Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ጉዞው

0 228

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ጉዞው

                                                       ታዬ ከበደ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ አገራት ያደረጓቸው ጉብኝቶች ውጤታማ ነበሩ። በተለይም በጂቡቲ ያደረጉት ጉብኝት የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከርና የሁለቱን አገሮች ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ናቸው። በጉብኝቱ ጊዜ ልዩ ልዩ ስምምነቶችን ማድረጋቸው ለአገራችን ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በተለይ የጂቡቲን ወደብ በጋራ በማልማት ኢትዮጵያ የንግድ ባለድርሻ እንድትሆን የሚያስችላት ስምምነት ለአካባቢያዊ ሰላም፣ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ትስሰር የላቀ ፋይዳ ያለው ነው።

ጂቡቲ የኢትዮጵያ ገቢና ወጨ ንግድ ዋነኛው የኮሪደር መስመር ናት። ምንም እንኳን አገራችን የራሷ ወደብ የሌላት ብትሆንም፣ በጂቡቲ ወደብን በገራ ለማልማት መፈራረሟ ትልቅ እመርታ ነው። የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያና ጅቡቲ በመሪዎቻቸው በኩል የደረሱት የመሰረተ ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ ስምምነት፤ አገራችንን በጅቡቲ የወደብ ድርሻ ባለቤት ጅቡቲንም በኢትዮጵያ በተመረጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ ባለ ድርሻ እንደሚያደርጋት መግለፃቸው ይታወሳል። ይህም ለሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ ውህደት ሌላኛው በር ከፋች ነው።

ኢትዮጵያና ጂቡቲ በወደብ ልማት፣ በእርሻ ልማት፣ በመንገድ ልማትና ሃገራቱን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመስራ ስምምነት ደርሰዋል። ስምምነቱም ሁለቱንም አገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

የተደረሰው ስምምነት የመሰረት ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ ስምምነት ኢትዮጵያን በጅቡቲ የወደብ ባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራት የሚያደርጋት ነው። ይህም ኢትዮጵያ በወደብ ክፍያ ውሳኔ ላይ ድምጽ እንዲኖራት የማስቻል አቅም ያለው ነው።  ጅቡቲም በኢትዮጵያ በተመረጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ በተመሳሳይ መልኩ ባለድርሻ ያደርጋታል። የመሰረተ ልማት የባለቤትነት ድርሻ ልውውጥ ስምምነቱም ሁለቱንም ሃገራት በእኩል ደረጃ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል ነው።

አገራቱ የሚኖራቸው ድርሻ ላይ የየአገራቱ ኩባንያዎች ሃብት፣ የንግድ መጠንና ትርፋቸው ታይቶ የሚወሰን ነው። ይህን ለማስፈጸምም በሁለቱ አገራት በኩል የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተቋቁሟል። ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ የሚያደርጉትን ጥናትም ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ።

በኢትዮጵያ በኩልም ጅቡቲ የምትሳተፍባቸው የተመረጡ መሰረተ ልማቶች በጥናት የሚወሰኑ ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በማስፈጸም ሂደት ውስጥ የፖሊሲ ለውጥ ጉዳይ የሚያስፈልግ ከሆነም፤ በተቋቋመው ኮሚቴ ወደፊት በሚደረግ ጥናት የሚለይ ይሆናል።

ይህ ሂደት ከፍተኛ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው። በመሆኑም በመሪዎቹ የተደረሰው ስምምነት የኢትዮጵያና የጅቡቲ ግንኙነት አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው። ይህ ከፍታ ሀገራችን የምትከተለውን አስተማማኝ የዲፕሎማሲ መንገድ የሚያመላክት ነው።

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢፌዴሪ ህገ- መንግሥት የአካባቢውንና ጎረቤት ሀገሮችን ለጋራ ጥቅምና ሠላም እንዲሰሩ የሚጋብዝ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ጥሏል፡፡ ይህ እንደ ቀድሞዎቹ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዎች የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን ቸል በማለትና ወደ ውጭ ያነጣጠረ ሳይሆን፤ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ሰላም በማስፈን በማረጋጋት ላይ ትኩረት በማድረግ  በአካባቢያችን ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂና አስተማማኝ ሠላም እንዲፈጠርና የጋራ ልማትና ትብብር እንዲጠናከር ማድረግ ነው፡፡

የውጭ ጉዳይና የሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና ሀገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ አለው፡፡ ፖሊሲውና ስትራቴጂው እንደሚያመለክተው ከማንኛውም ሀገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የሀገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ ያረጋግጣል፡፡

ደህንነታችንን ለማስጠበቅ ዋናው መሣሪያ ልማትና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ ማረጋገጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በዚህ ረገድ ተመስርቶም ዲፕሎማሲያችን በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትን ለመከላከል አቅም መገንባት ተኪ የሌለው ሚና እንደሚጫወት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂው ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲን በሀገር ደረጃ እውን ለማድረግ እየሰራች መሆኑን አመላካች ነው፡፡

አገራችን የራሳችንንና የአካባቢያችንን ህዝቦች ጥቅም ማዕከል በማድረግ የመደጋገፍ አቅጣጫን መከተል አስፈላጊነቱ የጐላ ነው። እናም ለዚህ ተግባራዊነትም መንግስታችን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ተፈላጊውን የልማት ተግባር በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መርህ የሀገሪቱን ገፅታ ከመለወጡ ባሻገር፤ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረኮችም ተሰሚነቷንና ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን ከፍ እንዲል አድርጓል።

አገራችን እያካሄደች ያለው ዲፕሎማሲ ስኬት አንዱ ማሳያ እየተመዘገበ ያለው ፈጣንና ተከታታይ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ነው። ይህ ፈጣንና ተከታታይ ልማትን በመደገፍ ረገድ የምጣኔ ሃብት ዲፕሎማሲው ጉልህ ሚና በመጫወቱ በችግር ጊዜም ለውጥ አምጪነታችን ተረጋግጧል።

በዚህ መሰረትም ከሁለቱ አገራት ባሻገር በአፍሪካ ቀንድ ሠላም ጉዳዮች ዙሪያ አቅሞቻቸውን ለማቀናጀት ተስማምተዋል። በተጨማሪም በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮቸ ዙሪያ በመከሩበት ወቅት ኢኮኖሚያዊ ትብብሩን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ ላይ ድርሻ ታለማለች።

እንዲሁም የጂቡቲ መንግስት በቴሌኮምና በሌሎች ልማቶች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ቢሰሩ ትስስሩን የበለጠ ሊያጠናክሩ ይችላሉ። በዝርዝር ጉዳዮች ላይ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትሮች እንዲሁም ሌሎች ተዛማች ተቋማት ጋር የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በማቋቋም ዝርዝር ሃሳብ ያቀርባሉ።

ይህ ሁኔታ አገራችን በምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዩች ከጎረቤት አገሮች ጋር ቅርርብ በመፍጠር የራሷን ሚና እየተወጣች ነው። በተለይም ከጂቡቲ ጋር ያላት የጠነከረ ፖሊሲ አሁን ያለንበት ግንኙነት ላይ አድርሶናል። መንግሥት ጂቡቲ ለአገራችን ያላትን ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የመጀመሪያዋ ተጎብኚ አገር ያደረጋት ከዚህ እውነታ በመነሳት ነው።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy