችን ህዝብ በአሁኑ ወቅት እንደ ሌሎች ህዝቦች ድህነትን “አሜን” ብለው ለመቀበል የማይችል ትከሻ እንዲኖራቸው ያደረገ ይመስለኛል።

 

ይህ ከድህነት ጋር ተስማምቶ ላለመኖር የወሰነ ህዝብ መፈጠሩም ልማታዊው መንግስት ሁሌም ለልማትና ብልፅግና ተግቶ እንዲሰራ የሚያደርገው ነው። ትናንት በሀገራችን ውስጥ የተገኙት ሁለንተናዊ ለውጦች እንዲጠናከሩለት እንጂ እንዲቀለበሱበት የማይሻው ይህ ህዝብ መንግስት የቤት ስራውን በትክክለኛው የአፈፃፃም መንገድ እንዲከውን የሚፈልግ ነው። ርግጥ የሀገራችን ህዝብ ‘ድህነትን የምሸከኝበት ትከሻ የለኝም’ ማለቱ ትክክልና ተገቢ ነው— ትናንት ዘሳፋሪ ስሙን ለመቀየር የሄደባቸውን ጎዳናዎች በሚገባ ያውቃልና። ግና ትናንት ምን ነበር?…እስቲ ወደ ኋላ በእዝነ-ልቦና ልመልሳችሁ።…

ሀገራችንና ህዝቦቿ በተለይ ከመጀመሪያው የተሃድሶ ወቅት ወዲህ ባሉት ዓመታት መንግስት የመሪነት ሚናውን ወስዶ ባከናወናቸው ድህነትን የመቀነስ ተግባራት፤ ሀገራችን ውስጥ ህዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ ፖለሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመከተል ለውጥ ማምጣት ተችሏል።

በእነዚህ ዓመታት በዋነኛነት የመንግስት አስተዳደርንና ሀገሪቱ የምትመራባቸውን ተቋማት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያልተማከሉ የማድረግ፣ ኢኮኖሚውን ከዕዝ ወደ ገበያ መር ስርዓት የማምጣት፣ በፖሊሲ መዛባት በጦርነትና በተፈጥሮዊ ክስተቶች ሳቢያ የተሽመደመደው ኢኮኖሚ አቅጣጫ እንዲቀየር የማድረግ ሰፊ ጥረት ተደርጓል።

መንግስት ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የተሟላ ዝግጅት በመደረጉና ህዝቡም መንግስት የቀረጻቸውን ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ በማድረጉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ወደ ተሻለ እመርታ ለመሸጋገር በቅቷል።

ላለፉት 16 ዓመታት መንግስት የተለማቸው የልማት ፕሮግራሞች ሀገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ እንደሚረዱ ታምኖባቸው በዚህም ከቀበሌ እስከ ሀገር አቀፍ ድረስ ህብረተሰቡን እንዲሁም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ያሉትን የልማት አጋሮች ለማሳተፍ በሚያስችል መልኩ የተቀረፁ ነበሩ።

እያንዳንዱ የልማት ዕቅድም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ብሎም የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በማገናዘብ የተቀየሱ በመሆናቸው የየራሳቸው መሰረታዊ የትኩረት አቅጣጫ ያላቸው እንደነበር አይዘነጋም። በዚህም ህዝቡን በበልማቱ ላይ በማንቀሳቀስ ባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ማስመዝገብ ተችሏል።

ይህ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት መጠን ትልቅ የገበያ ምንጭ ስለሆነና በተፈጠረውም አመቺ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ተበረታትተው በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሃብቶች በተለያዩ ዘርፎች እንዲንቀሳቀሱ አስችሏቸዋል። የተጀመረው ዕድገት በማስቀጠል ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በኢኮኖሚ ታላቅነቷን ልታስመሰክር እንደምትችል ታምኖበት ወደ ስራ ተገብቷል።  

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገሮችና ከዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ሲነጻጸር ሀገራችን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ መሰረታዊ የሆነ ለውጥ በማምጣት ላይ የሚገኝ ነው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ከዓለም አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ሲሆን፤ በተለይም የዓለም ኢኮኖሚ በ2002 ከዜሮ በታች ዕድገት ሲያስመዘግብ፤ ሀገራችን ግን የላቀ የኢኮኖሚ ዕድገት አፈጻጸም እንደነበራት መረጃዎች ያስረዳሉ። ይህ ድል የተገኘው መንግስትና ህዝብ ለእድገታቸው እጅ ለእጅ ተያይዘው በመስራታቸው ነው።

በተለያዩ ወቅቶች የተከናወኑ የኢኮኖሚ መዋቅር ማስተካከያና ማሻሻያ ፕሮግራሞች የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴውን ከማነቃቃታቸው ባሻገር፤ የኋሊት ሲጓዝ የነበረውን የኢኮኖሚ ዕድገት ትክክለኛ አቅጣጫውን ይዞ እንዲጓዝ ያደረጉ መሆናቸውን እየተመዘገቡ ካሉት ዘርፈ ብዙ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገቶች መገንዘብ የሚቻል ይመስለኛል።

ለፈጣንና ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገት የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ መኖር ወሳኝ መሆኑ ስለታመነበት፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የፊስካልና የሞኒተሪንግ ፖሊሲዎችን በማጣጣም እንዲሁም ዝቅተኛ የመንግስት በጀት ጉድለትንና የውጪ አሸፋፈን እንዲኖር በማድረግ ብሎም የገንዘብ እንቅስቃሴው ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዋጋ ዓመታዊ ዕድገት ጋር የተዛመደ እንዲሆንና የውጭ ምንዛሬ ምጣኔዎችን ለማስተካከል ጥረት በመደረጉም ውጤት ተገኝቷል።

በተለይ ባለፉት 14 ተከታታይ ዓመታት ለሁለት ዓበይት የኢኮኖሚ ዘርፎች (ለግብርና እና ለኢንዱስትሪ) ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአርሶና የአርብቶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ፣ የግሉ ዘርፍም በግብርና እንደሁም በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፎች እንዲሳተፍ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሀገራዊ ምርትን ለማሳደግ መቻሉን ያገኘኋቸው መረጃዎች ያስረዳሉ።

መንግስት ለመሰረተ ልማት ግንባታና ለስራው የሰው ሃይል ልማት በመንግስት የተሰጠው ትኩረት የላቀ በመሆኑ የተገኙ ውጤቶችም አበረታች መሆን ችለዋል። ርግጥም በመንገድ ግንባታ፣ በኤሌትሪክ ሃይልና በቴሌኮሙኒኬሽን እንዲሁም በንጹህ ውኃ አቅርቦት ረገድ የተገኘው መሻሻል አገልግሎቶቹን ለማስፋፋት የጠየቁት ከፍተኛ የፋይናንስና የሙያ ክህሎቶች፤ የተፈራውን ያህል ስራዎቹን ሊያስተጓጉሏቸው አለመቻላቸውን የተገኙት ውጤቶችን በማየት መመስከር የሚቻል ይመስለኛል።

የሀገራችን ኢኮኖሚ ከዛሬ 14 ዓመት ጀምሮ የሁለት አሃዝ ዕድገት በማስመዘገቡ፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዕድገት ጎዳና በአፍሪካ ከሚገኙ ሶስት ሀገራት ግንባር ቀደም በመሆን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ለማስመዝገብ በቅታለች። የተገኘው የኢኮኖሚ ዕድገትም ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ቁጥር እንዲቀንስና በየደረጃውም ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻለ ነው።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በገበያ ተኮር ሥርዓት እንዲራመድ በማድረግ፣ ዕድገቱ ቀጣይና ተከታታይ እንዲሆን ብሎም የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የቻለ ነው። በዚህም ሀገራችን ቀይሳ ወደ ተግባር ገብታ የፈፀመችው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም አበረታታች በሚባል ደረጃ ገቢራዊ ሆኗል። በልማት ዕቅዱ ዓመታት በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተከናውነዋል። በከተሞች በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፎች ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር የተደረጉት ጥረቶች በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

ልማታዊ የኢኮኖሚ አውታሩ ፈጣን ልማትን የማረጋገጥና ህዝብን በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እያደረገ ነው። በዚህም በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ ትግበራ ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአነስተኛና ጥቃቅን የተሰማሩ 4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር አስችሏል፡፡ ይህ ቁጥርም በሁለተኛው የልማት ዕቅድ ይበልጥ እንደሚጨምር ይጠበቃል።

መንግስት በአሁኑ ወቅት ሶስተኛ ዓመቱን በያዘው ሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሸን ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካትና የዕድገቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እየተገበረ ነው—ከህዝቡ ጋር በመሆን።

ርግጥ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታትም በገጠርም ሆነ በከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ካለው ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ተጠቃሚ በመሆን የነብስ ወከፍ ገቢያቸው እንዲያሳድጉ አስችሏቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሚሊዮነር ባለሃብቶች ቁጥር እያደገ እንዲመጣ አድርጓል። ይህ እመርታ በሁለተኛው የልማት እቅድ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዕቅዱ መጨረሻ በዚህ ረገድ የተሻለ ውጤት ይመዘገባል ተብሎ ይጠበቃል።

እናም የሀገራችን ህዝብ ይህ የልማት ዕድገትና ተጠቃሚነት እንዳይቀርበት መከራከሩና ጠያቂ መሆኑ ተገቢ ነው። ላለፉት የልማት ዓመታት የመጣበት መንገድና በሀገራችን የተገኙት ውጤቶች ይህን እንዲያደርግ ያስገድዱታል። ለድህነት ፊት መስጠትን አይፈልግም። ድህነትን የማይሸከመውን ጫንቃ ይዞ ለመንግስት የሚያቀርባቸው የተጨማሪ ተጠቃሚነት ጥያቄዎችና በየመድረኩ የሚያነሳቸው ክርክሮች ልማታዊውን መንግስት እንቅልፍ የማያስተኙ ናቸው። ለበለጠ ሀገራዊ ዕድገት እንዲተጋም ያደርጉታል።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy